Popular Posts

Wednesday, May 23, 2018

ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ

የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ። ምሳሌ 1፡7
ነፍስ ያለእውቀት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፡፡ ጥበብና እውቀት ከሚገኝበት መንገድ አንዱ ተግሳፅ ነው፡፡ ተግሳፅ የሰው ሃብት ነው፡፡ ተግሳፅን የሚሰማ ሰው ደግሞ ተግሳፅ ከክፉ ይጠብቀዋል፡፡
ተግሳፅን የማይሰማ ሰው ግን ያንኑ ስንፍና ሲደግመው ሳያድግና ሳይለወጥ እንደተፀፀተ ይኖራል፡፡ ሰነፍ ሰው በተግሳፅ ለመታረም ከመትጋተ ይልቅ ስንፍናው በህይወት ከፍተኛ ዋጋ እንዲከፍል ያደርገዋል፡፡
እውነትን ግዛ አትሽጣትም፥ ጥበብን ተግሣጽን ማስተዋልንም። ምሳሌ 23፡23
ሰው ስለዘለፋ እና ተግሳፅ ጥቅም እውቀት ከሌለው ዘለፋንና ተግሳፅን ይንቃል፡፡ ዘለፋና ተግሳፅ ያላቸውን ዋጋ የተረዳ ሰው ያከብራቸዋል፡፡ የተግሳፅን አስፈላጊነት የተረዳ ሰው ለተግሳፅ ሙሉ ልቡን ይሰጣል፡፡ የዘለፋን ጥቅም ያወቀ ሰው የዘለፋን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ እስከሚጠቀምበት ድረስ ዘለፋን አያልፈውም፡፡
ተግሣጽን ያዝ፥ አትተውም፤ ጠብቀው፥ እርሱ ሕይወትህ ነውና።ምሳሌ 4፡13
የዘለፋን ጥቅም የማያውቅ ሰው ግን የገሰፀው ሰው ጠላቱ ይመስለዋል፡፡ የተግሳፅን አስፈላጊነት ያልተረዳ ሰው ግን የሚገስፀው ሰው ያለአግባብ የሚጠቀምበት ይመስለዋል፡፡
በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። ማቴዎስ 7፡6
ሰው ከተግሳፅ ምን እጠቀማለሁ ማለቱ ግን ወሳኝ ነው፡፡ ተግሳፅ ራሳችንን እንድናይ ያደርገናል፡፡ ተግሳፅ እኔ ሃላፊነት የመወስደው ስለየቱ ጥፋት ነው ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡ ተግሳፅ ራሳችንን እንድናነፃ እድልን ይሰጠናል፡፡ ተግሳፅ ትክክል ብንሆን እንኳን ትክክል መሆናችንን ያፀናልናል፡፡    
ብልህ ሰው ህይወት ከሚገስፀው ሰው ቢገስፀው ይሻለዋል፡፡ ብልህ ሰው ውድቀት ከሚያዋርደው ዘለፋ ቢያዋርደው ይቀለዋል፡፡ ጠቢብ ሰው መከራ ከሚመክረው ሰው ቢመክረው ይሻለዋል፡፡
ዘለፋን የሚጠላ ገንዘቡ የማያደርግ ሰው ዘለፋን የሚንቅ ቸልተኛ ሰው በፍፃሜው እንዴት እንደሚፀፀት መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ አትናገሩኝ የሚል ሰው በትእቢቱ ይፀፀታል፡፡
በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ፥ ትላለህም፦ እንዴት ትምህርትን ጠላሁ፥ ልቤም ዘለፋን ናቀ! የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም። ምሳሌ 5፡11-13
ዘለፋን የሚታገስ ፡ በተግሳፅ ራሱን የሚያይ በተግሳፅ ተጠቅሞ ራሱን የሚያሻሻል ሰው እየለመለመ ፣ እያበበና እያፈራ ይቀጥላል፡፡
 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃሳብ #ጥበብ #ማስተዋል #ተግሳፅ #ዘለፋ #ጥበብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment