Popular Posts

Tuesday, May 1, 2018

ወንጌልን ስበኩ አስፈላጊ ከሆነ ቃልን ተጠቀሙ

ይህ የአሲሲ ቅዱስ ፍራንሲስ ንግግር ነው፡፡ ወንጌልን ለመስበክ መሰረት የሆነንን የወንጌልን ህይወት ለማሳየት የተነገረ ንግግር ነው፡፡ የወንጌል ቃል ካለወንጌል ህይወት ሙሉ አይሆንም ለማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የወንጌል ስብከት መሰረቱ የወንጌል ህይወት ነው ማለት ነው፡፡ የወንጌል ስብከት የንግግር ቃል ብቻ ሳይሆን ሙሉ የህይወት መሰጠት እንደሚጠይቅ ለማሳየት ነው፡፡
ወንጌልን ለሰዎች ስንናገር ሰዎች የምንነግራቸውን ነገር ከማመናቸው በፊት ስለንንግራችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ ሰዎች ስለምንሰብካቸው ቃል ትክክለኝነት የሚያረጋገጡት ደግሞ ህይወታችንን አይተው ነው፡፡
የምንኖረው ኑሮ ከምንሰብከው ስብከት ጋር አብሮ ካልሄደ ሰዎች ይህንን ወንጌል አይቀበሉም፡፡ የምንነግራቸው ቃል ከሚያውቋቸው ክርስትያኖች ህይወት ጋር አብሮ ከሄደ ብቻ ሰዎች ጌታን ለመቀበል ይወስናሉ፡፡
እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ማቴዎስ 5፡13-14
ሁላችንም ወደጌታ የመጣነው ተሰብኮልን ብቻ ሳይሆን የክርስትያኖችን የህይወት ንፅህና አይተንና የሚሰበከው ቃል ከህይወታቸው ጋር አንድ መሆኑን ነው፡፡ እኛም የምንሰብካቸው ሰዎች ጌታን ለመከተል የሚወስኑት ጌታን የሚከተሉትን ሰዎች ህይወት አይተው ነው፡፡
ጌታን የሚከተል ሰው ህይወት ካላጓጓቸው የምንነግራችው ቃል አያጓጓቸውም፡፡ የህይወት ጥራታችን ካጓጓቸው ግን የምንነግራችው ነገር ሁሉ ያጓጓቸዋል እንደእኛ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ሰው ካለንግግር በህይወት ብቻ ለወንጌል ሊማረክ ይችላል ካለወንጌል ህይወት ግን በንግግር ብቻ ለወንጌል ሊማረክ አይችልም፡፡
እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። 1 የጴጥሮስ 3፡1-2
የክርስትናን ህይወት ስንኖር የኢየሱስ ስም ተሸክመን እንኖራለን፡፡ የተጠራነው ኢየሱስን በምድር ላይ ለመወከል ነው፡፡ የተመረጥነው የኢየሱስን ስም እንድንሸከም ነው፡፡ የተጠራነው የኢየሱስን ስም በመልካም እንድናስጠራ ነው፡፡   
ጌታም፦ ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤  ሐዋርያት ሥራ 9፡15
የምናደርገው መልካም ነገር በሙሉ ሰዎች እግዚአብሄርን እንዲያመሰግኑ ወይም እንዳያመሰግኑ ያደርጋል፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡16
ራሳችንን እየካድን በፍቅር የምንኖር ከሆነ ለሰዎች ስለ ኢየሱስ የማያከራክር ፍፁም ምስክሮች እንሆናለን፡፡  
እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ። ዮሃንስ 13፡34-35
የምንኖረው ኑሮ ለክርስትና ምስከርነት ድጋፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ህይወታችንን በጥንቃቄ የምንኖር ከሆነ ሰዎች ጌታን እንዲከተሉ ጉልበትን እንሰጣቸዋለን፡፡ የምንኖረው ኑሮ እግዚአብሄርን በመፍራት ከሆነ ሌሎች ሰዎች እግዚአብሄርን እንዲፈሩ እናደርጋቸዋለን፡፡ እግዚአብሄርን የመፍራት ህይወታችን ሌሎች እኔስ ለምንድነው እግዚአብሄርን የማልፈራው እንዲሉ ያስገድዳቸዋል፡፡  
ያለ ነቀፋ መሆናችን ፣ የዋሆች መሆናችን ፣ ነውርም የሌለብን መሆናችን ፣ ሳናንጐራጉርና ክፉም ሳናስብ ሁሉን ማድረጋችን ብቻ በጨለማው አለም እንደብርሃን እንድንታይ ያደርገናል፡፡
በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ፊልጵስዩስ 2፡14-16
እያንዳንዱ ህይወታችን በሰዎች ይታያል፡፡ አንድ ነገር ሲደርስብን የምንሰጠው መልስ በሰዎች ትኩረት ውስጥ አለ፡፡ የምንኖረው ኑሮ ለክርስትና እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡ ለወንጌል ምስክርነታችን ዋናው መሰረት ጌታን የሚከተል ሰው በየእለት ኑሮው የሚኖረው ኑሮ ምስክርነት እንጂ የሚናገረው ሃይማኖታዊ ቃልና የሚያደርገው ሃይማኖታዊ ስርአት አይደለም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ወንጌል #ስብከት #ቃል #ዝራ #የምድርጨው #የአለምብርሃን #የአመፃገንዘብ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment