Popular Posts

Tuesday, January 30, 2018

ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ

ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡27
ስጋዊ ምኞት ከእግዚአብሄር በረከት የሚያጎድለን ጠላታችን ነው፡፡ ስጋ ወዳጅ አይደለም አይለመንም፡፡ ስጋ እንደ እኩያ ኣ እንደወዳጅ አይደራደሩትም፡፡ ወደ እሳት እየሄደ ያለን ህፃን እንደማይለምኑት ፣ እንደማይደራደሩትና ሮጠው በግድ እንደሚነጥቁት ስጋም እንዲሁ ነው፡
ስጋ የምታስብለት የምትንከባከበው አይደለም፡፡ ስጋ የምትጨክንበት ፣ የምታስርበውና የምትገድለው ነው፡፡ ስጋ የሚጠይቀውን ሃጢያት በከለከልከው መጠን እየደከመ ይሄዳል፡፡ ስጋ የሚፈልገውን ሃጢያት ባልሰጠኸው መጠን አቅም እያጣ ይሄዳል፡፡ ስጋ ላይ በጨከንክበት መጠን ይደክማል፡፡
ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ገላትያ 5፡16
የስጋ ጥያቄ ይችን ብቻ ስጠኝ ነው፡፡ የስጋ ጥያቄ አሁን ብቻ ነው፡፡ አሁን ብቻ ይህችን ብቻ ለሚለው ጥያቄ እሺ ካልከውና ሃጢያትን ካመቻቸህለት ስጋን ታበረታዋለህ፡፡ ስጋን ሃጢያት በሰጠኸው መጠን ፍላጎቱ እየጨመረ ፣ ተጨማሪ እየጠየቀና የጩኸቱ ድምፅ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስጋን ደግሞ አይ አይሆንም እምቢ ባልከው መጠን ድምፁ እየቀነሰ እየደከመ እየሞተ ይሄዳል፡፡
ስጋ እንደታሰረ ውሻ ነው፡፡ የታሰረ ውሻ ያስፈራራል ፣ መጣሁልህ ይላል ፣ በላሁህ ይላል፡፡ ግን እንደታሰረ ካወቅን ቦታ አንሰጠውም አንሰማውም፡፡ ስጋ እንደታሰረ ውሻ ቸል ሊባል ይገባዋል፡፡ ስጋ ካልሰማኸኝ አለቀልህ የሚለው ፉከራው ካለሰማኸው እጣ ፈንታው መድከምና መሞት እንጂ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ ስጋ ሊራብ ይገባዋል፡፡ ስጋ የሚፈልገው በመከልከል ሊሰቀልና ሊገደል ይገባዋል፡፡  
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ቅዱሳን የሚፈልገውን ባለማድረግ ስጋን ከምኞቱ ጋር እንደሰቀሉት የሚናገረው፡፡
የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። ገላትያ 5፡24
ስጋ ያለልክ እንዳይጠግብ ምግቡን ሃጢያት በመከልከል ልክ ማስገባት ያለብን እኛ ነን፡፡ ስጋን መጨቆን ያለብን እኛ ነን፡፡ ስጋን የመጨቆን ሃላፊነት የተጣለው በእኛ ላይ ነው፡፡ ስጋ ላይ መጨከን ያለብን እኛ ነን፡፡
ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም። ቆላስይስ ሰዎች 2፡23
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ለስጋ ምኞት እንዳናስብ እንዳናመቻችለት የሚያስጠነቅቀን፡፡
በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ሮሜ 13፡13-14
መንፈስ የሚቃወመውን ስጋን የምናዳክመው ስጋን በመጨቆን ነው፡፡ ለስጋ ባለማሰብና ለእርካታው ባለማቅረብ ነው መንፈስ እንዲያሸንፍ የምንረዳው፡፡ ስጋን በማስራብና በማዳከም ነው መንፈስ እንዲመራ የምናደርገው፡፡ ስጋ የምንቀርበው ሃሳቡን እህህ ብለን የምንሰማው አይደለም፡፡ ስጋን በፍጥነት የምንቃወመው ፣ ብዙ እንዲያወራ የማንፈቅድለት ፣ በሃይል የምንጎሽመውና ለእግዚአብሄር ሃሳብ የምናስገዛው ነው፡፡  
ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ስጋ #ምኞት #ማሰብ #ህይወት #ሞት #ደስታ #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና

ስጋ የሚበረታበት ዋናው መንገድ

ጌታ ኢየሱስን እንደ አዳኙ የተቀበለ ሰው ሁሉ አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ እንደ አዲስ ፍጥረት ለማፍራት ለእግዚአብሄር ነገር ግድ የሌለውን ስጋዊ ምኞትን እንቢ ማለት አለብን፡፡ ስጋ ደግሞ የእግዚአብሄርን ነገር የማይፈልግ በመንፈሳዊው ወጭ ለጊዜው ብቻ መደሰት መዝናናት የሚፈልግ ነው፡፡
ስጋ እንዲበረታና እርሱን እንዲመራው የሚያደርገው ሰው ነው፡፡ ሰው ስለስጋ በማሰብ ስጋዊ ምኞት እንዲያሸንፈው ያደርጋል፡፡ ነገር ግን በመንፈስ የሚመላለሱ ስጋን ከክፉ መሻቱ ጋር ሰቀሉት እንደሰቀሉት መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡
የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። ገላትያ 5፡24
ሰው ቁጭ ብሎ ስለስጋ የሚያስብ ፣ የሚያወጣና የሚያወርድ ከሆነ ለስጋ መጠንከርና ማሸነፍ ያመቻችለታል፡፡ ሰው ስጋውን ሰለማስደሰት ግድ የሚለውና ስጋውን ለማስደሰት የሚያስብና የሚያቅድ ከሆነ ስጋ እየበረታ እያሸነፈ ይሄዳል፡፡  
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ ሮሜ 8፡5-7
ስጋ እንዳይበረታና እንዳያሸንፍ የሚያደርገውም እንዲሁ ሰው ነው፡፡ ሰው ስጋን እንደጠላት በማየት ስለስጋ ባለማሰብ ስጋ እንዳያሸንፍ ማድረግ ይችላል፡፡ ሰው ስለስጋ ባለማሰብ ብቻ ስጋ ምኞቱን እንዳይፈፅም እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል፡፡ ሰው ስለስጋ ባለማሰብ በስጋ ላይ መንገድን ሁሉ ሊዘጋበት ይችላል፡፡  
ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ሮሜ 13፡12-14
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ስጋ #ምኞት #ማሰብ #ህይወት #ሞት #ደስታ #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና

Monday, January 29, 2018

አሮጌውን ሰው አስወግዱ

ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ ኤፌሶን 4፡22
አሮጌው ሰው ስጋዊ ባህሪ ነው፡፡ አሮጌው ሰው እግዚአብሄርን የማይፈልግ የምድራዊ ሰው ባህሪ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ለእግዚአብሄር ነገር ግድ የሌላው የተፈጥሯዊ ሰው ባህሪ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ለመንፈሳዊ ነገር ዋጋ የማይሰጥ ሰው ባህሪ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የተጣላ ሰው ሃሳብ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ለእግዚአብሄር የማይገዛ ሰው ሃሳብ ነው፡፡ አሮጌው ሰው እግዚአብሄርን ሊያስደስት የማይችል ሰው አካሄድ ነው፡፡
አሮጌው ሰው የስጋ ሃሳብ ነው፡፡ አሮጌው ሰው የሃጢያት ሃሳብ ነው፡፡ አሮጌው ሰው የክፉ ምኞት ሃሳብ ነው፡፡
ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። ሮሜ 8፡6-8
አሮጌው ሰው የሚፈልገው መዝናናት ፣ መብላት ፣ መጠጣት ፣ መስከር መደሰት ብቻ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ስለምንም ነገር ሃላፊነት መውሰድ አይፈልግም፡፡ አሮጌው ሰው በማንም እንደማይጠየቅ እንደማይፈረድበት ሃላፊነት የጎደለው ሰው አካሄድ ነው፡፡ አሮጌው ሰው ስለ ሰማይ ግድ የለውም አሮጌው ሰው አርቆ ሊያይ አይችልም አሮጌው ሰው የአሁን ሰው ብቻ ነው፡፡ አሮጌው ሰው አላማና ግን የለውንም ህይወት እንደነዳው የሚሄድ ራሱን የማይገዛ ሰው አካሄድ ነው፡፡  
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። ፊልጵስዩስ 3፡19
አሮጌው ሰው "ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ" እንደሚሉት አይነት ሰው ነው፡፡ ስጋ የእግዚአብሄር አላማ ፣ የእግዚአብሄር ፍቃድ ፣ ለእግዚአብሄር መኖር ፣ ጌታን መከተል ፣ ራስን መካድ ፣ ጌታን ማስደሰት የሚሉት ነገሮች አይገቡትም አይረዳቸውም፡፡
ለአሮጌው ሰው የእግዚአብሄር መንግስት የማይታይ የማይጨበጥ ነገር ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው የእግዚአብሄር ነገር ሞኝነትይ ነው፡፡
ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14
ለአሮጌው ሰው ፍቅር ሞኝነት ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው ራስ ወዳድነት የህይወት መንገድ ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው ስግብግብነት ህይወት ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው ትህትና ደካማነት ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው ምህረት ማድረግ አለማወቅ ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው ጥላቻ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው መስጠት ማካፈል ማባከን ነው፡፡ ለአሮጌው ሰው ትእቢት ሃያልነት ነው፡፡   
አሮጌውን ሰው አስወግዱ ሲል በአሮጌው ሰው አካሄድ አትሂዱ ማለት ነው፡፡ አሮጌውን ሰው አስወግዱ ሲል በአሮጌው ሰው አስተሳሰብ አትመሩ እያለን ነው፡፡ አሮገውን ሰው አስወግዱ ሲል አሮጌው ሰው ዋጋ ለሚሰጠው ነገር ዋጋ አትስጡ እያለን ነው፡፡
ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ሮሜ 13፡14
ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ ኤፌሶን 4፡22
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #ዘር #ባህሪ #አሮጌውሰው #ፊተኛ #አዲሱሰው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና

Sunday, January 28, 2018

የእምነት ያለህ አትበል

እግዚአብሄር ከሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ ስለፈለገ ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክንያት ከእግዚአብሄር ከተለያየም በኋላ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር እንዲገናኝ በዘመናት ሁሉ እግዚአብሄር ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል፡፡
እግዚአብሄር አሁንም ከሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ ስለሚፈልግ ከእርሱ ጋር የሚገናኝበትን መንገድ አዘጋጅቷል፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት የሚችለው በእምነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚደርሰው በእምነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚያገኘው በእምነት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጠይቆ የሚቀበለው በእምነት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ተግባብቶ የሚኖረው በእምነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚሰማውና የሚታዘዘው በእምነት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የሚራመደው በእምነት ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
እምነትን ለማግኘት ሰው እጅግ የተመረቀ ሰው መሆን የለበትም፡፡ እምነትን እንዲኖረው ሰው ቅዱስ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ሰው እምነት እንዲኖረው ሰማእት መሆን የለበትም፡፡
እምነት እጅግ ርቆ የተሰቀለ ዳቦ አይደለም፡፡ እምነት አንዳንድ ሰዎች ብቻ በድንገት የሚያገኙት እድል አይደለም፡፡ እምነት ለጥቂት ለተመረጡ ሰዎች የሚመጣ ገጠመኝ አይደለም፡፡ እምነት እጅግ ጥቂት ሰዎች ተመራምረው የሚደርሱበት ረቂቅ ነገር አይደለም፡፡
እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል መስማት የሚችል ሰው ሁሉ እምነት ሊኖረው ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያነብ ሰው ሁሉ እምነት ሊመጣለት ይችላል፡፡ እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚሰማ ማንኛውም ሰው እምነት ይመጣለታል፡፡
ሰው ዝም ብሎ እምነትን መመኘት የለበትም፡፡ ሰው እምነት እንዲኖረው ቁጭ ብሎ መጓጓት የለበትም፡፡ ሰው እምነት ያላቸውን ሰዎች ተመልክቶ በተስፋ መቁረጥ መቋመጥ የለበትም፡፡ ሰው እኔ እንግዲህ እምነትን ከየት አመጣዋለሁ ማለት የለበትም፡፡
ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፦ በልብህ፦ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም፦ በልብህ፦ ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ሮሜ 10፡6-8
እምነት ቀርቧል፡፡ እምነት በማንም ሰው ይገኛል፡፡ እምነት ለማንም ሰው የተሰወረ አይደለም፡፡ እምነት ከማንም ሰው ሩቅ አይደለም፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የማገኝበት እምነት ከየት ይገኛል ማለት አይችልም፡፡ ሰው የእምነት ያለህ እንዳይል እምነት እንዴት እንደሚገኝ በመፅሃፍ ቅዱስ ተፅፏል፡፡
እምነት የሚገኘው የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል አንብብ እምነት ይሆንልሃል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስማ የእምነት ሰው ትሆናለህ፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

ራስን መግዛት በሰይጣን ላይ በርን ይዘጋል

ሰይጣን የህይወት ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋ ነው እንጂ ስለሌላ አይመጣም፡፡ ሰይጣነ ስራው መስረቅ ማረድና ማጥፋት ነው፡፡ ሰይጣን ከዚህ ውጭ ስራ የለውም፡፡ ሰይጣን ተልእኮዬን ከግብ አደረስኩ የሚለው ሰዎች ሲሰረቁ ፣ ሲታረዱና ሲጠፉ ነው፡፡
ሰይጣን ደግሞ ይመጣል፡፡ ሰይጣን ይሰራል፡፡  
የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። ሉቃስ 8:12
ኢየሱስ የዚህ አለም ገዢ ይመጣል ከእኔ አንዳች የለውም ብሎዋል፡፡
ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤ ዮሃንስ 14፡30
ኢየሱስ ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋ የተራበ የዚህ አለም ገዢ እየመጣ ከእኔ አንዳች የለውም ሊል እንዴት ቻለ?  
እኛስ የዚህ አለም ገዢ እየመጣ በእኛ ላይ አንዳች እንዳይኖረው ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ሰይጣን በመስቀል ላይ በኢየሱስ ድል ስለተነሳ ተሸንፎዋል፡፡ ሰይጣን በግድ አስገድዶ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ነገር ግን ሰይጣን ሰውን የሚሰርቀው የሚያርደውና የሚያጠፋው በሰው ባህሪ ድክመት ተጠቅሞ ነው፡፡ ሰውጣን ሰውን ከመስረቅ ከማረድና ከማጥፋቱ በፊት ደካማ ባህሪውን ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን በሰው ውስጥ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነ ባህሪ ካላገኘ ሰውን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ አይቻለውም፡፡ ሰውን ለመስረቅ ሰይጣን በመጀመሪያ በሰው ውስጥ ጥላቻን ይፈልጋል፡፡ ሰውን ለማረድ ሰይጣን ቁጣን በሰው ውስጥ ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን ሰውን ለማጥፋት መጀመሪያ ትእቢትን በሰው ውስጥ ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን እነዚህን ባሪያት በውስጣችን ካላገኘ ይመጣል ግን ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ ሰይጣን እነዚህን እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆኑ ባህሪያት ካገኘ ህይወታችን ለመስረቅ ለማረድና ለማጥፋት ይመቸዋል፡፡
በፍቅር በሚኖር ሰው ለመጠቀም ሰይጣን አይችልም፡፡ በምህረት የሚኖረውን ሰው ለማረድ ሰይጣን አይችልም፡፡ ትሁት የሆነን ሰው ህይወት ለማጥፋት ሰይጣን አይችልም፡፡
ስለዚህ ሰይጣንን በተዘዋዋሪ መንገድ ከህይወታችን ለመከላከልና ለሰይጣን በህይወታችን ውስጥ ስፍራ ለማሳጣት ባህሪያችንን መከታታል ይኖርብናል፡፡ በህይወታችን በሰይጣን ጥቃት ላይ በር ለመግዛት በእግዚአብሄር ቃል እግዚአብሄር መምሰል መልካም ባህሪያችንን መገንባት ይኖርብናል፡፡  
ሰይጣን የሚወደውና የሚጠቀምበትን ባህሪ ከህይወታችን ካስወገድን የዚህ አለም ገዢ ይመጣል ከእኔ ግን አንዳች የለውም ማለት እንችላል፡፡
ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡26-27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና 

Saturday, January 27, 2018

እምነት ተስፋ አይደለም!

እምነት በተፈጥሮአዊው አለም የማይታየውን ማየት ነው፡፡ እምነት መንፈሳዊውን አለም ማየት መቻል ነው፡፡ እምነት ልእለ-ተፈጥሮአዊውን አለም ማየት ነው፡፡
እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ዕብራውያን 11፡1
እምነት ተስፋ የምናደርገውን ነገር የሚያስረግጥ ነገር ነው፡፡ እምነት የተስፋ ማረጋገጫ ነው፡፡ እምነት ተስፋችን እንደሚፈጸም ማረጋጫ ነው፡፡
እምነት ተስፋ ማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ እምነት ተስፋ የምናደርገውን ነገር ማስረጃ ነው፡፡ እምነት ተስፋችን እንደሚፈፀም ማረጋገጫው ነው፡፡
እምነትና ተስፋ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እውነት ነው ለእምነት ተስፋ ያስፈልጋል፡፡ ተስፋ ብቻ ግን አምነት አይደለም፡፡ ተስፋ እና የተስፋ ማረጋገጫው በአንድነት እምነት ይባላል፡፡
ተስፋ አንድ ነገር ወደፊት እንደሚሆን መጠበቅ ነው፡፡
በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን። ሮሜ 8፡24-25
ተስፋ አስፈላጊ ነው፡፡ ካለ ተስፋ እምነት አይኖርም፡፡ ተስፋ አለን ማለት ግን እምነት አለን ማለት አይደለም፡፡ አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ ይላል፡፡ . . . በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡24
አንድ ሰው ወደፊት እንደሚፈወስ ተስፋ አለኝ ካለ ተስፋ አለው ማለት ብቻ ነው፡፡ ተስፋ ብቻ ለመፈወስ አይበቃም፡፡ ተስፋና የተስፋው ማረጋገጫ የሆነው እምነት ሲኖረን እንፈውሳለን፡፡ ለመፈወስ ተስፋ ብቻ ሳይሆን እምነት ይጠይቃል፡፡
ሰው እምነት ሲኖረው ይፈወሳል፡፡ ሰው ግን በተስፋ ብቻ አይፈወስም፡፡ ተስፋው ማረጋገጫ ካለው ይፈወሳል፡፡ ተስፋ ማረጋገጫው እምነት ከሌለው አይፈውስም፡፡
ሰው እግዚአብሄር በኢየሱስ የሰራለትን ለፈውሱ የተከፈለለትን ክፍያ ከእግዚአብሄር ቃል ሲረዳ ይፈወሳል፡፡ ሰው በኢየሱስ መገረፍ ቁስል እንደተፈወሰ ሲያምን ተስፋ አያደርግም፡፡ ሰው በኢየሱስ መገረፍ ቁስል እንደተፈወሰ ሲያምን እምነቱን ይቀበላል፡፡
ሰው እንደተፈወሰ ሲያምን ተስፋ ማድረጉን ያቆማል፡፡ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ይላል መፅሃፍ ቅዱስ፡፡ የሚያየውን ተስፋ የሚያደርግ ሰው የለም፡፡ የሚያየውን ያመሰግንበታል ይጠቀምበታል እንጂ የሚያየውን ማንም ተስፋ አያደርገውም፡፡
እንደዚሁ በመገረፉ ቁስል እንደተፈወሰ ያመነ ሰው ተስፋ አያደርግም፡፡ ምክኒያቱ ተስፋ ሊመጣም ላይመጣም ይችላል፡፡ በመገረፉ ቁስል የተፈወሰ ሰው እግዚአብሄርን ስለፈውሱ ያመሰግናል እንደተፈወሰ ሰው ይኖራል፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የኢየሱስና የእኛ ልጅነት እንድነት እና ልዩነት

ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ ፅሁፌን ከሚከታተሉ ቅዱሳን መካከል በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ስላለ ልዩነት ብታስረዳ የሚል ጥያቄ ተቀብያለሁ፡፡ እኔም ይህ ለትምህርት ለሁላችን ይጠቅማለ ብዬ ስላሰብኩ ዛሬ ስለዚህ ሃሳብ በአጭሩ አንዳንድ ነገሮችን ላነሳ ወደድኩ፡፡ ትምህርቱ በጣም ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ ናቸው የምናለውን ብቻ መርጬ በአጭሩ አስረዳለሁ፡፡
የኢየሱስንና የእኛን የልጅነት አንድነትና ልዩነት ለመረዳት መጀመሪያ አንድነታችንን ብንመለከት ጥሩ መንደርደሪያ ይሰጠናል፡፡
የኢየሱስና የእኛ አንድነት
1.      ኢየሱስ በስጋ ነው የተወለደው እኛም በስጋ ነው የተወለድነው፡፡
ኢየሱስ የእኛን ስጋ ነው የለበሰው፡፡ የኢየሱስ ስጋ ከእኛ ስጋ በምንም አይለይም፡፡
እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ . . . በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራዊያን 2፡14-15
2.     ኢየሱስ እኛ በምንፈተንበት ፈተና ሁሉ ተፈትኗል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስ ስጋ ሃጢያትን የሚያሙዋልጭ ስጋ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አልስማማም፡፡ ኢየሱስ በስጋው ሃጢያት መስራት ባይችል ኖሮ አይፈተንም ነበር፡፡ ፈተና ያለው መውደቅ ስላለ ነው፡፡ አግዚአብሄር ይመስን ኢየሱስ ግን በሃጢያት ተፈተነ እንጂ በሃጢያት አልወደቀም፡፡
ኢየሱስ በሃጢያት የማይወድቅ ስጋ ቢኖረው ኖሮ ለእኛ የቅድስና ምሳሌ ሊሆንልን አይችልም ነበር፡፡
ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። ዕብራዊያን 4፡15
3.     ኢየሱስ በተፈጥሮአዊ መንገድ በጥበብ እና በሞገስ ያደግ ነበር እኛም እናድጋለን
እኛ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ብለን ተምረን በእግዚአብሄር ነገር እንደምናድግ ሁሉ ኢየሱስን ወደምድር ሲመጣ ራሱን ባዶ በማድረጉ የተነሳ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ሁለት ብሎ መማርና ማደግ ነበረበት፡፡
ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር። ሉቃስ 2፡52
4.     ኢየሱስ የሚያበረታው መንፈስ ቅዱስን መቀበል ነበረበት
በስጋው ወራት ካለመንፈስ ቅዱስ አሸናፊ የእግዚአብሄ ልጅ ሆኖ ማለፍ ስለማይችል መንፈስ ቅዱስን መሞላት አስፈልጎታል፡፡
ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ ሉቃስ 4፡1
5.     በእግዚአብሄር ከኢየሱስ ጋር እኩል ተወደናል
እግዚአብሄር ኢየሱስን ከሚወደው ያነሰ እኛን አይወደንም፡፡  
እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23
6.     ከኢየሱስ ጋር ወንድማማቾች ነን
ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ነው እኛም የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ ኢየሱስ ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን አላፈረብንም፡፡
የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13
7.     ኢየሱስን እንድንመስል ነው የተወሰንነው
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ ሮሜ 8፡29
ኢየሱስ ወደምድር የመጣው የእግዚአብሄር ልጅነትን ምሳሌ ሊያሳየን ናሙና ሊሆንልን ነው፡፡ አንድ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብር ሊያሳየን ነው፡፡
ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሃንስ 1፡14
8.     ኢየሱስ በምድር ላይ እንደተላከ እኛም ተልከናል፡፡
ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21

በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነገሮች መመልከት ይጠቅመናል፡፡
የኢየሱስና የእኛ ልዩነት
1.      ኢየሱስ ሃጢያት ሰርቶ አያውቅም እኛ ግን በንስሃ ከሃጢያታችን ተመልሰን ነው፡፡
እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21
2.     ኢየሱስ የሞተ መንፈስ ኖሮት አያውቅም እኛ ግን በአዳም በሃጢያት ከእግዚአብሄር የተለየው መንፈሳችን ዳግመኛ ተወልዶ ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
3.     ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የእግዚአብሄር ብቸኛ ልጁ ነበር፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃነስ 3፡16
4.     እኛ ከዳንን በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል
ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ከከፈለ በኋላ እና እኛም ለእኔ ነው ብለን ስንቀበለው የእግዚአብሄር ልጆች በመሆናችን የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ የነበረው ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል፡፡ አሁን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ እንጂ አንድያ ልጅ አይደለም፡፡  
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃነስ 1፡12
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30
5.     ኢየሱስ አዳኛችንና ቀዳሻችን ነው
ሁላችንም በሃጢያት እስራት ውስጥ ወድቀን በነበርን ጊዜ ስለሃጢያታችን እዳ መስዋእት የሆነልን ኢየሱስ ነው፡፡
የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13
6.     ኢየሱስ ጌታችን ነው እኛ ተከታዮቹ ነን
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሮሜ 10፡9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የልጅነትክብር #ናሙና #አንድያ #በኩር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ሞዴል #መምሰል #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, January 26, 2018

መጽናት ለምን

የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ዕብራውያን 10፡36
የምናየው ነገር ሁሉ የመጣው ከማይታየው ነገር ነው፡፡ የምናየው ነገር ሁሉ የማይታየው አለም ውስጥ የነበረ ነው፡፡ እምነትም የማይታየው አለም ውስጥ ያለውን ነገር አይቶ ወደሚታየው አለም እስኪመጣ መጠበቅ ነው፡፡  
ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። ዕብራውያን 11፡3
የእግዚአብሄ ፈቃድ ከመንፈሳዊው አለም ወደሚታየው አለም ከመምጣቱ በፊት የእኛን እምነትና ትግስት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ነው ስትፀልዩ እንደተቀበላችሁ እመኑ ይሆንላችኋል የሚለው፡፡ የሚታየው አለም ላይ ከመሆኑ በፊት ማመን ይጠይቃል፡፡  
ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ሉቃስ 11፡24
የእግዚአብሄር ፈቃድ ከማይታየው አለም ወደሚታየው አለም እስኪመጣ መጽናት ይጠይቃል፡፡ የእምነትን እርምጃ ከተራመድን በኋላ ውጤት እስከምናገኝ ድረስ መታገስ ወሳኝ ነው፡፡
በእምነት ጉዞ በተፈጥሮአዊ አይን የሚታየውን ባለማየት በመንፈሳዊ አይን የሚታየውን ደግሞ በማየት እንደሚቀበሉት መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17
እግዚአብሄር ተናገረን የእግዚአብሄን ፈቃድ አገኘን ማለት አካባቢ ሁሉ ከዚያ ቃል ጋር ከመቀጽበት ይስማማል ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውን የአካባቢ ሁኔታ ተቃራኒውን ሊናገር ይችላል፡፡ ስሜታችን ከእግዚአብሄር ፈቃድ ተቃራኒውን ሊያሰማን ይችላል፡፡
ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። መዝሙር 43፡5
እግዚአብሄር የተናገረንና የምናልፍበት ነገር እጅግ ሊለያይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ነው ሁኔታዎች እንዳያጠራጥሩን በልቡ ሳይጠራጠር ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡ ስሜታችንን ከተከተልን እንጠራጠራለን፡፡ ሁኔታውን ካየን እንጠራጠራለን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ሰምቶ በውሃ ላይ ይራመድ የጀመረው ጴጥሮስ መስመጥ የጀመረው የአካባቢውን ሁኔታ አይቶ ስለተቀበለው እና ስለፈራ ነው፡፡ 
ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ማቴዎስ 14፡30
ሁኔታም ሆነ ስሜታችን ሁለቱም ድንበራቸው የሚታየው አለም ብቻ ስለሆነና አቅማቸው ስለማይፈቅድ ስለእምነት እና ስለ እግዚአብሄር ፈቃድ ሊመሰክሩ አይችሉም፡፡
እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ማርቆስ 11፡23
የአካባቢያችን ሁኔታዎችና ስሜታችን ስለእግዚአብሄር ፈቃድ ሊመሰክሩ ብቁ አይደሉም፡፡ የአካባቢያችን ሁኔታዎችና ስሜታችን የምንታገሳቸው እንጂ ስለእምነት ነገር እውነተኛ ምስክሮች አይደሉም፡፡ 
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና የሚለው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

እምነትና ስሜት

እምነት በክርስትያን ህይወት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እንዲያውም ያለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት አይቻልም፡፡ ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻለም፡፡ ያለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር በሚገባ መኖር አይቻልም፡፡
ስሜት ደግሞ የአካባቢያችንን ሁኔታ የሚያሳውቀን የሰውነታችን ክፍል ነው፡፡ ስሜት በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን የምንረዳውን ነገር ያሳውቀናል፡፡ ስሜት ከአምስቱ የስሜት ህዋሳታችን በማየት ፣ በመስማት ፣ በመቅመስ ፣ በመዳደስና በማሽተት ከምንረዳው ነገር በላይ መሄድ አይችልም፡፡ ስሜት ድንበሩ ተፈጥሮአዊ አለም ብቻ ነው፡፡ ከተፈጥሮአዊ ወይም ከቁሳዊ አለም ያለፈን ነገር ስሜት መረዳት አይችልም፡፡   
እምነት ደግሞ በእነዚህ የስሜት ህዋሳቶቻችን ከምንረዳው ያለፈ በመንፈሳዊ አለም ያለውን ነገር ያያል ፣ ይሰማል ፣ ይቀምሳል ፣ ይዳስሳል እንዲሁም ያሸታል፡፡
የእምነት ክልል መንፈሳዊው አለም ፣ በአይን የማይታየው አለምና ልእለ ተፈጥሮአዊው አለም ነው፡፡ እምነት የሚያየው በተፈጥሮ አይን የማይታየውን ነው፡፡ እምነት የሚያየው በውስጠኛው በልቦና በመንፈስ አይን የሚታየውን ነው፡፡
ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡18-19
እምነት የሚደርሰው መንፈሳዊውን አለምን ነው፡፡ እምነት የሚደርሰው እና የሚይዘው በተፈጥሮአዊ እጃችን መያዝ የማንችለውን በመንፈሳዊ አለም ያለውን ነገር ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
የእምነት ክልል ከስሜት ክልል ያለፈ ስለሆነ የእምነትን ነገር ፣ የእግዚአብሄርን ነገር ፣ የመንፈስን ነገር በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን ልንረዳው አንችልም፡፡
ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14
እምነት የሚያየውን ነገር ስሜት በፍፁም አይረዳውም፡፡ ስሜት የሚረዳበት ክልል ተፈጥሮአዊው አለም ነው፡፡ እምነት ደግሞ የሚረዳበት ክልል መንፈሳዊው አለም ነው፡፡
ስለዚህ በእግዚአብሄር ቃል በእምነት የተረዳነው ነገር ከስሜታችን ጋር ሊቃረን ይችላል፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ አሸናፊ ነህ ሲል ስሜታችን የእግዚአብሄርን ቃል በእምነት መረዳት ስለማይችል የአካባቢውን ሁኔታ ብቻ ይናገራል፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ዕብራዊያን 10፡17
ስለዚህ ነው በእምነት የስሜትን ነገር መመልከት እና መከተል እንደሌለብን መጽሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡ በእንደ ጊዜ የማይታየውን በእምነት አይተንም የዙሪያችንን ሁኔታም አይተንም አይሆንም፡፡ ስለዚህ ነው በእምነት ስንኖር አካባቢያችንን የሚነግረንን ስሜታችንን መስማት እንደሌለብን መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ . . .  የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ