Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, November 29, 2017

ለውግዘት የተሳሳቱ መልሶች

በህይወታችንና በአገልግሎታችን ውግዘትና ተቃውሞ ይብዛም ይነስም በየጊዜው የሚከሰቱ ነገሮች ናቸው፡፡
ሰዎች በትክክለኛውም መንገድ ይሁን በተሳሳተ መንገድ ሊቃወሙንና ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል ተከትለው ትክክለኛውን እርምጃ ጠብቀው ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡
ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። ማቴዎስ 18፡15-17
ሰዎች ለትክክለኛውም ሆነ ለተሳሳተ ምክኒያት ሊቃወሙንና ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡ ሰዎች ከፍቅር ተነስተው እኛን ለማዳንና ከደከምንበት ለማቅናት የእኛን መመለስና እንደገና ጠቃሚ መሆን አልመው ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ ከቅናት ከጥላቻ መነሻ ሃሳብ /motive/ ስለ በለጥናቸው ፣ ስላደግንና ስለሰፋን ሊያወግዙንና ሊቃወሙን ይችላሉ፡፡
አንዳንዶቻችን እስከዛሬ ተወግዘን ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ ከአሁን በኋላ ልንወገዝ እንችላለን፡፡ አንዳንዶቻችን በአደባባይ እንወገዛለን ሌሎቻችን ደግሞ በቤተሰባችን በትምህርታችንም ይሁን በአካሄዳችን ልንወገዝ እንችላለን፡፡ በምንም መልኩ ቢሆን የሚመጣን ተቃውሞና ወገዛ የምንቀበልበትና የምናስተናግድበት የተሳሳተና ትክክለኛ መንገድ አለው፡፡ ወገዛን በትክክለፃው መንገድ ካስተናገድነው ይጠቅመናል በተሳሳተ መልኩ ከመለስነው ደግሞ አይጠቅመንም፡፡
ለተቃውሞ የምንመልስበት አምስት የተሳሳቱ መንገዶች
ጥላቻ
ሰውን ሁሉ ከመውደድ በስተቀር ማንንም ሰው እንድንጠላ መብት የለንም፡፡ ሰው ጠላኝ ብለን ብንጠላ የምንጎዳው እኛው ነን፡፡ የተሳሳተ ሰውን እንኳን ለመጥላት መብት የለንም፡፡  
እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። ሮሜ 13፡8
መልሶ ማውገዝ
ያወገዘንን ሰው መልሶ ማውገዝ ተሳስቷል የምንለውን ነገር እኛው መድገም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለት ስህተቶች አንድ ትክክል አያስገኙም፡፡ ትክክለኛ መፅሃፍ ቅዱሳዊ መንገዱን ሳይጠብቅ ነው ያወገዘኝ ብለን የምንለውንም ሰው ትክክለኛ መንገዱን ሳንጠብቅ በስሜታዊነት ማውገዝ ስህተትን በስህተት ለማረም እንደ መሞከር ከንቱ ጥረት ነው፡፡
ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ማቴዎስ 5፡38-39
እልኽ ውስጥ መግባት
እግዚአብሄር በህይወታችን የጠራን የተወሰነ ነገር እያለ ያንን ሃላፊነት ትተን የተቃውሞ መልስ ለመመለስ ጉልበታችንን ጊዜያችንን እውቀታችንምን ሁሉ ማባከን ስህተት ነው፡፡ ጥሪያችንን ትተን እልክ ውስጥ መግባት እግዚአብሄር የሰጠንን ተሰሚነት ፣ ፀጋና ፣ ጉልበትና ጊዜ አላስፈላጊ አታካራ ላይ ማዋል የህይወትና የአገልግሎት ብክነት ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ሃላፊነት እርግፍ አድርገን ትተን ለተቃውሞ የመልስ እርምጃ መራመድ ብክነት ነው፡፡ የተሳተን ተቃውሞን የምናሸንፍበት አንዱ መንገድ ትክክለኛውንም ነገር በማድረግ በመቀጠል ባለማቋረጥ ነው፡፡
ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። 2 ጢሞቴዎስ 4፡2
መራገም
በተሳሳተም ይሁን በትክክለኛ መነሻ ሃሳብ እንዲሁም በትክክለኛው መፅሃፍ ቅዱሳዊው መንገድ ይሁን በሌላ መንገድ የተቃወመንን  ሰው ለመርገም አልተጠራንም፡፡ ሰውን ለመባረክ መልካምነቱን ለመፈለግ ለመልካምነቱ ለመስራት ብቻ ተጠርተናል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመን የሚቃወመንን በእውነት በማመስገን በማክበር እድሉን ሌላውን ለማነፅ ልንጠቀምበት ይገባናል፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9
የተወገዝንበትን ነገር ይበልጥ ማጋነን
በተወገዝን ማግስት የተወገዝንበትን ነገር ይበልጥ ማፋፋም ማጋነን ትክክለኛው መንገድ አይደለም፡፡ ትምህርታችንና የህይወት መርሆዋችን ከሆነ ተቃውሞ ሲመጣ ካልለወጥነው እንኳን በዚያው ይቀጠላል እንጂ ይበልጥ ይበልጥ አይለጠጥም፡፡ ሌላው ፅንፍ የተሳሳተውን ሚዛናዊ አያደርገውም፡፡
በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ። ቲቶ 2:8
እራስን ከሰው ጋር አብሮ ማውገዝ
በተሳትነው ነገር ላይ ካልሆነ በስተቀር ስለተወገዝን በደፈናው ራስን ማውገዝ ሌላው ስህተት ነው፡፡ የተወገዝንበትን ነገር ራሱ መንፈስ ቅዱስ ሊመሰክርልን ይገባል እንጂ ሰዎች ስለፈረዱብን ብቻ ራሳችን ላይ መፍረድ ዋናው ስህተት ነው፡፡
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡3
ተቃውሞን በአጠቃላይ እንደ ክፉ ማየት
ተቃውሞ በራሱ ክፉም መልካምም አይደለም፡፡ ለተቃዋሚው ክፉ የሚያደርገው በንፁህ የልብ መነሻ ሀሳብ ካላደረገው ወይም ትክክለኛውን መፅሃፍ ቅዱሳዊ መርህ ሳይከተል በግብታዊነት ካደረገው ስህተት ይሆናል እንጂ ተቃውሞ በራሱ ስህተት አይደለም፡፡ ተወጋዡም ተቃውሞን እንከ እንቅፋትና እንደ ሰይጣን ስራ ካየው ከተቃውሞ ውስጥ ማውጣት ያለበትን ወሳኝ ጥቅም መጠቀም ያቅተዋል፡፡
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ኤፌሶን 5፡15-16
እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ሮሜ 8፡28
ተቃውሞን ከሰው ጋር ማያያዝ
ተቃውሞ ሲደርስብን የተቃውሞውን ይዘት ከመመልከት ይልቅ አከሌ የተቃወመኝ እንደዚህ ስለሆነ ነው ብብሎ ምክኒያት መስጠትና ከሰው ጋረ ማያያዝ ከተቃውሞ የሚገባንን ጥቅም እንዳናገኝ ያደርገናል፡፡ ተቃውሞ ያጠራናል፡፡ ተቃውሞን በሚገባ ከያዝነው ትሁት ያደርገናል በዚያም የእግዚአብሄር ፀጋ እንዲበዛለን ያደርገናል፡፡  
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5
እግዚአብሄር ቢፈቅድ በሚቀጥለው ፅሁፍ ትክክለኛው የውግዘትን መልሶች ሃሳብ ይዤላችሁ እቀርባለሁ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አገልጋይ #ወገዛ #ስህተተ #ልብ #መሪ #ህሊና #ቀራጭ #ወገዛ #ትህትና #ፀጋ #ተቃውሞ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መነሻሃሳብ #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የፍሬያማነት ብቸኛው መንገድ

በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። ዮሐንስ 15፡4
ፍሬያማነት ሁሉም ሊያገኘው የሚፈልገው እጅግ መልካም ነገር ነው፡፡ ፍሬያማነት የስኬት ፣ የብልፅግናና የሙላት ጣራ ነው፡፡ ፍሬያማ እንደ መሆናችን የሚያስደስት ነገር በምድር ላይ የለም፡፡
ፍሬማነት ሊታወቅ የማይችል ፣ ሊመዘን የማይችል ፣ ሊረዱት የማይችል ረቂቅ ነገር አይደለም፡፡
ፍሬያማነት በአጋጣሚ የምንመታው እድል አይደለም፡፡ የክርስትና ፍሬማነት እስከምናገኘው ድረስ እርግጠኛ የማንሆንበት መጀመሪያውና መጨረሻው የማይታወቅ በእድል ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም፡  
በክርስትና ፍሬያማነት የሚለካበት ከመረዳት በላይ የሆነ ውስብስብ መንገድ የለም፡፡ በክርስትና ፍሬያማ መሆናችን ወይም አለመሆናችን የሚለካው በአንድ መመዘኛ ብቻ ነው፡፡
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። ዮሐንስ 15፡4
የክርስትና ፍሬያማነት ብዙ አይነት ትርጉም የለውም፡፡ የክርስትናን ፍሬያማነት ሊገልፅልን የሚችለው የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡ የክርስትና ፍሬያማነት የሚወስነው እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡ ስለ ፍሬያማነተ ክርክር ቢነሳ ሊወስን የሚችል የመጨረሻው አካል እግዚአብሄር ነው፡፡ እግዚአብሄር ፍሬያማነት ይህ ነው ካለ ማንም አይከራከርም የክርክር ፍፃሜ ይሆናል፡፡
ፍሬያማነት በሰዎች የተለያዩ መመዘኛዎች አይመዘንም ፡፡ ፍሬያማነት በዘመኑ ሁኔታ አይለዋወጥም፡፡ የክርስትና ፍሬያማነት እንደሰው አይለያይም፡፡ የክርስትና ፍሬያማነት አንድና እንድ ብቻ ነው፡፡
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። ዮሐንስ 15፡4
በክርስትና ፍሬያማ ለመሆነ መንገዱ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ በክርስትና ፍሬያማ ለመሆን 99 መንገዶች የሉትም፡፡ በክርስትና ፍሬያማ ለመሆን ብዙ አማራጮች የሉትም፡፡ በክርስትያ ፍሬያማ የመሆን መንገዱን እኛ እንወስነውም፡፡  
በፍሬያማነት ለመኖር በኢየሱስ መኖር በቂ ነው፡፡ ፍሬያማነት የሚመዘነው ሃብት በማግኘታችን ፣ ዝነኛ በመሆናችን ወይም ደግሞ ታላቅ ነገር በመስራታችን አይደለም፡፡ ፍሬያማነት የሚመዘነው በኢየሱስ መኖራችን ብቻ ነው፡፡ በኢየሱስ የሚኖር ሰው ፍሬያማ ነው፡፡ በኢየሱስ የማይኖር ሰው ፍሬያማ አይደለም፡፡ በኢየሱስ መኖራችን ብቻ ፍሬያማ ያደርገናል፡፡ በኢየሱስ አለመኖራችን ብቻ ፍሬቢስ ያደርገናል፡፡ የሰው ፍሬያማነት የሚለካው በኢየሱስ በመኖሩ መጠን ነው፡፡ 50% በኢየሱስ የሚኖር ሰው 50% ፍሬያማ ይሆናል ፣ 10% በኢየሱስ የሚኖር 10% ፍሬያማ ይሆናል ፣ 100% በኢየሱስ የሚኖር 100% ፍሬያማ ይሆናል፡፡
በኢየሱስ በመኖራችን ብቻ በፍሬያማነት እየኖርን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢየሱስ መኖራችን ብቻውን ሌላ ሌላ ነገር ሳይጨምር በእውነት ፍሬያማ ያደርገናል፡፡  
የክርስትያን ፍሬያማነት ለመለካት ውስብስብ መመዘኛዎች የሉትም፡፡  የክርስትናን ፍሬያማነት ለመመዘን ያለው አንድ መስፈርት በኢየሱስ መኖር ነው፡፡
እንደ እግዚአብሄር መዝገበ ቃላት የክርስትና ፍሬያማነት ትርጉም በኢየሱስ መኖር ነው፡፡
የፍሬያማነት አንድና አንድ መመዘኛ በኢየሱስ መኖር ብቻ ነው፡፡ ፍሬያማነት ብዙ አማራጭ መንገዶች የሉትም፡፡ በኢየሱስ መኖር አንዱና ብቸኛ የፍሬያማነት መንገድ ነው፡፡
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። ዮሐንስ 15፡4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሬያማነት #ፍሬ #ማፍራት #ስኬት #በእኔኑሩ #ቃል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መመዘኛ #መስፈርት #ፅናት #ትግስት #መሪ

Saturday, November 25, 2017

ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት

ምግብ ለሰውነታችን እጅግ አስፈላጊ እንደሂነ ሁሉ የእግዚአብሄር ቃል ምግብ ለመንፈሳዊ ህይወታቸን አስፈላጊ ነው፡፡

በተፈጥሮ ለምግባችን እጅግ ልዩ ትኩረት እንደምንሰጥ ሁሉ ለመንፈሳዊ ምግባችን ልዩ ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ በስጋዊ ምግብ ለጥቂት ደቂቃ መራብ እንደማንፈልግ ሁሉ የእግዚአብሄር ቃል ረሃንብ ሳይረካ እንዲቆት ማድረግ የለዐብንም፡፡ ሰው መንፈሱ የሚኖረው የሚመገበው የሚበረታው መንፈስ የሆነውን የእግዚአብሄርን ቃል በመመገብ ነው፡፡

ለሰውነታችን ሁለንተናዊ እድገት የምግብ ጥራት ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ ለመንፈሳዊ ህይወታችን ጥራት የምንሰማው ቃል ጥራት ወሳኝ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል የሆነ ትምህርት ህይወታቸንነ ያሳድገዋል መንፈሳ አቅም ይሰጠናል ከመንፈሳዊ በሽታ የምንካላከልበት አቅም ይሰጠናል፡፡  

የምንበላው መግብ ከበሽታ እንደሚከላከልልን ሁሉ የምንሰማው ቃል ከመንፈሳ በሽታ ይከላከልልናል፡፡

በሳይንስ አብዛኛው በሽታ ምግብን በማስተካከል ብቻ መከላከል ይቻላል፡፡ እንዲሁ የምንሰማው የእግዚአብሄቃል በስጋዊ ባህሪ ውስጥ ያለውን የህይወት በሽታ ይከላከልልናል፡

ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ 1፡21

እንዲሁ በተፈጥሮ የምንበላው ምግብ በአንዳድዳ ነገር ከተበከለ ጤናችንን እንደሚጎዳው ሁሉ ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ የሆነ ትምህርት መንፈሳዊ ጤንናታችንን ይጎዳል እግዚአብሄር ካጠራን የህይወት አላማ ያሰናክላል፡፡ ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ጳውሎስ ለጢሞቲዮስ ለትምህርቱ እንዲጠነቅቅ የሚያዘው፡፡

ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና። 1ኛ ጢሞቴዎስ 4:16
ጤናማ ቃል ጤናማ ህይወት ይሰጣል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ቃል የመንፈሳዊ ህይወትን ጤንነት ያውካል፡፡ ጤናማ ትምህርት ህይወትን ያለመልማል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ትምህርት ህይወትን ያቀጭጫል፡፡ ጤናማ ትምህርት ለአግዚአብሄር ይበልጥ እንድንሰጥ ያበረታል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ትምህርት በእግዚአብሄር ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርጋል፡፡ ጤናማ ትምህርት በትክክለኛው ነገር ላይ እንድናተኩር ያደርጋል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ትምህርት በተሳሳተ ነገር ላይ አተኩረን ፍሬ ቢስ እንድንሆን ያደርጋል፡፡  
ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡10
በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤ 2 ጢሞቴዎስ 113
የሚቃወም ሰው ስለ እኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥ በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤ በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ። ቲቶ 27-8
ጤናማ ትምህርት አልጋ በአልጋ የሆነ ትምህርት ሳይሆን ለእግዚአብሄርና ለእግዚአብሄርር ብቻ እንድንኖር የሚያስጨክን አለምን እንድንክድ በምድር ላይ እንደ እንግዶችና መጻተኞች እንድንኖር የሚያበረታ ትምህርት ነው፡፡
ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ፥ በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃል የምትመገብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ። 1 ጢሞቴዎስ 4፡6
ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። 2 ጢሞቴዎስ 4፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #አስተማሪ #ቃልኪዳን #መልካምትምህርት #ጤንነት #ንፁህ #አትለፍ #ትምህርት # #ፍሬ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አትጨነቁ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

የፍላጎትና የቅንጦት መለያ መንገድ

የፍላጎትና የቅንጦት መለያ መንገድ
ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረው ሰው የተፈጠረው ለተወሰነ አላማና ግብ ነው፡፡ ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ሰው በምድር ላይ ማድረግ የሚችለው የተወሰነውን የእግዚአብሄርን ልዩ አላማ ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሄርን ስንከተል እርሱ የሚያስፈልገንን ሁሉ ያሟላል፡፡ እግዚአብሄር የሚያቀርብልን የሚያስፈልገንን ነገር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የምንፈልገውን ነገር ሁሉ አያቀርብልንም፡፡ ሰውም የሚያገኘው አቅርቦት በተጠራበት በተለየ አላማ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሰው የሚያቀርበው ለፈጠረው አላማ ብቻ ነው፡፡  የፈጠረው ሰው የሚያስፈልገው ነገር እንዳይጎድልበት እግዚአብሄር በትጋት ይሰራል፡፡ ለመሰረታዊ ፍላጎታችን ሁሉ እግዚአብሄር ሙሉ ሃላፊነትን ይወስዳል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ለቅንጦት ፍላጎታችን ሃላፊነት አይወስድም፡፡ 
የሰው ስኬት የሚወሰነው በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት በመቻሉ ላይ ነው፡የሰው ተግባራዊ ጥበብ የሚለካው በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳቱ ነው፡፡ በቅንጦትና በመሰረታዊ ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ አንዳንዴ ቀላል ባይሆንም ስለሁለቱ ልዩነት ከእግዚአብሄር ቃል መማር እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃልን ከተመለከትንና ከተረዳን ህይወታችንን በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ በማተኮር እግዚአብሄር የሚሰጠንን አቅርቦት ለታለመለት አላማ በሚገባ መጠቀም እንችላለን፡፡
ሁለት ተመሳሳይ ሰዎችን የሚለየው ይህ መርህ ነው፡፡ አንዱ ያገኘውን ነገር ሁሉ ራሱን በመግዛት በሚያስፈልገው በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ብቻ ያጠፋዋል፡፡ ሌላው ደግሞ በሚፈልገው ነገር ላይ ሁሉ ማጥፋት ሲጀምር የሚያስፈልገው ዋናው ነገር ይጎድለዋል፡፡
ለራሱ ባሪያ ሆኖ የተጠቃ ሰው እንጀራ ጐድሎት ራሱን ካከበረው ሰው ይሻላል። ምሳሌ 12፡9
የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል። ምሳሌ 12፡9 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ብዙን ጊዜ ችግራችን የእግዚአብሄር አቅርቦት ማግኘት እጥረት አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ችግራችን መሰረታዊ ፍላጎትንና ቅንጦትን መለየት  አለመቻላችንና ለመሰረታዊ ፍላጎት የተሰጠንን አቅርቦት በቅንጦት ላይ ስለምናውለው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከራሳችንና ከሰዎች ጋር ሰላም የምናጣው ከመሰረታዊ ፍላጎት አልፈን ለቅንጦት ስንሮጥ ነው፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡1፣3
በክርስትና ስኬታማ ለመሆን የመሰረታዊ ፍላጎት መርህ ሊገባን ይገባል፡፡ በህይወት ለመሳካት መሰረታዊ ፍላጎትን ከቅንጦት መለየት አስፈላጊ ስለሆነ ሁለቱን እንዴት እንደምንለይ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
መሰረታዊ ፍላጎትን መለያው መንገዶች
1.      መሰረታዊ ፍላጎት ግዴታ የሆነ ነገር ነው፡፡
መሰረታዊ ፍላጎት በጣም ግዴታ ከመሆኑ የተነሳ ፍላጎታችን ካልተሟላ የህይወት አላማችንን መፈፀም አንችልም፡፡ መሰረታዊ ፍላጎት እግዚአብሄር በምድር ላይ ያስቀመጠንን ልዩ አላማ ለመፈፀም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡
አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡8
አንዳንዴ ግን አጥተነው እስካላየን ድረስ ብዙ ነገሮች የሚያስፈክልጉን ይመስለናል፡፡ አጥተነው ግን ምንም ሳንሆን በተግባር እስካላየን ድረስ የማንረዳው ብዙ የሚያስፈልጉ የሚመስሉን ነገር ግን የማያስፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡12-13
ለምሳሌ የምግብ አላማ ብርታት መስጠት ፣ ሰውነታችንን መገንባትና ከበሽታ መከላለከል ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚያደርግልን ምግብ መብላት መሰረታዊ ፍላጎት ሲሆን ስለምግቡ ጣእም ፣ ስለምግቡ ትኩስነትና ቅዝቃዜ ከተነጋገርን ግን ስለመሰረታዊ ፍላጎት ሳይሆን ስለምቾት ወይም ቅንጦት እየተነጋገርን ነው፡፡ ቅንጦት ቢገኝ ጥሪ ነው ነገር ግን ግዴታ አይደለም፡፡
ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ። ሐጌ 1፡6
2.     መሰረታዊ ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡
በሁለቱ መካከል መምረጥ ግዴታ ከሆነብን የምንመርጠው ነገር መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ መሰረታዊ ፍላጎት የምናስቀድመው ነገር ነው፡፡ ቅንጦት ቢቆይ ችግር የለውም እንዲውም ባይገኝ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም የምንለው ነገር ቅንጦት እንጂ መሰረታዊ ፍላጎት አይደለም፡፡
ለዚህ ምሳሌ የሚሆንን የእስራኤል ህዝብ ነው፡፡ የእስራኤል ህዝብ ከግብፅ ሲወጡ በህይወታቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነፃነታቸው እንጂ በመንገድ ላይ የሚበሉት የምቾት ወይም የቅንጦት ምግብ አልነበረም፡፡ በምድር በዳ ሲጓዙ እግዚአብሄር ሁሉንም ፍላጎት የሚያሟላ ጉልበት የሚሰጥ ፣ ሰውነትን የሚገነባና ከበሽታ የሚከላከል ንጥረ ነገርን ሁሉ ያካተተመናን መናን ሰጣቸው፡፡ የእስራኤ ህዝብ ግን እንደለመዱት አይነት ሆድን ያዝ የሚያደርግ ከበድ ያለ ምግብ ስላልነበረ ስለመና በእግዚአብሄር ላይ አጉረመረሙ፡፡ የእስራኤል ህዝብ ጥያቁ የመሰረታዊ ፍላጎት ጥያቄ ሳይሆን የምቾትና የቅንጦት ጥያቄ ነበር፡፡
ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ፦ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። ዘኍልቍ 21፡5
በሁሉም የህይወታችን አቅጣጫ በመሰረታዊ ፍላጎትና በቅንጦት መካከል ያለውን ልዩነት ተረድረተን ለመሰረታዊ ፍላጎት ቅድሚያ ከሰጠን በህይወታችን ከእኛ አልፈን ብዙዎችን ማገልገል እንችላለን፡፡
ያም ሆነ ይህ የክርስትና የመጨረሻ ደረጃ የመጨረሻው የስኬት ጣራ ስለ መሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ታምኖ ጌታን መከተል ነው፡፡
ፀሎት፡ እግዚአብሄር አምላክ ሆይ ይህንን ቃል እንድሰማ ስለረዳኝ አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ በተማርኩት መሰረት ለመሰረታዊ ፋልጎት ቅድሚያ መሰጠት እችል ዘንድ ልዩነቱን ስለምታስተምረኝ አመሰግናለሁ፡፡ በእያንዳንዱም የህይወት ክፍሌ በሁለቱ መካከል መለየት አችል ዘንድ ጥበብን ስለምትሰጠኝና ስለምትረዳኝ አከብርሃለሁ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ስም አሜን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, November 22, 2017

ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰው ልዩ ምልክት

ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መስራት አይቻልም፡፡ እግዚአብሄር እምነትን ከእኛ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሄር ቃሉን እንድናምን ይፈልጋል፡፡ ከደህንነት ቀጥሎ መሰረታዊው እምነት ደግሞ እግዚአብሄር እንደሚያስፈልገን ሁሉ እንደሚያውቅና እንደሚጨምር ማመን ነው፡፡
ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-33
ሰው ስለሚበላው ስለሚጠጣውና ስለሚለብሰው ካመነ በነፃነት ለእግዚአብሔር መኖር ይችላል፡፡ ሰው ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ እግዚአብሄርን ካመነ በሁለንተናው እግዚአብሄርን ለማገልገል ይለቀቃል፡፡
እምነት የልብ ስለሆነ አንድ ሰው ማመኑና አለማመኑን ማወቅ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ስለሚበላና ስለሚለበስ የሚያምን ሰውም ምልክቶች ከእግዚአብሄር ቃል መመልከት እንችላለን፡፡  
1.      ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይጨነቅም፡፡
ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ጉልበቱን የእግዚአብሄርን ነገር በመፈለግ ላይ እንጂ በጭንቀት ላይ አያፈስም፡፡ የሚያምን ሰው የጭንቀትን ፍሬ ቢስነት ይረዳል፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን በመፈለግ ላይ ሙሉ በሙሉ ከመጠመዱ የተነሳ ለጭንቀት የሚተርፍ ትርፍ ጊዜና ጉልበት የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ጭንቀት ጉልበቱን እንዲበላ አይደፈቅድለትም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የማያምን ሰው የእግዚአብሄርን ስራ በሚሰራበት ጊዜና ጉልበቱ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱን በትክክለኛው በእግዚአብሄር መንግስት ላይ ማፍሰስን አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው ምንም ነገር በትክክል መስራት ሳይችል በጭንቀት ብቻ ካለፍሬ ይቀራል፡፡ የማያምን ሰው የሚያስጨንቀው ነገር ጌታ እንዲሆንበት ይፈቅድለታል፡፡ ስለመሰረታዊ ግፍላጎቱ የማያምን ሰው ይጨነቃል በጭንቀትም ውድ ህይወቱን ያባክናል፡፡
ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ማቴዎስ 6፡25
2.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይፀልያል፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከመጨነቅ ይልቅ ይፀልያል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው ይፀልያል በእምነትም ያመሰግናል፡፡ አማኝ የሚያስጨንቀውን ይጥላል በእግዚአብሄር ላይ መልሶም አይወስደውም፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይተማመናል ያርፋል፡፡  
የማያምን ሰው በመጨነቁ ትልቅ ስራ እንደሰራ ያስባል፡፡ የማያምን ሰው መፀለይ በሚገባው ጊዜ ሲጨነቅ ይውላል፡፡ የማያምን ሰው ጉልበቱንና ጊዜውን በጭንቀት ላይ ያሳልፋል፡፡ የማያምን ሰው ቢፀልይም  ጭንቀቱን መልሶ ይወስደዋል፡፡ የማያመን ሰው መጨነቁ የህይወት አንዱ ስራ ይመስለዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው ሸክሙን  በእግዚአብሄር ላይ እንዴት እንደሚጥለው አያውቅም፡፡ የማያምን ሰው በእግዚአብሄር እንዴት እንሚያርፍ አያውቅም፡፡
እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ማቴዎስ 11፡28
3.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ልቡን ይሰማል፡፡
እግዚአብሄርን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሞትክ አለቀልህ ጠፋህ የሚለውን የውጭውንና የአእምሮውን ድምፅ ሳይሆን የልቡን ድምፅ በዝምታ ይሰማል፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ቆላስይስ 3፡15
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው በአእምሮ የሚመጣውን ሃሳብ ሁሉ ያስተናግዳል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ይታወካል ሰላም የለውም፡፡
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። ዮሃነስ 14፡27
4.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይወራረዳል፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ይህን ካላገኘሁ አይሆንም የሚለው ፍላጎት የለም፡፡ የሚያምነ ሰው በምንም ነገር ውስጥ እግዚአብሄር እንደሚያስችለው ያምናል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው በከፍታም በዝቅታም በምንም ነገር ውስጥ በክርስቶስ እንደሚበረታ ያውቃል፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-23
ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው ሰው በእግዚአብሄር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ያውቃል፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴዎስ 4፡4
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው የሌለኝ ነገር የማያስፈልገኝ ነው ብሎ በእግዚአብሄር እረኝነትና  አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ ይታመናል፡፡
እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። ዮሃንስ 10፡10-11
ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር በሰጠው ነገር ብቻ መኖር እንደሚችል ያውቃል፡፡ ስለፍላጎቱ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር የሰጠው ነገር ለአላማው በቂ እንደሆነ ያምናል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር እቅርቦት ላይ ምንም ትችት የለውም፡፡
ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማየታመን ሰው ገንዘቡ ተቆጥሮ እሰካልገባ አያምንም፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሚያየውን ብቻ ያምናል፡፡
ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡7-8
5.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከአለም ፉክክር ራሱ ያገላል፡፡
እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው በአለም ካለ ክፉ የፉክክር መንፈስ በፈቃዱ ራሱን ያገላል፡፡ እግዚአብሄርን የሚታመን ሰው ከሌላው ጋር ተፎካክሮም ለእግዚአብሄር ኖሮም እንደማይችል ይረዳል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያምን ሰው የፉክክርን ክፋትና አታላይነት ይረዳል፡፡
ስለፍላጎቱ ጌታን የማያምን ግን ሰው የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ይጥራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው በሰው ፊት ሙሉ መስሎ ለመታየትና ላለመበለጥ ይዳክራል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው የሰውን ደረጃ ለማሟላት ህይወቱን ያባክናል፡፡ ስለፍላጎቱ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው ከጭንቀት አርፎ እግዚአብሄርን ማገልገል ያቅተዋል፡፡
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። ማቴዎስ 13፡22
6.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው የተረጋጋ ህይወት አለው፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው ከማረፍ ውጭ ሲቅበዘበዝ አይታይም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያምን ሰው አይናወጥም፡፡ ጌታን የሚያምን ሰው ለጌታ ሙሉ ለሙሉ ለመኖር ነፃ ነው፡፡ በጌታ የሚታመን ሰው የረካ በመሆኑ ሌላውን ለማርካት ይሮጣል፡፡
የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። ምሳሌ 11፥25
ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። ምሳሌ 17፡22
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ ሰላም ያለው ሰው ለሌላው ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍለጎቱ የረካ ሰው ትኩረቱ አንድ ስለሆነ ሰላሙን ሊወስድ የሚችል ምንም ሃይል አይኖርም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ያልረካ ሰው ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ ለማድረግ ስለሚሞክር ሁለቱንም ማድረግ ያቅተዋል፡፡ ስለፍላጎቱ በጌታ ያልታመነ ሰው ሌሎችን ስለማገልገልና ሌሎችን ስለመጥቀም ሲሰማ ቁጣ ቁጣ ይለዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያምን ሰው "ምስኪን እኔ" አስተሳብ "ለእኔስ ማን አለኝ?" የሚል ምስኪንነት አስተሳሰብ አለው፡፡
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም። ኢሳያስ 28፡16
7.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የሚያመን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው አይጣላም አይጨቃጨቅም፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው የእርሱን ነገር ከሰው ጋር አያያይዘውም፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን?ያዕቆብ 4፡1
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚያምን ሰው ሰውን የበረከቱ ምንጭ አያደርግም፡፡
ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማያመን ሰው ሰውን ለመጥቀም ሳይሆን በሰው ለመጠቀም ያስባል፡፡ ስለፍላጎቱ የማያንምን ሰው ከዚህ የምጠቀመው ምንድነው ብሎ ስለግል ጥቅሙ ሁሌ ያስባል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በጌታ የማይታመን ሰው የእግዚአብሄርን አቅርቦት ስለማያይ አገልግሎትን የጥቅም ማግኛ መንገድ ያደርገዋል፡፡ ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን የፀጋ ስጦታ በጥቅም ይቸረችረዋል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው እግዚአብሄር ለሌሎች ጥቅም የሰጠውን ነገር ሁሉ ወደግል ስሙ ያዞረዋል፡፡ ስለ መሰረታዊ ፍላጎቱ የማያምን ሰው በግል በማይጠቀምበት ምንም ነገር ውስጥ የመሳተፍ ሃሞቱ የለውም፡፡
ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። ማቴዎስ 10፡8
8.     ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ ጌታን የሚታመን ሰው ነውረኛ ረብን ይጠላል፡፡
ስለፍላጎቱ በአግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክቡርና ነውረኛን ጥቅምን ይለያል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው በፊቱ የመጣውን ሁሉ አያግበሰብስም፡፡ ስለፍላጎቱ የሚታመን ሰው ኩሩ ነው፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የሚያመን ሰው ለቀቅ ብሎ ይኖራል፡፡ በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው ክብር ከእግዚአብሄር ብቻ እንደሚመጣ ይረዳል፡፡
ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል። መዝሙር 75፡6-7
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው የጥቅም ደረጃ የለውም፡፡ ስለፍላጎቱ ጌታን የማይታመን ሰው የህይወት መርህ የለውም ወደተመቸው ይገለባበጣል፡፡ ስለፍላጎቱ የማይታመን ሰው ጥቅም ይሁን እንጂ የሚንቀውና እንቢ የሚለው ነገር የለም፡፡ በእግዚአብሄር የማይታመን ሰው እግዚአብሄር በክብር እንደሚባረክ አይረዳም፡፡  
አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ፊልጵስዩስ 4፡19 
የክርስትናም የመጨረሻ ደረጃና የስኬት ጣራ ስለመሰረታዊ ፍላጎት ጌታን ታምኖ ጌታን መከተል ነው፡፡ 
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ