Popular Posts

Saturday, May 20, 2017

የእምነት ጋሻ

የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ ኤፌሶን 6፡11-12፣16
ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ ጠላት ደግሞ ይህንን አይፈልግም፡፡ ጠላታችን ዲያቢሎስ የሚፈልገው የእግዚአብሄርን ሃሳብ እንድንጥል የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንከተልና የተፈጠርንበትን አላማ በመሳት ከንቱ እንድንሆን ነው፡፡
የጠላት ግቡ መስረቅ ማረድ ማጥፋት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ አላማ የለውም፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሃንስ 10፡10
የሰው ልጆችን ህይወት የሚሰርቅበት ፣ የሚያርደበትና የሚያጠፋበት መንገዱ በእግዚአብሄር ቃል እንዳይኖሩ ጥርጥርን ወደልባቸውና መላክ ነው፡፡ ዲያቢሎስ የመስረቅ የማረድ የማጥፋት አላማውን ለማሳካት የክፉ ሃሳብ ፍላፃዎችን ወደ እኛ ካለማሰለስ ይልካል፡፡ ይህ የክፋት ሃሳብ ህይወታችንን ለማቃጠልና ለማጥፋት የታለመ ነው፡፡
ኢየሱስ በዲያቢሎስ ሲፈተን የዲያቢሎስን የጥርጥር ቀስት በሙሉ የመለሰው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ (ማቴዎስ 4፡1-11) የእግዚአብሄርን ቃል የማያውቅና  የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት በሚመጣው እምነት ያልታጠቀ ክርስትያን ጋሻ ሳይዝ በጠላት ቀስት መካከል እንደተገኘ ሰው ነው፡፡   
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
የጠላት ዲያቢሎስን የክፋት እሳት ማጥፋት የምንችለው በእምነት ብቻ ነው፡፡ ራሳችንን ከዚህ የጥርጥር ቀስት መጠበቅ የምንችለው ራሳችንን በእምነት ምንጭ ቃል በመመገብ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል በቀጣይነት የማይሰማና እምነቱን የማይመግብ ሰው ለዚህ የጥርጥር ቀስት የተጋለጠ ይሆናል፡፡
ሰው በቀጣይነትና በትጋት የእግዚአብሄርን ቃል ካልመገበና ራሱን በእምነት ጋሻ ካላስታጠቀ ልቡ በፍላፃ ይወጋል፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ አጥብቀን ልባችንን እንድንጠብቅ የሚያዘን፡፡
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። ምሳሌ 4፡23
በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ ኤፌሶን 6፡16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእምነትተጋድሎ #የእግዚአብሄርቃል #ቃሉንመስማት #እወጃ #ፍላጻ #ጋሻ #መስማት #እቃጦር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment