Popular Posts

Tuesday, October 26, 2021

Monday, October 18, 2021

የሰላም ጥሪ

 


በታሪክ ሂደቶች ውስጥ ሰው ከሰው ጋር ቤተሰብ ከቤተሰብ ጋር ሀገር ከሃገር ጋር ወዘተ ይጋጫል። ለምን ተጋጩ አይባልም። ተጋጩ ማለት ደግሞ በቃ አለቀላቸው እስኪጨራረሱ ድረስ ችግራቸው መፍትሄ አያገኝም ማለት አይደለም። ተጋጩ ማለት ደግሞ አንዱ ሌላው  ላይ አይሎበት እስኪያሸንፈው ድረስ ምንም መፍትሄ የለም ማለት አይደለም።

ከግጭት  በኋላ ህይወት አለ ከግጭት በኋላ አብሮ መኖር አለ። ግጭት በሚገባ ከተያዘ ከግጭት በኋላ አንድነት ሊመጣ ይችላል።

የተጋጨ ቤተሰብ ሰላም ይፈጥራል በተለይ አብሮ የሚኖር ቤተሰብ ብዙ ነገር ስለሚያገናኘው ጠላትነት ይቅርብኝ አይጠቅመኝም ብሎ በመረዳት ጠላትነትን ይተዋል። ለሌላው ጥቅም ሲባል ያን ያህል የማይጎዳውንም ነገር ይተዋል። አንድነትን እና አብሮ መኖርን የሚያስብ ሰው ይነጋገራል ይታረቃል እንዲሁም በሚያስማሙት ጉዳዮች ላይ እንደገና አብሮ መስራት ይወስናል።

የተለያየ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር በአንድነት ለመኖርም ፈልጎም ደግሞም የእኔ መንገድ ብቻ ይሁን ብሎም ሰላም ሊገኝ አይችልም። አብሮ መኖር ሌላውን በቅንነት መቀበል መደራደር ሰጥቶ መቀበልንም ይጠይቃል።

መታረቅ ማለት አንዱ የአንዱን ውድቀት አለመፈለግና አንዱ ለአንዱ ጥፋት አለመስራት ማለት እንጂ ሌላው ወገን የሚለውን ሁሉ እሺ ብሎ መቀበል ማለት አይደለም። ብዙ ሰዎች እርቅ የሚያስደነግጣቸው ሌላው ወገን የሚጠይቀውን ሁሉ የሚቀበሉ ስለሚመስላቸው ነው።  መቀራረብ መነጋገር ማለት አንዱ የሌላውን ስጋት መስማት ፍላጎቱን ለመረዳት መሞከር አብሮ ለመኖር በተቻለ አቅም የሌላውን ስጋት ለመቀነስ መወሰን ማለት ነው።

አሁንም በኢትዮጲያ ውስጥ ከሞላ ጎደል አንድ አመት የሞላው ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል። ይህ ጦርነት ክቡሩን የሰው ህይወት እየቀጠፈ ጥላቻ ቂምና በቀልን እያስፋፋ ብዙዎችን ለአመታት ከኖሩበት ቤታቸው እያፈናቀለ በሁለቱም ወገኖች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድመት እያደረሰ ይገኛል።

በኢትዮጲያ መንግስትም ሆነ በህወአት በኩል እስካሁን ጎልቶ የሚታየው ሁለቱም ያላቸውን የተሻለ ጥቅም ተጠቅመው ጦርነቱን ለማሸነፍ መጣጣር ብቻ ነው። አሁን የሚታየው አንዱ አንዱን በማሳነስ ለማጥፋት እና ለመግደል መዘጋጀት ነው። አሁን የሚታየው አንዱ ለአንዱ የሚያኮስስ ስም በመስጠት አንዱ ሌላውን ከሰውነት ደረጃ ማሳነስ ነው። አሁን የሚታየው አንዱ ሌላውን ነገር እንደማይገባው ደንቆሮ እንደሆነ በእብደት እየተንቀሳሰቀ እንዳለ ማሳየት ነው። አሁን የሚታየው አንዱ ሌላውን የስልጣን ጥመኛ እንደሆነ እና ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲባል ምንም ነገር እንደሚያደርግና የሰው ጥፋት ግድ እንደማይለው መካሰስ ነው። አሁን የሚታየው እንዱ ሌላውን ስግብግብና ራስ ወዳድ እንደሆነ የሌላን ጥቅም ከግምት ውስጥ ሊያስገባ እንዳልተዘጋጀ መወነጃጀል ነው።

ለህዝብ ደህንነት ግድ የማይላቸው ጥቂት የፖለቲካ መሪዎች ሌላውን ከምድረገፅ ለማጥፋት ተከታዮቻቸውን ማነሳሳትና ማዝመት ከተራ የፖለቲካ ጥቅም የዘለለ  እናገለግለዋለን ለሚሉትን ህዝብ የሚጠቅመው ነገር አንዳች ፋይዳ የለውም። 

ይህ ስልት በጦርነቱ ህይወቱን እና አካሉን የሚያጣውን ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል በጥላቻ ለማነሳሳት እና ለማዝመት ይጠቅም ይሆናል። ይህ አካሄድ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በዚህ ውድድር በበዛበት አለም አገሪቱ ከድህነት እንድትወጣ   በኢኮኖሚ ራስዋን እንድትችል ለማድረግ የሚጠቅመው ምንም ፋይዳ የለም።

እውነት ነው መቼም ቢሆን ሊወጋን ሊገድለን የመጣን ወገን እጃችንን አጣጠፈን አስኪገድለን ድረስ አንጠብቀውም። ሊያጠፋን የመጣ እንከላከላለን። ራስን መከላከል ያለ ነው። ራስን ከመከላከል ያለፈ በተራዘመ ጦርነት ሌላውን ለማጥፋት ማጥቃት ግን ትልቅ ኪሳራ የሚያስከፍል ብልሹ ስልት ነው። አጥቂውና ተጠቂው በውል ባልታወቀበት ሁኔታ ሁለቱም ወገን ሊያጠቃቸው የመጣ ከሚመስላቸው ወገን ጋር እየተዋጉ መኖር ግን ጥበብ የጎደለው የጥፋት ጎዳና ነው። አንዱ አንዱን አጠቃኝ ከምድረ ገፅ ሊያጠፋኝ ነው ብሎ ምክኒያት እየሰጠ   የምዋጋው ራሴን ለመከላከል ለህልውናዬ ነው ብሎ በሚሟገትበት ሁኔታ በጦርነት መቀጠል ጥፋት እንጂ መፍትሄ አያመጣም። 

ወደድንም ጠላንም አንድ ወገን ሌላውን ወገን እንዲያጠቃ ያደረገው የራሱ ስጋት አለበት። በእኛ አስተያየት ስጋቱ ተቀባይነት ይኑረውም አይኑረውም ቢያንስ ስጋቱ እኛን እንዲያጠቃን አስችሎታል። ማንም ሰው በትክክለኛ አእምሮ ሰላምን አይጠላም። ታዲያ ሌላው ወገን ከእኛ ጋር ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ምክኒያት እንዳለ በትህትና ማመን እና መቀበል ብልህነት ነው። እንዲያው በደፈናው ሌላው ወገን ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ምንም አይነት ምክኒያት የለውም ብሎ ማመን ራስን ማታለል ነው። ሌላው ወገን ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ምክኒያት ምንድነው ብሎ በቅንነት መጠየቅ ለሰላም መፍትሄ አንድ እርምጃ ነው። 

ሌላው ወገን ስጋት ውስጥ እንዲገባ ያደረገውን ነገር መጠየቅ ደግሞ ሌላው ወገን ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ያደረገውን ነገር ተቀበልነው ስለትክክለኝነቱ ማረጋገጫ ሰጠንለት ከእርሱ ሃሳብ ጋር ተስማማን ማለት ደግሞ አይደለም። የሌላውን ወገን ስጋት መስማት በእኛ በኩል ስጋቱን ለመቀነስ ማድረግ የሚገባንን ነገር ሁሉ ማድረግ አብሮ በሰላም ለመኖር አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።  

ሌላው ወገን እንዲያጠቃን ያደረገውን እና ያጋጨንን ምክኒያት በቅንነት መስማት ተመሳሳይ ነገር ለወደፊት እንዳያጋጨን መነጋገር እና መደራደር ሌላውን መልሰን ገንዘባችን ማድረግ በስጋትና በጭንቀት ከመኖር ይገላግላል። ከሌላው ጋር መነጋገር እና መወያየት ወገናችን በጥላቻና በእልክ የሌላው መጠቀሚያ እንዳይሆን ያድነዋል።

በእልህና በአሳየዋለሁ ስሜት ጦርነቱን ማራዘም ሁለቱም ወገኖች ለእርዳታ ወደውጭ መንግስረታት እንዲዞሩ በማድረግ የጦር መሳሪያ የሚሸጡልንን አገሮች ከማበልፀግ ውጭ ለህዝቡ የሚጠቅመው ምንም ነገር የለምን። ለእርቅና ለድርድር አለመዘጋጀት በምድሪቱ መዋረድ የሚጠቀሙ አገሮች በሌላው ወገን ተጠቅመው አገሪቱን የውክልና የጦር ቀጠና እንዲያደርጉዋት መጋበዝ ነው። ከእኔ ይለፍ እርሱ ይጠቀም ብሎ አንዳንዱን ነገር መተው ግን ቢያንስ  አንድነቱን የምንፈገልገው የአገራችን ሰው ወገናችን እንዲጠቀም ያደርገዋል፡፡ ከወገናችን ጋር ለመታረቅ እንቢ ማለት ግን ገንዘባችን ማድረግ ያለብንን ወገናችንን ጠለኻት ከማድረግ አልፎ ጠላታችንን ያበዛዋል፡፡ 

አንዳችን የአንዳችንን የጦር ችሎታ ለማሳየት አንድ አመት ከበቂ በላይ ነው። ሁለቱም ወገኖች አገርን ለማጎሳቆል የሚበቃ ሃይል እንዳላቸው ባለፉት አንድ አመት አስመስክረዋል። እርሱ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ወገኖች ከውጭ ሃይል ጋር ሆነው በአገሪቱ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን አሰቃቂ የመከራ ጉልበት በግልጽ አሳይተዋል። አሁን ጥያቄው መሆን ያለበት ሃይል አላቸው የላቸውም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ሃይላቸውን መሞከር ሳይሆን ሃይላቸውንም ለጥፋት ሳይሆን ለሰላም እና ለልማት የመጠቀም ጉዳይ ላይ ነው። ሁለቱም ወገኖች የራሳቸው ጉልበት እንዳላቸው አይተናል እንመሰከርላቸዋለን።

ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ግጭት በግጭት እንደማይደመደም አንድ ቀን ድርድር ውስጥ እንደሚገቡ ሁለቱም ወገኖች ያውቁታል። ጥያቄው የፖለቲካ መሪዎች የሚደራደሩት በድህነቱ ወደ ወታደርነት የሚቀላቀለው ተራው ህዝብ አልቆ ወደ መሪዎቹና አዛዦቹ ደረጃ ሲደርስ መሆን ግን የለበትም። ጥፋት መቅረት ካለበት በተቻለ መጠንና ፍጥነት አንድ ተጨማሪ ሰው ሳይሞት አንድ ሰው ከሰላማዊ ኑሮው ሳይፈናቀል አሁን መሆን አለበት።

የህዝባቸው የሰላም ሃላፊነት እንዳለባቸው ሁለቱም ወገኖች በጠረጴዛ ዙሩያ ይቀመጡና ሃላፊነት እንደሚሰማቸው ሙሉ ሰዎች እንዲነጋገሩ ህዝቡ ይጠብቅባቸዋል።

ይህን ሁሉ ጊዜ አንዱ ሌላው ህሊና እንደሌለው ሊያሳየን ቢጥርም ሰው ህሊና እንዳለው በመነጋገር በመደራደር ብዙ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚችሉ እናውቃለን። በዚህም በዚያም ያሉት መሪዎች እመራዋለው አገለግለዋለሁ የሚሉት ህዝብ ጉስቁልና ህሊናቸውን ይነካቸዋል። በዚህም በዚያም ወገን ያሉ መሪዎች የሚመሩት ህዝብ እየታዘበቸው ነው። ህዝብ በምጥ የሰላምን መምጣት በጉጉት እየጠበቀ ነው። የሚመሩት ህዝብ ሃላፊነት እንዳለባቸው መጠን በሚያስማማቸው ነገር ላይ በፍጥነት መስማማት ይጠበቅባቸዋል። በሁሉም ነገር ላይ ይስማማሉ ብሎ መጠበቅም ሞኝነት ነው። ነገር ግን ጥላቻን አስወግደው ተኩስ ካቆሙ እና በዋና ዋና ነገሮች ላይ ለመደራደር ከተቀመጡ ቢያንስ ህዝቡ ወደ ሰላማዊ ህይወቱ ከተመለሰ ትልቅ ድል ነው። በድርድሩ እርስ በእርሳቸው መስማማት ካልቻሉ ደግሞ ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም የሚያምኗቸው እና ለአደራዳሪነት የሚቀበሏቸው አስታራቂዎች ወገኖች በመካከል ገብተው እንዲደራደሩ ይረዷቸዋው።

እንዲታወቅበት የማይፈልገው የሚደብቀው ነገር ከሌላ በስተቀር ህዝብን በቅንነት እመራለሁ ለሚል ሰው ሁለቱም የሚያሸንፉበትን የሰላምን መንገድ ድርድርን እንደድል እንጂ እንደ ሽንፈት አያየውም። እኔነታቸውንና ትምክታቸውን ጥለው የሚሊዮኖች ሃላፊነት እንዳለባቸው ሰዎች ቢነጋገሩና ቢደራደሩ ታሪክ በመልካምነት ያስታውሳቸዋል እንጂ ማንም አይንቃቸውም። 

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #እውነት #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ትህትና #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #መሪ