Popular Posts

Friday, March 31, 2017

ክርስትያን ራሱን ማግለል ያለበት ሰባቱ የፉክክር መድረኮች

ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር ለልዩ አላማ ፈጥሮናል፡፡ አንዳችን ከሌላችን የተለየ ጥሪ አለን፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ጥሪ መፈፀም የህይወት ምድብ ስራችንና ተልእኳችን ነው፡፡
እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠው ሃይልና ፀጋ ለዚህ እግዚአብሄ ለጠራን ተልእኮ የሚበቃ ነው፡፡ ከዚህ ተልእኮ የሚተርፍና የሚባክን ምንም ተጨማሪ ሃይል የለንም፡፡
ከዚህ አንፃር እያንዳንዳችን እግዚአብሄር በውስጣችን ያስቀመጠውን ጥሪ መከተል እንጂ ከእኛ እጅግ የተለየ ጥሪ ካለው ከጎረቤታችን ጋር መፎካከር አይገባንም፡፡ ከጎረቤታችን ጋር መፎካከር ጥሪያችንን እንድንጥልና ፍሬ ቢስ እንድንሆን ያደርገናል፡፡  
ከእኛ እጅግ የተለየ ጥሪ ካለው ከሌላው ሰው ጋር በመፎካከር እግዚአብሄር ከሰጠን ጥሪ ወደሃላ የሚጎትቱትን ነገሮች ፀንተን ልንቃወማቸው ይገባል፡፡
የአለምን አሰራር ተከትለን በኑሮ ትምህክት ወሰጥ እንድነጋባ የሚፈትኑትን ነገሮች ተቃቁመንና ከከንቱ ፉክክር ራሳችብን በፈቃዳችንም ራሳችንን አግልለን የተሰጠንን ሩጫ በትግስት እንሩጥ፡፡
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
በፈቃዳችን ራሳችንን ማግለል ያለብን የዘመናችን የፉክክር መድረኮች  
1.     በምንበላውና በምንጠጣው መመካት
ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ከፍ ላለ ጥሪ ተፈጥሯል፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር የማይኖር ሰው በመብላትና በመጠጣት ከመመካት ውጭ ሌላ የተሻለ ነገር ሊያደረግ አይችልም፡፡ ለእኛ የክርስቶስ ተከታዮች ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ እኛ የምንበላው እና የምንጠጣው ለመብለጥ ሳይሆን የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ለማስፈፀም ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማገልገል በምንበላበትና በምንጠጣበት አራት ኮከብ ሆቴል አንፎካከርም፡፡
መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡13
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንሰ 6፡27
2.    በምንለብሰው አንፎካከርም
ልብስ ሰውነትን ከመሸፈን ባለፈ በአለም ላይ ከፍተኛ የመፎካከሪያ መድረክ ነው፡፡ እከሌ የለበበሰወ ልብስ እንደዚህ አይነት ምልክት ነው፡፡ እከሌ ካለእንደዚህ አይነት ምርት ልብስ አይለብስም፡፡ እከሊት ቀሚስዋን የገዛችው በእንደዚህ አይነት ብር ነው በማለት ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ለመልበስ ይፎካከራሉ፡፡ ይህ ለክርስቲያን እጅግ ያነሰና የማይገባ ፉክክር በመሆኑ ክርስትያን ከዚህ የልብስ የውድድር መድረክ በፍጥነት ራሱን ማግለል አለበት፡፡ እኛን ሊያለብሰብንና ከዚህ እግዚአብሄር ካለበሰን የሞገስ መጠን በላይ ሊያሳምረን የሚችል ብራንድ የለም፡፡
እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? ማቴዎስ 6፡30
3.    በሚነዳው መኪና ውድነት መፎካከር
አለማዊያን ከቁሳቁስ ከፍ ያለ የሚወዳደሩበትር ነገር ስለሌላቸው በሚነዱት መኪና ይፎካከራሉ፡፡ በሚነዳው መኪና አይነትና ሞዴል ከማይመለከታቸው ሰዎች ጋር መፎካከር ለክርስቲያን የሚገባ አይደለም፡፡ የመኪና ጥቅም ሰውን ከ ሀ ወደ ለ ማድረስ ነው፡፡ እውነት ነው ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋው ሰዎች ተጨማሪ ምቾት ያለው መኪና ያስፈልጋቸዋል፡፡ የመኪናው ሞዴል ግን በመኪናው ተንቀሳቅሰን ከምንሰራ የእግዚአብሄር የአገልግሎት ጥሪ ይበልጥ መግነን የለበትም፡፡ ሰው ስለሚነዳው መኪና ከሌላው ጋር ከተፎካከረ በኑሮ ትህምክት ወጥመድ ውስጥ ወድቋል ማለት ነው፡፡
4.    ስለሚይዘው ስልክ ውድነትና ጥራት
መሰረታዊው የስልክ ጥቅም ሰውን ከሰው ጋር በድምፅ ማገናኘት መሆኑ አንዳንዴ ይረሳል፡፡ ስለዚህ ሰው ውድ ያልሆነ ስልክ ስለያዘ ተደብቆ ስልኩን የሚያነሳው ከሆነ በማይገባው የህይወት ፉክክር ውስጥ ወድቋል ማለት ነው፡፡ ሰው ውድ ባልሆነ ስልክ ከተዋረደ በውድ ስልክ ይመካል ማለት ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ከሚይዘው ስልክ 75 እጁን ቴክኖሎጂ  እንደማይጠቀምበት የእያንዳንዳችን የዘወትር እይታ ምስክር ነው፡፡ ብዙ ሰው ከሰው እንዳላንስ ብሎ በሚገዛው ውድ ስልክ ውድ ያልሆነ ስልክ ከሚያደርግለት ነገር በላይ አይጠቀምበትም፡፡ እውነት የምትጠቀምበት ከሆነ ደግሞ ውድ ስልክ ያስፈልግሃል እግዚአብሄርም ይሰጥሃል፡፡
5.    የመኖሪያ ቤት ውድነት ወይም አካባቢ
የሚኖርበት አካባቢ ለፉክክር የማይበቃ ስለሆነ አንገቱን አቀርቅሮ የሚገባና የሚወጣ ሰው ውድ ቦታ ቢኖር እንደማየመካ ምንም ማረጋገጫ የለውም፡፡ መኖሪያ ቤት ከመኖሪያ ቤትነት ባለፈ የሰው ልክ የሚለካበት ከሆነ አደጋ ነው፡፡ ልካችን የሚለካው በእግዚአብሄር ልጅነት ስለሆነ በዚህ በዘቀጠ የፉክክረ መድረክ ላይ በመገኘት በማይመጥነን ተራ ነገር ራሳችንን አናዋርድም፡፡
6.    ስምና ዝና
ከእግዚአብሄር ልጅነት በላይ ስልጣን የለም ፡፡ ከንጉስ የቤተሰብ አባልነት በላይ ዝና የለም፡፡ እግዚአብሄር በላያችን ያስቀመጠው ዝናና ስልጣን ለጥሪያችን በቂ ነው፡፡ ጥሪያችንን ለመከተል በተሰጠን ጉልበት ዝናን በማግኘት ሩጫ ላይ አናባክነውም፡፡ ከዚህ በላይ ዝነኛ ለመሆን ከማንም ጋር መፎካከር ለእግዚአብሄር አገልጋይነታችን ክብር አይመጥንም፡፡
7.    በልጆች ትምህርት ቤት
እኔ ልጆቼን የማስተምረው በወር ይህ ያህል እየከፈልኩ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ይህን ያህል እከፍላለሁ፡፡ የእኔ ልጆች ትምህርት ቤት እንዲህ ነው እንዲያ ነው በማለት ሰዎች በልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ ውድነት ይመካሉ፡፡
በእግዚአብሄር ከመመካት ውጭ ያለውን ትምክት እግዚአብሄር አይቀበለውም፡፡ በመክፈል ችሎታችን በተመካን ቁጥር ደግሞ እግዚአብሄር ልጆቻችንን እንዲባርክ ፣ ልባቸውን እንዲከፍትና እግዚአብሄር በወደፊታቸውና በተስፋቸው እንዲባርካቸው ጌታን ተስፋ ማድርግ ያቅተናል፡፡ ከጎረቤታችን ጋር በልጅ ትምህርት ቤት ፉክክረ ውስጥ ሳንገባ ፣ ሳንጨነቅ መክፈል የምንችለውን በአቅማችን እየከፈልን ስለ ልጆቻችን ወደፊት በእግዚአብሄርት መታመን ይገባናል፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
ስምንተኛውን በመጨመር ለፅሁፉ አስተዋፅኦ ያድርጉ፡፡
በህይወታችን እግዚአብሄር ያስቀመጠውን አላማ ለመፈፀም መብዛት አይጠይቅም፡፡ በምድር ላይ የተፈጠርንበትን የህይወት አላማ ላለመፈፀም ደግሞ መዋረድ አያግደንም፡፡ የእግዚአብሄርን ሃሳብ አገልገለን ለማለፍ የሚያስፈልገን  የእግዚአብሄር ሃይል ብቻ ነው፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ትምክት #ነፃነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አርነት #ፉክክር #ውድድር #ጥሪ #አላማ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

100% አስተማማኝ ፍጻሜና ተስፋ

ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
እግዚአብሄር እኛን የፈጠረው በአላማ ነው፡፡ ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር እኛን ከመፍጠሩ በፊት በምድር ላይ ምን እንድምናደርግ አላማውና እቅዱ ነበረው፡፡ በምድር ላይ ድንገት አልተፈጠርንም፡፡ እግዚአብሄር ከፈጠረን በኋላ አይደለም አሁን ምን ላድርጋቸው ብሎ ያሰበው፡፡ የተፈጠርንለት ልዩ የሆነ አላማ አለን፡፡ ዲዛይን የተደረግነውና የተፈጠርነው ስለዚያ ልዩ አላማ ነው፡፡
የተፈጠርንለትን ያንን አላማ በትጋት እግዚአብሄር እየሰራበት ነው፡፡ እግዚአብሄር በህይወት ንድፋችን ዝርዝር አፈፃፀም ላይ ዘወትር እየሰራበት ነው፡፡
እግዚአብሄር የህይወት እቅዳችንን የሚሰራው የፀሎት ጥያቄያችንን ሰብስቦና ቀጣጥሎ አይደለም፡፡ ወደምድር ከምምጣታችን በፊት እንድንፈፅመው አስቀድሞ የተዘጋጀ መልካም ስራ አለ፡፡  
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠርን የህይወት እቅዳችንን ከእግዚአብሄር ተቀብለን በዚያ ላይ መስራት ብቻ ነው እውነተኛ ስኬታማ የሚያደርገን፡፡
ስለዚህ ነው ይህንን እግዚአብሄር ለእኛ ያሰበውን ሃሳብ ለማወቅ እግዚአብሄርን መፈለግ ያለብን፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ ማለት ጥበብ ነው፡፡  በአካሄዳችን ሁሉ በፍፁም ልባችን እግዚአብሄርን መፈለግ ፍሬያማ ያደርገናል፡፡
እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርምያስ 29፡12-13
እግዚአብሄርን ፈልገን መቀበል ያለብን እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበው ሃሳብ መልካም ሃሳብ ነው፡፡ እግዚአብሄር መልካም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የማይለወጥ ሁለንተናው መልካመ የሆነ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያለው አላማ ፍቅር ነው፡፡  የእግዚአብሄር ሃሳብ ለእኛ ሁልጊዜ መልካም ነው፡፡
በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። መኃልየ መኃልይ  2፡4
ወደ እግዚአብሄር ፀልየን መረዳት ያለብን እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ሃሳብ ፍፃሜና ተስፋ ያለው ነው፡፡ እግዚአብሄር የመጨረሻውን ከመጀመሪያ ያያል፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ ያለው የፍፃሜ እቅድ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሃሳብ መጨረሻው የያማረ ነው፡፡ በህይወት ወደፊታችንና ፍፃሜያችን እንዲያምር እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ ከመፈልግ ውጭ አስተማማኝ መንገድ የለም፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበው ሃሳብ 100% አስተማማኝ ነው፡፡
እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ ስንከተል  በህይወታችን ሰላምን ማጣጣም እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ የሚያስበው ሃሳብ በጥቅሉ ሙሉ እና ምንም የሚጎድለው ነገር የሌለ በመሆኑ እውነተኛ እርካታን የምናገኘው ያንን ሃሳብ ስንከተል ብቻ ነው፡፡  እውነተኛ እርካታና የሚገኘው እቅዳችንን አምጥተን እግዚአብሄን ለማስፈለም ሳይሆን እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ሃሳብ በማግኘትና በመከተል ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተሰፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Thursday, March 30, 2017

መጋቢነትና የገቢ ምንጭ

ለቤተክርስቲያነ ከተሰጡት 5ቱ የአገልግሎትር ስጦታዎች አንዱ መጋቢነት ነው፡፡ መጋቢነት ለሰዎች ነፍስ የመትጋት ታላቅ ሃላፊነትን የሚጠይቅ አገልግሎት ነው፡፡
የመጋቢነትን አገልገሎት ዋጋ ሊከፍል የሚችል ገንዘብ የለም፡፡ መጋቢ በምድር ላይ እንደሚኖር እንደ ማንኛውም ሰው ገንዘብ በምድር ላይ ኑሮ ያስፈልገዋል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስም ስለ መጋቢ ብሎም ስለሌሎች የአገልግሎት ስጦታዎች የገቢ ምንጭ ያስተምራል፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ በኑሮ ሃሳብና በባለጠግነት ምኞት ሙሉ ፍሬ ስለማያፈሩ ሰዎች ስለሚያስተምር መጋቢም ሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ ከሚያደርጉት ነገሮች ራሱን ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡(ማርቆስ 4፡19) መጋቢ የገቢ ምንጩን ከየት ያገኛል፡፡ መጋቢ ስለገቢ ምንጩ ዘወር ማለት ያለበት ወደ ማን ነው?
1.      መጋቢ ለአቅርቦቱ ወደ እግዚአብሄር ብቻ ማየት ይገባዋል 
መጋቢ በመጀመሪያ የእግዚአብሄር ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ የሆነ ሰው ሁሉ ደግሞ የሚኖረው ስለሰራ ወይም ስላልሰራ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን እሰከፈለገ ድረስ እግዚአብሄር የሚያስፈልገውን የሚሰጠውና የሚንከባከበው የቤተሰቡን አባል ስለሆነ ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡33
በቤት የተወለደ ልጅን አባቱ የሚንከባከበው እንደስራው መጠን ሳይሆን እንደ ቤተሰቡ ደረጃ ነው፡፡ እንዲሁም መጋቢ የመጋቢነትን ታላቅ ሃላፊነት ከመቀበሉ በፊት የልጅነት መብት የመጠቀም እምነት ያስፈልገዋል፡፡ መጋቢ ከመሆኑ በፊት በእግዚአብሄርን አባትነትና አቅራቢነት እምነት ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ወደ መጋቢነቱ አገልግሎት ከመግባቱ በፊት ስለሚያስፈልገው ነገር እግዚአብሄርን ማመን ሊማር ይገባዋል፡፡
2.     መጋቢ ህዝቡን የገቢ ምንጭ ማድረግ የለበትም፡፡

መጋቢ የአቅርቦት ምንጩ እግዚአብሄርን ብቻ ማድረግ አለበት፡፡ መጋቢ የሚመግባቸውን ሰዎች ምንጩ ካደረገ ህይወቱ ይወሳሰባል ነፃም ሊሆን አይችልም፡፡ ሰው ሲቀንስና ሲጨምር ገቢው አብሮ ይጨምራል ይቀንሳል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠውን የመጋቢነት ሃላፊነት ለመወጣት ሳይሆን ገቢውን ለመጨመር በምንም መልኩ ህዝብን ለማብዛት ይፈተናል፡፡ መጋቢ የሚመራቸውን ሰዎች የገቢ ምንጩ ካደረገ እንደ ገቢው አመጣጥ ከፍ ዝቅ እንዳይል ብዙ ገንዘብ ያላቸውን ልዩ እንክብካቤ ለማድረግ ይፈተናል፡፡ መጋቢ እግዚአብሄርን የገቢ ምንጩ ካላደረገ የሚመራቸውን ለመገሰፅ አቅም ያጣል፡፡ መጋቢ ህዝቡን የገቢ ምንጩ ካደረገ የእግዚአብሄርን ቃል ለማመቻመች ይፈተናል፡፡     

3.     መጋቢ ስለ አቅራቦቱ የእግዚአብሄርን ቃል ማመን አለበት

መጋቢዎች የእግዚአብሄር ቃል የሚናገረውን ወንጌልን የሚሰራ በወንጌል ይኖር የሚለውን ቃል ለማመን ሲቸገሩ ሌላ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ይጥራሉ፡፡ ሌላ የገቢ ምንጭ መፍጠር በራሱ ችግር የለውም፡፡ አንዳንዶች መጋቢዎች ለቃሉና ለፀሎት ከመትጋት ውጭ ሌላ ስራ እየሰሩ የእግዚአብሄን ህዝብ የሚያገለግሉ የተባረኩ መጋቢዎች አሉ፡፡

ችግሩ መጋቢው ወንጌልን በሚሰራበት ጊዜና ጉልበት ሌላ የገቢ ምንጭ ማስገኛ ነገር ውስጥ ከገባ የሰዎችን ህይወት በትጋት የመስራት ስራው ይበደላል፡፡ መፅሃፍ ወንጌልን የሚሰራ በወንጌል ይኑር ያለው መጋቢው ለቃልና ለፀሎት እንዲተጋ ሌላ ጊዜውንና ጉልበቱን የሚከፋፈል ነገር ውስጥ እንዳይገባ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር መጋቢው ያለበትን ጫና ለመቀነስ የሚማረው ከሚያስተምረው ጋር መልካሙን ነገር ሁሉ መከፋፈል አለበት፡፡

ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል። ገላትያ 6፡6

እንዲሁም መጋቢዎች መንፈሳዊውን ነገር ዘርተው ከሚያገለግሉዋቸው ስጋዊን ነገር ቢያጭዱ ትልቅ ነገር አይደለም፡፡  

እኛ መንፈሳዊን ነገር የዘራንላችሁ ከሆንን የእናንተን የሥጋዊን ነገር እኛ ብናጭድ ትልቅ ነገር ነውን? 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡11

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #አቅርቦት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ገቢ #ቃል #መዝራት #ወንጌል #መጋቢ #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, March 29, 2017

ያለመናከል ቁልፎች

የክርስትና መንገድ ጀምረው የተሰናከሉ ልባቸው የቀዘቀዘና ወደሃላ የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለመሰናከል ግን ምንም አይነት ጥሩ ምክኒያት የለም፡፡ እግዚአብሄር በምንም ነገር እንዳንሰናከል ይፈልጋል፡፡   
በክርስትና ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ጥበብና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከሰው ጋር እንዴት እንደምንኖር ማወቅ ከፍ ካሉ እውቀቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በተለይ በሰዎች ላለመሰናከል መማር ረጅም መንገድ እንድንጓዝ ይረዳናል፡፡ እግዚአብሄር በነፃነት እንድናገለግለው ይፈልጋል፡፡
ከመሰናከል ተጠብቀን እግዚአብሄርን በሙላት እንድናገለግል የሚረዱ ሶስቱን መንገዶች እንመልከት፡፡
1.      ከሰው አለመጠበቅ

ብዙ ሰዎችን የሚያሰናክላቸው ከሰዎች መጠበቅ ነው፡፡ ሰዎች ምንም ሊያደርጉልን አይችሉም፡፡ ሰዎችን እግዚአብሄር ካልተጠቀመባቸው ምንም ሊያደርጉልን አይችሉም፡፡  እግዚአብሄር በጊዜው የተጠቀመባቸው ሰዎች ደግሞ ያላሰብነውንና ያልገመትነውን ነገር ሲያደርጉልን እናያለን፡፡ ላለመሰናከል ከሰው አለመጠበቅ ወሳኝ ነው፡፡ ከሰው ባልጠበቅን መጠን ሰው ባላደረገልን ጊዜ መሰናከላችን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ ከሰው በጠበቅን መጠን ሰው መልካም ባላደረገልን ጊዜ መሰናከላችን እንዲሁ ይጨምራል፡፡

እኛም እንዲሁ ለሰው የምናደርገው እግዚአብሄር ስለተጠቀመብን ብቻ እንደሆነ መርሳት የለብንም፡፡ ሰው መልካም ሊያደርግልን ቢጨነቅም እግዚአብሄር ካልተጠቀመበት ከመጨነቅ ውጭ ምንም ሊያደርግልን አይችልም፡፡

እግዚአብሔርን፦ አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። መዝሙር 16፡2

2.     ሰዎችን ጌታን በሚመስሉበት የህይወት ክፍላቸው ብቻ መከተል

ከመፅሃፍ ቅዱስ ቀጥሎ የሰዎች ህይወት ጌታን እንዴት እንደምንከተል ብዙ ጥበብን ይሰጠናል፡፡  ጌታን በሚመስሉበት የህይወታችው ክፍላቸው ሰዎች መከተል መፅሃፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ ነገር ግን ሰዎችን ሙሉ ለሙሉ መከተል ለመሰናከል ራስን መጋበዝ ነው፡፡

እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ። 1 ቆሮንቶስ 11፡1

3.     እኛ ለሰዎች በምናደርገው ነገር ላይ ብቻ ማተኮር
መፅሃፍ ቅዱስ ለተሳካ የክርስትና ህይወት
ጤናማ ያልሆነ በሌላ ሰው ላይ መደገፍ ለክርስትና ህይወት ጠንቅ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምታል፡፡ ሁለቱም አንድ  ስጋ ይሆናሉ የተባሉት ባልና ሚስት እንኳን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጤናማ ያልሆነ መደገፍ እንዳይኖራቸው መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡  
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡29-31
እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። ሉቃስ 6፡34
4.     በሰው ላይ እንድትደገፍ የሚያደርጉህን ነገሮች በፍጥነት ማስወገድ  
በሰው ላይ እንድንደገፍ የሚያደርጉን ነገሮች በቀነሱና ራሳችንን በቻልን ቁጥር የመሰናከያ ምክኒያቶች ይቀንሳሉ፡፡
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን። 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡11-12
5.     አይናችንን በጌታ ላይ ማድረግ

ሰዎችን እግዚአብሄር ሲጠቀምባቸው እናያለን፡፡ ሰዎችን እግዚአብሄር ሲጠቀምባቸው ባየን መጠን እግዚአብሄር ስለተጠቀመባቸው ብቻ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ ሰዎች የመልካምነት ምንጭ አይደሉም፡፡ የመልካምነት ብቸኛ ምንጭ እግዚአብሄር ነው፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ ሰው ሆኖ በተመላለሰ ጊዜ ቸር መምህር ሲሉት አይናቸውን ከስጋ ለባሽ ላይ አንስተው የቸርነት ምንጩ ላይ እንዲያደርጉ አስተምሮዋል፡፡
           ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ሉቃስ 18፡19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አትሰናከሉ #ነፃነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አርነት #ሃላፊመልክ #ቃል #ማሰላሰል #ጌታንማየት #ከሰውአለመጠበቅ #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

ሁሉን የሚችል አማኝ!

ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። ማርቆስ 9፡23
ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡፡
ሁሉ? አዎ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡፡
ተመልከቱ ለእኔ ለኢየሱስ ሁሉ ይቻላል አይደለም ያለው ኢየሱስ፡፡ ኢየሱስ ትሁት በመሆኑ ራሱን ከሁላችን ጋር አስተባብሮ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ይላል፡፡  
በእምነት ውስጥ ያለው እምቅ ጉልበት ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ካመንክ ለአንተ ሁሉ ይቻላል፡፡ ከአምንሽ ለአንቺ ሁሉ ይቻላል፡፡ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡፡
እግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ሁሉን ማድረግ ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ለሚያምን እንዲሁ ሁሉ ይቻለዋል፡፡ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡፡
እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት ነው፡፡ እምነት የሚመጣው የእግዚአበሄርን ፈቃድ ከመረዳት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለተረዳና እንደ ፈቃዱ ለሚኖር ሰው ሁሉ ይቻለዋል፡፡ የእግዚአብሄርን ልብ ተረድቶ እንደ እግዚአብሄር ሃሳብ ለኖረ ሰው ሁሉ ይቻላል፡፡ በሚያምነውን ሰው አንደበት የእግዚአብሄርን ቃል ሁሉን ማድረግ ይችላል፡፡ በሚያምነው ሰው ህይወት ውስጥ የእግዚአብሄር ቃል ሁሉን ማድረግ ይችላል፡፡
ለሚያምን ሰው ሁሉን ቻዩ የእግዚአብሄርን ቃል ሁሉን ይቻላል፡፡ ለሚያምን ሰው ሰማይና ምድርን የፈጠረውን የእግዚአብሄርን ቃል ሁሉ ያስችለዋል፡፡ በእግዚአብሄን ቃል የሚደገፍ ሰው አይወድቅም፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ሊቋቋም የሚችል እንደሌለ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያምነውን ሰው ሊቋቋም የሚችል ሃይል ከሰማይ በታች የለም፡፡ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡፡
ለሚያምን ሁሉ ይቻላል!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Tuesday, March 28, 2017

የሁለቱ ቅርጫቶች ባለቤት ታሪክ

አንድ የሰማሁትን ልብ የሚነካ ታሪክ ላካፍላችሁ፡፡ ታሪኩ በጣም ልቤን ስለነካኝና ስላስደነገጠኝ ምን ያህል ጊዜ ለሰዎች እንደተናገርኩት አላስታውሰውም፡፡
ታሪኩ እንደዚህ ነው፡፡ አንድ ክርስትያን ስለ አንዲት ክርስቲያን ሲፀልይ ራእይ ያያል፡፡ በራእዩም ውስጥ ሁለት ቅርጫቶችን ይመለከታል፡፡ አንደኛው ቅርጫት ሙሉ ነው ፡፡ አንደኛው ቅርጫት ግን ከሞላ ጎደል ባዶ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ክርስትያን ይህ ምንድነው ብሎ ጌታን ሲጠይቅ እግዚአብሄር ተናገረው፡፡
ይህ የምታየው የሞላው ቅርጫት የዚህች ሴት ልመናዋ ነው፡፡ ይህች ሴት መለመን ታውቅበታለች፡፡ ስለዚህ በትጋት ትለምነኛለች፡፡ ይህ የምታየው ከሞላ ጎደል ባዶው የዚህች ሴት የምስጋና ህይወትዋ ነው፡፡ ይህች ሴት እኔን እንዴት እንድምታመሰግን አታውቅም፡፡ እኔን ለማመስገን አትተጋም፡፡ እኔ ደግሞ ልመናዋን መመለስ እፈልጋለሁ፡፡
ለዚህች ሴት እንዲህ ብለህ ነገራት፡፡ እኔን ማመሰገን ጀምሪ፡፡ እኔን በነገር ሁሉ ማመስገን ተማሪ፡፡ እኔን የሚያመሰግን ህይወት ይኑርሽ፡፡ እኔን በትጋት ማመስገን ስትጀምሪ ይህ የፀሎት ልመናሽ ሁሉ እየተመለሰ ይሄዳል ብሎ ተናገረው፡፡
ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። 1 ጢሞቴዎስ 2፡2
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6
ወደ ደጆቹ በመገዛት፥ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፤ መዝሙር 100፡4
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አመስግኑ #መልካም #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ቸር #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

እግዚአብሔር መልካም

እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል። ናሆም 1፡7
ማስታዋሉ የማይመረመር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ መልካም ባይሆን እንዴት እንሆን ነበር? ሁሉን ያደርግ ዘንድ ቻይ የሆነ እግዚአብሄር መልካም ባይሆን ምን እንሆን እንደነበር ማሰብ ይከብዳል፡፡  
እግዚአብሄር ለመረዳት የሚያዳግተውን ሃይሉን የሚጠቀመው በመልካምነት ነው፡፡ እግዚአብሄር የማይመረመረውን ማስተዋሉንና ጥበቡን የሚጠቀመው በመልካምነት ነው፡፡
የእግዚአብሄር መልካምነት የማይለዋወጥ ቋሚ ነው፡፡ አንድ ቀን ይለወጥ ብለን የምንፈራው አይደለም፡፡
እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፥ ስለዚህ የጠፋችሁ አይደላችሁም። ሚልክያስ 3፡6
እግዚአብሄር ሁለንተናው መልካም ነው፡፡ እግዚአብሄርን በግራም በቀኝም ብታዩት መልካም ነው፡፡ እግዚአብሄር መልካም እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ያዕቆብ 1፡16-17
እግዚአብሄር መልካም ብቻ ሳይሆን የመልካምነትም ጣራው ነው፡፡ ስለ መልካምነት ክርክር ቢነሳ ሊፈታው የሚችል እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር መልካም ያለው መልካም ነው እግዚአብሄር መልካም ያላለው መልካም አይደለም፡፡
ስለዚህ ነው ሁል ጊዜ በነገር ሁሉ እግዚአብሄርን ማመሰገን መልካም የሆነው፡፡ እግዚአብሄር ሁለንተናው መልካም ስለሆነ እግዚአብሄን ማመስገን መልካም ነው፡፡ ሰው ሌላ ነገር አድርጎ ቢስት እግዚአብሄርን በማመስገኑ የሚሳሳት ሰው የለም፡፡
እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና። መዝሙር 92፡1፣4
በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡18
እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፡፡ መዝሙር 135፡3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አመስግኑ #መልካም #እምነት #ቃልኪዳን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ቸር #መንፈስ #መንፈስቅዱስ