Popular Posts

Follow by Email

Friday, June 30, 2017

የንጉስ ልጅነት ክብራችን አይፈቅደውም

ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለልንን የሃጢያት እዳ ለእኛ ነው ብለን የተቀበልነው ሁላችን የእግዚአብሄር ልጆች ሆነናል፡፡ ንጉሱ እግዚአብሄር ወደቤተሰቡ ተቀብሎናል፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ የራሱ የሆነ ዋጋ አሰጣጥና የክብር ደረጃ እንዳለው ሁሉ በእግዚአብሄር ቤተሰብ ውስጥ የንጉስ ልጆች የሚያደርጉዋቸውና የማያደርጓቸው ነገሮች አሉ፡፡ የንጉስ ልጅነት ክብራቸው የሚፈቅደው ነገር አለ የንጉስ ልጅነታቸው ክብር የማይፈቅደው ነገር አለ፡፡
የንጉስ ልጅነታችን ክብር የማይፈቅዳቸው ነገሮች
1.      #ውሸት ክብራችን አይፈቅደውም
ውሸት ሰውን ለሚፈሩ በሰው ፍርሃት ወጥመድ ውስጥ ለወደቁ ሰዎች ነው፡፡ እኛ እግዚአብሄርን ብቻ እንጂ ሰውን አንፈራም፡፡ ውሸት ማንነታቸውን ላልተቀበሉ ያልሆኑትን ለመሆን በመሞከር ጭንቅ ውስጥ ላሉ ሰዎች ነው፡፡ ውሸት ከልጅነት ክብራችን ዝቅ ስለሚያደርገን አንፈቅድም፡፡ እውነት የማንናገርለት ጥቅም የእኛ ደረጃ ስላይደለ እንንቀዋለን፡፡
የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤ዘካርያስ 8፡16
2.     #መጣላት ክብራችን አይፈቅድም
ለጥቅማችን መጣላት ክብራችን አይፈቅደውም፡፡ የሚባርክ እግዚአብሄር ስለሆነ በጥቅማችን ቢጣሉንም ፈቀቅ እንላለን፡፡ ሰዎች ቢጣሉንም እንተዋለን፡፡ ሰዎች ቢጣሉን ፈቀቅ እንላለን፡፡  
ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጕድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርስዋም አልተጣሉም፤ ስምዋንም ርኆቦት ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል፦ አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን። ዘፍጥረት 26፡22
እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ማቴዎስ 12፡18-19
3.     #መጨቃጨቅ ክብራችን አይፈቅድም
በእግዚአብሄር እናምናለን፡፡ ለጌታ ጊዜን እንሰጣለን፡፡ ሁሉን ነገር በእኔ መንገድ ካልሆነ ብለን በራስ ወዳድነት አንመላለስም፡፡ ጥቅማችንን ከማስከበር ከሰው ጋር አንጨቃጨቅም፡፡ ጥቅማችንን ለማስከበር ሰዎችን አናሳድምም፡፡ ጥቅማችንን ለማስከበር ሰይፍ አንመዝም፡፡ ከጥቅማችን በላይ ለሌላው ሰው እናስባለን እንጠነቀቃለን፡፡ ለመንጋው የማይራሩ ተብሎ እንደተፃፈ ለጥቅማችን ሰውን አንጎዳም፡፡ ስንጠጣበት የነበረውን ምንጭ ለእኔ ካልሆነ ለማንም አይሁን ብለን አደፍርሰን አንሄድም፡፡  
የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 1 ጢሞቴዎስ 3፡3
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ያዕቆብ 4፡1-2
4.     የስስታምን ምግብ መብላት ክብራችን አይፈቅድም
የሰውን ስጦታ ከመቀበላችን በፊት ልቡን እናያለን፡፡ በልቡ ስስትና ቅንአት ይዞ ከሰጠን አንቀበልም፡፡ ብላ ብሎን ቆይቶ የሚከፋው ከሆነ እርሱን ማስደሰት የመጀመሪያ አላማችን ስለሆነ ባለ መብላት እናስደስተዋለን፡፡
የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። ምሳሌ 23፡6-7
5.     ትምክታችንን ከንቱ የሚያደርግብንን ነገር ለማድረግ ክብራችን አይፈቅድም
ወንጌልን የሚሰሩት ስለሚያገኙት ጥቅም እንጂ ስለጥሪ ብለው አይደለም እንዲሉ አንፈቅድም፡፡ ወንጌልን የመስራታችንን መነሻ ሃሳብ (motive) ከሚጠራጠሩ ሰዎች ማንኛውንም ጥቅም አንቀበለም፡፡ ማንም ትንሽ ነገር ቢጎድልበት ጥሎ ነው የሚሄደው እንዲል አንፈቅድለትም፡፡ ወንጌልን ስለጥሪ ብቻ መስበካችን ትምክታችን ነው፡፡ ይህንን ትምክታችንን ከንቱ ከሚያደርጉ ሰዎች ስጦታን አንቀበለም፡፡
እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡15
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡19
6.     የመበለቶችን ቤት መበዝበዝ ክብራችን አይፈቅድም
በነፃ ተቀብላችኋል በነፃ ስጡ የተባልነውን መንፈሳዊ ነገራችንን ከሰዎች ለመጠቀሚያ አናደርገውም፡፡ የእግዚአብሄርን መንፈሳዊ ስጦታ አንነግድበትም፡፡ ለሰዎች ጥቅም የተሰጠንን መንፈሳዊ ስጦታ በማካበድ የሰዎችን ቤት አንበዘብዝም፡፡ በመንፈሳዊ ነገራችንን ተጠቅመን ሰዎችን ለግላዊ ጥቅም መጠቀሚያያችን ለማዋል ክብራችን አይፈቅድም፡፡
የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። ማርቆስ 12፡40
7.     ማንም ባለጠጋ አደረግኩህ እንዲል ክብራችን አይፈቅድም
እኛን ባለጠጋ የሚያደርግ እግዚአብሄር ነው፡፡ ባለጠጋ የምንሆነው ከእግዚአብሄር ጋር ባለን ቃል ኪዳን ነው፡፡ የእግዚአብሄን ምስጋና እንዲወስድ ማንም አንፈቅድም፡፡ ሰው የሆነ ነገር አድርጎልን አሳለፍኩለት በማለት የእግዚአብሄርን ምስጋና እንዲወስድ ምክኒያትን አንሰጥም፡፡ ስለእኛ መነሳት እግዚአብሄር ብቻውን ሊከበር ስለሚገባ ምስጋናውን ሊቀላቅል ከሚፈልግ ከማንኛውም ሰው አንቀበልም፡፡    
አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤ አንተ፦ አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ። ዘፍጥረት 14፡22-24
8.     ነውረኛ ጥቅምን አንወድም
በአራዳም በፋራም ብለን ጥቅምን አናሳድድም፡፡ ንፁህ ጥቅምን ብቻ እንቀበላለን፡፡ ነውረኛ ጥቅምን እንንቃለን፡፡ ጥቅም መምጣቱን ብቻ ሳይሆን የመጣበትንም መንገድ እናያለን፡፡ በንፁህ መንገድ የመጣውን እንቀበላለን በንፁህ መንገድ ካልመጣ ለክብራችን አይመጥንምና አንቀበልም፡፡ በነውር መንገድ የሚመጣ ጥቅምን እንንቃለን፡፡ ሰዎችን አታለን ተቆጣጥረን በመንፈሳዊ ስም አደናግረን እንዲሁም በመናገር ችሎታችን አዋክበንና የማይፈልጉትን አሳምነን ለመጠቀም የንጉስ ልጅነታችን ክብር አይፈቅድም፡፡  
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል።  1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እግዚአብሔር #አምላክ #ክብር #ምሪት #ሰላም #ቃል #እረፍት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Tuesday, June 27, 2017

ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የማይቻልበት 7 ምክኒያቶች

ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
1.      የሚታየው ሁሉ ከማይታየው ስለሆነ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማንችለው የሚታየው ነገር ሁሉ ምንጩ የማይታየው አለም መሆኑን ማመን ስለሆነ ነው፡፡ እምነት የሁሉም ነገር ምንጭ የሆነው የማይታየው ነገር ላይ ማተኮር  ነው፡፡ እምነት የማይታየው ነገር ላይ ለማተኮር የሚታየው ነገር ላይ አለማተኮት ነው፡፡ እምነት የሚታየውን አለመመልከት የማይታየውን መመልከት ስለሆነ ነው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
2.     አስፈላጊና ጉዳዬ ልንለው የሚገባው የማይታየውን ስለሆነ ነው
ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማይቻለው የማይታየውን ባንመለከት ሁሉን ነገር ስለምናጣ ነው፡፡ የሚታየውን ባንመለከት ምንም የምናጣው ነገር የለም፡፡ አስፈላጊው ነገር የማይታየው ነገር ነው፡፡ ህይወትን የሚሰጠው የማይታየው መንፈስ ነው፡፡ የህይወት ቁልፋችን ያለው በማይታየው ነገር ውስጥ ነው፡፡ የማንኛውም የህይወት ጥያቄያችንን የሚመልሰው የማይታየው ህይወትና መንፈስ የሆነው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ዮሃንስ 6፡63
3.     የማይታየው ወደሚታየው ለመምጣት ትግስት ስለሚጠይቅ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው የእምነት ውጤት ቅፅበታዊ ስላይደለ ነው፡፡ በመንፈሳዊ አለም ያለው ነገር ወደ ተፈጥሮአዊ አለም እንዲመጣ ትግስት ይጠይቃል፡፡ ትግስት ደግሞ ራስን መካድና ትህትናን ይጠይቃል፡፡   
በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። እንዲሁም እርሱ ከታገሰ በኋላ ተስፋውን አገኘ። ዕብራውያን 6፡11-12፣15
4.     የሚታየውን ማንም ሰው ማየት ስለሚችል ነው ፡፡
ያለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማይቻለው እምነት የማይታየውን በማየት በማይታየው ላይ ማተኮር ስለሆነ ነው፡፡ የሚታየውን ለማየት ጥረት አያስፈልግም፡፡ የማይታየውን ለማየት ግን በመጀመሪያ ኢየሱስን አዳኝ አድርጎ በመቀበል ከእግዚአብሄር መወለድ በመቀጠልም እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ፈቃድ ከቃሉ ፈልጎ ማግኘት እንዲሁም በፈቃዱ ላይ መቆም ይጠይቃል፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
5.     የእግዚአብሄርን ተስፋ ብቻ በመያዝ ስለሆነ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው እምነት በእግዚአብሄር ተስፋ ላይ ብቻ መቆም ስለሆነ ነው፡፡ እምነት ሌሎች ተስፋዎች አያስፈልጉትም፡፡ እምነት የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል በቂው ነው፡፡ እምነት ዝናብና ንፋስ አይደግፉትም፡፡
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። ሮሜ 4፡18
ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም። ሮሜ 4፡20-21
እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 2ኛ ነገሥት 3፡17
6.     እምነት ትጋትን ስለሚጠይቅ ነው
ካለ እምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው እምነት ትጋትን ስለሚጠይቅ ነው፡፡ እምነት የሚመጣው ከእግዚአብሄር ቃል ስለሆነ እምነት የእግዚአብሄርን ቃል መፈለግ ማሰላሰል መናገርና ማድረግ አድርጎም መታገስ ስለሚጠይቅ ነው፡፡ እምነት ሰነፎች እንደ እድል እጄ ይገባ ይሆናል ብለው የሚመኙት ነገር አይደለም፡፡ እምነት ተጋድሎ ነው፡፡
መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ዕብራውያን 10፡36
7.     የእምነት ምስክርነት እውነተኛ ምስክርነት ስለሆነ ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት የማይቻልበት ምክኒያት ሰው በእምነቱ ካልተመሰከረለት በምንም ነገር ሊመሰከርለት ስለማይችል ነው፡፡ በእምነቱ የተመሰከረለት ሰው ደግሞ በሁሉም ነገሩ ይመሰከርለታል፡፡ ምንም ነገር ብናደርግ ካለእምነት ከሆነ ሃጢያት ስለሆነ ነው፡፡(ሮሜ 14፡23) የሰው እውነተኛ ምስክርነት የእምነት ምስክርነት ነው፡፡
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና። ዕብራውያን 11፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የሰራዊት ጌታ እንደዚህ ይላል

የሰራዊት ጌታ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡፡ ትታመኑብኝ አልነበረምን? ሁሉን ጥላችሁ ተከትላችሁኝ አልነበረምን? ከእኔ ውጭ መተማመኛ ሳትፈልጉ አላገለገላችሁኝምን?
ታዲያ እኔን ታምናችሁ በወጣችሁ ጊዜ ምን ጎደለባችሁ? ታዲያ በላክኋችሁ ጊዜ ምን አጎደልኩባችሁ ይላል እግዚአብሄር? ያላደረግኩላችሁ ነገር ነበርን ይላል የሰራት ጌታ እግዚአብሄር?
ታዲያ አሁን ከእኔ ውጭ ደህንነትን ለምን ፈለጋችሁ? ታዲያ በቁሳቁስና በገንዘብ ደህንነትን ለምን ፈለጋችሁ ይላል እግዚአብሄር? ቦዶ እጃችሁን እንዳልተከተላችሁኝ ያላችሁ ለምን አልበቃ አላችሁ ይላል እግዚአብሄር? እኔ አልለወጥም ይላል እግዚአብሄር፡፡
ስትደገፉብኝ ፣ ፊቴን ስትፈልጉ ፣ ጌታ ጌታ ስትሉኝ ያረካኛል ይላል እግዚአብሄር፡፡ በእኔ ተደገፉብኝ ፣ እኔ ብቻ ደህንነታችሁ ልሁን ይላል እግዚአብሄር፡፡ ያላችሁ ምንም ነገራችሁ ደህንነት አይሁናችሁ ይላል እግዚአብሄር፡፡  
አሁንም ተመለሱ ይላል እግዚአብሄር፡፡ ቁሳቁስን ገንዘብን ከመፈለግ እኔን ፈልጉ ይላል እግዚአብሄር፡፡ በእኔ ውስጥ የህይወታችሁ ጥያቄ ሁሉ መልስ አለ ይላል እግዚአብሄር፡፡ የምትፈልጉት ሁሉ እኔ ውስጥ አለ ይላል እግዚአብሄር፡፡
እኔ አልለወጥም፡፡ እስከ ሽምግልና የምሸከምህ እኔ ነኝ ይላል እግዚአብሄር፡፡
ባላችሁ ነገር ሳይሆን በእኔ ላይ ስትደገፉ ደስ ይለኛል ይላል እግዚአብሄር፡፡ በእኔ ላይ ስትደገፉ ብቻ ያረካኛል ይላል እግዚአብሄር፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, June 26, 2017

የእውነተኛ ህይወት ብልጫ

እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። 1 የጴጥሮስ 3:1-2
አኗኗር ያሳምናል፡፡ ህይወት ይሰብካል፡፡ ሰዎች ሲሰበክላቸው እውነት ነውን ብለው የሰዎችን ኑሮ ነው የሚያዩት፡፡ የሰዎቹ ህይወት ከሚናገሩት አብሮ ካልሄደ ሰዎች አይቀበሉም፡፡ የህይወት ብላጫ እንደንግግር ብልጫ የማያከራክር ብልጫ ነው፡፡
ክርስትና ህይወት ነው፡፡ ክርስትና ክርስቶስን መከተል ነው፡፡ ክርስትና ለሞተልን ለእርሱ መኖር ነው፡፡ ክርስትና ብልጫ አለው፡፡ ብልጫ የሌለው ነገር ባዶ ሃይማኖት እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡
ይህ ሁሉ የሚሆነው በሚያስችል በእግዚአብሔር ፀጋ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር አብረን ለመስራት ግን አሰራሩን ማወቅ አለብን፡፡
1.      እውነተኛ የሚበልጥ መስጠት የሚለካው ከጉድለት ነው፡፡
በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። 2ኛ ቆሮንቶስ 8፡2-3
ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው። ማርቆስ ወንጌል 12፡43-44
2.     እውነተኛ የሚበልጥ ፍቅር የሚለካው ጠላትን በመውደድ ነው፡፡
እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። ማቴዎስ 5፡44-45
3.     እውነተኛ የሚበልጥ ትህትና የሚለካው ታናናሾችን በመቀበል ነው፡፡
እውነተኛ ትህትና ሰዎች በሚወድቁበትና በሚደክሙበት ጊዜ መሸከም እና መንከባከብ ነው፡፡
እንደዚህ ካሉ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን እንጂ እኔን አይቀበልም አላቸው። ማርቆስ 9፡37
4.     እውነተኛ የሚበልጥ እምነት የሚለካው የሚታይ ነገር በሌለ ጊዜ ነው፡፡
እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 2ኛ ነገሥት 3፡17
5.     እውነተኛ የሚበልጥ ድፍረት የሚለካው በሞት ጥላ መካከል ነው፡፡
የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። ዕብራውያን 10፡34-35
6.     እውነተኛ የሚበልጥ አምልኮ በእስርና በስቃይ መካከል ነው፡፡
በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ሐዋርያት 16፡23-25
7.     እውነተኛ የሚበልጥ ጥንካሬ የሚለካው በፈተና ቀን ነው፡፡
በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ምሳሌ 24፡10
8.     እውነተኛ የሚበልጥ ፀጋ የሚለካው በሁለተኛው ምእራፍ ነው
እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ማቴዎስ 5፡40-41
9.     እውነተኛ የሚበልጥ ምስጋና በወጀቡ መካከል ማመስገን ነው፡፡
ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት ሠዋ፥ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ፤ ምስጋና የሚሠዋ ያከብረኛል፤ የእግዚአብሔርን ማዳን ለእርሱ የማሳይበት መንገድ ከዚያ አለ። መዝሙር 50፡14፣23
10.    እውነተኛ የሚበልጥ ደስታ በጌታ እንጂ በሁኔታ አይደለም፡፡
ሰሙትም፥ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ሐዋርያት 5፡40-41
ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። ማቴዎስ 5፡11-12
11.     እውነተኛ የሚበልጥ ሰላም በወጀብ መካከል ነው፡፡
ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም፦ መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት። ማርቆስ 4፡37-38
አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። ፊልጵስዩስ 4፡7
12.    እውነተኛ የሚበልጥ ታላቅነት የሚለካው ለትንንሾች ያለ ዋጋ ከፍተኝነት ነው፡፡
ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ዝቅተኛ ኑሮ ወይም ዝቅተኛ ሥራ ለመሥራት ፍቀዱ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ሮሜ 12፡16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #መስጠት #እረፍት #ሰላም #ትህትና #ድፍረት #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ብልጫ #እምነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #ፍቅር #መፅሃፍቅዱስ #በደስታ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ