Popular Posts

Follow by Email

Sunday, June 16, 2019

ስምንቱ የአባቶች ቀን ውሳኔዎች


1.      ልጆቼን ልመክርና ልገስፅ ግን ላላቆጣ እወስናለሁ
እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡4
2.     ለልጆቼ በእግዚአብሄር ቃል ምሳሌ ለመሆን እወስናለሁ
ባገኘሁት ጊዜ ሁሉ የስጋ ልጆቼ ላልሆኑት የአባትነትን ምክርና እንክብካቤ እሰጣለሁ፡፡
3.     ልጆቼን የእግዚአብሄርን መንገድ ለማሳየት ለማስተማር እወስናለሁ፡፡
ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም። መጽሐፈ ምሳሌ 22፡6
4.     ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል በመትጋት ለማቅረብ  እወስናለሁ፡፡
ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 5፡8
5.     አባት ለሌለው ለድሃ አደጉ የመፍረድና የመከራከር መልካም ስራ በትጋት ለመስራት እወስናለሁ፡፡
መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። ትንቢተ ኢሳይያስ 1፡17
6.     የቤተሰቡን ችግር ከፊት ሆኜ ልጋፈጥ ችግሩ ወደ ቤተሰቤ እንዳይመጣ ቤተሰቤን ልከላከልና ጥላ ልሆናቸው እውስናለሁ፡፡
አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ መዝሙረ ዳዊት 103፡13
7.     በማንኛውም ሁኔታ ቤተሰቤን ላፅናና እና ላበረታታ እወስናለሁ፡፡
የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡3
8.     በስጋ ልጄ ላልሆነ በተለይ ይህ የአባትነት እድል ለማያገኘው በየትም ስፍራ ለማገኘው ልጅ በቻልኩት መጠን ሁሉ የአባትነት ተምሳሌ ልሆነው በህይወቱ ላይ አንድ የማበረታቻ ቃል አንኳን ቢሆን የአባትነትን አስተዋፅኦ ለማድረግ እወስናለሁ፡፡   
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
መልካም የአባቶች ቀን!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ወላጅ #ፍቅር #አባት #እርማት #ጥንካሬ #ራእይ #ደረጃመስጠት #ጥላ #ማበረታታት #አባትነት #ተግሳፅ  #መሪ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ልናጣው የማንችለው ነገር ሁሉ የእኛ አይደለም

ልናጣው የማንችለው ነገር ሁሉ የእኛ አይደለም
በህይወታችን ዘመን ብዙ በረከቶች ወደ ህይወታችን ይመጣሉ:: እኛን  ለመባረክና እና ለመጥቀም እግዚአብሔር ልዩ ልዩ መንገዶችን ይጠቀማል:: በህይወታችን ያለውን አላማውን ለመፈጸም እግዚአብሄር በብዙ አይነት እና በብዙ መንገድ የሚጠቀምባቸው ነገሮች ሁሉ የጊዜው ናቸው እንጂ ለዘላለም አይደሉም::
ከእግዚአብሔር ውጭ ምንም ቋሚ ነገር የለም:: ከእግዚአብሔር ውጭ የሚታየው ነገር ሁሉ ሃላፊ ነው::
ቋሚ ያልሆነን ነገር እንደ ጊዜያዊነቱ በትክክል መያዝ ከብዙ ጭንቀት ያድናል::
ከእግዚአብሔር ውጭ ይህን ካላገኘሁ አልኖርም የምንለው ምንም ነገር መኖር የለበትም::
እግዚአብሔር የሚሰጠንን ነገሮች  ጨምሮ አንድ ቀን እንደማንለያቸው አድርገን ውስጣችን ማስገባት ችግርን መጋበዝ ነው:: የራሳችንን ማንነትና ነፃነት እስከምናጣ ድረስ ሁኔታዎችን ውስጣችን መክተት ጊዜያዊዉን ነገር ስንለየው ስቃይ ውስጥ መግባት ያስገባናል:: የነገሮችን ጊዜያዊነትና ልካቸውን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ የሚለውን ቃል መከትል ጥበብ ነው::
አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም። 2ኛ ጢሞቴዎስ 4:5
ለዘላለም ከሚኖረው ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ ሁኔታዎችን ወደ ውስጣችን አለማስገባትና በውጭ መጠበቅ ስንለይ ከሚመጣ የመለያየት ስቃይ ይጠብቀናል::
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ . . . የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4:17-18
ብዙ ጊዜ ሰይጣን የሚያስፈራራንና እስራት ውስጥ የሚከተን ይህን ነገር ብታጣውስ ብሎ በማስፈራራት ነው:: እግዚአብሔርን አልጣው እንጂ ካለእርሱ መኖር የማልችለው ምንም ነገር የለም ካልን ለሰይጣን እድል ፈንታ አንሰጠውም:: ከእግዚአብሔር ውጭ ካለእርሱ መኖር አልችልም የምንለው ነገር ካለ በዘመናችን ሁሉ በፍርሃት ባርነት ውስጥ እንቆያለን ::
ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡27
በምንም ነገር በእውነት ተጠቃሚ የምንሆነው ላጣው አልችልም ብለን የምናስበውን ነገር ከሌለና ማንኛውንም ነገር ለማጣት ከተዘጋጀን ብቻ ነው::
ይህን ካጣኽው መኖር አትችልም የሚለው በፅኑ ልንቃወመው የሚገባ የሰይጣን ድምፅ ነው::
ልንይዘውና ልንጠቀምብት  እንጂ ምንም ነገር ሊይዘን እና ሊቆጣጠረን አይገባም::
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡29-31
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ፀሎት #ልመና #ምልጃ #ምስጋና #ውዳሴ #በመጠኑ #እንደፈቃዱ #መጠየቅ #መንበርከክ #ይቃትታል #መንፈስቅዱስ #እንዲሰማን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, June 14, 2019

እንደ ህፃናት ካልሆናችሁሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ እንዲህም አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። የማቴዎስ ወንጌል 18፡2-3
ሰው የተፈጠረው እንደ ህፃን የዋህ ተደርጎ ነው፡፡ አዳምና ሄዋን በሰይጣን ተንኮል አእምሮዋቸው ከመበላሸቱ በፊት እንደህፃን እግዚአብሄርን ሙሉ ለሙሉ ያምኑት ነበር፡፡ ከውድቀታቸው በፊት ለአዳምና እና ለሄዋን እግዚአብሄር አንድን ነገር አለ ማለት ሆነ ተደረገ ማለት ነበር፡፡ ከሃጢያት በኋላ ግን ሰው የህጻንነት የዋህነቱንና ገርነቱ አጥቷል፡፡
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡2-3
ህፃናት ከአዋቂዎች የተለየ ባህሪ አላቸው፡፡ ይህ ባህሪ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ በጣም የሚፈልግ ባህሪ ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ስርአት እንደ ህፃናት የሆኑ ሰዎች ብቻ እንዲከናወኑበት የተሰራ ስርአት ነው፡፡ እንደ ህፃን ለማይሆኑ ሰዎች የእግዚአብሄር መንግስት ለማደግና ለማፍራት ተስማሚ ስፍራ አይደለም፡፡ የህፃንነት ባህሪ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሁኔታዎችን ተቋቁመን እንድናልፍ የሚያደርግ ወሳኝ ባህሪ ነው፡፡ የህጻንነት ባህሪ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርገን እግዚአብሄር ወዳየልን የህይወት ከፍታ የምንወጣበት ባህሪ ነው፡፡
አንድ አዋቂ ሰው የልጆች አለም ውስጥ ገብቶ እንደ ልጆቹ መጫወቻውን ቦታ ሊደሰትበት ፣ ሊዝናናበት እና ሊጠቀምበት እንደማይችል ሁሉ እንደህፃን የማይሆን ሰው በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ደስተኛ ሊሆን ፣ በሚገባ ሊኖርና ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ከዋህነትና ከገርነት ጉድለት በአጠቃላይ እንደህፃናት ካለመሆን እንድንመለስና እንደ ህፃናት እንድንሆን እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡
በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ እጅግ ወሳኝ የሆነው የህፃናት ባህሪ ምን እንደሆነ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
1.      ህፃናት ቀጥተኛ ናቸው
ህፃናት በልባቸው የሚያስቡትና በአፋቸው የሚናገሩት የተለያየ አይደለም፡፡ ህፃናት በልባቸው አንድ ነገር በአፋቸው ሌላ ነገር የለም፡፡ ህፃናት አንድ ናቸው፡፡ ህፃናት በተንኮል ወይም በድብቅ ሃሳብ አእምሮዋቸው አልተበላሸም፡፡ ህፃናት ቀጥተኛና ንፁህ ናቸው፡፡ ህፃናት ቅን ናቸው፡፡
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡2-3
2.       ህፃናት  ለማመን ፈጣን ናቸው
ህፃናት ለማመን ይፈጥናሉ፡፡ ህፃናት በቀላሉ ራሳቸውን ይሰጣሉ፡፡ እኛም በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ቃሉን እንድናምን እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ በተስፋ ቃሉ ሙሉ ለሙሉ እንድንደገፍ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ለቃሉ ህጻናት እንድንሆንና በቃሉ የተናገረውን ነገር ሳንጠራጠር በፍጥነት እርምጃ እንድንወስድ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡  
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። የያዕቆብ መልእክት 1፡21
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ። 1 የጴጥሮስ መልእክት 2፡1-3
3.       ህፃናት በደልን አይቆጥሩም
እስከምትደነግጡ ድረስ ህፃናት በደልን በቶሎ ይረሳሉ፡፡ ህፃናት በደልን አያጠራቅሙም፡፡ ህፃናት ክፉን በክፉ ለመመለስ አያቅዱም፡፡ ህፃናት በደልን ይተዋሉ፡፡
ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡17
የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡5
4.     ህፃናት ትንሽ ስጦታ ያስደንቃቸዋል
ህግፃናት ያመሰግናሉ፡፡ ህፃናት ትንሽ ነገርን ማድነቅ ይችላሉ፡፡ ህፃናት ያላቸው ነገር ላይ እንጂ ያላገኙት ነገር ላይ አያተኩሩም፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡15
5.     ህፃናት አይጨነቁም
ህፃናት የሚኖሩት በዛሬ ውስጥ ነው፡፡ ህፃናት በትላንት ወይም በነገ ውስጥ አይኖሩም፡፡ ህፃናት የሚኖሩት እያንዳንዱን ቀን አንድ በአንድ ነው፡፡
ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡34
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ልብ #ህፃንነት #ብስለት #ጥበብ #ማስተዋል #አላማ #ቅንነት #የዋህነት #አለመጨነቅ #እምነት #ማድነቅ #ማመስገን #በደልንአይቆጥርም ##መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ጥሪ #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አንድነት #ትህትና #አክብሮት #ስልጣን #መሪ

Thursday, June 13, 2019

እንዳለ


ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
እንደ እውነቱ ከሆነ በእግዚአብሄር የማያምኑ ብዙ ሰዎች በምድር ላይ አሉ፡፡ እርሱም ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን የማያምኑ ብዙ የሃይማኖት ተከታዮች በምድር ላይ ይኖራሉ፡፡ እውነት ነው እግዚአብሄር የለም ብለው የሚያምኑ እና በግልፅ የሚናገሩ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን በልባቸው እግዚአብሄር የለም የሚሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ 
እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል። ወደ ቲቶ 1፡16
እግዚአብሄርን የሚያውቁ እንደሆነ በአፋቸው የሚናገሩ ነገር ግን በስራቸው የሚክዱት ብዙ ሰዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል፡፡ አስተውሉ ሰነፍ በአፉ አይደለም እግዚአብሔር የለም የሚለው፡፡ የሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም አስተሳሰብ የሚገለፀው በድርጊቱ ብቻ ነው፡፡ 
ሰነፍ በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም። መዝሙረ ዳዊት 141
በአፉ እግዚአብሄር አለ ብሎ የሚናገር ወይም እግዚአብሄር የለም ብሎ በአፉ የማይናገር ነገር ግን በልቡ እግዚአብሔር የለም የሚል የሰነፍ ሰውን ምልክቶችን እንመልከት፡፡
1.      እግዚአብሄርን እንደፈራጅ አያየውም
ሰው የፈለገውን ክፉ ነገር አድርጎ ከእርሱ በላይ ፈራጅ እንደሌለ እንደሚሄድ ካሰበ እግዚአብሄር እንዳለ አያምንም፡፡
2.     እግዚአብሄርን አይፈራም
ሰው ጥበቡ የማይመረመር ሃያል አምላክ እንዳል ካላመነ በስተቀር እግዚአብሄርን እንዴት ሊፈራ ይችላል፡፡ እግዚአብሄር እንዳለ የማያምን ሰው እግዚአብሄርን ሳይሆን ሰውን ይፈራል፡፡ በፊቱ ሁሉ ነገሮች የተራቆተና የተገለጠ አምላክ እንዳለ የማያምን ሰው ነገሮቹን ሁሉ በሰው ፊት ያደርጋል፡፡ ሁሉንም የሚያይ አምላክ እንዳለ የማያምን ሰው ከሰው በመደበቁ እና ሰውን በመዋሸቱ ብቻ እንደተሳካለት ያስባል፡፡  
እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። ወደ ዕብራውያን 4፡13
3.     ባለው ነገር ይመካል ይታመናል
እግዚአብሄር እንዳለ የሚያምን ሰው እግዚአብሄርን ከመታመን ውጭ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ባለው ነገር የሚታመን ሰው እግዚአብሄር እንዳለ አያምንም፡፡ እግዚአብሄር እንዳለ ባለማመኑ የሚመካበትና የሚደገፍነበት ቁሳቁስ ዝና እና ጥበብን ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24
4.     እግዚአብሄር የምድር ባለቤት እንደሆነ አይታመንም
ሰው እግዚአብሄር እንዳለ ካላመነ  በምድር ላይ ያለውን ነገር ሁሉ እግዚአብሄር እንደፈጠረ እና እርሱ ባለቤት እንደሆነ አይረዳም፡፡ ሰው ምድር አንድ ባለቤት እንዳለው ሰው አስተዳዳሪ እና ባላአደራ እንጂ የምንም ነገር ባለቤት እንዳልሆነ የሚረዳው እግዚአብሄር እንዳለ ሲያመን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንዳለ የማያምን ሰው በጊዜያዊነት በታማኝነት ተጠቅሞ ከማለፍ ይልቅ የምድር ነገር ባለቤት ለመሆን ሲፍጨረጨር ህይወቱን በከንቱ ይፈጃል፡፡
ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2፡8
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

Wednesday, June 12, 2019

አትሳቱ


አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡33
የእግዚአብሔርን ህግ መከተል ከህመም ያሳርፋል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ማዳማጥ እግዚአብሄርን ለህይወታችን ያለውን ፈቃዱን ከመሳት ያድናል፡፡ ለእግዚአብሄር ቃል የዋህ መሆን ከብዙ ጥፋት ያድናል፡፡
ከእግዚአብሄር በላይ ያወቅን ሲመስለን ራሳችንን እንጎዳለን፡፡ ለእግዚአብሄር ትእዛዝ ቸልተኞች ስንሆን የማይገባንን ዋጋ እንከፍላለን፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ አትሳቱ ይላል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ አይምሰላችሁ ይለናል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ አትሸወዱ ብሎ በብርቱ ይመክረናል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ አትሳቱ ያለበት ምክኒያት ይህ ነገር ሰው ብዙ ሰው ብዙ ጊዜ የሚሳሳትበት ነገር ስለሆነ ነው፡፡ ሰው ብዙ ጊዜ ከሆነው በላይ ጠንካራ የሆነ ይመስለዋል፡፡ ሰው ብዙ ጊዜ ከሆነው በላይ ጠቢብ እንደሆነ ሲመስለው ይሸወዳል፡፡
እግዚአብሄር አዋቂ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄር አታድርግ ያለውን አድርጎ በሰላም እንደሚኖር ካሰበ ሞኝ ሆኖዋል፡፡ ሰው እግዚአብሄር ተው ያለውን ሳይተው እንደማይወድቅ ካሰበ ተታሏል፡፡
እግዚአብሄር አትሳቱ ይለናል፡፡ በምን ብለን መጠየቅ እና ትእዛዙን በፍጥነት ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ብልህነት ነው፡፡
እግዚአብሄር በተለይ በክፉ ባልነጀርነት አትሳቱ ብሎ ይመክረናል ያስጠነቅቀናል፡፡ ክፉ ባልንጀራ ይዞ ክፉ አልሆንም የሚል ሰው ለራሱ ከሚገባው በላይ ግምት እየሰጠ ነው፡፡ ክፉ ባልንጀነት ይዞ አልስትም ማለት በከንቱ በራስ መመካት ነው፡፡ የክፉ ባልንጀርነት ውጤት እኔን አይነካኝም ብሎ ማሰብ ትእቢት ነው፡፡
ወደድንም ጠላንም ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል፡፡ በክፉ ባልንጀርነት ቆይተን አለን ያልነው መልካም አመል  ቢጠፋ አንደነቅ፡፡ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ይበላል፡፡
ስለምድራዊ ህይወት ብቻ ከሚያስብ ሰው ጋር ያለ ወዳጅነት የሰውን የሰማያዊ አስተሳብ ያጠፋል፡፡ በቁሳቁስ ላይ ብቻ ከሚያተኩር  ሰው ጋር ያለ ባልንጀርነት ስለመንፈሳዊ ያለን ትኩረት ቢያደበዝዘው አያስገርምም፡፡ ስለሆድ ብቻ ከሚያስብ ሰው ጋር ያለ ባልንጀርነት  ይዋል ይደር እንጂ የፍቅርና የአገልግሎት ዘርን ከውስጣችን ያመክነዋል፡፡ ስለጥርጥር ከሚያስብ ሰው ጋር ያለ ግንኙነት እምነታችንን ባይጎዳው ይገርማል፡፡    
መልካሙን አመል ከመጠበቅ ይልቅ ከክፉ ባልንጀርነት ራስህን መጠበቅ ይቀላል፡፡ በክፉ ባልንጀርነት መካካል መልካምን አመል ለመጠበቅ ከመሞከር ይልቅ ክፉ ባልንጀርነት ላይ መጨከንና ከክፉ ባልንጀርነት ፈጥኖ መለየት ይቀላል፡፡ በክፉ ባልንጀርነት ውስጥ መልካም አመልይ ይዞ ከመቆየት ይልቅ ክፉ ባልንጀርነትን በፍጥነት መቁረጥ በቀላሉ ከመከራ ይገላግላል፡፡
አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡33
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ወዳጅ #ጓደኛ #መታመን #ጥበብ #ፍቅር #ባልንጀርነት #መልካም #አመል #ክፉ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Tuesday, June 11, 2019

የህይወት ከንቱነትበኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። መጽሐፈ መክብብ 1፡1-2
ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥሮአል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በክብሩ ፈጥሮታል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ግን ይህን የከበረ ህይወት በክብር የሚይዘው ሁሉም ሰው አይደለም፡፡
እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ።  ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡17
እግዚአብሔር በሰው ላይ ከፍ ያለ ዋጋ ቢያደርግም ለህይወቱ የሚገባውን ዋጋ የሚሰጠው ሰው ግን ሁሉም አይደለም፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠ የከበረው ህይወት እንደ እግዚአብሔር መንገድ ካልተኖረ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ሊሆን ይችላል፡፡
ሰው የራሱ ፈቃድ አለው፡፡ ሰው ህይወቱን በፈለገው መንገድ የመምራት ሙሉ ፈቃድ ያለው ተደርጎ ተፈጥሮአል፡፡ ሰው ህይወቱን አክብሮ ህይወቱን በክብር ሊመራ ወይም ሰው ህይወቱን ሊንቅ የተፈጠረበትን አላማ ሊስትና የማይገባውን ኑሮ ሊኖር ይችላል፡
ህይወትን ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ሊያደርጉ የሚችሉ አምስት ነገሮችን ከመፅሃፍ ቅዱስ እንመልከት
1.      አላማ ቢስ ህይወትን መኖር
ለእግዚአብሔር አላማ ተፈጥሮ እያለ ሰው ለህይወቱ የእግዚአብሄርን አላማ የማይፈልግና የማይከተል ከሆነ ህይወቱ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ሰው አላማ በእግዚአብሔር ቃል በኩል የተፈጠረለትን የእግዚአብሔርን አላማ ካልፈፀመ ህይወት ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡
ጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። ትንቢተ ኢሳይያስ 40፡6-8
2.     በፍቅር አለመኖር
ሰው በፍቅር ለመኖር ተፈጥሮአል፡፡ ከፍቅር ያነሰ ምንም አይነት ህይወት ለሰው ከንቱ ነው፡፡ ህይወት ዋጋ የሚኖረው በፍቅር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰው ምንም ዝነኛ ፣ ጥበበኛ ፣ ሃያል እና ባለጠጋ ቢሆን ፍቅር ግን ከሌለው ከንቱ ነው፡፡
ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡2-3
3.     በጥንቃቄ አለመኖር
ሰው ዘመኑን በጥንቃቄ ካልያዘው ያባክነዋል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን ህይወት አጭርና በጥንቃቄ መኖር ያለበት ነው፡፡ ትንሽ ጥንቃቄ ጉድለት ለብዙ ክፋት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ 
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡15-16
በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡13-14
ሰው በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖር አድርጎ በጥንቃቄ ካልኖረ ህይወት ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡
4.     እንደ እንግዳ አለመኖር  
የምድር ህይወት አጭር ነው፡፡ የምድር ህይወት የእንግድነት ህይወት ነው፡፡ የምድር ህይወት ጊዜያዊ መተላለፊያ ህይወት ነው፡፡ አንድ ቀን በፈጠረን በጌታችን ፊት እንቀርባለን፡፡ አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ቅርቦ እንደሚጠየቅ ተደርጎ ካልተኖረ ህይወት ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ 
በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፡19፣32
5.     በእምነት አለመኖር 
ሰው የተፈጠረው የእግዚአብሔር ቃል ሰምቶ እንደእግዚአብሔር ቃል እና እንደፈቃዱ በእምነት እንዲኖር ነው፡፡ ሰው በእምነት ካልኖረ ከእግዚአብሔር ጋር ሊገናኝ እና በምንም መልኩ እግዚአብሔርን ሊያስደስት አይችልም፡፡ ሰው በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቹ ብቻ በሚያየውና በሚሰማው ብቻ ከተመላለሰ ከእግዚአብሄር ጋር የሚያገናኘው ምንም መስመር ስለሌለ ህይወቱን ከንቱ ያደርገዋል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
ሰው እግዚአብሔርን በቃሉ ካላመነ ሊከተለው ፣ እራሱን ለጌታ ሊሰጥና እግዚአብሔር ወደአየለት የክብር ደረጃ ሊደርስ አይችልም፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። የማቴዎስ ወንጌል 16፡25
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ፍቅር #አላማ #እምነት #ጥንቃቄ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መውደድ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ