Popular Posts

Sunday, May 17, 2026

የምንሞትለት እንጂ የምንገድልለት አምላክም ሆነ ሀይማኖት የለንም!

 የምንሞትለት እንጂ የምንገድልለት አምላክም ሆነ ሀይማኖት የለንም! 


አምላክ ሀያል ነው የእኛ እርዳታ አይፈልግም። እንዲገድሉለት የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት እውነተኛ ሀይማኖት አይደለም። የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት ሀሰተኛ ሀይማኖት ነው። የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት ከሰይጣን ነው። 

ብዙ ሀይማኖቶች በምድር ላይ ቢኖሩም በአጠቃላይ ምድር ላይ ያሉት ሁለት አይነት ሀይማኖቶች ብቻ ናቸው። በምድር ላይ እውነተኛ እና ሀሰተኛ ሀይማኖት አለ። እግዚአብሔር አንድ ነው። ከአንድ በላይ እውነተኛ ሀይማኖት ሊኖር አይችልም። በአለም ላይ ከአንድ በላይ  ሀሰተኛ ሀይማኖት ሊኖር ግን ይችላል። 

ታዲያ ሀይማኖት መያዙ ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ መያዛችንን እርግጠኛ እንሁን። እኔን በተመለከተ ፍለጋ አቁሜያለው እውነተኛውን አምላክ አግኝቻለሁ።

እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። ዮሐንስ 17:3 ሁሉም ሀይማኖት ወደ አንድ ፈጣሪ ያደርሳል የሚሉ በሰይጣን የተታለሉ ናቸው። 

ኢየሱስም አለው፡— እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ዮሐንስ 14:6 

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 

Sunday, April 12, 2026

ከእርሱ ጋር አስነሣን !



ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፣6 7

ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ስለእኛ ነው። ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው እኛ በሃጢያታችን ምክኒያት ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላላም እንዳንለያይ ነው።

ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፣21 22

ክርስቶስ ኢየሱስ የሞተው እኛ በሃጢያታችን መሞት የነበረበንን ሞት ነው። ክርስቶስ የሞተው በእኛ ምትክ ነው። ክርስቶስ የሞተው ለእኛ ነው።

በመጀመሪያ ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላላም እንዲኖር ነበር። በእግዚአብሔር የተፈጠረው ሃጢያትን የማያውቅ  ፍጹም ሰው ነበር።

ሰው ከእግዚአብሔር የተለየው ሃጢያት በሰራ ጊዜ ነበር።

እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፣16  17

ክርስቶስ የመጣው እኛ ወደፊት እንዳንሞት ከእግዚአብሔርም ጋር ለዘላላም እንዳንለያይ ነው።

ክርስቶስ ሃጢያት ያልተገኘበት ፍጹም ነው። ክርስቶስ መሞት አይገባውም  ነበር። ክርስቶስ የሞተው እኛ ሞት ሰለሚገባን ነበር። ክርስቶስ የሞተው እኛን ከሞት ሊያስነሳን በእኛ ምትክ ነው።  

ክርስቶስ የሞተው ለእኛ ትንሳኤን ሊሰጠን ነው።

እኛ ከክርስቶስ ጋር አብረነው ካልተነሳን ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።

የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ "ከእለታት አንድ ቀን ክርስቶስ ከሞት ተነሳ" ብለን ብቻ የምናስታውሰው የክርስቶስ ታሪክ አይደለም። የክርስቶስ ትንሳኤ የእኛም ከሙታን የመነሳት ልምምድ ነው። በክርስቶስ ሞትና ተንሳኤ የምናምን ሁላችን ከሞት ተነስተናል።

ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፣5-7

የትንሳኤ በአል የክርስቶስ ብቻ ሳይሆን የእኛም የትንሳኤ በአል ነው።

መልካም የትንሳኤ በአል

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa