Popular Posts

Friday, May 4, 2018

እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅም

እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። ሮሜ 8፡26-27
ፀሎት ወሳኝ የህይወታችን ክፍል ነው፡፡ ፀሎት እንደ እስትንፋስ ይቆጠራል፡፡ ሰው ሳይተነፍስ መኖር እንደማይችል ሁሉ ሰው ሳይፀልይ በእግዚአብሄር መኖር አይችልም፡፡
ክርስትና ወግና ስርአትን ብቻ የመጠበቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ክርስትና ህይወት ነው፡፡ በክርስትና ህይወታችን በሁሉም ነገር በእግዚአብሄር መንፈስ ላይ መደገፍ እንዳለብን ሁሉ በፀሎትም በእግዚአብሄር መደገፍ ይገባናል፡፡
ነገር ግን የተሳካን የፀሎት ህይወት በራሳችን አናመጣውም፡፡ የቱም እውቀታችን የተሳካ የፀሎት ህይወት ሊያመጣልንም አይችልም፡፡ የቱም የክርስትና ልምዳችን በራሱ የተሳካን የፀሎት ህይወት ሊያመጣልን አይችልም፡፡
እንዲያውም እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅም፡፡
በምድር ያለነው የእግዚአብሄርን አላማ ለመፈፀም እንጂ የምንፈልገውን ነገር ለማድረግ አይደለም፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስን በመቀበል የዳነው አስቀድሞ በክርስቶስ ኢየሱስ የተዘጋጀውን መልካሙን ስራ ለመፈፀም ነው፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
የምንፀልየው የራሳችንን ጉዳይ ለማስፈፀም አይደለም፡፡ የምንፀልየው የእግዚአብሄርን አላማ ለማወቅና ለመከተል ነው፡፡ አሁን ስለምን መፀለይ እንዳለብን የእግዚአብሄርን ሃሳብ የሚያውቀው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ማወቅ ካለብን መንፈስ ቅዱስ ሊገልጥልን ይገባል፡፡ ካለመንፈስ ቅዱስ ምሪት የእግዚአብሄርን ሃሳብ ምን አሁን ምን መፀለይ እንዳለብን አናውቅም፡፡ በአእምሯችን የመጣውን ብቻ መናገር ወደ ውጤት አያደርስም፡፡
መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10-12
በራሳችን የእግዚአብሄርን ፈቃድ አናውቅም፡፡ በራሳችን የእግዚአብሄርን አላማ አንረዳም፡፡ በራሳችን ምን መፀለይ እንደሚገባን አናውቅም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ምን መፀለይ እንዳለብን ያለማወቅ ድካማችንን ሊያግዘን ያስፈልጋል፡፡
ለእግዚአብሄር ከመናገራችን በፊት መንፈሱን ልንሰማ ይገባል፡፡ መንፈሱን ሰምተን የምንናገረው ነገር ሁሉ ውጤት አለው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር የሚያየውና የሚያውቀው መንፈስ ያለማወቅ ድካማችንን ያግዛል፡፡
ፍሬያማ የፀሎት ህይወት የሚሰጠንና ፀሎታችንን ወደ ውጤት የሚያደርሰው እንደው መፀለይ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መፀለይ ነው፡፡  
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። ሮሜ 8፡26-27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ፀሎት #ልመና #ምልጃ #ምስጋና #ውዳሴ #ይማልዳል #እንደፈቃዱ #መንፈስቅዱስ #እንዲሰማን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ይቃትታል

No comments:

Post a Comment