Popular Posts

Showing posts with label Amharic. Show all posts
Showing posts with label Amharic. Show all posts

Wednesday, August 12, 2020

አንተን ካገኘሁ ጀምሮ ህይወቴ በአንተ አምሮ

 

አንተን ካገኘሁ ጀምሮ
ህይወቴ በአንተ አምሮ
የምህረትን ብዛት አልችልም ልገልጣት
የፍቅርህን ብዛት አልችልም ልገልጣት
ዘማሪ አገኘሁ ይደግ

Monday, June 29, 2020

እግዚአብሔር ትልቅ ዘማሪት ህሊና ካሳሁን



እግዚአብሔር
ትልቅ (Egziabhier
Teleq) - ህሊና ካሳሁን

ችግር
ምንድን ነው ከሙላትህ ፊት ሲቆም
ጭንቀት
ምንድን ነው ከሰላምህ ፊት ሲቆም
ድካም
ምንድን ነው ከጉልበትህ ፊት ሲቆም
ማጣት
ምንድን ነው ከዙፋንህ ፊት ሲቆም

ይሟሟሉ
ይቀልጣሉ መገኘትህን ሲረዱ
የከበዱት
ዙፋን ስጡኝ ያሉ
ለቀው
ሄዱ እያፈሩ (x)

እግዚአብሔር
ትልቅ (x)

ከተራራው
በላይ ትልቅ
ከከበደው
በላይ ትልቅ
ከነገሩኝ
በላይ ትልቅ
ከችግሩ
በላይ ትልቅ

መንፈስ
ቅዱስ ትልቅ (x)

ከጨነቀኝ
በላይ ትልቅ
ከነገሩኝ
በላይ ትልቅ
ከሰበክነው
በላይ ትልቅ
ካመለኩት
በላይ ትልቅ

የሰልፉ
አለቃ ብቻህን ምትገዛ
ምድርን
ፍጥረትን በቃልህ ያጸናህ (x)
ዕድሜ
ማይወጣልህ ኃይልህ አይለካ
ምሽግ
መጠለያ ክንድህ የበረታ (x)

ገብተህ
በእኔ ጓዳ (x)
ኧረ
ለምን ልፍራ

መንፈስ
ቅዱስ ትልቅ ()

ከጨነቀኝ
በላይ ትልቅ
ከነገሩኝ
በላይ ትልቅ
ከሰበክነው
በላይ ትልቅ
ካመለኩት
በላይ ትልቅ

Tuesday, June 23, 2020

በምድራዊ እውቀት የማይደረስበት መንፈሳዊ ክልል



ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

በህይወታችን ላይ የሚነጣጠሩ ብዙ ጥቃቶች ከምናስበው በላይ መንፈሳዊ ናቸው፡፡

ለምሳሌ የጤና መታወክ ሲደርስብን ቶሎ የሚመጣልን የሳይንሱ እውቀትና የሳይንሱ መፍትሄ ነው፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን ቁሳዊ እናደርገዋለን፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን በህክምና እውቀት ብቻ ልንተረጉመው እንፈተናለን፡፡

የበላሁት ምግብ ነው ወይም ቫይረስ ነው ብለን እንደሰው ልማድ ብቻ ጥቃቱን ልንዋጋው እንፈልጋለን፡፡ እንደሰው ልማድ ተዋግተን ከተሳካልን እሰየው፡፡ የሰይጣን ስራ ለማፍረስ ያለንን ነገር ሁሉ እምነታችን እና እውቀታችንን ሁሉ እንጠቀማለን፡፡

እንደሰው ልማድ ብቻ ከመዋጋት ያለፈ ነገር የሚጠይቅ ብዙ የዲያቢሎስ ጥቃት አለ፡፡  

የሰው ልጆች ጥቃት በቀጥታ ባይሆንም ቢያንስ በተዘዋዋሪ ከሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን ሌላ ራእይ የለውም፡፡ ራእዩ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ብቻ ነው፡፡

ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። የዮሐንስ ወንጌል 10፡10

አንዳንዴ ሰይጣን በመንፈሱ በቀጥታ ባያጠቃንም ማድረግ ያለብንን ነገር በቸልተኝነት እንዳናደርግ በአእምሮዋችንም ቢሆን ያጠቃናል፡፡ ወይም የእግዚአብሄርን አላማ በምድር ላይ እንዳንፈፅም በፍርሃት ሽባ ያደርገናል፡፡ ሌላም ጊዜ በፀጋ ከተቀበልነው በሽታን በእኛ ላይ ሊያደርግ ይሞክራል፡፡

ተዘዋዋሪ የሰይጣን አላማ ቢሆኑም ንፅህናን ባለመጠበቅ የሚመጡ በሽታዎች ከሰይጣን አላማ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ጥንቃቄያችንንም ተጠቅሞ ከጠላት ጥቃት ያስመልጠናል፡፡

ተጠንቅቀንም እግዚአብሄር አስመለጠን ነው የምንለው እንጂ ጥንቃቄያችንም ፍፁም በማይሆነው በጥንቃቄያችንም አንታመንም፡፡

እግዚአብሄር ለእኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለደህንታችን ያለውንም ነገር ሁሉ ይጠቀማል፡፡ እግዚአብሄር የዶክተሮችን ጥበብ ተጠቅሞ በሽታን ይዋጋልናል፡፡ የዲያቢሎስን ስራ ለማፍረስ ያለንን ምድራዊ እውቀት እና መንፈሳዊ እውቀርት ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ ሰይጣን በህይወታቸን በጤናችን ምንም ስፍራ እንዳያገኝ እስከመጨረሻው ፀንተን እንቃወመዋለን፡፡

በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡9

ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፡8

ከዶክተሮች እውቀት በላይ ያለ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ዶክተሮች በምድራዊ ጥበባቸው የማይደርሱበት መንፈሳዊ ክልል አለ፡፡

ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።  1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡14

እግዚአብሄር እምነታችንን ተጠቅሞ ከበሽታው ጀርባ ያለውን መንፈሱን በኢየሱስ ስም እንድንቃወመው አይናችንን ይከፍታል ይመራናል፡፡

ይህችን ሴት በወቅቱ ዶክተሮች ጋር ብትታይ ዶክተሮች በምድራዊ እውቀታቸው የማይረዱት መንፈሳዊ ክልል ስላለ ስለበሽታዋ አንድ ምክኒያት ይሰጧታል፡፡  

ኢየሱስ ግን ከዚህ በሽታ ጀርባ ያለውን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣውን ሰይጣንን አየው፡፡ ኢየሱስ በሽታውን ሳይሆን ከበሽታው በስተጀርባ ያለውን የበሽታውን ምንጭ አደረቀው፡፡

ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


Sunday, June 21, 2020

ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። መጽሐፈ መክብብ 3፡12-13 ፣ 8፡5

ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። መጽሐፈ መክብብ 3፡12-13 ፣ 8፡5

Monday, June 15, 2020

እግዚአብሔር የሚቀጣው እንዲበድል ያደረገውን ስጋዊ ፍላጎት ነው


ብዙ ሰዎች በደልን እንዴት እንደሚይዙ ስላማያውቁ በህይወታቸው ዘመን ይሰቃያሉ፡፡ ገንዘባችንን እንዴት እንድምንይዝ ፣ ጤናችንን እንዴት እንድምንጠበቅ ፣ ስራችንን እንዴት እንደምንሰራ የመሳሰሉትን ከምናውቀው እውቀት በላይ ከሰው ጋር እንዴት እንድምንኖር ማወቅ ከብዙ ኪሳራ ከብዙ የስሜት በሽታ ብሎም ከብዙ ችግሮች ይጠብቀናል፡፡

ሰውን እንድናምን ከሰው ጋር እንድንኖር ተፈጥረናል፡፡ ሰው ጠቃሚ እንደመሆኑም መጠን ግን በተለያየ ጊዜም ይበድለናል፡፡

ሰው አውቆም ይሁን ሳያውቅ ሰውን ስለሚበድል ሰው ሰውን የመበደሉ እውነት የማይቀር ነገር ነው፡፡ ዋናው ነገር ሰው ሰው ሰውን ይበድላለ ወይ የሚለው ጥያቄ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር የተበደለው ሰው በደሉን እንዴት ይይዘዋል የሚለው ጥያቁ ነው፡፡ ሰው ለበደል እንዴት እንደሚመልስ ካወቀ ያርፋል፡፡

ሰው በደሉን በትክክል ከያዘው ይማርበታል ያድግበታል የተሻለ ሰው ሆኖ ይለወጥበታል፡፡ ሰው በደሉን በትክክል ካልያዘው ይሰቃይበታል ህይወቱን ያባክንበታል፡፡

ሰው ሲበድለን በመጀመሪያ ደረጃ ነፃ የሚያወጣን ነገር ስለበደሉ የተቻለንን ያህል ሃላፊነት መውሰዳችን ነው፡፡ እርሱ 100 % ጥፋተኛ ነው እኔ 0% ጥፋተኛ ነኝ የሚለው ነገር አያዋጣም፡፡ ቢያንስ ሲያጠፋ እኛ ጥፋቱን የመለስንበት መንገገድ ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡

ሁለተኛ እግዚአብሄር የሚቀጣው የበደለውን ሰውዬ ሳይሆን እንዲበድል ያደረገውን ስጋዊ ፍላጎት ነው፡፡

ሶስተኛ ማወቅ ያለብን እርሱን እንዲበድል ያደረገው ያው ስጋዊ ፍላጎት እኛም ውስጥ እንደሚኖር አውቀን ትምህርትና ግሳፄ መውሰድ ነው፡፡ እኔ እንደዚህ መበደል አልችልም ማለት ሞኝነት ነው፡፡ በበዳዩ ውስጥ ያየነውን የስጋ አስከፊነት ካየን እኛ ውስጥ ያለው ስጋ በሌሎች ላይ ተመሳሳይ በደል እንዳያደርግ እንጨክንበታለን፡፡

አራተኛ የበደለን ሰው እስኪወድቅ አለመጠበቅ ነው፡፡ ሰው ስራውን ትቶ የበደለኝ ሰው ከመቼ መቼ ይቀጣል እያለ ስለበደለው ሰው የሚከታተል ከሆነ የራሱን የህይወት አላማ ትቶ ስቶዋል ማለት ነው፡፡ ከበደለው ሰው ጋር በመፎካከር የህይወት አላማውን አሽቀንጥሮ የሚጥል ሰው የህይወት አላማው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የማያውቅ ሰው ነው፡፡

የበደለ ሰው ስጋ በአስቸጋሪ ነገር ውስጥ በማለፍ የስጋ ፍላጎቱ ሊገደል ይችላል፡፡ በደል ያስደረገው ያ ስጋዊ ፍላጎት ዛሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በምን መጠን በምን ሁኔታ ይቀጣ አታውቅምና ትተኸው ህይወትህን ኑር፡፡

ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡19

አንተን ስለበደለህ እንዲጠፋ ከመፈለግ ይልቅ ሰው እንዲለወጥ እንዲሻሻል እንዲመለስ ፀልይለት፡፡ አንተን ስለበደለ እንዲቀጣ ብቻ ሳይሆን በዚህ አጋጣሚ እንዲመለስ እንዲስተካከል ፈልግ፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡1

አንተ የበደለህ ሰው እርዳታህን በሚፈልግበት ጊዜ መርዳትህ እንዳልበደለህ አይናገርምና እርዳው፡፡ የበደለ ሰው ይታዘንለታል እንጂ አይቀናበትም፡፡

ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡20

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #ምህረት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 


Sunday, April 26, 2020

በምድር ያለነው


በተለያየ ጊዜ በህይወታችን የተለያዩ ተግዳሮቶች ይመጣሉ፡፡ ታዲያ ይህን አልፈው ይሆን ብለን የምናስብበት ውጥረት በህይወታችን ይመጣል፡፡ እንደዚህ አይነት ውጥረት በህይወታችን ሲገጥመን "በምድር ላይ ያለሁት ለምንድነው?" ብለን ይህን ጥያቄ ከልባችን እንጠይቃለን፡፡
በምድር ላይ ያለሁት ለምንድነው? የሚለው ጥያቄ ሁል ጊዜ መጠየቅና በትክክል መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
እውነት ግን በምድር ላይ ያለነው ለምንድነው?
የማንሞተው ለምንድነው ? ወይም መሞት የማንፈልገው ለምንድነው ?
በምድር ላይ ያለነው ስላልሞትን ነው ? ወይስ በምድር ላይ ስለመኖራችን ሌላ አለማ አለ?
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው አስቦና አቅዶና በአላማ ነው፡፡
እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ኦሪት ዘፍጥረት 1፡26-27
ወደምድር ከመምጣታችን በፊት ወደምድር የመጣንበት ልዩ አላማ ነበር፡፡
ማንም ሰው በድንገት ውይም በአጋጣሚ በምድር ላይ የተወለደ ሰው የለም፡፡ ሰው በምድር ላይ የመወለዱ ምልክት ከመወለዱ በፊት የተወለደበት ልዩ አላማ የመኖሩ ምልክት ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርሚያስ 29፡11
እኛ በምድር ላይ ለመኖር ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር በምድር ላይ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በምድር ላይ ለመኖር ካለን ፍላጎት በላይ በምድር ላይ እንድንኖር የተፈለገበት የእግዚአብሄር አላማ ይበልጣል፡፡
በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። ምሳሌ 19፡21
በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። ኢሳያስ 46፡10
ይህን በህይወታችን ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ ስንረዳ እናርፋለን፡፡
እግዚአብሄር እንዴት እንደሚወደን ስንረዳ እና በህይወት ለመኖራችን ልዩ አላማ እንዳለው ስንረዳ ከፍርሃት ነፃ እንወጣለን፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡18-19
ፍርሃት የእግዚአብሄርን ፍቅር የመረዳታችንን ደረጃ ያመለክታል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያለውን የፍቅር አላማ በተረዳን መጠን ፍርሃት ከህይወታችን ቦታ እያጣ ይሄዳል፡፡  
የእግዚአብሄርን ፍቅር በተረዳን መጠን ከፍርሃት ነፃ እንወጣለን፡፡ እግዚአብሄር እንዴት በፍቅር እንደሚያየን በህይወታች ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን የፍቅር አላማ እየተረዳን ስንመጣ በፍርሃት ሳይሆን በፍቅር እንንቀሳቀሳለን፡፡
የእግዚአብሄርን የፍቅር አለማ ስንረዳ የሚያንቃቅሰን ፍርሃት ሳይሆን ፍቅር ብቻ ይሆናል፡፡
በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 2፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አላማ #ተስፋ #ፍፃሜ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተስፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11


Thursday, April 23, 2020

እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል። አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ። የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል። እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል። አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ። እግዚአብሔርም በላይህ የሚቆሙትን ጠላቶችህን በፊትህ የተመቱ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፥ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ። እግዚአብሔር በረከቱ በአንተ ላይ በጐተራህ በእጅህም ሥራ ሁሉ እንዲወርድ ያዝዛል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል። የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። የምድር አሕዛብም ሁሉ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል። እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥህ ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው በምድርህ ላይ፥ በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ እግዚአብሔር በጎነቱን በላይህ ያበዛል። እግዚአብሔርም ለምድርህ በወራቱ ዝናብ ይሰጥ ዘንድ፥ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለብዙ አሕዝብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም። ዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም። ኦሪት ዘዳግም 28፡1-14


Tuesday, April 14, 2020

በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። መዝሙረ ዳዊት 118:8

በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። መዝሙረ ዳዊት 118:8

Saturday, April 4, 2020

ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?


ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? 1 የዮሐንስ መልእክት 4:20
ፍቅር ረቂቅ ሃሳብ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን እወደዋለሁ ቢል እግዚአብሄርን አትወድም ብለን መከራከር አንችልም፡፡ ሰው እግዚአብሄርን እወዳለሁ ሲል እውነተኝነቱን በቀጥታ ለማረጋገጥ ቀላል አይደለም፡፡ ምክኒያቱም ፍቅር የልብ ስለሆነና የሰው ልብ ደግሞ ተከፍቶ ስለማይታይና ስለማይታወቅ ነው፡፡
ፍቅር የልብ መሰጠት ስለሆነ ሰው እግዚአብሄርን መውደዱ የሚረጋገጥበት ቀጥተኛ መንገድ የለም፡፡ ሰው እግዚአብሄርን መውደዱንና አለመውደዱን በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የሚያመለክቱ ነገሮች ግን አሉ፡፡ እኛም እግዚአብሄርን እንዴት እንድምንወድ የምንፈትንባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ፡፡
ሰው እግዚአብሄርን መውደዱ መለኪያው ሰውን መውደዱ ነው፡
ሰውን የመውደድ ጥቂቱን መመዘኛ የማያማላ ሰው እግዚአብሄርን እወዳለሁ ቢል ውሸቱን ነው፡፡ ሰው የሚያየውን ሰው ካልወደደ የማያየውን እግዚአብሄርን እንደማይወድ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡
ለሰው ቅርቡ የሚያየውን ሰውን መውደድ ነው፡፡ ለሰው የሚቀለው ለሚያየው ሰው መልካምን ማድረግ ነው፡፡ ለሰው የሚቀለው የሚያየውን ሰውን በርህራሄ ማየት ነው፡፡ ለሰው የሚቀለው የሚያየውን የሚዳስሰውን ሰውን መቀበል ነው፡፡ ለሰው የሚቀለው የሚያየውን ሰውን መታገስ ነው፡፡ ለሰው የሚቀለው ከሚያየውን ሰው ጋር በትህትና መኖር ነው፡፡
ሰው እግዚአብሄርን እወዳለሁ እግዚአብሄርን አከብራለሁ የሚለው ለእግዚአብሄር ያለን አክብሮት ለሰው እንዳለን አክብሮት በቀጥታ የማይታይ ስለሆነ ይሆናል፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ፍቅር አለኝ የሚለው ስለማይታይ ይሆናል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ፊት ትሁት ነኝ የሚለው በቀጥታ ትህትናው በቀጥታ ስለማይለካ ይሆናል፡፡
ሰው ለሚያየው ሰው መልካምን ካላደረገ ለእግዚአብሄር መልካም ያደርጋል ማለት ዘበት ነው፡፡ ሰው የሚያየውን ሰውን ካልተቀበለ የማያየውን እግዚአብሄርን ይቀበላል ማለት ውሸት ነው፡፡ ሰው የሚያየውን ሰውን በርህራሄ ካላየ የማያየውን እግዚአብሄርን ይወዳል ማለት ከንቱ ነው፡፡ ሰው የሚያየውን ሰው ካልታገሰ እግዚአብሄርን እታገሳለሁ ማለቱ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ሰው ከሚያየው ከሰው ጋር በትህትና መኖር ካልቻለ እኔ በእግዚአብሄር ፊት ትሁት ነኝ ቢል ተታልሎዋል፡፡
ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4:20
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ሰላም #እምነት #ሃሳብ #ጥበብ #ማስተዋል #ፍቅር #ትህትና #ርህራሄ #መልካም #ጠብ #መልካም #ፍርድ #እውቅና #ፍፁም #ችግር #መፍትሄ #አላማ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, March 20, 2020

እግዚአብሔር ተቀብሎታል


በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ። ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደ ተፈቀደለት የሚያምን አለ፥ ደካማው ግን አትክልት ይበላል። የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 14:1-3  
በዚህ ጊዜ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ መከላለያ መንገዶች መካከል በክርስትያኖች መካከል መለያየት ይታያል፡፡ መለያየት በራሱ ክፉ አይደለም፡፡ መለያየትን ተመስርቶ እርስ በእርስ መናናቅ እና መፈራረድ ግን ክፉ ነው፡፡
1.       ተጨማሪ ቫይታሚን የሚወስደው የማይወስደውን አይፍድበት፡፡
2.       ሆስፒታል ሔዶ የሚመረመረው የማይመረመረውን አይናቀው፡፡
3.       የፊት መሸፈኛ ወይም ጓንት የሚያደርገው የፊት መሸፈኛ የማያደርገው ላይ አይፍረድበት
4.       የቤተክርስትያንን ስብሰባ የሚካፈለው የማይካፈለውን አይናቀው፡፡
5.       የሚጨብጠው የማይጨብጠውን አይናቀው፡፡  
6.       ከቤቱ የሚወጣው የማይወጣውን አይፍረድበት፡፡  
አንተም በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። ወደ ሮሜ ሰዎች 14፡10
እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3፡15-16
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ