Popular Posts

Showing posts with label covenant. Show all posts
Showing posts with label covenant. Show all posts

Sunday, May 17, 2026

የምንሞትለት እንጂ የምንገድልለት አምላክም ሆነ ሀይማኖት የለንም!

 የምንሞትለት እንጂ የምንገድልለት አምላክም ሆነ ሀይማኖት የለንም! 


አምላክ ሀያል ነው የእኛ እርዳታ አይፈልግም። እንዲገድሉለት የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት እውነተኛ ሀይማኖት አይደለም። የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት ሀሰተኛ ሀይማኖት ነው። የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት ከሰይጣን ነው። 

ብዙ ሀይማኖቶች በምድር ላይ ቢኖሩም በአጠቃላይ ምድር ላይ ያሉት ሁለት አይነት ሀይማኖቶች ብቻ ናቸው። በምድር ላይ እውነተኛ እና ሀሰተኛ ሀይማኖት አለ። እግዚአብሔር አንድ ነው። ከአንድ በላይ እውነተኛ ሀይማኖት ሊኖር አይችልም። በአለም ላይ ከአንድ በላይ  ሀሰተኛ ሀይማኖት ሊኖር ግን ይችላል። 

ታዲያ ሀይማኖት መያዙ ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ መያዛችንን እርግጠኛ እንሁን። እኔን በተመለከተ ፍለጋ አቁሜያለው እውነተኛውን አምላክ አግኝቻለሁ።

እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። ዮሐንስ 17:3 ሁሉም ሀይማኖት ወደ አንድ ፈጣሪ ያደርሳል የሚሉ በሰይጣን የተታለሉ ናቸው። 

ኢየሱስም አለው፡— እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ዮሐንስ 14:6 

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 

Sunday, April 12, 2026

ከእርሱ ጋር አስነሣን !



ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፣6 7

ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ስለእኛ ነው። ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው እኛ በሃጢያታችን ምክኒያት ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላላም እንዳንለያይ ነው።

ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፣21 22

ክርስቶስ ኢየሱስ የሞተው እኛ በሃጢያታችን መሞት የነበረበንን ሞት ነው። ክርስቶስ የሞተው በእኛ ምትክ ነው። ክርስቶስ የሞተው ለእኛ ነው።

በመጀመሪያ ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላላም እንዲኖር ነበር። በእግዚአብሔር የተፈጠረው ሃጢያትን የማያውቅ  ፍጹም ሰው ነበር።

ሰው ከእግዚአብሔር የተለየው ሃጢያት በሰራ ጊዜ ነበር።

እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፣16  17

ክርስቶስ የመጣው እኛ ወደፊት እንዳንሞት ከእግዚአብሔርም ጋር ለዘላላም እንዳንለያይ ነው።

ክርስቶስ ሃጢያት ያልተገኘበት ፍጹም ነው። ክርስቶስ መሞት አይገባውም  ነበር። ክርስቶስ የሞተው እኛ ሞት ሰለሚገባን ነበር። ክርስቶስ የሞተው እኛን ከሞት ሊያስነሳን በእኛ ምትክ ነው።  

ክርስቶስ የሞተው ለእኛ ትንሳኤን ሊሰጠን ነው።

እኛ ከክርስቶስ ጋር አብረነው ካልተነሳን ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።

የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ "ከእለታት አንድ ቀን ክርስቶስ ከሞት ተነሳ" ብለን ብቻ የምናስታውሰው የክርስቶስ ታሪክ አይደለም። የክርስቶስ ትንሳኤ የእኛም ከሙታን የመነሳት ልምምድ ነው። በክርስቶስ ሞትና ተንሳኤ የምናምን ሁላችን ከሞት ተነስተናል።

ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፣5-7

የትንሳኤ በአል የክርስቶስ ብቻ ሳይሆን የእኛም የትንሳኤ በአል ነው።

መልካም የትንሳኤ በአል

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

Tuesday, June 23, 2020

በምድራዊ እውቀት የማይደረስበት መንፈሳዊ ክልል



ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

በህይወታችን ላይ የሚነጣጠሩ ብዙ ጥቃቶች ከምናስበው በላይ መንፈሳዊ ናቸው፡፡

ለምሳሌ የጤና መታወክ ሲደርስብን ቶሎ የሚመጣልን የሳይንሱ እውቀትና የሳይንሱ መፍትሄ ነው፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን ቁሳዊ እናደርገዋለን፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን በህክምና እውቀት ብቻ ልንተረጉመው እንፈተናለን፡፡

የበላሁት ምግብ ነው ወይም ቫይረስ ነው ብለን እንደሰው ልማድ ብቻ ጥቃቱን ልንዋጋው እንፈልጋለን፡፡ እንደሰው ልማድ ተዋግተን ከተሳካልን እሰየው፡፡ የሰይጣን ስራ ለማፍረስ ያለንን ነገር ሁሉ እምነታችን እና እውቀታችንን ሁሉ እንጠቀማለን፡፡

እንደሰው ልማድ ብቻ ከመዋጋት ያለፈ ነገር የሚጠይቅ ብዙ የዲያቢሎስ ጥቃት አለ፡፡  

የሰው ልጆች ጥቃት በቀጥታ ባይሆንም ቢያንስ በተዘዋዋሪ ከሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን ሌላ ራእይ የለውም፡፡ ራእዩ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ብቻ ነው፡፡

ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። የዮሐንስ ወንጌል 10፡10

አንዳንዴ ሰይጣን በመንፈሱ በቀጥታ ባያጠቃንም ማድረግ ያለብንን ነገር በቸልተኝነት እንዳናደርግ በአእምሮዋችንም ቢሆን ያጠቃናል፡፡ ወይም የእግዚአብሄርን አላማ በምድር ላይ እንዳንፈፅም በፍርሃት ሽባ ያደርገናል፡፡ ሌላም ጊዜ በፀጋ ከተቀበልነው በሽታን በእኛ ላይ ሊያደርግ ይሞክራል፡፡

ተዘዋዋሪ የሰይጣን አላማ ቢሆኑም ንፅህናን ባለመጠበቅ የሚመጡ በሽታዎች ከሰይጣን አላማ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ጥንቃቄያችንንም ተጠቅሞ ከጠላት ጥቃት ያስመልጠናል፡፡

ተጠንቅቀንም እግዚአብሄር አስመለጠን ነው የምንለው እንጂ ጥንቃቄያችንም ፍፁም በማይሆነው በጥንቃቄያችንም አንታመንም፡፡

እግዚአብሄር ለእኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለደህንታችን ያለውንም ነገር ሁሉ ይጠቀማል፡፡ እግዚአብሄር የዶክተሮችን ጥበብ ተጠቅሞ በሽታን ይዋጋልናል፡፡ የዲያቢሎስን ስራ ለማፍረስ ያለንን ምድራዊ እውቀት እና መንፈሳዊ እውቀርት ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ ሰይጣን በህይወታቸን በጤናችን ምንም ስፍራ እንዳያገኝ እስከመጨረሻው ፀንተን እንቃወመዋለን፡፡

በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡9

ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፡8

ከዶክተሮች እውቀት በላይ ያለ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ዶክተሮች በምድራዊ ጥበባቸው የማይደርሱበት መንፈሳዊ ክልል አለ፡፡

ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።  1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡14

እግዚአብሄር እምነታችንን ተጠቅሞ ከበሽታው ጀርባ ያለውን መንፈሱን በኢየሱስ ስም እንድንቃወመው አይናችንን ይከፍታል ይመራናል፡፡

ይህችን ሴት በወቅቱ ዶክተሮች ጋር ብትታይ ዶክተሮች በምድራዊ እውቀታቸው የማይረዱት መንፈሳዊ ክልል ስላለ ስለበሽታዋ አንድ ምክኒያት ይሰጧታል፡፡  

ኢየሱስ ግን ከዚህ በሽታ ጀርባ ያለውን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣውን ሰይጣንን አየው፡፡ ኢየሱስ በሽታውን ሳይሆን ከበሽታው በስተጀርባ ያለውን የበሽታውን ምንጭ አደረቀው፡፡

ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


Sunday, June 21, 2020

ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። መጽሐፈ መክብብ 3፡12-13 ፣ 8፡5

ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። መጽሐፈ መክብብ 3፡12-13 ፣ 8፡5

Sunday, April 26, 2020

በምድር ያለነው


በተለያየ ጊዜ በህይወታችን የተለያዩ ተግዳሮቶች ይመጣሉ፡፡ ታዲያ ይህን አልፈው ይሆን ብለን የምናስብበት ውጥረት በህይወታችን ይመጣል፡፡ እንደዚህ አይነት ውጥረት በህይወታችን ሲገጥመን "በምድር ላይ ያለሁት ለምንድነው?" ብለን ይህን ጥያቄ ከልባችን እንጠይቃለን፡፡
በምድር ላይ ያለሁት ለምንድነው? የሚለው ጥያቄ ሁል ጊዜ መጠየቅና በትክክል መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
እውነት ግን በምድር ላይ ያለነው ለምንድነው?
የማንሞተው ለምንድነው ? ወይም መሞት የማንፈልገው ለምንድነው ?
በምድር ላይ ያለነው ስላልሞትን ነው ? ወይስ በምድር ላይ ስለመኖራችን ሌላ አለማ አለ?
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው አስቦና አቅዶና በአላማ ነው፡፡
እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ኦሪት ዘፍጥረት 1፡26-27
ወደምድር ከመምጣታችን በፊት ወደምድር የመጣንበት ልዩ አላማ ነበር፡፡
ማንም ሰው በድንገት ውይም በአጋጣሚ በምድር ላይ የተወለደ ሰው የለም፡፡ ሰው በምድር ላይ የመወለዱ ምልክት ከመወለዱ በፊት የተወለደበት ልዩ አላማ የመኖሩ ምልክት ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርሚያስ 29፡11
እኛ በምድር ላይ ለመኖር ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር በምድር ላይ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በምድር ላይ ለመኖር ካለን ፍላጎት በላይ በምድር ላይ እንድንኖር የተፈለገበት የእግዚአብሄር አላማ ይበልጣል፡፡
በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። ምሳሌ 19፡21
በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። ኢሳያስ 46፡10
ይህን በህይወታችን ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ ስንረዳ እናርፋለን፡፡
እግዚአብሄር እንዴት እንደሚወደን ስንረዳ እና በህይወት ለመኖራችን ልዩ አላማ እንዳለው ስንረዳ ከፍርሃት ነፃ እንወጣለን፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡18-19
ፍርሃት የእግዚአብሄርን ፍቅር የመረዳታችንን ደረጃ ያመለክታል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያለውን የፍቅር አላማ በተረዳን መጠን ፍርሃት ከህይወታችን ቦታ እያጣ ይሄዳል፡፡  
የእግዚአብሄርን ፍቅር በተረዳን መጠን ከፍርሃት ነፃ እንወጣለን፡፡ እግዚአብሄር እንዴት በፍቅር እንደሚያየን በህይወታች ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን የፍቅር አላማ እየተረዳን ስንመጣ በፍርሃት ሳይሆን በፍቅር እንንቀሳቀሳለን፡፡
የእግዚአብሄርን የፍቅር አለማ ስንረዳ የሚያንቃቅሰን ፍርሃት ሳይሆን ፍቅር ብቻ ይሆናል፡፡
በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 2፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አላማ #ተስፋ #ፍፃሜ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተስፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, February 12, 2020

ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም



ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም። መጽሐፈ መክብብ 11፡4
ህይወት የእምነት ጉዞ ነው፡፡ ህይወትን በሚገባ ማጣጣም ከፈለግክ በእምነት መኖር መጀመር አለብህ፡፡ በእምነት መራመድ ካልጀመርክ የህይወትን እውነተኛውን ጣእም በፍፁም አታገኘውም፡፡ ሰው መኖር የሚጀምረው በእምነት መራመድ ሲጀምር ብቻ ነው፡፡ የሰው እውነተኛ መኖሪያ የእግዚአብሄር ቃል እምነት ነው፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 4፡4
ሰው ዲዛይን የተደረገው ለእምነት ኑሮ ነው፡፡ ሰው የሚኖረው በእምነት ነው፡፡
እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ትንቢተ ዕንባቆም 2፡4
እምነት የሚመጣው ከእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡17
በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ለተፈጠረው ክቡር ለሆነው ሰው ለሰው ልጅ ከእግዚአብሄ ቃል ያነሰ ኑሮ አይገባውም፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 4፡4
የሰው እውነተኛ እርካታ በእምነት ሲኖር ነው፡፡
ነገሮች ሆነው ከማየትህ በፊት የእግዚአብሄርን ቃል አምነህ እርምጃ ካለወሰድክ ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አትችልም፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር የምትገናኘው በስጋ አይን የማይታየውን መንፈስ የሆነውን እግዚአብሄርን የምትሰማው ፣ እግዚአብሄርን የምትነካው ፣ እግዚአብሄርን የምታየው ሁሉ በእምነት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ነገር ሁሉ በእምነት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። መዝሙረ ዳዊት 33፥4
ነገሮች ተለውጠው ደስ ለመሰኘት የምትጠብቅ ከሆነ ደስ መሰኘቱን እርሳው፡፡ ነገሩን የሚለውጠው በእምነት እርምጃ በመውሰድ ደስ በመሰኘትህ ብቻ ነው፡፡
የምትፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ኪስህ ከገቡ በኋላ እፎይ ለማለት እየጠበቅክ ከሆነ የማይፈፀም ተስፋ እየጠበክ ነው፡፡
ለማመን ፀሎትህ እስኪመለስ እየጠበቅክ ከሆነ ፀሎትህ ለመፈፀም የአንተን እምነት እየጠበቀ ነው፡፡
እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። የማርቆስ ወንጌል 11፡23-24
ሁሉ ደህና ነው ለማለት ነገሮች ሁሉ ተስተካክለው እስክታይ አየጠበቅክ ከሆነ በከንቱ ትጠብቃለህ፡፡   
ከመዝራትህ በፊት ሁኔታዎችን እየጠበቅክ ከሆነ መቼም አታጭድም፡፡
ምልክት ከማየትህ በፊት ማመን አለብህ፡፡ እምነትንም የሚያመጣው የእግዚአብሄር ቃል እንጂ ምልክት እምነትን አያመጣም፡፡ ምልክቱን የሚያመጣው እምነትህ ነው፡፡  
ከውጤት እና ከምልክት በፊት የእምነት እርምጃ ይቀድማል፡፡
እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፥ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኛዋለህና። መጽሐፈ መክብብ 11፡1
አስቀድመው ምልክትን የሚፈልጉ ካላየሁ አላምንም የሚሉ ሰዎች እግዚአብሄርን የማይፈልጉ አሿፊ ሰዎች ናቸው፡፡
ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ። የማቴዎስ ወንጌል 16፡1፣4
ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም። መጽሐፈ መክብብ 11፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ወንጌል #ስብከት #ቃል #ዝራ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

Saturday, January 28, 2017

የቃልኪዳን ስምረት

ቃልኪዳን በአለም ላይ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ሃሳቦች አንዱ ነው፡፡ ብዙ ወሳኝ ነገሮች የሚደረጉት በቃልኪዳን ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት በአለም ላይ ያለን ሃብትና እምቅ ጉልበት አለመረዳት ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት አላማን መሳት ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት ፍሬቢስ መሆን ነው፡፡
ቃልኪዳን በሁለት ወገኖች መካካል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ አንዱ ወገን ለሌላው ወገን የሚያደርግለት ነገር ሌላኛውም እንዲሁ ለሌላው የሚያድርገለት ነገር አለ፡፡
እኛ በብዙ ነገሮች የተወሰንን ስለሆንን ሁሉንም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ ለወሳኝ ነገሮች  የቃልኪዳን አጋር ያስፈልገናል፡፡ ቃልኪዳን ደግሞ በራስ ድርሻ ላይ ብቻ ማተኮርን ይጠይቃል፡፡
በአለም ላይ ያለው ችግር በራስ ሃላፊነት ላይ ያለማተኮር ችግር ነው፡፡ በአለም ላይ ያለው ግራ መጋባት የመጣው የስራ ክፍፍልን ካለመረዳትና የራስን ድርሻ ብቻ ፈፅሞ ካለማረፍ የሚመነጭ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ህብረትን ፈልጎ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እያደረገ ምድርን የሚያስተዳድርለትን የሚረዳውና የሚግባባው ፍጥረት ፈልጎ ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ ዘፍጥረት 1  
ሰው በሃጢያትም ከወደቀ በኋላ እግዚአብሄር የሰው ልጆችን ለመድረስና አላማውን በምድር ላይ ለማስፈፀም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እግዚአብሄር በዘመናት መካከል ከአብርሃም ፣ ከኖህ ፣ ከእስራኤል ህዝብ ጋር ቃልኪዳን ሲያደርግ ነበር፡፡
አሁንም በዚህ ዘመን እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ላይ መስዋእትነት ከእኛ ጋር ኪዳን ገብቷል፡፡ እግዚአብሄር መንግስቱን የሚሰራለትና የሚያስፋፋለት ሰው ፈልጎ ከእኛ ጋር ቃልኪዳን ገብቷል፡፡
ነገር ግን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ ሰዎችን ግራ የሚያጋባቸው የቃል ኪዳን የስራ ድርሻ ነው፡፡ አሁንም በዘመናችን ሰዎች እግዚአብሄር ወዳየላቸው የህይወት ከፍታ እንዳይገቡ የሚያግዳቸው የቃልኪዳንን ድርሻን አለመረዳት ነው፡፡
ለምሳሌ ሰዎች የሚበላና የሚጠጣ የሚለበስ በመፈለግ ህይወታቸውን የሚያባክኑት የእግዚአብሄርን አቅርቦት የቃልኪዳን ድርሻ ባለመረዳት ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
በዚህ የቃል ኪዳን ስምምነት መሰረት የሰው ድርሻ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ በእግዚአብሄ ፊት ትክክለኛ ነገር ማድረጉን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሰው ድርሻ እግዚአብሄን በምድር መወከል ነው፡፡ የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄር መንግስት ደህንነት ማሰብ ነው፡፡ የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄር መንግስት ማሸነፍና መስፋፋት መስራት ነው፡፡  የሰው ድርሻ የእግዚአብሄን ቤተክርስትያን በጎነት መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ የመንግስቱን አባላት መንከባከብና ማስነሳት ነው፡፡
እግዚአብሄር መንፈስ ስለሆነና በስጋ ውስጥ ስለማይኖር በምድር ላይ ይህንን እንድናደርግለት የጠራን እኛን ነው፡፡ እኛ ይህንን ማድረግ እንችላል፡፡ በዚህ ማድረግ በምንችለው ድርሻ ላይ ብቻ ብናተኩር ውጤታማ እንሆናለን እግዚአብሄርንም በሙላት አገልግለን እናልፋለን፡፡    
የእግዚአብሄ ድርሻ ደግሞ ለሰው የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር ማሟላት ነው፡፡ ይህንን እንዲህ አድርገው ብሎ የሚመክረው የለም፡፡ ይህን ደግሞ እርሱ ያደርገዋል፡፡
አሁን ሰው የተሰጠውን ይህንን በቂ ሃላፊነት ጥሎ እግዚአብሄር እንዴት እንደሚንካከበው ቁጭ ብሎ ቢጨነቅ ከንቱ ነው፡፡ ሰው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር ማድረግ አይችልምና እግዚአብሄር የሰጠውን መንግቱንና ፅድቁን የመፈለግ ሃላፊነቱን እየጣለ ነው፡፡ እግዚአብሄር እኔን በትክክል ይይዘኝ ይሆን ብሎ ሲፈራ ድርሻውን መወጣት ያቅተዋል፡፡ እግዚአብሄር አያያዙን ያውቅበት ይሆን ብሎ ሰው ቢያወጣና ቢያወርድ ህይወቱን እያባከነ ነው፡፡
ሰው በህይወቱ ይህን የቃል ኪዳን ሃላፊነት ካልተረዳና በራሱ ሃላፊነት ብቻ ላይ ካላተኮረ የእስራኤል ህዝብ የሴይርን ተራራ እንደዞሩት ይዞራል እንጂ እግዚአብሄር ወዳሰበለት ግብ አይደርስም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #አትጨነቁ #ቃልኪዳን #መታመን #መደገፍ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, December 30, 2016

እግዚአብሄርን የማመስገን መልካምነት

እግዚአብሄርን ለማመስገን ብዙ ምክኒያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እግዚአብሄርን ለማመስገን የሁሉም ሰው የጋራ ምክኒያት የሆነው አንድ ምክኒያት ነው፡፡ ሰው ሌላ ምክኒያት ቢያጣ እንኳን በዚህ ምክኒያት እግዚአብሄርን ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡ ሰው ምክኒያት ቢያጣ እንኳን ይህ ምክኒያት እግዚአብሄርን ለማመስገን በቂ ነው፡፡
መፅሃፍም ቅዱስም ይህን ምክኒያት እግዚአብሄርን ለማመስገን ምክኒያት አድርጎ ደጋግሞ ፅፎታል፡፡
እግዚአብሄር መልካም ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁለንተናው መልካም ነው፡፡ እግዚአብሄር አይለወጥም ሁልጊዜም መልካም ነው፡፡
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ያዕቆብ 1፡16-17
የመልካምነት ትርጉሙ ቢያከራክር እንኳን ለመልስ እግዚአብሄርን ማየት በቂ ነው፡፡ እግዚአብሄር የመልካምነት ማጣቀሻ (Refrence) ነው፡፡ ሰው በሚያነበው መፅሃፍ ላይ ያለን ቃል ትርጉም ባይረዳ ማጣቀሻን ይፈልግና የቃሉን ትርጉም ያያል፡፡ እንደዚሁ የመልካምነት ትርጉሙ ቢያጠራጥር እግዚአብሄር ጋር መልሱ አይታጣም፡፡
እግዚአብሄር መልካም ብቻ ሳይሆን የመልካምነትም ደረጃ መዳቢ ነው፡፡ እሱ መልካም ያለው መልካም ነው እርሱ መልካም አይደለም ያለው መልካም አይደለም፡፡ ስለ መልካምነት የመጨረሻው ወሳኝ አካል እግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚያርመው የለም፡፡ እግዚአብሄርም ማንንም አያማክርም፡፡
እግዚአብሄርን መልካም ስለሆነና ምንም የማይወጣለት ፍፁም መልካም ስለሆነ እግዚአብሄርን ማመስገን መልካም ነው፡፡ ሰው በምንም ነገር ቢሳሳት እግዚአብሄርን ስለማመስገኑ በጭራሽ አይሳሳትም፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ምንም የሚወጣለት ነገር የለም፡፡  
እግዚአብሄር መልካም ስለሆነ ምስጋና ይገባዋል፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ይገባል፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ውበት አለው፡፡ እግዚአብሄርን ማመስገን ያማረ ነው፡፡
እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው። መዝሙር 147፡1
ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፤ መዝሙር 135፡1፣3
እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤ በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ። መዝሙር 92፡1-3
ሃሌ ሉያ። ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ መዝሙር 107፡1
ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና። መዝሙር 118፡ 1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #አመስግኑ #መልካም #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #አብርሃም #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

የወዳጅነት ጥበብ

በሰው ህይወት ውስጥ በጣም ከፍተኛ ስፍራ ካላቸው ነገሮች አንዱ ወዳጅነት ነው፡፡  
ወዳጅነት የሌላውን ስሜት መረዳት ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት የሌላን ድንበር ማክበር ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት አንዱ ሌላውን ማገልገልን ይጠይቃል፡፡ ወዳጅነት አንዱ የአንዱን ሸክምን መሸከምን ይጠይቃል፡፡
ሰው የራሱ የግሌ የሚለው ክልል አለው፡፡ ሰው ለራሱ ብቻ የሚያስቀረው ሚስጥር ሊኖረው ይችላል፡፡ ሰው ለራሱ ብቻ የሚፈቅደው ግላዊነት ይኖረዋል፡፡ ያንን የግል ክልል ማክበር ወዳጅነትን ያጠናክራል፡፡
ወዳጅነት አንዱ ለሌላው መድረስን ያካትታል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ እንደሚወድ ያስተምረናል፡፡  
ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል ምሳሌ 17፡17
ወዳጅነት ሃላፊነት ነው ፡፡ ወዳጅነት ማካፈል ነው፡፡ ወዳጅነት ለሌላው መገኘት ነው፡፡ ወዳጅነት መስጠት ነው፡፡ ሰው ለሁሉም ሊሰጥ አይችልም፡፡ ለሁሉም ሊሰጥ የሚፈልግ ሰው ለማንም ሳይሰጥ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ መርጠን በመልካም በወዳጅነት ላይ ኢንቨስት እንድናደርግ የሚያስተምረን፡፡
ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ። ምሳሌ 18፥24
ወዳጅነት በአንድ ዘመን ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ወዳጅነት ለትውልድ ይተላለፋል፡፡ አንዳንዴ ከዘመድ ይልቅ ወዳጅ ቀድሞ ይደርሳል ይጠቅማልም፡፡
ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል። ምሳሌ 27፥10
ወዳጅነት በመተማመን ላይ ብቻ ይመሰረታል፡፡ ስለዚህ ነው ወዳጅነት በአንድ ለሊት የማይገነባው፡፡ አንዱ ለሌላው ያለውን መሰጠት በማየት ነው አንዱ ለሌላው ራሱን የሚሰጠው፡፡ ወዳጁ ያለውን ታማኝነት በማየት ነው በታማኝነት ራሱን ለወዳጅነቱ ቀስ በቀስ የሚሰጠው፡፡ ወዳጅነትን ሊያፈርስ የሚመጣውን ነገር በጥንቃቄ መከታተል ይጠይቃል፡፡
ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል። ምሳሌ 16፥28
ወዳጅ በመልካም መንገድ በወዳጁ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ ትጉህ ወዳጅ ወዳጁን ትጉህ ያደርገዋል፡፡ አስተዋይ ወዳጅ ወዳጁን ማስተዋል እንዲጨምር ይረዳዋል፡፡ እንደ ወዳጅ በወዳጁ ላይ ተፅእኖ ለማድርግ ሰፊ እድል ያለው የለም፡፡
ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል። ምሳሌ 13፡20
ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል። ምሳሌ 27፡17
ጻድቅ ለባልንጀራው መንገዱን ያሳያል፤ የኀጥኣን መንገድ ግን ታስታቸዋለች። ምሳሌ 12፡26
ወዳጅ ያሳርፋል፡፡ ወዳጅ ያስደስታል፡፡
ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ እንዲሁ ነፍስ በወዳጁ ምክር ደስ ይላታል። ምሳሌ 27፡9
በተቃራኒው ደግሞ ከክፉ ባልንጀርነት መሸሽ ህይወትን ይጠብቃል፡፡ በባልንጀርነት አመል እንዳይበላሽ መጠንቀቀ ያስፈልጋል፡፡
ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋር አትሂድ፥ መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። ምሳሌ 22፡24-25
አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡33
ወዳጅነት ምህረት ይቅር ማለት መሸከም ይጠይቃል፡፡ ማንም ሰው የማንወድለት ይህን ቢያስተካክል የምንለው ነገር አለው፡፡ ሁሉም ነገሩ የሚያስደስተን ሰው በምድር ላይ የለም፡፡ ስለዚህ ሌላውን መሸከም የሰውን መልካምነት እንድንጠቀም ያስችለናል፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ግን መለየት ነው የሚፈልገው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ወረተኛ ነው፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው በወዳጅነት አይፀናም፡፡ ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ከወዳጅነት በላይ ሌሎች ጥቅሞችን በማስቀደም ታላቁን ስጦታ ወዳጅነትን ይጥላል፡፡
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፡1
ወዳጅነትን የሚያከብር ሰው በምህረት ይመላለሳል፡፡ ለወዳጅነት ዋጋ የሚሰጥ ሰው ወዳጅነትን የሚያጠፋውን ነገር ላለማድረግ ይጠነቀቃል ዋጋም ይከፍላል፡፡
ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል። ምሳሌ 17፡9
ወዳጅነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ወዳጅ ወዳጁን እጅግ በጣም ከማመኑ የተነሳ ከጠላት መሳም ይልቅ የወዳጅ ማቁሰል እንኳን ተቀባይነት አለው፡፡
የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል። የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው። ምሳሌ 27፡5-6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ወዳጅ #ጓደኛ #መታመን #ጥበብ #ፍቅር #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, December 28, 2016

የዝምታ አምልኮ

ከእግዚአብሄር ጋር ላለን ግንኙነት መጠናከር ጠቃሚ ከሆኑ የተለያዩ የጥሞና መንገዶች አንዱ ዝምታ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት ስምረት የሚለካበት አንዱ መንገድ ዝምታ ነው፡፡
ስጋ ሁል ጊዜ መናገር ይፈልጋል፡፡ ስጋ የሚረካው በመናገር ነው፡፡ ስጋ በህይወት የመጡትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚሞክረው በመናገር ብዛት ነው፡፡ ስለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ አልናገርም ብለን ስንወስን ስጋ ከውስጣችን ሲጮህና ሲቃወም የምንሰማው፡፡ ስጋ ራሱን የሚያረካው በመናገር ነው፡፡
ስጋ ዝም ማለትና ማረፍ አይፈልግም፡፡ ስጋ ነገሮችን በንግግር መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ስጋ ለእግዚአብሄር ጊዜ መስጠት አይፈልግም፡፡ ስጋ ለእግዚአብሄር ስፍራን በመስጠት በዝምታ መጠበቅ አይፈልግም፡፡ ስጋ ዝምታን እንደ ሽንፈትና እንደ አቅመቢስነት ነው የሚያየው፡፡ አንደበቱን መግታት የማይችል ብዙ የሚለፈልፍ ሰው ካያችሁ በስጋው የተሸነፈ ሰው ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
ፀጥታ የመታመን ምልክት ነው፡፡ ፀጥ የሚለው እግዚአብሄር የልብን ጩኸት ይሰማል የሚል ሰው ነው፡፡ ፀጥ የሚል ሰው የህይወት ቁልፉ እግዚአብሄር ጋር እንጂ ሰው ጋር እንደሌለ የሚያምን ሰው ነው፡፡ ፀጥ የሚል ሰው የሰው ቁጣ የእግዚአብሄርን ፅድቅ እንደማይሰራ (ያዕቆብ 1፡20) የተረዳ ሰው ነው፡፡ ያልታመነ ሰው ይናወጣል፡፡ ያላመነ ሰው በፀጥታ መቀመጥ አይችልም፡፡
የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ ኢሳይያስ 30፡15
ሳንናወጥ በዝምታ እግዚአብሄርን መጠበቅ በእግዚአብሄር ላይ መደገፋችንን ያሳያል፡፡ በፀጥታ እግዚአብሄርን መጠበቃችን ለእግዚአብሄር ስፍራን መስጠታችንን ያሳያል፡፡ በፀጥታ መቀመጣችን "ካለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና" (ዮሐንስ 15፡5) ያለውን ቃል በማመን በእርሱ ላይ እርፍ ማለታችንን ያሳያል፡፡ ፀጥታችን እግዚአብሄር ምድርን እንደሚገዛ ማመናችንን ያሳያል፡፡
ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ። መዝሙር 46፡10
በዝምታ የሚኖር ሰው ሃይሉን ባላስፈላጊ መናወጥ አያባክንም፡፡ በእርግጥም በዝምታ እግዚአብሄርን የሚጠብቅ ሰው ሃይሉን እንደንስር ያድሳል፡፡
እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም። ኢሳይያስ 40፡31
የምናድርበት መንገድ ነው፡፡ ዝምታ ለእግዚአብሄር የምናመልክበት መንገድ ነው፡፡ ዝምታ ለእግዚአብሄር የምንገዛበት መንገድ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ልንከተለው ስለሚገባው ስለኢየሱስ ዝምታ መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ማቴዎስ 12፡18-19

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ዝምታ #ማረፍ #መታመን #መደገፍ #ፀጥታ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ