Popular Posts

Wednesday, May 30, 2018

የእምነት ማጣት አስራ አንዱ ምልክቶች

የእግዚአብሄር መንግስት የመንፈስ መንግስት ነው፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር የምናደርገው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም፡፡ ለክርስትና ህይወት እምነት ወሳኝ ነው፡፡
እግዚአብሄር የሚሰራው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚጠቀመው እምነት ያለውን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር ለመስራት እምነት ያለውን ሰው ይፈልጋል፡፡ ካለእምነት እግዚአብሄርን  ማስደሰት አይቻለም፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ጊዜ ምንም ታላቅ ሃይል ቢኖረውም ሰዎችን ለመርዳት ቢፈልግም እምነት ላልነበራቸው ሰዎች ምንም ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡
በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም። ማቴዎስ 13፡58
እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ ስለ ምን ትፈራላችሁ? ማቴዎስ 8:26
ኢየሱስም መልሶ፦ የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ። ማቴዎስ 17፡17
ሰው እግዚአብሄርን አላምንም ብሎ ላይናገር ይችላል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄርን የማያምን ሰው ስራው ይናገራል፡፡ እምነት ያለው ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች እንዳሉ ሁሉ የማያምን ሰው የሚያሳያቸው ምልከቶች አሉ፡፡
1.      የማያምን ሰው ጠማማ ነው
የማያምን ሰው ቅን ሊሆን አይችልም፡፡ የማያምን ሰው የዋህ ሊሆን አይችልም፡፡ የሚያምን ሰው የእግዚአብሄርን መንገድ ስለማይከተል የራሱን የጠማማነትን መንገድ ይከተላል፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ። ማቴዎስ 17፡17
2.     የማያምን ሰው ኩራተኛ ሰው ነው
የሚያምን ሰው የሚታወቀው በትህትናው ሲሆን የማያምን ሰው የሚታወቀው በትእቢቱ ነው፡፡ የማያምን ሰው በእግዚአብሄር ሳይሆን በራሱ ይተማመናል፡፡ የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ላይ ይደገፋል፡፡
እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ዕንባቆም 2፡4
3.     የማያምን ሰው ፈሪ ነው
የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይደፍራል የማያምን ሰው ግን ፍርሃት አለበት፡፡ በእግዚአብሄር የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ልቡ ስለሚጠበቅ ያርፋል፡፡ የማያምን ሰው ግን ልቡ በምንም ላይ ስለማያርፍ ይፈራል፡፡ የማያምን ሰው የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያደርገው ከፍቅር ድፍረት ሳይሆን ከፍርሃት ነው፡፡ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፣ ስለ ምን ትፈራላችሁ? ማቴዎስ 8:26
4.     የማያምን ሰው ፍቅር ይጎድለዋል
የሚያምን ሰው ፍቅር የሆነውን እግዚአብሄርን ስለሚያምን በፍቅር ለመኖር አይፈራም፡፡ የማምን ሰው ግን የእግዚአብሄርን ፍቅር ስለማያምን እና ስለማይቀበል ራሱም በፍቅር ለመኖር ራሱን አይሰጥም፡፡ የማምን ሰው ከፍቅር ይልቅ ሌላ የራሱን መንገድ ይፈልጋል፡፡
እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡13
5.     የማያምን ሰው በምድር ጥበብ ይመላለሳል
ከእግዚአብሄር የሆነው ንፅህ ጥበብ የሚገኘው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሄርን የማያምን ሰው ይህን ንፁህ ጥበብ በምድራዊ ተንኮል ይለውጠዋል፡፡
ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ያዕቆብ 3፡14-16
6.     የማያምን ሰው ይቸኩላል
የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ጊዜ ይተማመናል፡፡ የሚያምን ሰው የእግዚአብሄርን እርምጃ ይታገሳል፡፡ የማያምን ሰው ግን የእግዚአብሄርን ጊዜ ስለማያምነው ይቸኩላል፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 13፡11
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም።ምሳሌ 28፡20
7.     የማያምን ሰው ከሰው ጋር ይጣላል፡፡
የማያምን ሰው በረከቱን የያዘው ሰው ስለሚመስለው ከሰው ጋር ይጣላል፡፡ የማያምን ሰው ከሰው ስለሚጠብቅ በሰው ይሰናከላል፡፡ የመያምን ሰው መንፈሳዊውን አለም በእምነት ስለማያይ የጦር እቃው ስጋዊ ብቻ ነው፡፡ የሚያምን ሰው ግን ከእግዚአብሄር ስለሚጠብቅ በሰው አይሰናከልም፡፡ የሚያምን ሰው ከሰው ባሻገር መንፈሳዊውን አለም ስለሚያይ የጦር መሳሪያው ስጋዊ አይደለም፡፡  
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡1-3
በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ 2 ቆሮንቶስ 10፡3-4
8.     የማያምን ሰው በጥበቡ በሃይሉና በብልጥግናው ይመካል
የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር ይመካል፡፡ የማያምን ሰው ግን የእግዚአብሄር ሃብት የእኔ ሃብት ነው ስለማይል መሰብሰብ ማከማቸት ይፈልጋል፡፡ የሚያምን ሰው እግዚአብሄር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም ስለሚል ማግበስበስ አያስፈልገውም፡፡ የማያምን ሰው ግን እረኛውን ስለማያምን እረኛ የሚያደርገው ጥበቡን ሃይሉንና ባለጠግነቱን ነው፡፡ የሚያምን ሰው የነገሮች ሁሉ ቁልፍ እግዚአብሄር ጋር እንጂ ጥበብ ፣ ሃይልና ባለጠግነት ጋር እንዳይደለ ያውቃል፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርሚያስ 9፡23-24
9.     የማያምን ሰው ይጨነቃል
የሚያምን ሰው የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቅን ሲፈልግ እግዚአብሄር በምድር የሚያስፈልገው እንደሚያሟላለት ስለሚያምን አይጨነቅም፡፡ እግዚአብሄርን የማያምን ሰው ግን ስለመሰረታዊ ፍላጎቱ በመጨነቅ እግዚአብሄር ይጨመርላችኋል ያለውን በመፈልግ ህይወቱን ያባክናል፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31፣33
10.    የማያምን ሰው ያጉረመርማል
የሚያምን ሰው በእግዚአብሄር መልካምነት ስለሚተማመን ሁልጊዜ በእግዚአብሄር ደስ ይለዋል፡፡ የማያምን ሰው ደስታው በሁኔታዎች ብቻ ስለሆነ ያጉረመርማል፡፡ የሚያምን ሰው እግዚአብሄርን መልካምነት ስለሚያይ በእግዚአብሄር ላይ ጥያቄ የለውም፡፡
ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጐርጕሩ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡10
11.     የማያምን ሰው ይመኛል
የሚያምን ሰው ምንም እንዳልጎደለው ራሱን ያማጥናል፡፡ የሚያምን ሰው ጉድለቱን በሚሸፍን ድካምን በሚሞላ የእግዚአብሄር ፀጋ ስለሚተማመን አይመኝም፡፡ የማያምን ሰው ግን ሁሌ እግዚአብሄር ያልሰጠውን ነገር ይመኛል፡፡ የሚያምን ሰው ራሱን በሁኔታዎች ሁሉ ራሱን ያማጥናል፡፡
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡11-13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጭንቀት #ፍርሃት #ፍቅር #ተንኮል #ጠማማነት #ኩራት #ቅን #እምነት #ተንኮል #ምኞት #ሰላም #ኢየሱስ #ጌታ #ሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment