Popular Posts

Follow by Email

Thursday, August 31, 2017

እኅት ሚስታችንን

እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፥ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን? 1 ቆሮንቶስ 95
የጋብቻ ግንኙነት የሚጀመረው በእህትነትና በወንድምነት ነው፡፡ ወንድ የሚያጋባው በጌታ እህቱ የሆነችውን ሴት ነው፡፡ ሴት የምታገባው በጌታ ወንድሟ የሆነውን ወንድ ነው፡፡ የትዳር መሰረቱ በጌታ የእህትነትና የወንድምነት ዝምድና ነው፡፡
ትዳር ከትዳር የፍቅር ግንኙነት አይጀምርም፡፡ ትዳር የሚጀምረው ከወንድምነት ፍቅር ነው፡፡ ትዳር የሚጀምረው ከእህትነት ፍቅር ነው፡፡ የትዳር የፍቅር ግንኙነት የሚጀመረው ከእህትነት የፍቅርና የርህራሔ ግንኘነት ነው፡፡ የትዳር የፍቅር ግንኙነት የሚጀምረው ከወንድምነት የፍቅርና የርህራሔ ግንኙነት ነው፡፡ ትዳር የሚጀምረው ከቤተሰብነት የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡
የክርስትያናዊ ጋብቻ ግንኙነት መሰረቱ የእህትነትና የወንድምነት ግንኙነት ነው፡፡ የጋብቻ ግንኙነት መሰረቱ የቤተሰብነት ግንኙነት ነው፡፡ የትዳር የርህራሔና የፍቅር ግንኙነት የሚጀምረው ከወንድምነትና ከእህትነት የርህራሄና የፍቅር ግንኙነት ነው፡፡
ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡39
ባልና ሚስት ከመሆናቸው በፊት እህትነትና ወንድም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የባልና የሚስት ፍቅር ከማሳየታቸው በፊት የወንድምና የእህት ፍቅር ሊያሳዩ ይገባቸዋል፡፡ እንዲያውም ለባልና ለሚስትነት ፍቅር መሰረት የሚሆነው የእህትነትና የወንድምነት ፍቅር ነው፡፡ ለባልነትና ለሚስትነት ዝቅተኛው መመዘኛ የእህትነትና የወንድምነት ፍቅር ነው፡፡ የእህትነትና የወንድምነት ፍቅር የሌላቸው የባልነትና  የሚስትነት ፍቅር ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ከባልነቱ በፊት ወንድምነቱ ይቀድማል ከሚስትነትዋ በፊት እህትነትዋ ይቀድማል፡፡ ባልና ሚስትነቱ ወንድምና እህትነቱን በፍፁም አይሽረውም፡፡
በትዳር የእህትነትና የወንድምነት ፍቅር እየጨመረ ሊሄድ ይገባዋል እንጂ ሊቀንስ አይገባውም፡፡ ባልና ሚስት በሆኑም ጊዜ ወንድምና እህትነቱ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ በትዳር የወንድምነትና የእህትነት ፍቅር እየጨመረ ሊሄድ ይገባዋል እንጂ በባልነትና በሚስትነት ፍቅር ሊተካ አይገባውም፡፡ በትዳር ባለቤትህ እህትህ ነች፡፡ በትዳር ባለቤትሽ ወንድምሽ ነው፡፡ በትዳርም የእህትነትና የወንድምነት ፍቅር ከባልነትና ከሚስትነት ፍቅር ይቀድማል፡፡ የወንድምና እህትነቱ ፍቅር ለባልና ለሚስትነቱ ፍቅር ጉልበት ይሰጠዋል፡፡
የእህትነትና የወንድምነት ፍቅር ከትዳር ፍቅር መቅደሙ በቻ ሳይሆን የእህትነትና የወንድምነት ፍቅር ለትዳር መሰረት ነው፡፡ ከትዳርም በኋላ እንዲሁ በሰማይ የሚዘልቀው የወንድምነትና የእህትነት ግንኙነት እንጂ የባልነትና የሚስትነት ግንኙነት አይደለም፡፡
በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም። ማቴዎስ 22፡30
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #አንድስጋ #እውነት #እህትነት #ወንድምነት #መውደድ #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Wednesday, August 30, 2017

የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል

እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፦ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። ማቴዎስ 19:4-6
ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል
ሰው ሁሉን ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ሰው ውስን ነው፡፡ ሚስት ከባል ልዩ ፍቅር ትፈልጋለች፡፡ ሰው ከሚስቱ ጋር ለመጣበቅ  ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡  ሰው አባቱንና እናቱን ሳይተው ከሚስቱ ጋር መጣበቅ አይችልም፡፡ ሰው አባቱንና እናቱን ካልተወ በስተቀር ከሚስቱ ጋር የሚጣበቅበት አቅም አይኖረውም፡፡ ሚስት ከምትፈልገው ልዩ እንክብካቤና ፍቅር አንፃር ሰው አባቱንና እናቱን ሳይተው በሚስቱ መጣበቅ አይችልም፡፡ ሰው አባቱንና እናቱን ሳይተው ከሚስቱ ጋር መጣበቅ የሚችልበት ትርፍ አቅም የለውም፡፡ ሰው ለሚስቱ ሙሉ ፍቅርና ትኩረት ለመስጠት እንዲችል እናቱንና አባቱን መተው ግዴታው ነው፡፡
ከሚስቱም ጋር ይተባበራል
ፍቅር በመረዳት ራስን ከሌላው ጋር ማስተባበር ነው፡፡ ፍቅር የሌላውን ድካም የራስ ድካም አድርጎ መሸከም ነው፡፡ ፍቅር የሌላውን ገመና እንደራሰ ገመና መሸፈን ነው፡፡ ፍቅር በሌላው ስም መጠራት ለመጠራት መፍቀድ ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ደረጃ ጋር ራስን ማስተባበር ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን ሳያሻሽሉ እንዳለ መቀበል ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ጋር ለመቆጠር መፍቀድ ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ጋር ማበር ነው፡፡ ፍቅር  ሌላው ካለው ፣ ከሆነውና ከሚያደርገው ጋር ማበር ነው፡፡
ሰው እናቱንና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፡፡  ሰው ከሚስቱ ጋር ራሱን ያስተባብራል፡፡ ሰው የሚስቱን ስም ይወስዳል፡፡ ሰው የሚስቱን ነገር እንደራሱ ይቀበላል፡፡ ሰው ለሚስቱ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡  ሰው ከሚስቱ ጋር ይቆጠራል፡፡ ሰው የሚስቱን ደረጃ ይወስዳል፡፡ ሰው ሚስቱ ካላት ፣ ከሆነችውንና ከምታደርገው ነገር ጋር ያብራል፡፡
ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ
አንድ ስጋ መሆን ማለት መዋሃድ ማለት ነው፡፡ አንድ ስጋ መሆን ማለት ሌላውን እንደራስ መውደድ ማለት ነው፡፡ አንድ ስጋ መሆን ማለት አለመለያየት አለመከፋፈል አንድ መሆን ማለት ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ስለፍቅር ሲናገር ሌላውን የመውደድ ደረጃ ራስን የመውደድ ደረጃ እንደሆነ ያሰተምራል፡፡ ሰው ግፋ ቢል ራሱን በሚያከብርበት አከባበር ብቻ ነው ሌላውን ሊያከብር የሚችለው፡፡ ሰው ራሱን በሚወድበት መውደድ ነው ሌላውን መውደድ የሚችለው፡፡ ሰው ለራሱ ዋጋ በሚሰጥበት ደረጃ ብቻ ነው ለሌላው ዋጋ ሊሰጥ የሚችለው፡፡ ሰው ለራሱ በሚሳሳበት መጠን ብቻ ነው ለሌላው ሊሳሳ የሚችለው፡፡ ሰው ነፍሱን ከሚወድበት መጠን በላይ የሌላውን ነፍስ አይወድም፡፡ ሰው ራሱን በሚንከባከብበት መጠን ብቻ ነው ሌላውን ሰው የሚንከባከበው፡፡
ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ማርቆስ 12፡31
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል ያለው፡፡
እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ኤፌሶን 5፡28-31
ሰው ለራሱ አክብሮት እንዳለው የሚታየው ለሚስቱ በሚያሳየው አክብሮት ነው፡፡ የገዛ ስጋውን የሚጠላ ሰው እንደሌለ ሁሉና ሰው ስጋውን እንደሚመግበውና እንደሚንከባከበው ሁሉ ሰውም ሚስቱን ይመግባል ይንከባከባል፡፡ ራሴን እወዳለሁ ስጋዬን አልወደውም የሚል ሰው እንደሌለ ሁሉ ለራሱ አክብሮትና ፍቅር ያለው ሰው ለሚስቱ አክብሮትና ፍቅር ይኖረዋል፡፡   
እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ዘፍጥረት 2፡22-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #ፍቅር #መውደድ #ይተዋል #ይጣበቃል #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Tuesday, August 29, 2017

ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም

እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። ዘፍጥረት 2፡18
ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ሲል እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው ምን አይነት ሰው እንደነበር እንመልከት፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰው ስንመለከት ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለውን ሰው መመልከት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለው ማንኛውምንም ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለው ሙሉ የሆነን ሰው ነው፡፡  
እግዚአብሔር የፈጠረው ሙሉ ሰውን ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር የተሳካ ግንኙነት የነበረውን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በእግዚአብንሔር የረካን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው አንድ ሴትን ሊያስተዳድር የሚችል ሙሉ ብቃት ያለውን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ጎዶሎን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው 50 % ሰውን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው 100% ሰውን ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ቤተሰብ ሊመራ የሚችልን ሙሉ ሰውን ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ተለዋዋጭ ስሜቱን የሚከተልን ሰው ሳይሆን ሚስቱን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሊወድድ የሚችልን የውሳኔን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ለቤተሰቡ ሊያቀርብ የሚችል ጠንካራን ሰራተኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ቤተሰብን ሊሸከም የሚችል ሙሉ ሰውን ነው፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው ሙሉ የምታደርገኝን ሴት እፈልጋለሁ ብሎ በጉድለት የሚጮኽን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ተግዳሮት ሲመጣ የሚሸሽና በእርሱ ፋንታ የምታምንለትን ሴት የሚፈልግን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ተባርኮ ለበረከት የሚሆንን ወንድ እንጂ ከምስኪንነት የምታነሳውን ሴት የሚፈልግን ወንድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በእግዚአብሔር ግንኙነት የረካን ወንድ እንጂ የምታሳልፍለትን ሴት የሚጠብቅን ወንድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ጎዶሎን ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ባለ ራእይን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በመስጠት በመባረክ በማካፈል ላይ ያተኮረን ሰው ነው፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው ስልጣኑን ከማወቁ የተነሳ ሺን የሚያሳድድን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ሰው እግዚአብሔር ባዘጋጀው አሰራር በትዳር ከአንድ ሴት ጋር አስር ሺን ሊያሳድድ የተዘጋጀን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው አንድን ሴት ሊባርክ የተዘጋጀን የተባረከን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው አንድን ሴት ሊመራትና የተሻለውን ከውስጥዋ ሊየወጣ የተዘጋጀን ሰው ነው፡፡
እግዚአብሔር የፈጠረው በራስዋ የረካች አንድን ባለራእይ ልትረዳ የተዘጋጀችን ሴት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው የሚያነሳትን ባል የምትፈልግን ሴት ሳይሆን እግዚአብሔር ስለእኔ ምክኒያት ቤቱን ይባርካል ብላ የምታምንን የእምነትን ሴት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው የሚያሳልፍላትን ባል የምትፈልግን ሴት ሳይሆን እንደ ልጅ ከአባት እንዴት በፀሎት እንደምትቀበል የምታውቅን ሴት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው በመስጠት በመባረክ በማካፈል ላይ ያተኮረችን ሴት ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ስለግንኙነት በረከት ሲናገር አንዱ ሺህ ሁለቱ ደግሞ ሁለት ሺህ ያሳድዳሉ አይደለም የሚለው፡፡ እንደዚያ ከሆነማ ሁለቱም ጎዶሎ በመሆናቸው 50 % ሊያዋጡ ነው ማለት ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ግን በህብረት ውስጥ ስለተቀመጣው ታላቅ እምቅ ሃይልክ ሲናገር አንዱ ሺህ ሁለቱ ደግሞ አስር ሺህ ያሳድዳሉ ነው የሚለው፡፡
ወንድና ሴት ከመጋባታቸው በፊት ሁለቱም በጌታ ሙሉ መሆን አለባቸው፡፡ በጌታ ሙሉ የሆነውን ሰው ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ያለው፡፡ ወንድ 100 % ሴትም መቶ % ሲሆኑ ነው ሲያብሩ አስር ሺህ የሚያሳድዱትና እግዚአብሔ በህብረት ውስጥ ያስቀመጠውን እምቅ ጉልበት የሚለቁት፡፡
ወንድና ሴት ግን ጎዶሎዎች ከሆኑና እርሱም በጎዶሎነት አስተሳሰብ ሙሉ የሚያደርገው ኢየሱስ ላይ ካላተኮረና የምትሞላውን ከፈለገ እርስዋም በዋናው በሚያረካው በእግዚአብሔር ካልረካችና በምስኪንነት አስተሳሰብ የሚሞላትን ከፈለገች ሁለቱም ሳይገናኙ መሃል ላይ ይቀራሉ፡፡ ሁለቱም ሙሉ የሚያደርጋቸውን ክርስቶስን ትተው በጎዶሎነት የሚሞላቸውን ሲፈልጉ እግዚአብሔር በትዳር ውስጥ ያስቀመጠው ታላቅ ሃይል ሳይገለጥ ይቀራል፡፡
ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም ያልሆነው ጎዶሎው እንዲሞላ ሳይሆን ሙላቱ እንዳይባክን ነው፡፡
ስለዚህ ነው ሰው ካገባም በኋላ አላግባብ በሚስቱ ላይ እንዳይደገፍ የእግዚአብሔር ቃል የሚመክረው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ያላገባ ሰው በእግዚአብሔር ላይ መደገፉን እንዳይለውጥ የሚመክረው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ሰው ለትዳሩ በሚሰጠው በሚያበረክተውና በሚያካፍለው ነገር ላይ እንጂ ከትዳሩ በሚጠቀመው ነገር ላይ ያለልክ እንዳይደገፍ የሚመክረው፡፡
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡29
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Monday, August 28, 2017

ትዳር የእግዚአብሔር ስርአት

ትዳር የሰው ሃሳብ አይደለም፡፡ ትዳር የሰው ፈጠራ አይደለም፡፡ ትዳር የሰው እቅድ አይደለም፡፡ ትዳር የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው፡፡ ትዳር እግዚአብሔር ራሱ ያቋቋመው ተቋም ነው፡፡ ትዳር የእግዚአብሔር ስርአት ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት። ዘፍጥረት 2፡18
አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር። ዘፍጥረት 2፡20-25
ትዳርን አለመቃወም የእግዚአብሄርን መንግስት አለመቃወም ነው፡፡ ትዳርን አለመቃወም የእግዚአብሄርን አሰራር አለመቃወም ነው፡፡ ለትዳር መስራት ለእግዚአብሄር መንግስት መስራት ነው፡፡ ትዳርን ማክበር የእግዚአብሄርን ስርአት ማክበር ነው፡፡ ትዳርን መውደድ እግዚአብሔርን መውደድ ነው፡፡ ትዳርን ማክበር እግዚአብርን ማክበር ነው፡፡
መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ዕብራውያን 13፡4
ትዳርን መቃወም የእግዚአብሔርን ስርአት መቃወም ነው፡፡ ትዳርን መቃወም አግዚአብሔርን መቃወም ነው፡፡ የትዳር መጠንከር የእግዚአብሔር መንግስት መጠንከር አንዱ አካል ነው፡፡
ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። ሮሜ 13፡2
ኢየሱስ ስለመጋባት ሲናገር በመጀመሪያ ግን እንደዚህ አልነበረም በማለት የእግዚአብሄርን ሃሳብ ለመረዳት የመጀመሪያውን የጥንቱን የእግዚአብሄርን ሃሳብ መረዳት ወሳኝ እንደሆነ ይነግረናል፡፡
እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፦ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። እነርሱም፦ እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። እርሱም፦ ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። ማቴዎስ 19፡4-8
የመጀመሪያው ኦሪጂናል የእግዚአብሄር ሃሳብ እውነት ነው፡፡ ሰው የሚጠቀመው ከእውነት ጋር ሲስማማ ነው እንጂ ከእውነት ተቃራኒ ሲሆን አይደለም፡፡ ሰው ከእውነት ተቃራኒ ሲሆን ይጎዳል፡፡ እጅግ ጠቢብ ሰው ከእውነት ጋር ይወግናል እንጂ በእውነት ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡  
ሐዋሪያው ጳውሎስ ከእውነት ጋር መወገን እንጂ ከኦሪጂናል በእግዚአብሄር ሃሳብ ላይ ወይም በእውነት ላይ ምንም ማድረግ እንደማይችል የተናገረው፡፡
ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡8
ስለዚህ ነው ኢየሱስ እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው በማለት የሚያስጠነቅቀን፡፡
እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። ማርቆስ 10፡9
ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5-6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Sunday, August 27, 2017

ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው

21 ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ።
22 ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤
23 ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና።
24 ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ።
25-26 ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤
27 እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።
28 እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤
29-30 ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል።
31 ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
32 ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ።
33 ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን
ትፍራ።
ኤፌሶን 5፡21-33
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Saturday, August 26, 2017

የስኬት መመዘኛ

ስኬት ሰፊ ትርጉም ያለው ሃሳብ ሲሆን ትርጉሙም የተፈለገውን ውጤት ማግኘትና አለማን መፈፀም ማለት ነው፡፡ ተፈላጊው ውጤት ወይም አላማ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ደግሞ መመለስ የስኬትን ትከክለፃ ትርጉም እንድናገኘው ይረዳናል፡፡
በስኬት ምን ውጤት ወይም አላ እንደምናገኝ ከማየታችን በፊት ስኬት ማለት ምን ውጤትና አለማ ማሳካተ እንዳልሆነ እንመልከት፡፡ በስኬት ማፍኘት ያለብንን ውጤትና መምታት ያለብንን አላማ ምን እንዳይደለ ማየት ስለ ስኬት ትርጉም ትክክለኛውን ብርሃን ይሰጠናል፡፡
ስኬት የልጅነት ህልማችንን መፈፀም አይደለም፡፡
አንዳንድ ሰዎች ስኬት የሚመስለዓቸው በልጅነታቸው ሲያስቡት ሲመኙ የነበሩትን ነገር መፈኘም ነው፡፡ ነገር ግን ስጀኬት የልጅነት አላችንን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ማስፈፀም አይደለም፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ የተመኙትነ ነገር ሁሉ አድርገው ሁሉ ከንቱ ነው ያሉትን ሰዎች ስንመለከት እወነተኛ ስኬት የልጅነት ህልማችንን መፈፀም አነዳይደለ እናስተውላለን፡፡
ስኬት ሰው የደረሰበት መድረስ አይደለም፡፡
ስኬት ሰው የደረሰበት መድረስ አይደለም፡፡ ስኬት ሰው የደረሰበት መድረስ ነው ካልን የትኛው ሰው የሚለውንም ጥያቄ መመለስ አለብን፡፡ ስኬት ከሰው ጋር መወዳደር አይደለም፡፡ ከሰው ጋር ተወዳድሮ ያሸነፈ ሰው ከስኬት የወደቀ ሰው ነመው፡፡ ስኬት ከሰው ጋር ተወዳድሮ ማሸነፍ አይደለም፡፡ ስኬት ሰው የደረሰበት መድረስ አይደለም፡፡
ስኬት ለእግዚአብሔር በማቀድ መፈፀም አይደለም
ስኬት እግዚአብሔር እንዲህ ይፈልጋል ብሎ በመገመት እና በማድረግ አይለካም፡፡ ስኬት ለእግዚአበሔር ጥሩ በማቀድ አይለካም፡፡
የሰማሁትን አስተማሪ ታሪክ ላካፍላችሁ፡፡ ተማሪው የመመረቂያ ፅሁፍ እንዲፅፍ በታዘዘው መሰረት ፅሁፉን ያቀርባል፡፡ አስተማሪው ጠርቶ እንዲህ ይለዋል፡፡ ፅሁፉ በጣም ጥሩ ይዘት ነው ያለው ፣ በጣም ጥሩ አቀራረብ ነው ያለው ፣ በጣም ጥሩ ነጥቦች ነው የነሳኸው ፣ በጣም ጥሩ ፅሁፍ ነው ነገር ግን የቤት ስራው ይህ አልነበረም አለው ይባላል፡፡ ለእግዚአብሔ ጥሩ ነገር ከሰራን በሁዋላ እግዚአብሔር ግን የኔ ሃሳብ አይደለም ካለን ህይወታችንን አባክነነዋል፡፡
ስኬት ምን የልጅነታችንን ህልም በማሳደድ በዚያም ውጤቶችን በማግኘትና እንዲሁም ስኬት ለእግዚአብሔር በማቀድና እቅዱን ግብ በመምታት እንደማይለካ ካየን አሁን ደግሞ ስኬት በምን እንደሚለካ እንመልከት፡፡
1.      ስኬት የእግዚአብሔርን አላማ በመስፈፀም ይለካል፡፡  
የተፈደጠርነው ለእግዚአብሔር ክብርና አላማ ነው፡፡ ስኬት የሚለካው የራሳችንን አላማ በማስፈፀም ሳይሆን እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለውን አላማ በመከተል ነው፡፡ ስኬት ከመሬት ተነስረን ለእግዚአብሔር እንዲህ ላድርግለት በማለት የሚመጣ ሳይሆን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ከራሱ ከእግዚአብሔር ፈልጎና አውቆ በመታዘዝ ይለካል፡፡ ለእግዚአብሔር አዳዲስ ሃሳቦችን አንፈጥርለትም፡፡ ለእግዚአብሔር ትልልቅ ነገሮችን አናልምለትም፡፡ እግዚአብሔር ስለእያንዳንዱ ነገር አላማና እቅድ አለው፡፡ ስኬታችን ያለንን አላማ በማግኘትና በመከተል ይለካል፡፡
ስለዚሁ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን፥ ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም፤ ቆላስይስ 1፡9
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
2.     ስኬት ክህሎታችንን በመግለፅ ይለካል፡፡
ወደ እዚህ ምድር ስንመጣ ቤተክርስትያንን ብሎም የአለም ህዝብን ለማገልገል ለምድር ከሚያስፈልገው ክህሎትና ተሰጥኦ ጋር ተፈጥረናል፡፡ በቤተክርስትያንም እንዲሁ እያንዳንዳችን ከአካሉ ውስጥ የተሰጠን የተለየ የስራ ድርሻ ያለን ብልቶች ነን፡፡ ስኬታችን የሚለካው እያንዳንዳችን ያሰኘንን ነገር በማድረግ ሳይሆን እግዚአብሔር የጠራንን ልዩ የብልትነት የስራ ድርሻ በመወጣቱ ላይ ነው፡፡
እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ኤፌሶን 4፡1
ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10
3.     ስኬት ራሳችንን በመሆን ይለካል፡፡
ስኬት የሚለካው ሌላውን በመምሰል ሳይሆን ራሳችንን በመቀበልና በመሆን ነው፡፡ ስኬት የሚለካው ሌላውን ሰው በመሆን ድራማ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው አንድን አቢይ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ተደጋጋሚ ቅጂ አብዮችን አይፈልግም፡፡ እግዚአብሔርም ልጁን ኢየሱስን የሚገልፀው በእያንዳንዳችን ሁኔታ ነው፡፡
ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ገላትያ 1፡15-16
ሌላውን እንድትሆኑ በሚፈትነው በዚህ የውድድርና የፉክክር ዘመን ሌላውን ለመሆን ከመፍጨርጨር አርፈን ራሳችንን መሆን ስኬት ነው፡፡ አንተ ባለህ ደረጃ ፣ ባለህ ስጦታ ፣ ባለህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ደስተኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር በህይወት ላለህ ጥሪ ፍፁም አድርጎ ስለፈጠረህ ስለሆንከው ነገር አያፍርም ይቅርታም አይጠይቅም፡፡ አንተም ስላለህና ስለሆንከው ነገር በአሰራሩ እንድታፍርና እንድትሸማቀቅ እግዚአብሔር አይፈለግም፡፡ እግዚአብሔር ራስህን እንድትሆን ይፈልጋል፡፡ በህይወትህ ያስቀመጠውን አላማ በሙላት ትፈፅም ዘንድ ራስህን መሆን ትልቅ ነፃነት ይሰጥሃል፡፡ ተዋናኝ መሆን ከባድ ነገር ነው፡፡ ተዋናኝነት ለጥቂት ደቂቃ ድራማ ብዙ ልምምድ ፣ ጉልበትንና ጊዜን ይፈጃል፡፡ ህይወቱን መኖር ትቶ ሌላውን ለመምሰል ከሚለማመድ ሰው በላይ ህይወቱን የሚያባክን ሰው የለም፡፡
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡12
4.     ስኬት በክርስቶስ የሆነውን በመተግበርና በመኖር ይላካል፡፡
ስኬት እግዚአብሔር በክርስቶስ ያዘጋጀልንን ህይወት በመለማመድ ይለካል፡፡ በክርስትያ ህይወት የመጨረሻው ስኬት በክርስቶስ የሆነውን መኖር ነው፡፡ የክርስትና የመጨረሻው ደረጃ ክርስቶስን እንድንመስል የተፈጠርንበትን አላማ መፈፀም ነው፡፡ የክርስትያን ስኬት የሚለካው በህይወቱ በሚታየው ክርስቶሳዊ ባህሪ ነው፡፡ የክርስትያን የመጨረሻው ግብ ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ 
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30
እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። 1 ቆሮንቶስ 11፡1
5.     ስኬት በፍቅር በመኖር ይለካል፡፡
የህግ ፍፃሜ ፍቅር ነው፡፡ የህግ ትእዛዛቶች ሁሉ ሲጨመቁ የሚሰጡት በፍቅር መኖርን ነው፡፡ በፍቅር ከሚኖር ሰው በላይ በምድር ላይ ስኬታማ ሰው የለም፡፡
የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1፡5
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ስኬት #ወንጌል #ፍቅር #በክርስቶስ #የጌታፈቃድ #የጌታአላማ #ባለጠጋ #ጠቢባን #ሃያላን #ሞገስ #ክንውን #በረከት #ቃል #ፀሎት #አምልኮ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, August 25, 2017

ኃጢአት አይገዛችሁምና

ሃጢያት አስከፊ መንፈሳዊ በሽታ ነው፡፡ ሰዎች ለብዙ በሽታዎች መድሃኒት ሰርተዋል ለሌሎቹም በሽታዎች መድሃኒት ለመስራት እጅግ ይጥራሉ፡፡ ከበሽታዎች ሁሉ የከፋው በሽታ ደግሞ ሃጢያት ነው፡፡ ከእስራቶች ሁሉ አስከፊው እስራት የሃጢያት እስራት ነው፡፡ የሃጢያት መድሃኒት ያለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ሰዎችን ከእግዚአብሄር የለየውንና ከአላማቸው ያሰናከላቸውን የሃጢያትን መድሃኒይት ለሰው ላመምጣት ነው፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ሰዎችን ከሃጢያት ለማዳን ነው፡፡
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
ከሃጢያት ካልዳንክ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበትን ዋናውን አላማ ስተኸዋል ማለት ነው፡፡ ሃጢያት አሁንም የሚገዛህ ከሆነ ስለመዳን ያልተረዳኸው ነገር አለ ማለት ነው፡፡   
ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤ መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል። ቲቶ 2፡11-14
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ለሁለት ምክኒያቶች ነው፡፡
ኢየሱስ ወደምድር የመጣበት ምክኒያት ከዚህ በፊት የሰራነውን ሃጢያት እዳ ለመክፈልና በደሙ ሃጢያታችንን ለማጠብ የሃጢያት ይቅርታን እንድናገኝ ስለሃጢያታችን በመስቀል መስዋእት ሊሆን ነው፡፡
በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ኤፌሶን 1፡7
ኢየሱስ ሃጢያታችን ይቅር ብሎን ብቻ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ከሃጢያት የበላይ የምንሆንበትን አሰራር ባያዘጋጅ ኖሮ ከሃጢያት የዳንን ሳንሆን ሃጢያት የሚገዛን ባዶ ሃይማኖተኞች ብቻ እንሆን ነበር፡፡
ኢየሱስ ግን ስለበፊቱ ሃጢያታችን እዳ መክፈል ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ ተመልሰን በሃጢያት እንዳንኖር ሃጢያት የሚያሰራንን ስጋዊ ባህሪያችንን በመስቀል ላይ ለመስቀል ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው ለሃጢያት ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ሃጢያት እንዳይገዛን ሃጢያተኛ ባህሪያችንን በመስቀል ላይ ለመግደል ነው፡፡   
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ለራሱ አይደለም፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው ለእኛ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰቀለው እኛን ወክሎና ተክቶ ነው፡፡ የኢየሱስ ስጋ በመስቀል ላይ የተሰቀለው የእኛን ሃጢያተኛ ስጋ ይዞና ተክቶ ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሰቀል ስጋዊ ባህሪያችን አብሮ ተሰቅሎዋል፡፡ የኢየሱስ ስጋ በመስቀል ላይ ሲሞት ስጋዊ ባህሪያችን አብሮ ተገድሎዋል፡፡ አሁን ስጋዊ ባህሪያችን ተሽሮዋል፡፡
ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6
ሃጢያተኛ ባህሪያችን ተሽሮዋል፡፡ ያልተረዳ ሰው ብቻ ነው የተሻረ ነገር እንዲገዛው የሚፈቅድ፡፡ የተታለለ ሰው ብቻ ነው የተሻረ ነገር እንዲገዛው የሚፈቅድ፡፡ አሁን ሃጢያት አይገዛንም፡፡
ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ የሚለው፡፡
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው የሚያስመካው የእርሱ ጉልበት ሳይሆን ሃጢያተኛ ስጋው በመስቀል ላይ እንዲሰቀልና ከሃጢያት እንዲድን ያደረገው የእግዚአብሄር አሰራር እንደሆነ የሚናገረው፡፡
ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ገላትያ 6፡14
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ትንሳኤ #ሃይል #ስልጣን #ስጋ #ስጋዊባህሪ #መስቀል #ኃጢያት #ፋሲካ #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Thursday, August 24, 2017

ለእግዚአብሄር ፈንታ ስጡ እንጂ

እግዚአብሄርን የመራንን ነገሮች ስናደርግ አንዳንዴ ሰዎች ላይረዱን ይችላሉ፡፡ የሚመለከታቸው ሰዎች ካልተረዱን ደግሞ በራሳችን ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ አብረናቸው የእግዚአብሄርን ስራ እንድንሰራ የተሰጡን ሰዎች ካልተረዱን ለእግዚአብሄር መልቀቅ አለብን፡፡ የራሳችንን ድርሻ ከተወጣን በኋላ ለእግዚአብሄር አሰራር ደግሞ ጊዜና ስፍራ መስጠት አለብን፡፡ ለእግዚአብሄር አንድ እያንዳንዱ ሰው ነገር ለማድረግ ራሱ አጥብቆ መረዳት አለብት፡፡
ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ ሮሜ 4፡20
እግዚአብሄርም ሰዎች ያላወቁትንና ያልተረዱትን ነገር እንዲያደርጉ አይጠብቅም፡፡ እኛን እግዚአብሄር ተናገረን ብለን ሰዎችን ማስገደድ አንችልም፡፡ እኛ ነፃ ፈቃድ እንዳለን ሁሉ ሌሎች ሰዎችም አይ አይደለም ለማለት ፈቃድ እንዳላቸው ማወቅና መቀበል ይገባናል፡፡ ከእግዚአብሄር የሆነውን ለሚመለከታቸው ሰዎች ከተናገርን በኋላ ራሳችን ለማስፈፀም መሞከር በእግዚአብሄር ሳይሆን በራስ መተማመን ነው፡፡
ድርሻችንን ከተወጣን በኋላ ማረፍና ለእኛ እንደተናገረን እግዚአብሄር ራሱ እንዲናገራቸው ጊዜ መስጠት ወሳኝ ነው፡፡ እኛን እንደተናገረን ራሱ እግዚአብሄር እንዲናገራቸው እድሉን ካልሰጠን ሰዎች የተናገርነው ነገር የእኛን የራስ ወዳድነት ፍላጎት አድርገው ሊረዱት ይችላሉ፡፡ ይዘን የመጣነው ሃሳብ የእኛ የግላችን ሃሳብ እንዳልሆነና የሃሳቡ ዋናው ባለቤት እግዚአብሄር እንደሆነ ለማሳየት እኛ ዝም ማለት ይገባናል፡፡ እኛ ዝም ካላልንና ሰዎች የእግዚአብሄርን ድምፅ አጥርተው ካልሰሙ የእግዚአብሄርና የእኛን ድምፅ ይቀላቀልባቸዋል፡፡ ስለአንድ ነገር የእግዚአብሄርን ድምፅ ለራሳቸው መስማት የሚችሉት እኛ ዝም ስንልና ጊዜ ስንሰጥ ብቻ ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡19
እግዚአብሄር ከግርግር ባሻገር ለራሳቸው የሚናገራቸው ስንታገስና ጊዜ ስንሰጥ ነው፡፡ ሰዎች የራሳችንን ጥቅም እንደምናሳድንድ ካሰቡ ስሜታቸው ይረበሻል፡፡ በዚህም ሁኔታ ጌታን በትክክል መስማት ይሳናቸዋል፡፡ እኛ ዝም በምንልበት ጊዜ ግን እግዚአብሄር ራሱ በዝምታ እንዲናገራቸው ምቹ ሁኔታን እንፈጥርላቸዋለን፡፡  
ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። ሆሴዕ 2፡16
በአለም ላይ በአማኞች ብዛት ታላቁን ቤተክርስትያን የመሩት መጋቢ ዲቪድ ዮንጊ ቾ በኮሪያ የኢኮኖሚ ውጥረት ጊዜ እግዚአብሄር 10 ሺህ ሰው የሚይዝ ቤተክርትስትያን እንዲሰሩ እንደተናገራቸው ይመሰክራሉ፡፡ ስለዚያም እያፀለዩ እያሉ እግዚአብሄር ለሚስታቸው ቤት መስሪያ ያጠራቀሙትን ገንዘብ የመጀመሪያው መዋጮ አድርገው እንዲሰጡት ይናገራቸዋል፡፡ በእጃቸው የነበረው ብቻኛው ገንዘብ የሚስታቸው ገንዘብ ነበር፡፡ በኮሪያ ባህል ባል ለሚስቱ ቤት ይገዛ ስለነበር እሳቸው ለሚስታቸው ቤት ለመግዛት ያጠራቀሙት የሚስታቸው ቤት መግዣ ገንዘብ ነበር፡፡ እሳቸው ለሚስታቸው እግዚአብሄር ገንዘቡን እንዲሰጡ እንደተናገራቸው ይነግሩዋታል፡፡  የሚስታቸው መለስ ግን ያንን ገንዘብ ለመስጠት በፍፁም እንዳታስብ የሚል ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ያለችውን ሰምተሃል ብለው ፀልየው ይተዉታል፡፡
ሚስታቸው ግን ልትትወው አልቻለችም፡፡ ሚስታቸው እንቅልፍ አጣች፡፡ እኔ ተኝቼ እነሳለሁ እርስዋ ግን ሌሊቱን ሙሉ ትገላበጣለች እንጂ እንቅልፍ በአይኑዋ አልዞረም ይላሉ፡፡ በእንቅልፍ ማጣት አይንዋ እያበጠ ሄደች፡፡ በሰባተኛው ቀን ይላሉ ቾ ያንን ገንዘብ ውሰደው አለችኝ ብለው ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜ በሰጡ ጊዜ እግዚአብሄር ከሚመለከተው ሰው ጋር ነገሮችን እንደጨረሰ ይመሰክራሉ፡፡
እግዚአብሄር የተናገረንን ለሚመለከታቸው ሰዎች ካሳየን በኋላ መታገስ እና ጊዜ መስጠት እግዚአብሄር ደግሞ በራሱ መንገድ እንዲናገራቸው እድልን ይሰጠዋል፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜ ካልሰጠን የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት ስንሮጥ እንደ ራስ ወዳድ ሰዎች ለጥቅማችን የምንከራከር ይመስላል፡፡ ስለዚህ ነው ከቤተክርስትያን መሪነት መመዘኛዎች አንዱ አለመከራከርና አለመጨቃጨቅ የሆነው፡፡   
የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡3
ስለዚህ ነው ሰው ካንተ ጋር ቦክስ ወይም ቡጢ ሊገጥምህ ሲፈልግ አንተ ከቦክሱ ሜዳ ውጣና ባንተ ፋንታ እግዚአብሄርን ወደ ቦክሱ ሜዳው አስገባው የሚባለው፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ፋንታ የሚዋጋው እኛ ከሰዎች ጋር ውጊያን ስናቆም ብቻ ነው፡፡ እራሳችንን የምናየውና ከተሳሳትን የምንታረመው ለእገዚአብሄር አሰራር ጊዜ ስንሰጥ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርም በማሸነፋችን ክብሩን የሚወስደው እኛ ለእግዚአብሄር አሰራር ጊዜና እድል ስንሰጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። ዘፀአት 14፡14
እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም ውጡባቸው። 2ኛ ዜና 20፡17
እግዚአብሄር የመራንን ከተናገርን በኋላና እግዚአብሄር ያለንን ካደረግን በኋላ ካላረፍን በስተቀር የእኛ ስራ እንጂ የእግዚአብሄ ስራ አይሆንም ፣ የእኛ ሃይል እንጀ የእግዚአብሄር ሃይል አይሆንም እንዲሁም የእኛ ጥበብ እንጂ የእግዚአብሄር ጥበብን አይሆንም፡፡
ኢዮአስም እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ፦ ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው። መሣፍንት 6፡31
እኛ ከእግዚአብሄር ጋር አብረን ሰራተኛ ነን እንጂ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ የእግዚአብሄርን ስራ የምንሰራ ብቸኛ ባለቤቶች እና ተሟጋቾች አይደለንም፡፡ መስራት የምንችለውን ካደረግን በኋላ ለዋናው ባለቤት ጊዜውንና ስፍራውን እንለቃለን፡፡  
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ስፍራ #እውቀት #ጥበብ #ቦክስ #ቡጢ #የማይጨቃጨቅ #ገር #የማይከራከር #ክርስትያን #አማርኛ #ፍጥነት #ማስተዋል #መፅሃፍቅዱስ #ፈንታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #እድል #ጊዜ