Popular Posts

Wednesday, May 2, 2018

ማስተዋሉም አይመረመርም

ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡17-18
የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሄር እኛን አያየንም መንገዳችንን አያውቅም፡፡ የእስራኤል ህዝብ እንደተረሱ እንደማይታዩ ተሰምቶዋቸው የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡
ስሜታችንን መስማት ባይኖርብንም አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሄር ሩቅ እንደሆነ እንደማይሰማ እንደማያይ እንደማይፈርድ የሚሰማን ጊዜ አለ፡፡ ትክክለኛውን ነገር እንዳረግን እየተሰማን ነገሮች እንደምንፈልጋቸው ሳይሄዱ ሲቀሩ እውነት እግዚአብሄር ያያል? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ሁሉንም ነገር ትክክል ካደረግን በኋላ ይሰምራል ያልነው ነገር እንዳሰብነው ሳይሰምር ሲቀሩ የሚሰማንን ስሜት ነበር የእስራኤል ህዝብን ይሰማው የነበረው፡፡
የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሄር ፍርድን አይፈርድም ብለው ያስቡ ነበር፡፡ በፅድቅ ኖሬ እግዚአብሄር ይፈርድልኛል ብሎ በሚያስበው ሁኔታ እግዚአብሄር ሳይፈርድ ሲቀር እስራኤል በእግዚአብሄር ላይ ይናገር ነበር፡፡ በትክክል ከኖረ በኋላ እግዚአብሄር ነገሮችን ያስተካክላል ብሎ ባሰበው ሁኔታ ነገሮች ስላልተስተካከሉ እስራኤል የተሰማው ስሜት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ነበር፡፡
አምላካዊ መልሱ ግን እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ ነው የሚል ነው፡፡ እግዚአብሄር መሪነትን እየተለማመደ ያለ ጀማሪ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር እየሞከረ እየተሳሳተ የሚለምድ ተለማማጅ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የማያወቀውን እያወቀ ልምድን በማካበት የተሻለ መሪ ለመሆን የሚጥር መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ ነው፡፡
ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን። 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡17
እግዚአብሄር ጠላቶቹን አሸንፎ የነገሰ ንጉስ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የዘመናት ንጉስ ነው፡፡  
እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ኤርሚያስ 10፡10
እግዚአብሄር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ውስጥ ያለውን ሁሉ ነገር የፈጠረና የሚያስተዳደር ነው፡፡ እግዚአብሄር የባህር ዳርቻን የወሰነ ነው፡፡
ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥ ምሳሌ 8፡29
የእግዚአብሄር ማስተዋሉ አይመረመርም፡፡ እግዚአብሄርንም ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት እኛ ራሳችን እግዚአብሄር መሆን አለብን፡፡ በፍጥረት አቅማችን እግዚአብሄን ሙሉ ለሙሉ አናውቀውም፡፡
እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም። ኢዮብ 36፡26
ሰው ማድረግ የሚችለው አንድ የተሻለ ነገር በእግዚአብሄር መልካምነትና ሃያልነት ላይ መደገፍ ብቻ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር በእርሱ ላይ ባለው የፍቅር አላማ ላይ ከመደገፍ በላይ ምንም ተስፋ የለውም፡፡
ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡17-18
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መኖሪያህእግዚአብሄር #እውቀት #ጥበብ #ሃይል #እንፍዋለት #አልፋ #ኦሜጋ #መጀመሪያ #መጨረሻ #ክርስትያን #አማርኛ #መደገፍ #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ፅድቅ #ማመን #አይመረመርም #ስልጣን

No comments:

Post a Comment