Popular Posts

Tuesday, May 1, 2018

የልብ ዓይን መብራት ሶስቱ ጣምራ ፋይዳዎች

ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡16-19
በምድር ላይ የአይናችን ወሳኝ ጤንነት ወሳኝ ነው፡፡ አይናችን በትክክል ሲያይ ከብዙ ችግሮች እናመልጣለን፡፡ አይናቸው አጥርቶ ማየት የማይችሉ ሰዎች ከብዙ ነገር ይጎድላሉ፡፡ አይኑ የበራለለት ሰው ራሱን ችሎ ውሳኔዎችን መወሰን ይችላል፡፡ አይኑ የበራለት ሰው ስለሚያይ ትክክለኛ ውሳኔን እንዲወስን ያስችለዋል፡፡
በተፈጥሮአዊ አይናችን ወሳኝ አንደሆነ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የልባችን አይን ጤንነትነ አጥርቶ ማየት ለክርስትና ፍሬያማነት ወሳኝ ነው፡፡ አይኑ የተከፈተለት ሰው እድልን ማየት ይችላል፡፡ አይኑ የተከፈተለት ሰው በረከቱን አይቶ መጠቀም ይችላል፡፡ እይታችን የህይወታችንን ጥራትና ልቀት ይወስነዋል፡፡
እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል። 2ኛ የጴጥሮስ 1፡9
ሃዋሪያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስትያኖች ይፀልይ የነበረውና እግዚአብሄርን ማሳሰብ አልተውም አላቆምም የሚለው የልቦናቸው አይኖች እንዲበሩ ነበር፡፡
የልቦናችን አይኖች ሲበሩ የምናውቃቸው ወይም በትክክል የምናስተውላቸው ሶስቱ የእግዚአብሄር ታላላቅ ስጦታዎች  
የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን
እግዚአብሄር ወደምን ተስፋ እንደጠራን ማወቅ ህይወታችንን ያሳርፋል፡፡ ተስፋ ያለን ሰዎች ነን፡፡ እንደ እኛ ታላቅ ተስፋ ያለው ሰው የለም፡፡ የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው፡፡ ከሞት ወደ ህይወት ተሸጋገረናል፡፡ ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር እንኖራለን፡፡
በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን
በክርስቶስ ወራሾች ተደርገናል፡፡ የእግዚአብሄር ወራሾች ነን፡፡ የወረስነው እግዚአብሄርን ነው፡፡ የወረስነው ብርና ወርቅ አይደለም፡፡ ያለን ርስት እጅግ የከበረ ነው፡፡
ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። ሮሜ 8፡17
የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ወራች ነን፡፡
ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም። ኤፌሶን 3፡5-6
በብርሃን ርስትን እንድንካፈል ያበቃንን እግዚአብሄርን ልናመሰግነው ይገባል፡፡
ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። ቆላስይስ 1፡12
ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን
በምድር ላይ ሞት ሃያል ነበር፡፡ የእግዚአብሄር የሃይል ታላቅነት የተገለጠው ኢየሱስን ከሙታን በማስነሳት ነው፡፡ የመጨረሻው ሃይል ሞት በክርስቶስ ትንሳኤ ድል ተነስቶዋል፡፡ ይህ ታላቅ ሃይል በህይወታችን አለ፡፡ ይህን ታላቅ ሃይል ማየት ከቻልን አለምን እናሸንፋለን፡፡
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እይታ #አይን #ቃል #የጠራ #ኩል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment