Popular Posts

Monday, October 31, 2016

የተሳካ ጓደኝነት

ሰው ሰው የራሱ ፈቃድ ያለውና የተከበረ ፍጡር ስለሆነ ከሰው ጋር ያለ ግንኙነት እጅግ ጥበብን የሚጠይቅ ችሎታ ነው፡፡ ሰው ምንም ያህል የጠፈር እውቀት ቢኖረው ሰውን መያዝ ችሎታ ከጎደለው ብዙ ነገር ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሰው ምንም ያህል የፊዚክስ ችሎታ ቢኖረው ከጓደኛ ጋር እንዴት እንደሚኖር ካላወቀ ህይወቱን ሊደሰትበት ያቅተዋል፡፡
ካለግንኙነትና ካለ ህብረት ሰው በራሱ ውስን ነው ፍሬ ሊያፈራ በህይወቱም ሊከናወን አይችልም፡፡
ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ ምሳሌ 13፡20
ለሰዎች የህይወት ስኬት የሚያስፈልገውን ነገር እግዚአብሄር ያስቀመጠው በሰው ውስጥ ነው፡፡
ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል። ምሳሌ 27፡17
ከዚህ አንፃር ስለጓደኝነት ወይም ስለ ባለንጀራነት የተረዳሁትን ጥቂት ምክሮች ላካፍላችሁ
  • ግንኙነት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰው ይፈልገናል እኛም ሰውን እንፈልጋለን፡፡ እኛ ሰውን ለጓደኝነት መፈለጋችን ሰውም እኛን ለጓደኝነት መፈለጉ ትክክለኛ ነገር ጤናማነት ነው፡፡
  • በጓደኝነት የሌላውንም ፍላጎት ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ እኛን ብዙም የማያስደስተንን ነገር ስለጓደኝነት ብለን የማድረግ ትህትናን ይጠይቃል፡፡ ጓደኝነት የሚሰምረው ሌላውን ለማስደሰት በማተኮር ላይ ነው፡፡
እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። ፊልጵስዩስ 2፡4
  • በጓደኛችን ላይ የምንወደውና የምናከበረው ባህሪ ይኖራል፡፡ የጓደኛዬን ሁለንተና እወዳለሁ ማለት ውሸት ነው፡፡ የምንወደውና የምንጠቀምበት ባህሪና ጥንካሬ እንዳለ ሁሉ የምንሸከመው ባህሪም ይኖራል፡፡
  • በጓደኛችን ላይ የማንወደውን አመል እንዲስተካከል በፍቅር የራሳችንን አስተዋፅኦ እናደርጋለን፡፡ እንዲሁም ያንን የማንወደውን ነገር ደግሞ እኛም ተቀብለነው እንዳናደርገው መልካም አመላችን እንዳይጠፋ መጠንቀቅ አለብን፡፡ እንዲያውም ክፉ አመል እንደሚጋባብን ካየን የወዳጅነቱን ድንበር ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
ከቍጡ ሰው ጋር ባልንጀራ አትሁን፥ ከወፈፍተኛም ጋት አትሂድ፥ መንገዱን እንዳትማር ለነፍስህም ወጥመድ እንዳታገኝህ። ምሳሌ 22፡24-25
  • ፈጥኖ ወደ ወዳጅነት ውስጥ መግባት አደገኛ ነው፡፡ ግንኙነት ጠቃሚ እንደመሆኑ መጠን በሚገባ ካልያዝነው አፍራሽ ሊሆን ይችላል፡፡
አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡33
  • ከሌላው ጓደኛ ጋር መሰጠት ጋር የተመጣጠነ መሰጠት ይኑርህ፡፡ ከአንዱ ወገን ብቻ የሚመጣ በጣም ያልተመጣጠነ መሰጠት ጤናማ ግንኙነትን አያመለክትም፡፡ እግዚአብሄር እንኳን ልጁን ኢየሱስን በመስቀል ላይ እንዲሞት ከሰጠን በኋላ እስክንቀበለው ጠበቀን እንጂ ራሱን በአንድ ለሊት ሁሉንም ዝርግፍ አድርጎ አልሰጠንም፡፡
ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።ዮሃንስ 14፡23
  • ወዳጅነታችን ለሁልጊዜ ቢሆን መልካም ነው፡፡ ካልተቻለ ግን ወዳጅነታችን ጊዜው ሲያልቅ በቀስታ መለየት መልካም ነው፡፡ ከጓደኝነት ተጣልቶና ተበጣብጦ መለያየት አያስፈልግም፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ወዳጅነት #ጓደኛ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ጓደኝነት #መንፈስቅዱስ #ባልንጀራ #ልብ #ስለሁሉሞተ

Sunday, October 30, 2016

የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ

ዶክተር አሳየኸኝ በርሄ ስለጋብቻ ሲያስተምሩ የወደፊት የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማወቅ ለሚደረግ ፀሎት ሰባት ጠቃሚ መርሆዎችን ተናግረዋል፡፡ ይህን ከእናንተ ጋር ለመካፈል ወደድኩ፡፡
ይህ የፀሎትና የእግዚአብሄርን ፈቃድ መለያ መመሪያ ማንም ሰው ለሌሎች የህይወት ክፍሎች ለመወሰንና ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግና የሚጠቅሙ የፀሎት መርሆዎች ናቸው፡፡
1. ስትፀልይ ወስነህ አትፀልይ፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማወቅ ስትፀልይ የምታደርገውን አውቀህ እግዚአብሄር እንዲያፀናልህ ብቻ አትፈልግ፡፡ እግዚአብሄር በህይወትህ በእያንዳንዱ ደረጃ መካተት ይፈልጋል፡፡ የምትፈልገውን መርጠህ ጨርሰህ እግዚአብሄር ማህተም ብቻ እንዲያደርግልህ አትፈልግ፡፡ ስትፀልይ ገለልተኛ ኒውትራል ሆነህ ፀልይ፡፡ አስቀድመህ ወስነህ ከፀለይክ እግዚአብሄር ቢናገርህም መስማት ያቅትሃል፡፡
ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ማቴዎስ 26፡39
2. የመንፈስ ቅዱስን መቃተት ጠብቅ እግዚአብሄር በምርጫህ ውስጥ መካተቱን የምታውቀው ስትፀልይ የመንፈስ ቅዱስ መቃተትን ስታገኝ ነው፡፡ ስትፀልይ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ ማግኘትህን የእግዚአብሄር በመለየት ፀሎትህ እንደተካተተ እርግጠኛ ሁን፡፡ ስትፀልይ የመንፈስ ቅዱስን መቃተት እሰኪሰማህ ድረስ ፀልይ፡፡
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ሮሜ 8፡26
3. መነሻ ሃሳብህን ሞቲቭህን ፈትሽ ለትዳር ጓደኛ ምርጫ ስትፀልይ የውስጥ ሃሳብህን ወይም ሞቲቭህን መዝን፡፡ ምርጫህን ልትመርጥ የቻልከው ለምን እንደሆነ ራስህን በቅንነት ጠይቅ፡፡ ሰው በስጋ ሃሳብ ተነስቶ ሊፀልይ ይችላል፡፡ እግዚአብሄር የሚመልሰው ፀሎት ግን ሞቲቩን ለማጥራት ራሱን የሚፈትሽና ራሱን የሚያስተካክል ሰው ፀሎት ነው፡፡
የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል። ምሳሌ 16፡2
4. ካንተ በመንፈሳዊ ነገር ከበሰሉ ሰዎች ምክርን ጠይቅ፡፡ ይህ ማለት እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢያትን ጠይቅ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ምርጫን እንዴት ልትመርጥ እንደምትችል የምርጫህን መመዘኛዎች እንደ እግዚአብሄር ቃል ሊያስተካክሉ የሚችሉ በቃሉ የበሰሉ ለህይወትህ እውነተኛ ሸክም ያላቸውን ሰዎች ምክርን ተቀበል፡፡
በመልካም ሥርዓት ሰልፍ ታደርጋለህ፤ ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው። ምሳሌ 24፡6
5. እግዚአብሄር ማረጋገጫን እንኪሰጥህ ጠብቅ፡፡ እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በተለያዩ መንገዶች ቃሉን ያፀናል፡፡ ስለዚህ በአንድ ሃሳብና በአንድ ምሪት ብቻ ከመሄድ ማረጋገጫዎችን ጠብቅ፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ሮሜ 8፡16
6. ምርጫን ስታደርግ የእግዚአብሄር ሰላም በልብህ እንዳለ እርግጠኛ ሁን፡፡ የእግዚአብሄር ሃሳብ ያለበት ነገር ሁሉ በውጭህ ረብሻ ቢሆንም በውስጥ ሰላም ይኖርሃል፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ያለበትን ነገር ለማድረግ ስታስብ በአእምሮህ እንኳን ረብሻ ቢኖርም በልብህ ግን ሰላም ይኖራል፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15
7. ሌላው የእግዚአብሄር ፈቃድ ማረጋገጫው እግዚአብሄር በሮችን ይከፍታል፡፡ እግዚአብሄር ለፈቃዱ የሚያስፈልጉትን አቅርቦቶች ይሰጣል፡፡ የተሳኩ ነገሮች ሁሉ የእግዚአብሄር ፈቃድ ናቸው ባንልም የእግዚአብሄር እጅ ያለበት ግን ይሳካል ነገሮችም ይሰካካሉ፡፡
እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። መዝሙር 23፡1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #ስለሁሉሞተ

Saturday, October 29, 2016

ለራሳቸው እንዳይኖሩ

በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15
ክርስትና ወግን እና ስርአትን በመጠበቅ ብቻ የምንኖረው ሃይማኖት አይደለም፡፡ ክርስትና አንዳንድ ስርአቶችን በመጠበቅ ብቻ የፈለግነውን ህይወት የምንኖርበት ሃይማኖር አይደለም፡፡ ክርስትና አትንካ አትቅመስ በሚሉት ስርአቶች የሚረካ ሃይማኖት አይደለም፡፡
ኢየሱስ እኛን ለማዳን የከፈለው ወግና ስርአትን መጠበቅ አይደለም፡፡ ኢየሱስ እኛን ለማዳን የከፈለው ብርና ወርቅ አይደለም፡፡ ኢየሱስ እኛን ለማዳን የከፈለው ህይወትን ነው፡፡ ኢየሱስ እኛን ለማዳን የከፈለው ህይወቱን ነው፡፡ ኢየሱስ የሞተው እኛን ለማዳን ነው፡፡
ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ሮሜ 5፡8
ኢየሱስ እኛን ለማዳን ሞቶልናል፡፡ ኢየሱስ እኛን ለመታደግ ራሱን ሰጥቶዋል፡፡ ኢየሱስ እኛን ለማዳን ነው ነፍሱን ሰጥቶዋል፡፡ ኢየሱስ ነፍሱን አሳልፎ የሰጠው እኛ የፈለግነውን ኑሮ እንድንኖር አይደለም፡፡ ኢየሱስ ስለእኛ የሞተው እኛ ለእርሱ እንድንኖር ነው፡፡
ኢየሱስ የሞተው ወደፊት ለራሳችን እንዳንኖር ነው፡፡ አየሱስ ለእኛ የሞተው እኛ ለራሳችን እንድሞት ነው፡፡ ኢየሱስ ለእኛ የሞተው ለእርሱ ለሞተልን ብቻ እንድንኖር ነው፡፡
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #ስለሁሉሞተ

ፍቅር ይታገሣል

ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤1ኛ ቆሮንቶስ 13፡4
የፍቅር ትርጉሙ ሌላውን ሰው በመረዳት ከዛ ሰው ጋር ራስን ማስተባበር ነው፡፡ Love is identifying self with the other in understanding.
ፍቅር አለም በራሱ ዙሪያ እንደምትዞር አያስብም፡፡ ፍቅር የራሱን ፍላጎት ብቻ አይመለከተም፡፡ ፍቅር ራስ ወዳድ አይደለም፡፡
ፍቅር ለሌላው እውቅና ይሰጣል፡፡ ፍቅር ለሌላው ፍላጎት ቦታ አለው፡፡ ፍቅር ሌላውን የሚያከብር ልብ አለው፡፡ ፍቅር የሌላው እርምጃ የሚታገስ ልብ አለው፡፡
ፍቅር ይታገሳል፡፡ ፍቅር ቻይ ነው፡፡ ፍቅር አይቸኩልም፡፡ ፍቅር አሁን ካልሆነ አይልም፡፡ ፍቅር ይቆያል፡፡ ፍቅር ይጠብቃል፡፡ ፍቅር ነገሩ በጊዜው እንደሚሆን ያምናል፡፡
ፍቅር ይታገሳል፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትዕግስት #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ

Friday, October 28, 2016

የልብ ጽላት

በየትኛውም የህይወት መሰክ ወደ ውጤት ለመድረስ እቅድ ያስፈልጋል፡፡ እቅዳችን ደግሞ ሊመዘን የሚችል እቅድ መሆን አለበት፡፡ ስንደርስበት ደረስንበርት የምንለው ስንደርስበት የምናውቀው እቅድ ያስፈልገናል፡፡ አጠቃላይ የሆነና ዝርዝር ያልሆነ እቅድ አፈፃፀሙ ሊለካ አይችልም፡፡
በክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ አገልግሎትና አገልጋይ የአገልግሎት ውጤት የሚመዘንባቸው ብዙ መንገዶች ይኖራሉ፡፡
አገልጋይ የሚመዘንበት ብዙ መንገድ ቢኖርም እንደዚህ ግን የአገልግሎት ውጤትን በግልፅ የሚያንፀባርቅ የአገልግሎት ውጤት መለኪያ መንገድ የለም፡፡
እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ። ቆላስይስ 1፡28-29
ሐዋሪያው ስለአገልግሎቱ ሲገልፅ የአገልግሎቱ ውጤት ምስክሮች ያገለገላቸው ሰዎች ህይወት መሆኑን ይናገራል፡፡ እንዳገለገልናቸው ሰዎች የህይወት ለውጥ ስለአገልግሎታችን ስለኬታማነት የሚናገርና የሚመሰክር ምንም መመዘኛ የለም፡፡
ስለ ሐዋሪያው አገልግሎት የሚናገረው በተገልጋዮቹ በልባችን የተፃፈው የክርስቶስ መልክት እንደሆነ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መንፈስ የተፃፈ መልእክት የማያሻማ የአገልግሎት ውጤት ምስክር ወረቀት ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ የሚያነቡት በክርስቶስ የተለወጠ ልብ የአገልግሎታችን ውጤታማነት ማረጋገጫ ነው፡፡
እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎች የማመስገኛ መልእክት ወደ እናንተ ወይስ ከእናንተ ያስፈልገን ይሆንን? ሰዎች ሁሉ የሚያውቁትና የሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 3:1-3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ

ሙሉ ስልጣን ተሰጥቶናል

ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና . . . ማቴዎስ 28፡18

በመጀመሪያ ሰው ከሙሉ ስልጣን ጋር ተፈጥሮ ነበር፡፡

እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍጥረት 1፡28

ሰው በሃጢያት እግዚአብሄር ላይ በማመፁ ስልጣኑን ሙሉ ለሙሉ አጣው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠውን ስልጣን ባለመታዘዝ ምክኒያት ለሰይጣን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ስለዚህ ነው ሰይጣን የዚህ አለም ገዢ ተብሎ የተጠቀሰው ፡፡

ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡4

ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣበት ዋነኛው አላማ የዲያቢሎስን ስራ ሊያፈርስና ሰው ለሰይጣን አሳልፎ የሰጠውን ስልጣን መመለስ ነው፡፡ ኢየሱስ የሰውን ስጋ ለብሶ ወደምድር የመጣውና ሰይጣንን ድል የነሳው ለራሱ ሳይሆን ለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ ሰይጣንን ያሸነፈው በእኛ ምትክ ሆኖ ለእኛ ነው፡፡

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15

አሁንም ሰው ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታው ሲቀበለው የልጅነት ስልጣኑ ይመለሳል፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12

የእግዚአብሄር ልጅ የሆነ ሰው ሁሉ ሰይጣንን መቃወም ይችላል፡፡ በሰይጣን ላይ ሙሉ ስልጣን ስላለን ስንቃወመው መሸሽ እንጂ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡

እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ያዕቆብ 4፡7

ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ስልጣን #ሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ሃይለኛ #ጩኽ #በረከት #ትግስት #መሪ

Thursday, October 27, 2016

መንታ መንገድ

ከስር መሰረቱ መረዳት ከፈለግን የዘፍጥረት መፅሃፍ ስለሰው መጀመሪያ ብዙ ነገርሮችን ያስተምረናል፡፡ እግዚአብሄር ሰውን እንዴት እንደፈጠረውና የእግዚአብሄር የመጀመሪያው እቅዱ ምን እንደነበረ የምንረዳው በመጀመሪያ ያለውን ታሪክ ስናይ ነው፡፡ ሰውን እግዚአብሄር ሲፈጥረው ለክብሩ ነው የፈጠረው፡፡ ሰውን እግዚአብሄር ሲፈጥረው ሙሉ ለሙሉ በምድር ላይ እንዲወክለው ነው የፈጠረው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በየዋህነት ሁሉ በፍፁም መታዘዝ እንዲከተለው ነው፡፡ በእርሱ ላይ ሙሉ መደገፍ አንዲኖረው ነው እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17
ሰው እግዚአብሄርን በሙሉ ቅንነት ሲከተል በነበረበት ጊዜ ሰው አንድነቱ ተጠብቆ በፍፁም ሰላም ይኖር ነበር፡፡ ሰው አንድ እውቀት ብቻ ነበር የነበረው፡፡ ሰው የነበረው እውቀት በእግዚአብሄር ላይ ሙሉ ለሙሉ በመደገፍ ከእግዚአብሄር ጋር መፍሰስ ነበር፡፡ ሰው በአንድ መንገድ ብቻ በህይወት ነበር የሚኖረው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን መከተል ብቻ እንጂ መልካምንና ክፉን ማወቅና መለየት የለበትም ነበር፡፡ ሰው የህይወትን ዛፍ ፍሬ ብቻ ነበር የሚያውቀው በህይወትም ዛፍ ፍሬ ብቻ ነበር በህይወት የሚኖረው፡፡
ሰይጣን ወደ ሰው በቀረበ ጊዜ ግን ሁለትን እውቀት የምትሰጥን የዛፍ ፍሬ አስተዋወቀው፡፡ ሰው በህይወት ዛፍ ፍሬ በመኖርና መልካምና ክፉውን በምታሳውቀው ዛፍ ፍሬ መካከል መረጠ፡፡ ሰይጣን በአንድነት በህይወት ይኖር የነበረውን አዳምን ክፉና መልካም የምታስታውቀውን ሁለትን መንገድ አስተዋወቀው፡፡
ሰው ክፉውንም መልካምንም ቢመርጥ እንደ ህይወት ዛፍ ፍሬ መሆን አልቻለም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ላይ ያለውን ፍፁም መደገፍ ጣለ፡፡ አሁን ሰው በራሱ ማስተዋል መደገፍ አለበት፡፡ አሁን ሰው በራሱ "ይህ ክፉ ነው" "ይህ መልካም" ብሎ መለየት ነበረበት፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ላይ በመደገፍ ብቻ ከእግዚአብሄር ጋር መፍሰስ አልቻለም፡፡
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ ምሳሌ 3፡5-7
አሁንም በራሳችን ማስተዋል በመደገፍ የእግዚአብሄርን ፍፁም ሃሳብ መከተል አንችልም፡፡ የእግዚአብሄርን ሃሳብ በራሳችን ማስተዋል ልናገኘው በፍፁም አንችልም፡፡
ኢየሱስ ስለዚህ ነው ወደ ምድር የመጣውና የሃጢያት እዳችንን ሁሉ የከፈለው፡፡ ኢየሱስን የተቀበልን ሁላችን የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡
አሁን የእግዚአብሄር መንፈስ በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡ አሁን ወደ ህይወት የሚመራው የህይወት መንፈስ ህግ በውስጣችን ይኖራል፡፡ በልባችን የሚኖረውን መንፈስን በቅንነት ከተከተልን እንደ እግዚአብሄር እንደልቡና እንደ ሃሳቡ ማድረግ እንችላለን፡፡ መንፈሱን በመከተል በህይወት መኖር እንችላለን፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ሮሜ 8፡2
መልካምና ክፉ ለመለየት በራሳችን ማስተዋል መደገፍ ትተን በውስጣችን የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስን ብቻ በመከተል ከሃጢያትና ከሞት ህግ ነፃ መሆን እንችላለን፡፡
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡20፣27
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ምሪት #መንፈስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የህይወትመንፈስህግ #መንፈስቅዱስ #በረከት #ትግስት #መሪ

Wednesday, October 26, 2016

እኔም እመልስልሃለሁ ይላል እግዚአብሔር


ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ። ኤርምያስ 33፡3
እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡፡ ወደ እኔ ጩኽ!
እግዚአብሄርን የማንፈልግበት የህይወት ክፍል የለም፡፡ እግዚአብሄር የማያስፈልገን የህይወት ደቂቃና ሰከንድ የለም፡፡ እግዚአብሄር የማያስፈልገን ምንም የህይወት ሃላፊነት የለም፡፡ እግዚአብሄር የማያስፈልገን ምንም የህይወት ደረጃ የለም፡፡
ባደግን በተለወጥን ቁጥር ይበልጥ ወደ እርሱ መፀጮኽ እንዳለብን እንረዳለን፡፡ ባወቅንና በተረዳን ቁጥር ወደ እርሱ ጩኸን ፀልየን አንጠግብም፡፡ ብዙ የህይወት ደረጃዎች ላይ በደረስን መጠን እግዚአብሄርን የማንፈልግበት ዝርዝር ጥቃቅን የህይወት መስክ እንደሌለ እንረዳለን፡፡
የፀሎታችን ተጠቃሚ እንድንሆን እግዚአብሄርም ሁል ጊዜ የሚጠይቀን ወደ እርሱ እንድንጮኽ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ ከእኛ የሚጠብቀው የእኛን ወደ እርሱ አብዝተን መጮኻችንን ነው፡፡
አንተ የማታውቅውን ታላቅና ሃይለኛን ነገር አሳይሃለሁ፡፡
እንዴት አይነት የተስፋ ቃል ነው ?
አንተ የማታውቀውን ይላል እግዚአብሄር፡፡ ይገርማል፡፡
እግዚአብሄር ሲያስደንቀን ኖሮዋል፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው ማስተዋሉም አይመረመርም፡፡ ይህ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል ወደ እኔ ጩኽ አንተ የማታውቀውን ነገር አሳይሃለሁ፡፡
እንደዚህ ልብን በደስታ ፈንጠዚያ የሚሞላ የተስፋ ቃል የለም፡፡
አንተ የማታውቀውን አዲስን ነገር እግዚአብሄር ሊያደርግ ወደ እርሱ እስከምትፀልይ እየጠበቀህ ነው፡፡ ታላቁ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል ወደ እኔ ጩኽ እኔም እመልስልሃለሁ ፣ አንተም የማታውቅውን ታላቅን ነገር አሳይሃለሁ፡፡
ትንሽ ነገር አይደለም ታላቅ ነገር ተዘጋጅቶልሃል፡፡ ታላቅ ነገር ምን እንደሆነ መገመት ሊያቅትህ ሁሉ ይችላል፡፡ መገመት ቢያቅትህም እግዚአብሄር ግን እንዲህ ይላል ወደ እኔ ጩኽ፥ አንተም የማታውቀውን ታላቅ ነገር አሳይሃለሁ፡፡
እግዚአብሄር ሃያል አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰራዊት አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር በሃይሉ ታላቅን ነገር ያደርጋል፡፡ ይህ እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡፡ ወደ እኔ ጩኽ፥ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ።
ወደ እኔ ጩኽ፥ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ። ኤርምያስ 33፡1-3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፀሎት #ታላቅ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ሃይለኛ #ጩኽ #በረከት #ትግስት #መሪ