Popular Posts

Follow by Email

Thursday, May 24, 2018

አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን

ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ማቴዎስ 26፡39
ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42
አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። ማርቆስ 14፡36
እኛ ለእግዚአብሄር ክብር ለመኖር የተጠራን ሁላችን ለእግዚአብሄር መኖር እንፈልጋላን፡፡ ኢየሱስን ስንከተል ለክብሩ ለመኖር ወስነን ነው፡፡ ኢየሱስን የተከተልነው ለሞተልንና ለተነሳው ለኢየሱስ እንጂ ወደፊት ለራሳችን ላለመኖር ነው፡፡
በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።  2ኛ ቆሮንቶስ 5፡15
በተለያየ ጊዜያት በህይወታችን የተለያዩ ምርጫዎች ይቀርቡልናል፡፡ በተለይ ኢየሱስን በሁለንተናችን ለመከተል የወሰንንእኛ ክርስትያኖች በየጊዜው የእኛ ፍላጎትና የእግዚአብሄር ፍላጎት ሲለያይ እንመለከታለን፡፡ በህይወት ጉዞዋችን እኛ የምንፈቅደውና እግዚአብሄር የሚፈቅደው በፊታችን እንደምርጫ ሲቀርብልን እናገኛለን፡፡፡ እኛ በህይወታችን እንዲሆን የምንወደው ነገር እግዚአብሄር የማይወደው ነገር ይሆንና እጅግ እንጨነቃለን፡፡ ወይም እኛ የማንወደው ነገርን እግዚአብሄር ይህንን እወዳለሁ ሲለን የእግዚአብሄርን ወይም የእኛን ለመምረጥ በውሳኔ መካከል ራሳችንን እናገኛለን፡፡
የራሳችንን ፈቃድ መከተል ለጊዜው ደስ ይል ይሆናል እንጂ ዘለቄታዊነት የለውም፡፡ የራሳችንን ፍላጎት መከተል እኛን ከእግዚአብሄር ፈቃድ በረከቶች ውጭ ያደርገናል፡፡ የራሳችን ፈቃድ መከተል በምድር ላይ ያለንን አንድ የህይወት እድል እንድናባክነው ያደርገናል፡፡  የራሳችንን ፍላጎት መከተል የእግዚአብሄር አብሮነት ያሳጣናል፡፡ የራሳችን ፍላጎት መከተል ክስረት ያመጣብናል፡፡ የራሳችንን ፍላጎት መከተል በእግዚአብሄር ፊት ያለንን ድፍረት ያሳጣናል፡፡
የእኛ ምርጫ ችግር አለበት፡፡ የእኛ ምርጫ ሁሉን የማያውቅ ሰው ምርጫ ነው፡፡ የእኛ ምርጫ እውቀት የጎደለው ሰው ምርጫ ነው፡፡ የእኛ መርጫ እንከን አያጣውም፡፡ በአለም ላይ የእጅግ ጥበበኛው ሰው ምርጫ ፍፁም አይደለም ጉድለት አለበት፡፡
የእግዚአብሄር ምርጫ ሁሉ የሚችል አምላክ ምርጫ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ ሁሉን የሚያውቅ ጌታ ምርጫ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ የቅዱስ አምላክ ምርጫ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ የፍቅር አምላክ ምርጫ ነው፡፡  
ስለዚህ ነው በራሳችን ፈቃድና በእግዚአብሄር ፈቃድ መካካል የምንጨነቀው፡፡ የእኛ ምርጫ ምን ያህን እንከን እንዳበት ስለምናውቅ በራሳችን መንገድ ላመሄድ ከራሳችን ጋር እንከራከራለን፡፡ በራሳችን ማስተዋል መደገፍ ስለማንፈልግ ነው ሁልጊዜ የእግዚአብሄርን ምርጫ መከተል የምንፈልገው፡፡
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ምሳሌ 3፡5
የእግዚአብሄር ምርጫ የተሳሳተና የማይመስል ብዙዎች የማይደግፉት ቢሆን እንኳን የእርሱ ምርጫ ከየትኛውም መርጫችን የተሻለ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ምርጫ ሞኝነት ቢመስል እንኳን የእግዚአብሄር ሞኝነት ከሰው ጥበብ ይጠበባል፡፡
ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡25
ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 2242
ፀሎት

እግዚአብሄር ሆይ ስለተናገርከኝ ስለዚህ ቃል አመሰግንሃለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በሁለንተናዬ ለአንተ መኖር እፈልጋለሁ፡፡ የአንተን ፈቃድ ብቻ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ፈቃድህን ስለምትገልጥልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ፈቃድህን እንድከተል ሃይል ስለምትሆነኝ ፀጋህን ስለምታበዛልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አንተን በሁለንተናዬ እስከመጨረሻው ተከትዬህ ስለማልፍ አመሰግንሃለሁ፡፡ ስለ ሁሉም ተመስገን ፡፡ በኢየሱስ ስም ፡፡ አሜን 

No comments:

Post a Comment