Popular Posts

Follow by Email

Friday, September 29, 2017

እንደ እርሱ ያለ ረዳት

አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤ ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። ዘፍጥረት 2፡20
እግዚአብሄር ሰውን ከፈጠረ በኋላ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም በማለት የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት ሲል እንመለከታለን፡፡ ከዚያም እግዚአብሄር የምድርን እንስሳትን ሁሉ በምን ስም እንደሚጠራቸው ያይ ዘንድ በፊቱ አሳለፈለት፡፡ ሰው ግን ለሁሉም ስም ካወጣ በኋላ ብቸኛ ነበር፡፡ ለሰው ግን እርሱንም የሚመስል እንደ እርሱ የሚያስብ እንደ እርሱ የሚናገር እንደ እርሱ የሚሰው አልተገኘለትም ነበር፡፡ ለአዳም እንደ እርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር፡
በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሄር ሁሉንም ነገር ከፈጠረ በኋላ እንደእርሱ ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ከፈጠረ በኋላ ወንድና ሴት ልጆች የቤተሰቡ አባል አልነበሩም ነበር፡፡ ስለዚህ ነው እግዚአብሄር ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ብሎ የተናገረው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው እርሱን የሚመስል ፣ ከእርሱ ጋር የሚግባባ ፣ እንደ እርሱ የሚሰማው ፣ እንደ እርሱ የሚያስብ እንደ እርሱ ያለ ወዳጅ ፈልጎ ነው ፡፡
እግዚአብሄር ሰውን ሳይሰስት በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው እርሱን የሚረዳው እንደ እርሱ ያለ ረዳት ፈልጎ ነው፡፡
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ዘፍጥረት 1፡27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መንፈስ #ነፍስ  #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ወዳጅ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ

Tuesday, September 26, 2017

የስጋ መስቀል አይጠቅምም

ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል። እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን? ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል። በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም። ሮሜ 2፡25-29
መፅሃፍ ቅዱስ ስለ ስጋ እና ስለልብ መገረዝ ይናገራል፡፡ በብሉይ ኪዳን ስጋቸውን ስለሚገረዙ ሰዎች ነገር ግን ልባቸው ስላልተገረዘ የእግዚአብሄርን ቃል ስለማይጠብቁ ሰዎች ይናገራል፡፡ ሰው ልቡ ካልተገረዘና በእግዚአብሄር መንገድ ካልሄደ የስጋው መገረዝ ለሰው ምንም አይጠቅመውም፡፡ ነገር ግን ስጋው ያልተገረዘ ልቡ የተገረዘ ሰው እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡ እግዚአብሄር የውጭውን ስርአት ሳይሆን የልብን ነገር ነው የሚመለከተው፡፡
አሁን ማንሳት የፈለግኩት ስለግርዘት ሳይሆን ሰለመስቀል ነው፡፡ የመስቀልን በአል በየአመቱ በደማቅ ሁኔታ ብናከብር ነገር ግን የመስቀል ህይወት ከሌለን ምንም አይጠቅመንም፡፡ ይልቁንም የመስቀልን በአል የማያከብር ነገር ግን መስቀልን በህይወቱ የሚለማመድ ሰው ይሻላል፡፡
የመስቀልን በአል በየአመቱ ብናከብር የመስቀል ቃል በህይወታችን ከሌለ ምንም አይጠቅመንም፡፡ የመስቀል ቅርፅ በአንገታችን ብናስር የመስቀል ህይወት ግን በልባችን ከሌለ ምንም አይጠቅመንም፡፡
1.      መስቀል ኢየሱስ የሞተበት ነው፡፡
መስቀል ኢየሱስ ስለሃጢያችን የውርደትርን ሞት እንደሞተ ይናገራል፡፡ መስቀል ስለኢየሱስ መስዋእትነት ይናገራል፡፡ መስቀል ኢየሱስ በእኛ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ይናገራል፡፡
ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ማቴዎስ 26፡28
2.     የመስቀሉ አሰራር ዘላለማችን የሚወስን ነው፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ ለአንዳንዶች ሞኝነት ነው ለሌሎች የእግዚአብሄር የማዳኛ ሃይል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የመስቀሉን አሰራር በፍፁም አይቀበሉትም ሌሎቹ ደግሞ ሁለንተናቸው መስቀል ነው፡፡ ለኢየሱስ የመስቀል ስራ ያለን እምነት ዘላለማችንን ይወስነዋል፡፡ ኢየሱስ ወደምድር የመጣው ሰዎችን ከሃጢያት ሊያድን በመሆኑ የመስቀሉን ትምህርት የተቀበሉ ሰዎች ከሃጢያት ባርነት ነፃ ይወጣሉ፡፡  
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡18
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ማቴዎስ 1፡21
3.     መስቀል ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ደሙን እንዳፈሰሰ ይናገራል፡፡
መስቀል ሃጢያታችንን በደሙ ሊያጥብ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ደሙን እንዳፈሰሰ ይናገራል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ያለደም ስርየት የለም እንደሚል የሃጢያታችንን ይቅርታ የምናገኘው ሃይማኖታው ስርአት ስለፈፀምን ሳይሆን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ያፈሰሰልንን ደም ለእኔ ነው ብለን ስንቀበል ነው፡፡
ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ዕብራውያን 9፡14
4.     መስቀል ከእግዚአብሄር ጋር ሰላምን እንዳገኘን ይናገራል፡፡
ኢየሱስ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በመስቀሉ እንደሻረው መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰውና የእግዚአብሄርን ጠላትነት ሻረ፡፡ ማንም ሰው ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራለትን ስራ ቢቀበል እግዚአብሄር ወደቤተሰቡ ይቀበለዋል፡፡ 
እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። ኤፌሶን 2፡14-16
5.     መስቀል እኛም አብረነው እንደተሰቀል ይናገራል፡፡
መስቀል ስላለፈው ሃጢያት ይቅርታ ብቻ ሳይሆን በሃጢያት ላይ ሃይል ስላገኘንበት የእግዚአብሄር አሰራር ይናገራል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የእኛን የሃጢያተኛ ስጋ ወክሎ ነው የሞተው፡፡ በኢየሱስ ስጋ የእኛ የሃጢያት ስጋ ተገድሎዋል፡፡ ኢየሱስ ይቅር ያለው ያለፈውን ሃጢያታችንን ብቻ ሳይሆን ኢየሱስን ከተቀበልን በኋላ ሃጢያት እንዳንሰራ የሃጢያተኛ ባህሪያችንን በመስቀሉ ላይ ገድሎታል፡፡
ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ። ሮሜ 8፡3-4
ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና። ሮሜ 6፡6
6.     መስቀል ለሞተልን እንድንኖር ይናገራል፡፡
መስቀል ስለኢየሱስ ሞት ብቻ ሳይሆን ሰለእኛም ሞት ይናገራል፡፡ መስቀል ኢየሱስ ስለእኛ ስለመሞቱ ብቻ ሳይሆን እኛ ለአለም  ስለመሞታችንን ይናገራል፡፡
ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። ገላትያ 6፡14
7.     መስቀል በየእለቱ ለስጋችን ፈቃድ ስለምንሞትበት የእግዚአብሄር አሰራር ይናገራል፡፡  
መስቀል የስጋችንን ፈቃድ በየእለቱ እንቢ የምንልበት ነው፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ በእያንዳንዱ ቀን የሃጢያተኛ ስጋችንን ፈቃድ እንቢ ለማለት ሃይልን የምናገኝበት የእግዚአብሄር አሰራር ነው፡፡
ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ሮሜ 8፡36
8.     የክርስትና ስብከት ልቡ ያለው መስቀል ላይ ነው፡፡
ሞት የሌለው መስቀል ጌጥ እንጂ ምንም አይደለም፡፡ መስቀል የሌለው ስብከትም ሆነ ትምህርት ክርስትና አይደለም፡፡ የመስቀል ህይወት የሌለው በአል ድግስ እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡ ኢየሱስ ለእናንተ ሞቶዋል ለሃጢያትና ለአለም ሞታችኋል ለክርስቶስ ኑሩ የማይል ስብከት መፅሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡1-2
ባገኘነው አጋጣሚ መስቀልን ማክበር አለብን ነገር ግን በህየወት የማይከበር መስቀል ለምንም አይጠቅምም፡፡  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #መስቀል #ስቅለት #ሃጢያት #ሞት #ስቅለት #ጠቦት #መጋረጃ #ደም #ትንሳኤ #ስርየት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተፈፀመ #ቤተመቅደስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Monday, September 25, 2017

የመገለጥ እውቀት የምናገኝባቸው አራቱ መንገዶች

የአእምሮ  እውቀት ብቻ በራሱ መጥፎ ባይሆንም እንደመገለጥ እውቀት የሰውን ህይወት አይለውጥም፡፡ ህይወታችን በመገለጥ እውቀት ካልተለወጠ ደግሞ እግዚአብሄር በምድር ሰርተን አንድናልፍ ያዘጋጀልንን መልካሙን ስራ ፈፅመን ልናከብረው አንችልምን፡፡ የአእምሮን እውቀት የምናገኘው መፅሃፍ ቅዱስን በማንበብ ብቻ ነው፡፡ የመገለጥ እውቀት ግን መፅሃፍ ቅዱስን በማንበብ ብቻ ወደእኛ ሊመጣ አይችልም፡፡ በህይወታችን የመገለጥ እውቀትን ሊያመጡ የሚችሉትን ነገሮች ካደረግን የመገለጥ እውቀት ወደ ህይወታችን ይመጣል በዚያም ህይወታችን ይለወጣል፡፡ እኛ የመገለጥ እውቀት እንድናገኝ ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር የመገለጥ እውቀት እንድናገኝ ይፈልጋል፡፡
የመገለጥ እውቀት ለማግኘት የመጀመሪያው ደረጃ ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በስተቀር ምንም ስለ ኢየሱስ በታሪክ ቢያውቅ እግዚአብሄርን ግን ሊያውቀው አይችልም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት በመካከላችን ሆና ሳለ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሄርን መንግስት ሊያያት አይችልም፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
የመገለጥ እውቀት ለማግኘት ራስህ ትሁት በማድረግ ባወቅነው እውቀት እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር የመገለጥ እውቀት የሚሰጠን እንድንኩራራበት ሳይሆን እርሱን አንድንታዘዘውና ለክብሩ እንድንኖር ነው፡፡ እግዚአብሄር የመገለጥ እውቀት ከመስጠቱ በፊት ባለን እውቀት ምን ያህል ታማኞች እንደሆንንና እንደታዘዘነው ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ፍላጎታችን እግዚአብሄርን ለመታዘዝ ካልሆነ እግዚአብሄር የመገለጥ እውቀት ለእኛ በመስጠት እውቀትን አያባክነውም፡፡
በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። ሉቃስ 8፡15
የመገለጥ እውቀት ለማግኘት ቃሉን ማሰላሰል ወሳኝ ነው፡፡ ለቃሉ የመጀመሪያውን ስፍራ መስጠታችን ቃሉን እንድናሰላስለው ያደርገናል፡፡ በዚህም በቃሉ ውስጥ ያለውን ጭማቂ ማግኘት እንችላለን፡፡  የአእምሮ እውቀት ከእኛ ጋር የሚዋሃደውና የሚጠቅመን ለቃሉ የመጀመሪያውን ስፍራ በህይወታችን ስንሰጥና ቃሉን እንደ ባጣ ቆየኝ ካላየነው ነው፡፡ የአእምሮ እውቀት ከእኛ ጋር በእምነት የሚዋሃደው ቃሉን ስናከብርና ቃሉን ሰናሰላስለው ነው፡፡
ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። ዕብራውያን 4፡2
የመገለጥ እወቀት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ፊት በመፈለግ ነው፡፡
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ኤፌሶን 1፡17
ፀሎት
እግዚአብሄር አባት ሆይ ስለህይወቴ አመሰግንሃለሁ፡፡ በምድር ላይ የሰጠኸኝን ስራ ሰርቼ ላከብርህ እፈልጋለሁ፡፡ ህይወቴ እንዲለወጥ በሁለንተናዬ ክርስቶስን እንድመስል እፈልጋለሁ፡፡  ብዙዎችን የሚነካ እና የሚደርስ ህይወት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ህይወቴን የሚለውጠውን ይህን የመገለጥ እውቀት እንድስትሰጠኝ እለምንሃለሁ፡፡ ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በጌታ በኢየሱስ ስም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #መገለጥ #እውቀት #ቅድሚያ #መታዘዝ #ርስት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ማሰላሰል #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ቅድሚያመስጠት #ጥሪ #ክብር #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አእምሮ #ሰላም #ማስተዋል #ልጅ

Sunday, September 24, 2017

የመገለጥ እውቀት እና የአእምሮ እውቀት

መፅሃፍ ቅዱስ ነፍስ ያለእውቅት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም ሲል የአእምሮ እውቀትን ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስለመፅሃፍ ቅዱስ ብዙ የአእምሮ እውቀት አላቸው ነገር ግን እውቀቱ ለህይወት ለውጥ ምንም አይጠቅማቸውም፡፡ የአእምሮ እውቀት በተግባር ሊተረጎም የማይችል ውስን እውቀት ነው፡፡ የአእምሮ እውቀት መፅሃፍ ቅዱስን እንደማንኛውም መፅሃፍ በመሸምደድ የሚገኝ እውቀት ነው፡፡ የአእምሮ እውቀት መፅሃፍ ቅዱስን እንደ ታሪክና ፊዚክስ በማጥናት የሚገኝ ውስን እውቀት ነው፡፡
የአእምሮ እውቀት ብቻ ነፃ አያወጣም፡፡ ነፃ የሚያወጣው የመገለጥ እወቀት ነው፡፡ ሰው ያለው የአእምሮ እውቀት ይሁን ወይም የመገለጥ እውቀት የሚፈተነው የሚያውቀውቅን በመተግበሩና ባለመተግበሩ ነው፡፡ የአእምሮ እውቀት ያለው ሰው የሚያውቀውን ማድረግ አይችልም፡፡ ስለአንድ ነገር ያለህ እውቀት ነገሩን እንድታደርገው ካላስቻለህ ያለህ የአእምሮ ብቻ እውቀት ነው፡፡
ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። ያዕቆብ 1፡22-25
የአእምሮ እውቀት ብቻ ያለው ሰው የመገለጥ እውቀት እንዳለው ሰው ልቡ ሰፊ አይደለም፡፡ የአእምሮ እውቀት ያለው ሰው ደካማን ከማገዝ ይልቅ ርህራሄ ስለሚጎድለው በደካማ ሰው ላይ በጭካኔ ይፈርዳል፡፡ የመገለጥ እውቀት ያለው ሰው ግን በቤተሰብነት ስሜት ሌሎችን ይረዳል ያነሳል፡፡ የአእምሮ እውቀት ብቻ ያለው ሰው ፊደሉን ብቻ ነው የሚያወቀው፡፡ የመገለጥ እውቀት ያለው ሰው የሚያስችለው ሃይል መንፈሱም ያውቀዋል፡፡
እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡6
የአእምሮ እውቀት ያለው ሰው ስለእግዚአብሄር ያለው እውቀት የሰሚ ሰሚ እውቀት አለው፡፡ የመገለጥ እውቀት ያለው ሰው እግዚአብሄር ራሱን ያውቀዋል፡፡ የአእምሮ ብቻ እውቀት ብቻ ያለው ሰው እውቀቱ የሚቆመው በአእምሮ ብቻ ነው እንጂ ከህይወቱ ጋር አልተዋሃደም፡፡
ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። ዕብራውያን 4፡2
የመገለጥ እውቀት ያለው ሰው ቃሉ በህይወቱ ተዋህዶታል፡፡ የአእምሮ እውቀት ብቻ ያለው ሰው የሚመራው በአእምሮው ብቻ ነው፡፡ የመገለጥ እውቀት ያለወ ሰው የሚመራው በልቡ መንፈስ ነው፡፡
እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም። እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። ዮሃንስ 5፡38-40
የአእምሮ እውቀት ያለው ሰው እውቀት ያለው ይመስለዋል ግን ያለው ተግባራዊ እውቀት ስላልሆነ ለተግባራዊው እውቀት ራሱን ይዘጋል፡፡ የአእምሮ እውቀት ያለው ሰው ያወቀ እየመሰለው ራሱን ያታልላል፡፡ የመገለጥ እውቀት ያለው ሰው እግዚአብሄርን በሙላት አገልግሎ ያልፋል፡፡
ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ዮሃንስ 6፡63
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #መገለጥ #እውቀት #ቅድሚያ #መታዘዝ #ርስት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ባለጠግነት #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ሃይል #ጥሪ #ክብር #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አእምሮ #ሰላም #ማስተዋል #ልጅ

Saturday, September 23, 2017

የእውቀት ማጣት አምስቱ ምልክቶች

እውቀት ብርሃን ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ቃል እውቀት ከሌላው ነገር ሁሉ ይጨላልምበታል፡፡ ሰው ትክክለኛው የመፀሃፍ ቅዱስ እውቀት ከሌላው ኑሮው በሙከራና በውድቀት የተሞላ ይሆናል፡፡
ሰው በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ሲሞላ የእግዚአብሄርን መንግስት በደስታ ማገልገል ይችላል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ሲሞላ ነገሮችን እንደ አመጣጣቸው መያዝ እና ማስተናገድ ይችላል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር እውቀት ሲሞላ ሁኔታዎችን ሁሉ በማስተዋል ተጋፍጦ ከነገሮች በላይ አሸናፊ ይሆናል፡፡
ሰው የቃሉ እውቀት ከሌላው ቅድሚያ መስጠትን አያውቅም፡፡
የህይወት ስኬት የሚለካው በህይወት ቅድሚያ መስጠትን በማወቅ ላይ ነው፡፡ ለምን ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ካወቅንና የህይወት ሃላፊነቶችን ሁሉ በቦታ በቦታቸው ካስቀመጥናቸው አሸናፊ መሆን እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል እውቀት የሌለው ሰው ግን የቱን ከየቱ እንደሚያደርገው ስለማያውቅ ሃይሉን በማይገባ ጥቃቅን ነገር ላይ ያባክንና ሃይሉን ማጥፋት ባለበት ነገር ላይ የሚገባውን ሳያደርግ ይቀራል፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
እውቀት የሌለው ሰው ለምን እንደተጠራ አያውቅም፡፡
እውቀት የሌለው ሰው እግዚአብሄር ለምን እንደጠራው ስለማይረዳ ሁሉም ውስጥ በመግባት ጉልበሩን ሲጨርስ ይኖራል፡፡ የሰው ጉልበት ውስን ነው፡፡ ሰው ሁሉንም ነገር ለማድረግ ከሞከረ ምንም ነገር ሳያደርግ ይቀራል፡፡ የቃሉ አውቀት የሚያስፈልገው እግዚአብሄር ለምን እንደጠራን እንድናውቅ ነው፡፡ ለምን እንደተጠራ የሚያውቅ ሰው በአትኩሮት የህይወት ሩጫን በሚገባ መሮጥ እና መፈፀም ይችላል፡፡ ለምን እንደተጠራ የሚያውቅ ሰው ግቡን እስኪመታ አያርፍም፡፡ የቃሉ እውቀት ያለው ሰው አላማውን ከግብ ሲያደርሷ ያርፋል በህይወቱም ይደሰታል፡፡   
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን . . . ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡17-19
መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡7
እውቀት የጎደለው ሰው በእግዚአብሄር ፊት ያለውን የክብር ደረጃ አይረዳም፡፡
በእግዚአብሄር ያለንን ቦታ ማወቃችን ካለፉክክር ሌሎችን እንድናገለግል ይረዳናል፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለውን ቦታ ያልተረዳ ሰው እግዚአብሄር አክብሮት እያለ ቦታውን ከፍ ለማድርግ ህይወቱን በከንቱ ይፈጃል፡፡ በእግዚአብሄር ያለውን የክብር ቦታ የማያውቅ ሰው ማንንም ማገልገል ሳይችል በምስኪንነት አስተሳሰብ ራሱን ብቻ በማገልገል ላይ ተጠምዶ ራሱን ያባክናል፡፡ ኢየሱስ በምድር ላይ ትሁት ሆኖ ለእግዚአብሄር አብ እስከሞት ድረስ በሚገባ እንዲታዘዝ ያደረገው ማንነቱን ማወቁ ነው፡፡     
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ ዮሃንስ 13፡3-4
እውቀት የጎደለው ሃብታም ሰው ሃብታም ለመሆን በከንቱ ይጥራል፡፡
እውቀት የሌላው ሰው በሁሉ ባለጠጋ ተደርጎ ሳለ ሃብታም ለመሆን በሚደረግ ጥረት በአልባሌ ነገር ህይወቱን ይፈጃል፡፡ ስለ እረኛው በቂ እውቀት የሌለው ሰው ያጣው ነገር እንዳለ ስለሚሰማው ያንን ነገር ለማሟላት እግዚአብሄር የሰጠውን የህይወት ሃላፊነት ይተዋል፡፡ እውቀት የጎደለው ሰው ያለውን የርስት ክብር ስለማይረዳ የሚያልፍ የምድር ርስት ለማከማቸት ቅድሚያ በመስጠት ህይወቱን ያባክናል፡፡
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ . . . በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን . . . ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡17-19
እውቀት የጎደለው ሰው በተሰጠው ሃይል መጠቀም ያቅተዋል፡፡
ኢየሱስን አዳኙ አድርጎ የተቀበለ ሰው ሁሉ የእግዚአብሄር ታላቅ ሃይል በውስጡ ይኖራል፡፡ ሰው ግን በውስጡ ያለውን ሃይል ካልተረዳ በድካምና በሽንፈት ሊኖር ይችላል፡፡ እግዚአብሄር የሁሉ አሸናፊ አድርጎት እያለ ካላወቀ በሁሉ ተሸንፎ ይኖራል፡፡
የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ . . . ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡17-19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #እውቀት #ቅድሚያ #መታዘዝ #ርስት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ባለጠግነት #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ሃይል #ጥሪ #ክብር #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አእምሮ #ሰላም #ማስተዋል #ልጅ

Friday, September 22, 2017

የእውቀት ማጣት አደጋ

ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ምሳሌ 192
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለልንን የሃጢያት ዋጋ ለእኔ ነው ብለን ስንቀበል እግዚአብሄር ይቀበለናል፡፡ እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ የመስቀል ስራ ስንቀበል ዳግመኛ እንወለዳለን፡፡ ሰው ከእናትና አባቱ በስጋ ሲወለድ ወደዚህ ምድር ይገባል፡፡ ሰው ደግሞ የእግዚአብሄርን ቃል ሰምቶ ሲቀበል ዳግመኛ ይወለዳል፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም። ዮሃንስ 1፡12-13
በክርስቶስ የሆነ ሰው አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ ሰው ዳግመኛ ሲወለድ መንፈሱ አዲስ ነው፡፡
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17
ሰው አዲስ ፍጥረት ቢሆንም በነፍሱ ውስጥ ለዘመናት የተቀመጠ አለማዊ እውቀት ብንን ብሎ አይጠፋም፡፡ ዳግመኛ የተወለደው ሰው አሮጌውን የአለም እውቀት በአዲሱ የእግዚአብሄር ቃል እውቀት መተካት ይገባዋል፡፡ ዳግም የተወለደው ሰው ነፍስ አለማዊ እውቀት በቃሉ እውቀት ካልተተካ ሰው ዳግመኛ ተወልዶ እንደ አለማዊ ሰው በሃጢያት እና በሽንፈት ሊኖር ይችላል፡፡ ነፍስ ካለቃሉ እውቀት ከሆነች በምታውቀው በአለማዊ አሰራር እውቀት ብቻ ስለምትኖር መለወጥ ያቅታታል፡፡ ነፍስ በእግዚአብሔር ቃል እውቀት ከአለማዊ እውቀት መዳን አለባት፡፡
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ 1፡21
ነፍስ የእግዚአብሄር ቃል እውቀት ከሌላት ለእግዚአብሄር መኖር ያቅታታል፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት አሰራርና የአለም አሰራር እጅግ ስለሚለያይ ነፍስ የእግዚአብሄር ቃል እውቀት ከሌላት በምድር ላይ የተጠራችበትን አላማ መፈፀም ያቅታታል፡፡  
ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ምሳሌ 19፡2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #እውቀት #መልካም #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አእምሮ #ሰላም #ማስተዋል #ልጅ

Thursday, September 21, 2017

በእውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ

የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3
በመጀመሪያም ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ የሰው የእግዚአብሄር መልክ እና አምሳል የጠፋው ሰው በሃጢያት ሲወድቅ ነው፡፡ በኢየሱስ የሃጢያታችን እዳ የተከፈለው ወደዚህ ወደጥንቱ የመለኮት ህብረት እንድንመለስ ነው፡፡ እግዚአብሄር በመለኮት ክብር ጠርቶናል፡፡ እግዚአብሄር በዚህ በታላቅ ክብር ቢጠራንም እውቀቱ ከሌላን እንደ ተራ ሰው ልንኖር እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር በመለኮት ሃይል ቢጠራንም እንደ ደካማ ተሸናፊ ልንሆን እንችላለን፡፡ ስለዚህ ነው እውቀት ወሳኝ የሆነው፡፡
እውቀታችን ባደገ ቁጥር ፀጋ ይበዛልናል፡፡
ህይወትን በሚገባ ለመያዝ ሃይል ይጠይቃል፡፡ አንድ ነገርን ለእግዚአብሄር ለማድረግ የእግዚአብሄር የሚያስችል ሃይል ወሳኝ ነው፡፡ ኢየሱስን ለተቀበለ ሰው ሁሉ የሚያስችል ሃይል የእግዚአብሄር ፀጋ ተዘጋጅቶዋል፡፡ በዚህ ፀጋ ለመኖር በዚህ የሚያስችል ሃይል ተጠቃሚ ለመሆንና ለእግዚአብሄር ለመኖርና እግዚአብሄርን ለማገልገል እውቀት ያስፈልገናል፡፡ እውቀታችን ሲበዛ በህይወታችን የሚሰራው ፀጋ ይበዛል፡፡ እውቀታችን ሲበዛ ለህይወትና እግዚአብሄርን ለመምሰል የተሰጠንን ተረድተን በዚያ መብት መመላለስ እንጀምራለን፡፡ እውቀታችን በበዛ መጠን በህይወታችን የሚፈሰው ፀጋ ይበዛል፡፡ እውቀታችን በበዛ መጠን በህይወታችን ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ ፈፅመን ማለፍ እንችላለን፡፡
እውቀታችን ባደገ ቁጠር ሰላማችን ይበዛልናል፡፡
አሁን ያለን የሰላም መጠን ያለንን የእውቀት መጠን ያሳያል፡፡ እግዚአብሄር ለህይወትና እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚያስፈልገንን ሁሉ ቢሰጠንም ካለን እውቀት መጠን በላይ ሰላም ሊኖረን አይችልም፡፡ እውቀታችን ሲጨምር ሰላማችን ይጨምራል፡፡ እውቀታችን ሲበዛ ሰላማችን ይበዛል፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2 ጴጥሮስ 12-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ፀጋ #መልካም #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አእምሮ #ሰላም #ማስተዋል #ልጅ

Wednesday, September 20, 2017

ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም

ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም
ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ምሳሌ 19፡2
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራልንን የደህነት ስራ በማመን ኢየሱስን ከተቀበልን በኋላ በክርስቶስ እንዴት እንደምንኖር ማወቅ ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡ ሰው በቃሉ እውቀት ነፍሱን ካላደሰ ጌታን ተቀብሎ እንዳልተቀበለ ሰው በአሮጌ ማንነቱ ሊኖር ይችላል፡፡
ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ኤፌሶን 4፡22-24
ሰው በሃጢያት ምክኒያት አስተሳሰቡ ተበላሽቶዋል፡፡ ሰው ኢየሱስን ተቀብሎ በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ነፍሱን ካላዳናት በስተቀር የሰይጣን እስረኛ ሆና ልትቆይ ትችላለች፡፡ ሰው ኢየሱስን ተቀብሎ በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ካልታጠቀ የእግዚአብሄርን አላማ በህይወቱ ሊፈፅም አይችልም፡፡ ሰው ከልጅነቱ በተለያየ መንገድ የሰማው እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነ የአለም አሰራር በነፍሱ ውስጥ አለ፡፡ ሰው ዳግመኛ ከእግዚአብሄር ቃል ተወልዶ ወደ እግዚአብሄ ምንግስት ሲገባ በእግዚአብሄር ቃል ነፍሱን ማደስ አለበት፡፡ ነፍሱን በእግዚአብሄር ቃል የሚያድስ ሰው ብቻ ነው ነፍሱን ከአለማዊ ክፉ አስተሳሰብና ከሰይጣን ጥቃት የሚያድናት፡፡
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ 1፡21
ሰው በክርስቶስ ከእግዚአብሄር ጋር ታርቆ እንደባይተዋር ሊኖር ይችላል፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ እውቀት ከሌላው በሽንፈት ሊኖር ይችላል፡፡ ሰው በክርስቶስ ወደ እግዚአብሄር መንግስት ተቀላቅሎ ሳለ የእግዚአብሄር ቃል እውቀት ከሌለው የእግዚአብሄርን አላማ በህይወቱ ሳይፈጽም እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ኖሮ ሊያልፍ ይችላል፡፡
ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ። መዝሙር 49፡12
ኢየሱስን ለተቀበለ ሰው በክርስቶስ ታላቅ አርነት ተዘጋጅቶለት እያለ የቃሉ እውቀት ከሌለው በእስራት ሊኖር ይችላል፡፡ የኢየሱስን አዳኝነት መቀበል ለመዳን የመጀመሪያው ደረጃ ቢሆንም ሰው እውነትን አውቆ ካልኖረበት ነፃ መውጣት በፍፁም አይችልም፡፡
ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፦ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። ዮሃንስ 8፡21-32
እግዚአብሄር በክርስቶስ ሁሉን ስላዘጋጀልን ከእኛ የሚጠበቀው እግዚአብሄርንና ክርስቶስን በማወቅ ፀጋና ሰላም እንዲበዛል ነው፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ንስሃ #መልካም #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #አእምሮ #ሰላም #ማስተዋል #ልጅ