Popular Posts

Saturday, August 19, 2017

የእግዚአብሔርን ድምፅ እንዳንሰማ የሚያግዱን አራት እንቅፋቶች

እግዚአብሔርን ሰውን ሲፈጥረው ከሰው ጋር በደንብ መነጋገር እንዲችል በመልኩና በአምሳሉ ነው የፈጠረው፡፡ እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ ለፈጠረው ለሰው ይናገራል፡፡
የእግዚአብሔርና የሰው ግንኙነት በሃጢያት ምክኒያት ከተበላሸም በኋላ ኢየሱስ ስለሃጢያታችን እንደሞተ የተቀበልን ሁሉ እግዚአብሔር እንደልጅ ይናገረናል፡፡ እግዚአብሔርን እንደ ቤተሰብ አባል ለመስማት ኢየሱስን መቀበል በቂ ነው፡፡ እኛ እግዚአብሔርን መስማት ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሊናገረንና እኛም እንድንሰማው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ልጅ አድርጎ ከተቀበልን ጊዜ ጀምሮ ይናገራል፡፡ እኛም እግዚአብሔርን መስማት እንችላን፡፡
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። ዮሃንስ 7፡17
እግዚአብሔር ስለሚናገፈር እኛም እግዚአብሔርን ለመስማት መዘገጋጀት አለብን፡፡ እግዚአብሔርን አጥርተን ለመስማት ማድረግ ያለብንን ነገሮች እንመልከት፡፡
እግዚአብሔርን አለመስማት የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶችና እንዴት እንደምናልፍ እንመልከት
1.      ከባቢው ውስጥ አለመገኘት
እግዚአብሔር ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ሲናገር አጥርቶ ለመስማት በእግዚአብሔር ቃል ከባቢ ውስጥ መገኘት ይጠበቅብናል፡፡  የእግዚአብሔርን ቃል ስንሰማና ስናሰላስለው የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማትና ለመለየት ቀላል ይሆንልናል፡፡ የእግዚአብሔርን ድምፅና የስጋችንን ድምፅ ለመለየት የእግዚአብሔር ቃል ከባቢ ውስጥ መቆየት ግዴታ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚያሰላስል ሰው የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመለየት ችሎታው ከፍ ይላል፡፡
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ኢያሱ 1፡8
በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ፊልጵስዩስ 4፡8
2.     ራስን ትሁት አለማድረግ
እግዚአብሔርን ለመስማት ራስን ትሁት ማድረግና ለእግዚአብሔር ድምፅ ጊዜን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የማናውቀው ብዙ ነገር እነዳለ እግዚአብሔር ደግሞ ሁሉንም እንደሚያውቅ እውቅና ካልሰጠን እግዚአብሔርን እንዳንሰማ ያግደናል፡፡ ያወቅን ሲመስለን እግዚአብሔር ሲናገር መስማት አንችልም፡፡ እግዚአብሔር በሰማይ እንዳለ እኛም በምድር እንዳለን በብርቱ ካልፈለግነውና በዝግታና በትህትና ካልቀረብን እግዚአብሔርን መስማት ያቅተናል፡፡ ሌላ አማራጭ ይዘን እንድንፈልገው እግዚአብሔር አይፈልግም፡፡
ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፤ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። መክብብ 5፡1-2
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። ኢሳይያስ 66፡1-2
እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርምያስ 29፡13
3.     እግዚአብሔርን ለመስማት ጊዜ አለመስጠት፡፡
በምድር ብዙ ድምፆች ስላሉ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንዳንለይ ይገዳደራሉ፡፡ እግዚአብሔርን እንዳንሰማ የመያወናብዱ ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ ሌሎችን ነገሮች ከመስማት ራሳችንን አግልለን እግዚአብሔርን ለመስማት ራሳችንን ማዘጋጀት የእኛ ድርሻ ነው፡፡ አንዳንዴ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማት ሌሎቹን ድምፆች ሁሉ ውጭ ማስቀረት አለብን፡፡  
እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። ሐዋርያት 13፡2
አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ማቴዎስ 6፡6
4.     እግዚአብሔርን ድምፅ በአእምሮ መፈለግ፡፡
የእግዚአብሔር ድምፅ የሚሰማው በልብ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በጎና መልካም በመለያ አእችምሮዋችን እንወስነውም፡፡ እግዚአብሔር የሚናገረው በመንፈስ ቅዱስ በልባችን ነው፡፡ ሰዎች መልካም የሚሉት ሁሉ ለእግዚአብሔር መልካም ላይሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ክፉ የሚሉት ሁሉ ለእግዚአብሔር ክፉ ላይሆን ይችላል፡፡ በአእምሮዋችን ክፉና መልካም መለኪያ ብቻ የእግዚአብሔርን ድምፅ መለካት የእግዚአብሔርን ድምፅ ስንሰማ እንዳልየው ያግደናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ሮሜ 8፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ምሪት #ጆሮ #ትህትና #ቃል #ድምፅ #አእምሮ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


No comments:

Post a Comment