Popular Posts

Follow by Email

Sunday, April 30, 2017

እግዚአብሔርን አመልካለሁ

የዚያን ጊዜም፦ ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ? አሉት። እርሱም፦ እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ አላቸው። ዮናስ 1፡8-9
ነቢዩ ዮናስን ስራህ ምንድነው ብለው በጠየቁት ጊዜ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ ብሎ ነበር የመለሰው፡፡
እግዚአብሄርን ማምለክ በሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ ቤተክርስትያን አዳራሽ መሄድ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ መዘመር አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ሁለንተናችነን የሚጠይቅ መሰጠት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ 24 ሰአትና 7 ቀን የሚጠይቅ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ከንግግር ያለፈ ሙሉ አስተሳሰብንና ሙሉ ድርጊትን የሚጠይቅ መሰጠት ነው፡፡  
እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት
1.      እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን መፍራት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ቅዱስ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሃያል አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረንና ህይወታችንን በእጁ የያዘ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ከእግዚአብሄር ጋር በጥንቃቄ መኖር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን አለመናቅ ማክበር ማለት ነው፡፡  
የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። ዘጸአት 20፡7
2.     እግዚአብሄርን  ማምለክ ማለት ለእግዚአብሄር አምላክነት እውቅና መስጠት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን እንደ በላይ አምላክ ማየት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት በምናደርገው በማንኛውም ነገር የእርሱን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ማስገባት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርብን ማምለክ ማለት ለእግዚአብሄርን ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው፡፡
ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። ሮሜ 1፡20-21
3.     እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ለእግዚአብሄር መገዛት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ለእግዚአብሄር እሺ ማለት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን መስማትና መታዘዝ ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ያዕቆብ 4፡7
4.     እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት የእግዚአብሄር ባሪያ መሆን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት የራስን ፈቃድ ለእግዚአብሄር አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ለእኛ ደስታ ሳይሆን ለእሱ ደስታ መኖት ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። ያዕቆብ 1፡1
5.     እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት በእግዚአብሄር መልካምነት መሳብ መደነቅ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት በእግዚአብሄር ባህሪ መማረክ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምልክ ማለት በእግዚአብሄር አሰራራ መዋጥ ማለት ነው፡፡
በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ራእይ 1፡16-17
በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥ ለስሙም ዘምሩ፥ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ። እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፦ ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ። መዝሙር 66፡2-3
6.     እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን ማፍቀር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ከምንም ነገር በላይ እግዚአብሄርን መውደድ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ከምንም በላይ ለእግዚአብሄር ያለንን ፍቅር ማስበለጥ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ሙሉ ትኩረታችንን ለእግዚአብሄር መስጠት ማለት ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ማርቆስ 12፡29-30
7.     እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት በእግዚአብሄር መታመን ማለት ነው፡፡
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ ምሳሌ 3፡5
8.      በእግዚአብሄር ደስ መሰኘት ማለት ነው፡፡ አግዚአብሄርን ማምለክ ማለት በእግዚአብሄር መመካት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምልክ ማለት በእግዚአብሄር ከፍ ከፍ ማልት ነማለት ነው፡፡
በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። መዝሙር 105፡3
9.     እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን ብቻ ተስፋ ማድረግ ማለት ነው፡፡
አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው። መዝሙር 39፡7
10.    እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ከምንም ነገር በላይ እግዚአብሄርን መፈለግ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት ምንንም ነገር ከእግዚአብሄር አለማስተካከል ማለት ነው፡፡
ባለጠጎች ደኸዩ፥ ተራቡም፥ እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም። መዝሙር 34፡10
11.     እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን ከሌሎች ነገሮች ለይቶ ማየት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማምለክ ማለት እግዚአብሄርን ከሌሎች ነገሮች ጋር አለመቀላቀል ማለት ነው፡፡
ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡14-15
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጌታ #አምላክ #ኢየሱስ #ቃል #መገዛት #አምልኮ #መስማት #መታዘዝ #መውደድ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መከተል #መፅሃፍቅዱስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Saturday, April 29, 2017

ገዳም አይቀድስም ከተማ አያረክስም

ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠረን ለእግዚአብሄርና ለእግዚአብሄር ብቻ ለመኖር ከመፈለጋችን የተነሳ ከከተማ ወጥተን የሆነ ቦታ ሄደን ብቻችንን ብንሆን እንመኛለን፡፡ በአካባቢያችን ያለውን የሰውን የአለማዊነት ምኞት በመፀየፍ ነፍሳችን ትጨነቃለች፡፡
ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና፡፡ 2ኛ ጴጥሮስ 2፡7-8
ችግሩ ግን ሃጢያት ያለው በከተማ ውስጥ አይደለም፡፡ ቅድስም ያለው በገዳም ውስጥ አይደለም፡፡ ሃጢያት ያለው በሰው ልብ ውስጥ ነው፡፡
ለውጭው ነገራቸው እጅግ የሚጨነቁትንና ውጫዊ ነገር ያረክሰናል ብለው ለሚያስቡት ፈሪሳዊያን ኢየሱስ የውጭ ነገር ሰውን እንደማያረክስ ሰውን የሚያረክሰው የሰው የልብ ሃሳብ እንደሆነ ያስተምራቸዋል፡፡ ክፉ ሃሳብ የሚመጣው ከትልቅ ከተማ ውስጥ አይደለም፡፡ ክፉ ሃሳብ የሚወጣው ከሰው ልብ ውስጥ ነው፡፡  
ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ማቴዎስ 15፡18-19
ስለዚህ ኢየሱስ በልባቸው እንዲቀደሱ ቅድስና በቦታ ለውጥ ሳይሆን ቅድስና በልብ ለውጥ እንደሚመጣ ሲያስተምራቸው እንመለከታለን፡፡፡ ሰው ልቡን ከክፉ ሃሳብ ካጠራ አለሙን ከተማም ይሁን ገጠር ያጠራዋል፡፡ ሰው የልቡ ሃሳብ ከክፋት ካልጠራ ግን ከተማም ይኑር ገዳምም ይግባ ዋጋ ከአለም እርኩሰት መለየት አይችልም፡፡   
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ። ማቴዎስ 23፡25-26
ስለዚህ ነው ሰው አለምን ከመምሰል የሚድነው ገዳም በመኖር ወይም ከተማ ባለመኖር ሳይሆን ሰው አለምን የማይመስለው በአስተሳሰብ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ሰው በእግዚአብሄር ቃል አስተሳሰብ በልቡ መታደስ ካለተለወጠ የትም የትም ቢኖር አለማዊ አስተሳሰብ ይኖረዋል፡፡ ሰው ደግሞ በእግዚአብሄር ቃል አስተሳሰቡ ከተለወጠ ቅልጥ ያለው መሃል ከተማ እየኖረ አለምን ሳይመስል በቅድስና እግዚአብሄርን አስከብሮ ይኖራል፡፡
ኢየሱስ በቃሉ አማካኝነት እዚሁ በአለም እያለን እንድንቀደስ እንጂ ከአለም እንዲያወጣን አልፀለየም ፡፡  
ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ዮሃንስ 17፡15-17
አለምም የሚባለው የሃጢያተኝነት ምኞት እንጂ ከተማ አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃሳብ #አእምሮ #ልብ #ገዳም #አለም #እግዚአብሔርንመፍራት #ጥበብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የጥበብ መጀመሪያ ምንጭ

ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ የሰው መረዳት ዝቅተኛው መመዘኛ እግዚአብሄርን መፍራቱ ነው፡፡ የሰው መረዳት የሚጀምረው ከእግዚአብሄር ጋር እንዴት እንደሚኖር በማወቁ ነው፡፡ የሰው እውቀቱ የሚለካው በትንሹ ለእግዚአብሄር አምላክነት እውቅና መስጠቱ በማወቁ ነው፡፡ የሰው እውቀቱ የሚታየው ከእግዚአብሄር ከፈጣሪው ጋር ያለውን ግንኙነት በመረዳቱ ነው፡፡ 
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ምሳሌ 1፡7
ሰው እጅግ የተዋጣለት የጠፈር ተመራማሪ ቢሆን ከእግዚአብሄር ጋር ግን እንዴት እንደሚኖር ካላወቀ ምንም አያውቅም፡፡ ሰው በሌላ በብዙ ነገር የተሳካለት አዋቂ ሆኖ ለፈጠረው ለእግዚአብሄር እውቅና መስጠት ካላወቀ ሀ ሁ አልቆጠረም ማለት ነው፡፡ ሰው በሌላ ነገር የተካነ ሆኖ ለክብሩ ከፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር ስላለው ግንኙነት መረዳቱ ከሌለው ምንም አያውቅም ማለት ነው፡፡ ሰው ምንም ቢያውቅ ለእግዚአብሄር ፈጣሪነትና ባለቤትነት እውቅና ካለሰጠ የእውቀት መጀመሪያ ላይ አልደረሰም ማለት ነው፡፡    
እግዚአብሄን መፍራት ግን ከድርጊት አይጀመርም፡፡ በድርጊታችን እግዚአብሄርን ለመፍራት መፍጨርጨር የለብንም፡፡ በድርጊታችን አግዚአብሄርን ለመፍራት የድርጊታችንን ምንጩን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ በንግግራችን እና በድርጊታችን እግዚአብሄርን ለመፍራት ንግግራችንና ድርጊታችን የሚመጣበትን ምንጩ አስተሳሰባችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡
መጽፅሃፍ ቅዱስ የማንኛውም ድርጊት ምንጩ ሃሳብ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡ እንዲያውም ሰው በልቡ እንደሚያስበው እንደዚሁ እንደሆነ መፅሃፍ ያስተምረናል፡፡ በአስተሳሰብ ህይወቱ እግዚአንብሄርን የሚፈራ ሰው በንግግሩ እግዚአብሄርን ይፈራል፡፡ በአስተሳሰቡ እግዚአብሄርን የሚፈራ በራሱ በድርጊቱ እግዚአብሄርን ይፈራል፡፡
በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ምሳሌ 23፡7
ስለዚህ ነው ኢየሱስ ፈሪሳዊያንን እናንተን የሚያረክሳችሁ ድርጊት ሳይሆን የልባችሁ ሃሳብ ነው እያለ የሚወቅሳቸው፡፡
ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ማቴዎስ 15፡18-19
ሰው እግዚአብሄርን በእውነት የሚፈራው በሃሳብ ደረጃ ነው፡፡ ሰው በሃሳብ ደረጃ እግዚአብሄርን ከፈራ ከመቀፅበት በንግግርም ሆነ በድርጊት እግዚአብሄርን የመፍራት ህይወት ይኖረዋል፡፡ ሰው ግን በአስተሳሰብ ህይወቱ እግዚአብሄርን ካልፈራና ስርአት አልባ ከሆነ በድርጊቱ እግዚአብሄን መፍራት አይችልም፡፡ ሰው ሰው አያየኝም ብሎ ክፉን ቢያስብ በንግግሩና በድርጊቱ ሰው ያየዋል፡፡  
ጌታም እንዲህ አለው፦ አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል፡፡ ሉቃስ 11፡39
ስለዚህ በአስተሳሰባችን እግዚአብሄርን በመፍራት እግዚአብሄርን የመፍራት ህይወት ይኑረን፡፡
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ምሳሌ 1፡7
ፀሎት
እግዚአብሄር ሆይ በአስተሳሰቤ አንተን እፈራለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ወደ አእምሮዬ የመጣውን ሃሳብ ሁሉ አላስብም፡፡ እግዚአብሄር ሆይ የማስበውን ማንኛውንም ሃሳብ አንተን በመፍራት አስባለሁ፡፡ እግዚአብሄ ሆይ እንደቃልህ ያልሆነን ሃሳብ ከአእምሮዬ አሽቀንጥሬ እጥላለሁ፡፡ አንደ ቃልህ ያልሆነውን ሃሳብ በአእምሮዬ አላስተናገድም፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በአስተሳሰብ ህይወቴ አንተን በመፍራት ወዳዘጋጀህልኝ በረከት ውስጥ እገባለሁ፡፡ ስላስተማርከኝ አመሰግናለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም ፡፡ አሜን
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃሳብ #አእምሮ #ልብ #እግዚአብሔርንመፍራት #ጥበብ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Thursday, April 27, 2017

የፃድቃን የማንነት ሚስጥር ሲገለጥ

ፃድቃን ማናቸው የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ፅድቅ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡
ፅድቅ ካለፍርሃትና ካለበታችነት ስሜት በእግዚአብሄር ፊት መቆም ነው፡፡
ሰው በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ጋር ተጣልቷል፡፡ እግዚአብሄር ቅዱስ ነው ፡፡ ሰው በሃጢያት ምክኒትት ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ጋር ተለያይቷል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ጠላት ነው፡፡ ፃዲቅ ማለት በክርስቶስ የመስቀል ሞትና ትንሳኤ ከእግዚአብሄር ጋር የታረቀና ካለሃፍረት ፣ካለበታችነት ስሜትና ካለፍርሃት በእግዚአብሄር ፊት በድፍረት የሚቆም ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ዕብራውያን 4፡16
ፅድቅ ማለት ተቀባይነት ማግኘት ማለት ነው፡፡
ፃድቃን ማለት ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሃጢያት እዳቸውን እንደከፈለ ስላመኑ በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት የእግዚአብሄር ልጆች የሆኑ ማለት ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐንስ 1፡12
ፅድቅ ማለት ተቀባይነት ያለው ፣ ንፁህና ትክክል ማለት ነው፡፡
ፃድቃን ማለት በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ምክኒያት ሃጢያታቸው ስለተደመሰሰላቸው ከዚህ በፊት ሃጢያት እንዳላደረጉ ተደርገው እንደንፁህ ሰው በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ማለት ነው፡፡ ፃድቃን ኢየሱስ የእነርሱንም ሃጢያት ወስዶ የእርሱን ፅድቅ የሰጣቸው ናቸው፡፡
እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21
ፅድቅ ማለት ፀደቀ ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ህይወትን መዝራት መለምለም ማለት ነው፡፡
በሃጢያት ምክኒያት ሁሉም ሰው በመንፈሱ ሙት ነው፡፡ በመንፈሱ ሙት የሆነው ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ስራ በኩል ህይወትን ሲያገኝ ህይወትን ዘራ ለመለመ ፀደቀ ይባላል፡፡
ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። ሮሜ ሰዎች 3፡23-24
ፅድቅ ማለት በእግዚአብሄር አሰራር ማመን ማለት ነው፡፡ 
ፃድቃን ማለት በእግዚአብሄር አሰራር የሚያምኑ አማኞች ማለት ነው፡፡ ፃድቃን ማለት ለመዳን ዘመናቸውን ሁሉ የሚሰሩ ማለት ሳይሆን ፃድቃን ማለት እግዚአብሄር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ የተቀበሉ ፣ ኢየሱስ በእነርሱ ምትክ በመስቀል ላይ እንደሞተና የሃጢያታቸውን እዳ ሁሉ እንደከፈለ የሚያምኑና የመዳንን ነፃ ስጦታ በእምነት የተቀበሉ ማለት ነው፡፡  
ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ኤፌሶን 2፡8
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፃዲቅ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ፃድቃን #መዳን #ፀጋ #ህይወት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Wednesday, April 26, 2017

የሰው አካሄድ

የሰው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጸናል፥ መንገዱንም ይወድዳል። መዝሙር 37፡23
ሰውን እግዚአብሄር የፈጠረው ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር በእያንዳንዱ የህይወት ክፍላችን ውሰጥ ሙሉ ለሙሉ ይካተታል፡፡ እግዚአብሄር የህይወታችን ዝርዝር ነገሮች ሁሉ ግድ ይሉታል፡፡
አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ። ሉቃስ 12፡6-7
እግዚአብሄር የፈጠረን በአላማ ነው፡፡ ወደ ምድር ከመምጣታችን በፊት የተዘጋጀ የምንሰራው መልካም ስራ አለ፡፡ ወደ ምድር የመጣነው እግዚአብሄር አስቀድሞ ያየልንን መልካም ስራ ለመስራት ነው፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
እግዚአብሄር ለእድል የሚተወው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገውን ያውቃል፡፡ የሚታዘዘውና ራሱን የሚሰጠው ካገኘ ደግሞ በትጋት ይሰራዋል፡፡
ስለዚህ ነው እግዚአብሄር የሰውን አካሄድ በትጋት የሚመራው፡፡ እግዚአብሄር እንዲመራን ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር ሊመራን ይፈልጋል፡፡  
የሰው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጸናል፥ መንገዱንም ይወድዳል። ቢወድቅም ለድንጋፄ አይጣልም፥ እግዚአብሔር እጁን ይዞ ይደግፈዋልና። መዝሙር 37፡23-24
የእግዚአብሄርንም መንገድ ፈልጎ አካሄዱ የማይፀና ሰው የለም፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #አካሄድ #እርምጃ #ሰላም  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #መናገር #መንገድ #ትግስት #መሪ

Tuesday, April 25, 2017

የሰውና የሰይጣን ሃሳብ

ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠረ ለእግዚአብሄር ክብር ካልኖረ በሰይጣን ተገዝቷል ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚታለሉት ቀንድ ያበቀለ አውሬ አይነት ሰይጣን በህይወታቸው ካልመጣ ከሰይጣን ጥቃት ነፃ እንደሆኑ ስለሚመስላው ነው፡፡ ሰይጣን የሚሰራው በግልፅ አይደለም፡፡ ሰይጣን የሚሰራው በማታለል ነው፡፡ በሰው ስጋ የሚሰራው ሰይጣን ነው፡፡ በሰው ምኞት የሚሰራው ሰይጣን ነው፡፡ የስጋችንንና የልቦናችንን ፈቃድ ካደረግን በሰይጣን ፈቃድ እየተመላለስን ነው፡፡
በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን ኤፌሶን 2፡1-3
በምድር ላይ ሁለት አይነት ሃሳብ ብቻ ነው ያለው፡፡ የእግዚአብሄር ሃሳብ አለ፡፡ የእግዚአብሄር ያልሆነ ሃሳብ አለ፡፡ የእግዚአብሄር ያልሆነው ሃሳብ ሁሉ የሰው ሃሳብ ነው የሰይጣንም ሃሳብ ነው፡፡
በምድር ላይም ያለው ጥበብ ሁለት አይነት ጥበብ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ጥበብ አለ፡፡ የእግዚአብሄር ያልሆነ ጥበብ አለ፡፡ ይህ የእግዚአብሄር ያልሆነው ጥበብ የሥጋና የአጋንንትም ጥበብ ነው፡፡
ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ያዕቆብ 3፡14-15
ሰይጣን እፃን ለማጥቃት የሚጠቀመው የስጋን ሃሳብ ተጠቅሞ ነው፡፡ ሰይጣን እኔ ሰይጣን ነኝ ብሎ ሳይሆን የሚመጣው ለሰው ስጋ በሚመች ሃሳብ ነው፡፡
ኢየሱስ ጴጥሮስን አንተ ሰይጣን ብሎ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ብሎ ሲገስፀው እናያለን፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ለመተላለፍ የሰይጣንን ሃሳብ ማሰብ የለበትም፡፡ ሰው የሰውን ሃሳብ ካሰበ በተዘዋዋሪ የሰይጣንን ሃሳብ አሰበ ማለት ነው፡፡ ሰይጣን እኔ ሰይጣን ነኝ አገልግሉኝ ብሎ ሳይሆን የሚመጣው የራስ ወዳድነትን ሰውኛን ሃሳብ እንድናስብ በማድረግ ነው፡፡
እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው። ማቴዎስ 16፡23
እግዚአብሄር በፍጹም ልባችን በፍጹም ነፍሳችን በፍጹም ኃይላችን በፍጹም አሳባችን እንድንወደው ስለሚፈልግ ራስ ወዳድነት ካለብን በተዘዋዋሪ ሰይጣንን እያገለገልን ነው እንጂ እግዚአብሄርን እየወደድን አይደለም፡፡
ዓለምን በሚወድ ውስጥ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም የሚለው ለዚህ ነው፡፡ አለምን መውደድ በተዘዋዋሪ ሰይጣንን ማገልገል ነው፡፡
ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15
በህይወታችን ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ ለመሳት የሰይጣን አምላኪ መሆን የለብንም ከእግዚአብሄር ጋር ለመተላለፍ እንደሰው ልማድ መመላለስ ይበቃናል፡፡  
ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? 1 ቆሮንቶስ 3፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሰይጣን #ዲያብሎስን #ሽንገላ #ሃሳብ #የስጋፈቃድ #የልቦናፈቃድ #ምኞት #አእምሮ #ልብ #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ስብከት #እምነት #ነፃነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Monday, April 24, 2017

ማንም ያለው ነገር

እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ማርቆስ  11፡23-24
የእግዚአብሄር ልጅነት ክብር ታላቅ ክብር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ ንግግር ታላቅ ሃይል ያለው ንግግር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ የእምነት ቃል ሃያል ቃል ነው፡፡
ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን ይሆንለታል፡፡  
የምንለው ነገር ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄር ልጅነታችንን ስልጣን የምንገልፀው በመናገር ነው፡፡ በንግግራችን ውስጥ ታላቅ ስልጣን  አለ፡፡
ለንግግራችን ሃይል የሚሰጠው እምነታችን ነው፡፡
በንግግር የሚገለፅ እምነት ነገሮችን ይለውጣል፡፡ አምነን የምንናገረው ነገር ይሆናል፡፡ አምነን የምናዘው ተራራ ይታዘዛል፡፡
እምነትን የሚያመጣው ደግሞ የእግዚአብሄርን ቃል መረዳታችን ነው፡፡ እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት ነው፡፡ እምነት የእግዚአብሄርን ቃል እውነት ነው ብሎ መቀበል ነው፡፡ እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል በመቀበል ነው፡፡
እምነትን የሚያጠፋውን ጥርጥርን ደግሞ መዋጋት አለብን፡፡ ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ የሆነን ነገር ከሰማን እና ትኩረታችንን ከሰጠነው ጥርጥር ወደልባችን ይገባል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ከሰማንና ከተቀበልን በኋላ ልባችንን ለተቃራኒ ነገር መዝጋት አለብን፡፡
ለእግዚአብሄር ቃል ልባችንን እንደከፈተን ሁሉ እንደ እግዚአብሄር ቃል ላልሆነ ሃሳብ ደግሞ ልባችንን መዝጋት አለብን፡፡ የጥርጥር ሃሳብ ወደ አእምሮዋችን ሲመጣ በፍጥነት አውጥተን መጣል አለብን፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነ የጥርጥር ሃሳብ ለጥቂት ጊዜ እንኳን በአእምሮዋችን እንዲቆይ መፍቀድ የለብንም፡፡  
ስለ አለንበት ሁኔታ የእግዚአብሄርን ቃል ከፈለግህንና ካገኘንም በኋላ በቃሉ ላይ መቆም አለብን፡፡ ቃሉን በእምነት መናገር አለብን፡፡ ቃላችን ከእግዚአብሄ ቃል ጋር መስማማት አለበት፡፡ የምንናገረውን የእግዚአብሄ ቃል ካለጥርጥር መናገር ማለት ይገባናል፡፡
እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። ማርቆስ  11፡23-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ጥርጥር #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Sunday, April 23, 2017

በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል

የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ ኢሳይያስ 30፡15
እግዚአብሄር እንዲሰራ ሰው ሊያርፍ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ካላረፈ እግዚአብሄር ወይም አይሰራም ቢሰራም ደግሞ እግዚአብሄ እንደሰራ አያስታውቅም፡፡ ሰው ካላረፈ እግዚአብሄር ብቻውን ክብሩን ሊወስድ አይችልም፡፡ ሰው ካላረፈ የሰውና የእግዚአብሄር ክብር ይደባለቃል፡፡
ሰው በእረፍት ሆኖ እግዚአብሄር ሲሰራ ብቻ ነው ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሄር ክብሩን መስጠት የሚችለው፡፡ ሰው ሳያርፍ ምንም ነገር ቢሆንለት እንኳን "እግዚአብሄር ረድቶኛል እኔም ግን ቀላል ሰው አይደለሁም" ነው የሚለው፡
እግዚአብሄር እንድንሰራ እንኳን የሚፈልገው በእረፍት ነው፡፡ ስራችንነን እንኳን አንድንጀምር የሚፈልገው በእርሱ ካረፍን በኋላ ነው፡፡ ከስራ በፊት አንኳን መጀመሪያ በእርሱ እንድናርፍ ይፈልጋል፡፡    
ለእግዚአብሄር ምንም ነገር ካደረግንለት እግዚአብሄር አስቀድሞ ሰርቶ እንደጨረሰው በማመን መሆን አለበት፡፡ ወደምድር የመጣነው እንኳን እግዚአብሄር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ስራ ለመስራት እንጂ ለስራ ፈጠራ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከመስራታችን በፊት በእግዚአብሄር ዘንድ አንደተሰራ አውቀን በምድር ላይ ለማስፈፀም ብቻ እንደሆነ ማወቅ ይገባናል፡፡
ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። ኤፌሶን 1፡4-6
ለእግዚአብሄር ምንም ከማድረጋችን በፊት እንድናርፍ መፈለጉ ብቻ ሳይሆን በስራ መካከል እንድናርፍ ይፈልጋል፡፡  
ስንሰራም በእረፍት እንድንሰራ ነው እግዚአብሄር የሚፈልገው፡፡ ሳናርፍ የምንሰራውን ምንም ነገር እግዚአብሄር አይፈልገውም፡፡ ስለፀሎት አንኳን መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር ሳትለምኑት ምን እንምደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል ነው የሚለው፡
አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ። ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና። ማቴዎስ 6፡7-8
ስለዚህ ስንፀልይ እንኳን አዲስን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ልንቆረቁር እንደሆነ ሊሰማን አይገባንም፡፡ በእውነት የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት ከፈለግን አስቀድሞ የተሰራውን ስራ መከተል ብቻ ነው፡፡
ሰለዚህ ነው ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አባቴ ይሰራል እኔም እሰራለሁ በማለት ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ እነደሚሰራ የሚናገረው፡፡
ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሃንስ 5፡17
እግዚአብሄር በትጋት እየሰራ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚሰራውን ነገር ተረድተን ከእርሱ ጋር አብረን መስራት ከሁሉም የሚበልጥ የተሻለ ነገር ነው፡፡  
በማረፍ ከብክነት እንድናለን፡፡ በማረክ አግዚአብሄር በማይዘራበት እንዳንዘራ እንጠበቃለን፡፡ በማረፍ እግዚአብሄር በሌለበት እንዳንሰራ እንጠበቃለን፡፡ በማረፍ ከከንቱ ድካም እንድናለን፡፡
እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ። መዝሙር 127፡1-2
የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ ኢሳይያስ 30፡15
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እረፍት #ቅድሚያ #እምነት #መደገፍ #ሰንበት #ማረፍ #ፅድቁን #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ፀጥታ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ