Popular Posts

Tuesday, January 31, 2017

ከአሸናፊዎች እንበልጣለን

በአለም ላይ ብዙ ሃያላንና አሸናፊዎች አሉ፡፡ አለም ሰዎችን በሚያንበረክኩ ብዙ አዋራጆች የተሞላች ነች፡፡ በአለማችን ደካሞች በሃያላን ሲሸነፉ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ሰዎች በአሸናፊዎች በየእለቱ ይሸነፋሉ፡፡
ሌሎችን ተሸነፉ ማለት እኛ እንሸነፋለን ማለት አይደለም፡፡ ለእኛ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ሽንፈት የእኛ እጣ ፋንታ አይደለም፡፡ አሸናፊነት እጣ ፈንታችን ነው፡፡ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ከእኛ ጋር ሆኖ ፣ ለእኛ ሆኖ እና በእኛ ውስጥ ሆኖ ከማሸነፍ ውጭ ምንም ሊታሰብ አይችልም፡፡   
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ። ሮሜ 8፡37-39
እርግጥ ነው እግዚአብሄር ለአሸናፊነት ጠርቶናል ስንል በአለም ላይ ያለውን ሁኔታ እየካድን አይደለም፡፡ እኛ ክርስቶስን የምንከተል የበላይ ነን የምንለው በራሳችን ጉልበት ሳይሆን በእግዚአብሄር ስለተወደድን ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በራሳችን ጥረትና መንገድ ሳይሆን በወደደን በእርሱ በክርስቶስ ነው፡፡ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን ስንል እስከመጨረሻው በሚያፀናን በክርስቶስ ፍቅር ተመክተን ነው፡፡
በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ ፊልጵስዩስ 1፡6
እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። ዮሐንስ 10፡28
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው አለምን ያሸነፈውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለምንከተል ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞቱ በሻረው በኢየሱስ ነፃ ስለወጣን ነው፡፡
እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ ዕብራውያን 2፡14-15
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው የሰይጣን ሃይላት ሁሉ በሻረው በክርስቶስ ስለተሞላን ነው፡፡ ከአሸናፊዎች የምንበልጠው ክርስቶስ የአሸናፊውን ስልጣን ስለገፈፈው ነው፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2፡15
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ የሚንበረከኩለት ክርስቶስ ጌታችን ስለሆነ ነው፡፡  
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ ፊልጵስዩስ 2፡9-10
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው የሰይጣን ሃይላት ሁሉ በሻረው በክርስቶስ ስለተሞላን ነው፡፡
ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ቆላስይስ 2፡10
ከአሸናፊዎች የምንበልጠው አሸናፊውን አለም ባሸነፈው በክርስቶስ ስለምንታመን ነው፡፡
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ሃያል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አሸናፊ #አለቅነት #ስልጣናት #ስልጣን #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Sunday, January 29, 2017

ቅዱሳት መፅሃፍት


የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16-17
ለተሳካ የክርስትና ህይወት የእግዚአብሄር ቃል አስፈላጊነት ወሳኝ ነው፡፡ ካለ እግዚአብሄር ቃል እውነተኛ ስኬት የሚታሰብም አይደለም፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ እውቀት የሚገኝ ስኬት አስተማማኝና ዘለቄታዊ ስኬት ነው፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄር መንፈስ ያለበት መፅሃፍ
መፅሃፍ ቅዱስ የሰው ሃሳብ አይደለም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርን ልብ ማሳያ መነፅር ነው፡፡
መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10
እግዚአብሄር ሰውን ለክብሩ እንደ መፍጠሩ መጠን ሰው እግዚአብሄርን አስከብሮ የሚያልፈው በእግዚአብሄር መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ሊያስከብርና ሊያስደስት አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰው ልጅን የሚያስተዳደረው በራሱ መንገድ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን መንገድ መረዳት የምንችለውና የቃልኪዳኑን ህግና ስርአት የምንረዳውና የምንከተለው ከመፅሃፍ ቅዱስ ነው፡፡
ለትምህርት ይጠቅማል
እውነተኛ ትምህርት የሚገኘው ከመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ የጥበብ መጀመሪያ የሆነውን እግዚአብሄርን ከመፍራት ጀምሮ እውነተኛ እወቀትን የምናገኘው በመፅሃፍ ቅዱስ ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሄርን እውነተኛ እውቀትን ያካልፋል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ በህይወት እጅግ ወሳኝ ስለሆኑ ስለ እግዚአብሄር ፣ ስለሰው ፣ ስለሰይጣን ፣ ስለምድር ፣ ስለአለም ፣ ስለሃጢያት ፣ ስለስኬት ፣ ስለዘላለማዊ ህይወት ስለመሳሰሉት ሁሉ ያስተምራል፡፡
ለተግሣጽ ይጠቅማል
እግዚአብሄር ማንንም አይፈራም፡፡ እግዚአብሄ የሚፈልገውን በመፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ ፅፎታል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ መልካም የሚያደርግን ሰው ያበረታታል እንዲሁም ክፉ የሚያደርግን ሰው ይገስፃል፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የማያደርጉትን እንደልባቸው የሚኖሩትን ሰዎች ይገስፃል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ እንደመስታወት ተመስሏል፡፡ መስታወት ያለንበትን ሁኔታ እንዳለን የሚያሳየን  መፅሃፍ ቅዱስ መልካምና ክፉዋችንን በግልፅ በማሳየት ይገስፀናል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ተመለሱ ፣ አይጠቅማችሁም ፣ ይጎዳችኋል ብሎ የተሳሳቱ ሰዎችን ይገስፃል፡፡
ልብንም ለማቅናት ይጠቅማል
ልብ በጣም ክፉና አስቸጋሪ በጥንቃቄና በትጋት ልንይዘው የሚገባው ነገር ነው፡፡ ልብ ከተጣመመ ሰው ይጣመማል ልብ ከቀና ሰው ይቀናል፡፡ ብዙ መፅሃፍት ስለስጋ ተናግረዋል ስለልብ ትክክለኛውን እውቀት የምናገኝበት እንደመፅፍ ቅዱስ ያለ መፅሃፍ ግን የለም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ የልባችንን ሁኔታ ፍንትው አድርጎ አሳይቶ ይመልሰናል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ማንም ሳይንቲስት ሊደርስበት የማይችለውን ልባችንን ይደርሳል፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ማንም ሊያደርገው የማይችለው መንፈስና ነፍስን እስኪለይ ድረስ ይወጋል የልብንም ስሜትና ሃሳብ ይመረምራል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራውያን 4፡12
በጽድቅም ላለው ምክር
የመፅሃፍ ቅዱስን ምክር ተቀብሎ የሚሳሳት የለም፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ በእውነት ይመክራል፡፡ የእግዚአብሄን የልብ ሃሳብ የምናገኘው በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ነው፡፡ የመፅሃፍ ቅዱስ ምክር የማይረባውን እንዳንከተል የሚጠቅመውን አንድንይዝ ይመክራል፡፡ ከመፅሃፍ ቅዱስ ውጭ ፅድቅን ከፈለግን እንሳሳታለን፡፡
እግዚአብሄርን በሙላት የምንከተል ፍፁማን ሰዎች የሚያደርግን የቅዱሳት መፅሃፍት እውቀት ነው፡፡
ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15-17

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #ምክር #ቃልኪዳን #ተግሳፅ #ትምህርት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቅዱሳትመፅሃፍት  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የእግዚአብሄርመንፈስ #የእግዚአብሄርቃል

ያንቃል

የእግዚአብሄር ቃል የሚሰራ ነው፡፡  
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራውያን 4፡12
እምነትም ደግሞ የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት ነው፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
ሰው የሰማው ቃል በህይወቱ ፍሬ እንዳያፈራ የሚያግደው የኑሮ ሃሳብና የባለጠግነት ምኞት ነው፡፡
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። ማቴዎስ 13፥22
በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፥ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። ማርቆስ 4፡18-19
የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን እነዳይታነቅና ፍሬ ቢስ እንዳይሆን ነው መኝሃፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ እንዳንጨነቅ የሚያዘን፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። ፊልጵስዩስ 4፡6
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። ማቴዎስ 6፡33-34
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #አትጨነቁ #ቃልኪዳን #ቃሉንያንቃለ #ፍሬ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አትጨነቁ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Friday, January 27, 2017

የቃልኪዳን ስምረት

ቃልኪዳን በአለም ላይ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ሃሳቦች አንዱ ነው፡፡ ብዙ ወሳኝ ነገሮች የሚደረጉት በቃልኪዳን ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት በአለም ላይ ያለን ሃብትና እምቅ ጉልበት አለመረዳት ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት አላማን መሳት ነው፡፡ ቃልኪዳንን አለመረዳት ፍሬቢስ መሆን ነው፡፡
ቃልኪዳን በሁለት ወገኖች መካካል የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ አንዱ ወገን ለሌላው ወገን የሚያደርግለት ነገር ሌላኛውም እንዲሁ ለሌላው የሚያድርገለት ነገር አለ፡፡
እኛ በብዙ ነገሮች የተወሰንን ስለሆንን ሁሉንም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ ለወሳኝ ነገሮች  የቃልኪዳን አጋር ያስፈልገናል፡፡ ቃልኪዳን ደግሞ በራስ ድርሻ ላይ ብቻ ማተኮርን ይጠይቃል፡፡
በአለም ላይ ያለው ችግር በራስ ሃላፊነት ላይ ያለማተኮር ችግር ነው፡፡ በአለም ላይ ያለው ግራ መጋባት የመጣው የስራ ክፍፍልን ካለመረዳትና የራስን ድርሻ ብቻ ፈፅሞ ካለማረፍ የሚመነጭ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ህብረትን ፈልጎ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት እያደረገ ምድርን የሚያስተዳድርለትን የሚረዳውና የሚግባባው ፍጥረት ፈልጎ ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ ዘፍጥረት 1  
ሰው በሃጢያትም ከወደቀ በኋላ እግዚአብሄር የሰው ልጆችን ለመድረስና አላማውን በምድር ላይ ለማስፈፀም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እግዚአብሄር በዘመናት መካከል ከአብርሃም ፣ ከኖህ ፣ ከእስራኤል ህዝብ ጋር ቃልኪዳን ሲያደርግ ነበር፡፡
አሁንም በዚህ ዘመን እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ላይ መስዋእትነት ከእኛ ጋር ኪዳን ገብቷል፡፡ እግዚአብሄር መንግስቱን የሚሰራለትና የሚያስፋፋለት ሰው ፈልጎ ከእኛ ጋር ቃልኪዳን ገብቷል፡፡
ነገር ግን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ ሰዎችን ግራ የሚያጋባቸው የቃል ኪዳን የስራ ድርሻ ነው፡፡ አሁንም በዘመናችን ሰዎች እግዚአብሄር ወዳየላቸው የህይወት ከፍታ እንዳይገቡ የሚያግዳቸው የቃልኪዳንን ድርሻን አለመረዳት ነው፡፡
ለምሳሌ ሰዎች የሚበላና የሚጠጣ የሚለበስ በመፈለግ ህይወታቸውን የሚያባክኑት የእግዚአብሄርን አቅርቦት የቃልኪዳን ድርሻ ባለመረዳት ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
በዚህ የቃል ኪዳን ስምምነት መሰረት የሰው ድርሻ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ በእግዚአብሄ ፊት ትክክለኛ ነገር ማድረጉን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሰው ድርሻ እግዚአብሄን በምድር መወከል ነው፡፡ የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄር መንግስት ደህንነት ማሰብ ነው፡፡ የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄር መንግስት ማሸነፍና መስፋፋት መስራት ነው፡፡  የሰው ድርሻ የእግዚአብሄን ቤተክርስትያን በጎነት መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ የመንግስቱን አባላት መንከባከብና ማስነሳት ነው፡፡
እግዚአብሄር መንፈስ ስለሆነና በስጋ ውስጥ ስለማይኖር በምድር ላይ ይህንን እንድናደርግለት የጠራን እኛን ነው፡፡ እኛ ይህንን ማድረግ እንችላል፡፡ በዚህ ማድረግ በምንችለው ድርሻ ላይ ብቻ ብናተኩር ውጤታማ እንሆናለን እግዚአብሄርንም በሙላት አገልግለን እናልፋለን፡፡    
የእግዚአብሄ ድርሻ ደግሞ ለሰው የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር ማሟላት ነው፡፡ ይህንን እንዲህ አድርገው ብሎ የሚመክረው የለም፡፡ ይህን ደግሞ እርሱ ያደርገዋል፡፡
አሁን ሰው የተሰጠውን ይህንን በቂ ሃላፊነት ጥሎ እግዚአብሄር እንዴት እንደሚንካከበው ቁጭ ብሎ ቢጨነቅ ከንቱ ነው፡፡ ሰው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር ማድረግ አይችልምና እግዚአብሄር የሰጠውን መንግቱንና ፅድቁን የመፈለግ ሃላፊነቱን እየጣለ ነው፡፡ እግዚአብሄር እኔን በትክክል ይይዘኝ ይሆን ብሎ ሲፈራ ድርሻውን መወጣት ያቅተዋል፡፡ እግዚአብሄር አያያዙን ያውቅበት ይሆን ብሎ ሰው ቢያወጣና ቢያወርድ ህይወቱን እያባከነ ነው፡፡
ሰው በህይወቱ ይህን የቃል ኪዳን ሃላፊነት ካልተረዳና በራሱ ሃላፊነት ብቻ ላይ ካላተኮረ የእስራኤል ህዝብ የሴይርን ተራራ እንደዞሩት ይዞራል እንጂ እግዚአብሄር ወዳሰበለት ግብ አይደርስም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #አትጨነቁ #ቃልኪዳን #መታመን #መደገፍ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Thursday, January 26, 2017

የዘላለም አምላክ

አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳይያስ 40፡28
አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሄ ፊት የምናገራቸው ነገሮች እግዚአብሄርን የማያከብሩ አላዋቂነታችንን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሄር በላይ ያወቅን ይመስለናል፡፡ ለእግዚአብሄር ምክር መለገስ የምንችል ይመስለናል፡፡ ስንደክም እግዚአብሄርም አብሮን የሚደክም የቆሎ ጓደኛችን ይመስለናል፡፡ እግዚአብሄር አባታችንም ቢሆን የቆሎ ጓደኛችን ግን አይደለም፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ግንኙነት በጥንቃቄ ልናደርገው ይገባል፡፡ አክብሮት የጎደላቸውና ንግግሮችና ዝንባሌዎች ከህይወታችን ልናስወግድና በትህትና ከእግዚአብሄር ጋር ልንኖር ይገባል፡፡  
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? . . . ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ሚክያስ 6፡8
ልትሰማና ልታውቅ ይገባል ይላል እግዚአብሄር፡፡ የዚህ ሁሉ ንግግር ምንጩ አለማወቅ ነው፡፡
እግዚአብሄ የዘላለም አምላክ ነው
አግዚአብሄር ተለማማጅ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አንተን እንዴት እንደሚመራ ፣ አንተን እንዴት እንደሚይዝህና እንደሚንከባከብህ ፣ አንተን እንዴት እንደሚያስተዳድርህ ከጊዜ ወደጊዜ ልምድን እያካበተ የሚሄድ መሪ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከዘላለም የነበረ መሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከዘመናት ጀምሮ ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ ነው፡፡
እግዚአብሄር እንዴት ሊይዝህ እንደሚገባው ለመምከር ከዳዳህ እባክህ አፍህን አታበላሽ፡፡ እግዚአብሄርን አትመክረውም፡፡
የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ሮሜ 11፡34-35
እግዚአብሄር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው
እግዚአብሄር ሃያል ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ቻይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያለውን የሃይል መጠን ተረድተን አንጨርሰውም፡፡ እግዚአብሄር በምድር ውስጥ እንዳንድ ነገሮችን ያገኘ ሳይንቲስት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር በቀናት የፈጠራቸውን ነገሮች የአለም ምርጥ ሳይንቲስቶች በክፍለ ዘመናት ሁሉ ተማራምረው ተመራምረው ተመራምረው አልጨረሱትም፡፡  
የእግዚአብሄር ማስተዋል አይመረመርም
እግዚአብሄርን ተረድተን ለመጨረስ መሞከር የውድቀት መጀመሪያ ነው፡፡ ማድረግ የምንችለው የተሻለው ነገር በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ማረፍ ብልህነት ነው፡፡ በእግዚአብሄር በጎነት ላይ መደገፍ ጥበብ ነው፡፡ የሚያስጨንቀንን በእርሱ ላይ መጣል የአባት ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ኤርምያስ 29፡11-13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሄር #የዘላለምአምላክ #የምድርዳርቻ #መታመን #መደገፍ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, January 25, 2017

መሳጭ ታሪክ

ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤
አንድ የሰማሁትን ልቤን የነካኝን ታሪክ ላካፍላችሁ፡፡
በክርስትያን ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ልጅ ወደ ታላቅ እህቱ ይሄድና እግዚአብሄርን ማየት እፈልጋለሁ ይላታል፡፡ እህቱም አይደለም እኮ እግዚአብሄር አይታይም ብላ ትመልስለታለች፡፡ በመልሱ ያልረካው ልጅ ወደ እናቱ ጋር ይሄድና እማዬ  እንዴት ነው እግዚአብሄርን ላየው የምችለው ይላታል፡፡ እሱዋም እግዚአብሄር የሚታየው በቃሉ ነው ብላ ትመልስለታለች፡፡ በእህቱም በእናቱም መልስ ያልረካው ልጅ በእርጅና ምክኒያት አይናቸው ወደፈዘዘ ወደአያቱ ይቀርብና አያቴ እግዚአብሄርን ማየት እፈልጋለሁ ብዬ እህቴን ብጠይቃት እግዚአብሄር አይታይም አለችኝ እናቴ ደግሞ እግዚአብሄር በቃሉ ነው እንጂ አይታይም አለችኝ፡፡ ፊታቸው በደስታ የበራው አያቱ ልጄ አሁን አሁንማ ከእርሱ በስተቀር ሌላ ምንም ነገርም አልታይም ብሎኛል አሉት ይባላል፡፡
በእነዚህ መካከል የነበረው ልዩነት የእይታ ልዩነት ነው፡፡ ለአያትየው መንፈሳዊው አለም ፍንትው ብሎ ከመታየቱ የተነሳ የምድራዊው ነገር ጨልሞባቸዋል፡፡
ኢየሱስ ጌታና ንጉሷ የሆነባት የእግዚአብሄር መንግስት በመካከላችን አለች፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያቱ እንደሞተለት አምኖ ዳግመኛ ያልተወለደ ማንም ሰው የእግዚአብሄርን መንግስት ሊያይ አይችልም፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።ዮሐንስ 3፡3
ዳግመኛ እንደተወለድን እንደ እኛ ባለጠጋ ሰው የለም፡፡ ግን ማየት ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን አይናችን ተከፍቶ ካላየን ባለጠጋ ለመሆን በከንቱ በመድከም ጊዜያችንን እናባክናለን፡፡
ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡18-19
የሰው ጤንነት አይን ነው፡፡ አይኑ የታመመና በትክክል የማያይ ሁለንተናው ይጨልማል፡፡
መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! ማቴዎስ 6፡21-23
መንፈሳዊውን አለም ማየት የተሳናትን የቤተክርስትያን መሪ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ ይላል ጌታ፡፡ ሰው ካላየ ደሃ ሆኖ ባለጠጋ ነኝ ብሎ ይመካል ራቁቱን ሆኖ የዘነጠ ይመስለዋል፡፡
ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። ራእይ 3፡18
ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 118-19
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እይታ #አይን #ቃል #የጠራ #ኩል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

በገድል አምናለሁ!

መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
የምንኖረው ጠላት ዲያቢሎስ በሚሰራበት አለም ውስጥ ነው፡፡ ኢየሱስን ለመከተል ስንወስን በቅፅበት የሰይጣን ጠላቶች ሆነናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር በምድር የሰጠንን ሃላፊነት ሰርቶ ለማለፍ ተጋድሎ ይጠይቃል፡፡
ይህ የእምነት ተጋድሎ እግዚአብሄ የሰጠን ተጋድሎ ስለሆነ መልካም ተጋድሎ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያልሰጠን ተጋድሎዎች በሙሉ መልካም ተጋድሎዎች አይደሉም ውጤትና ፍሬም የላቸውም፡፡ ሰው በራስ አነሳሽነት የሚታገላቸው ተጋድሎዎች ውጤት አልባና የብክነት ተጋድሎዎች ናቸው፡፡
ለምሳሌ ሰው ከሰው ጋር ያለው ተጋድሎ ፣ ከሰው ጋር ያለ ፉክክርና ከንቱ ውድድር መልካም ያልሆነ ተጋድሎ ነው፡፡ ከሰው ጋር የምናደርገው የጦርና የጠብ ተጋድሎ እግዚአብሄር የሰጠን መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡2-3
ሰው በራሱ መንገድ እግዚአበሄርን ለማስደሰት የሚያደርገው ተጋድሎ መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡ መልካም ተጋድሎ እግዚአብሄር ለሰው ልጅ ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ኢየሱስን አዳኝና ጌታ አድርጎ መቀበል ነው፡፡ ሰው ግንብ ይህንን ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለለትን የሃጢያት እዳ ክፍያ ትቶ በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ለማስደሰት መሞከር መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡  ሰው በግብረገብ ለመዳን መሞከርና መፍጨርጨር ኢየሱስ የከፈለውን መስዋእት ከንቱ ስለሚያደርገው መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡ ሰው በራሱ ህግን ለመፈፀም መሞከር እግዚአብሄር የሚፈልገው ውጤታማ ተጋድሎ አይደለም፡፡ ህግን ጠብቆ ለመዳን መሞከር ከነፃ የእግዚአብሄር ስጦታ ከደህንነት ፀጋ መንገድ መውደቅ ነው፡፡   
በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። ገላትያ 5፡4
ስለሚበላና ስለሚጠጣ የምንጨነቀው ጭንቀትና ተጋድሎ እግዚአብሄር ጎሽ የሚለው ተጋድሎ አይደለም፡፡ ሰው አስቀድሞ የእግዚአብሄርን መንግስት መፈለግ ነው ያለበት፡፡ ሰው ግን የእግዚአብሄርን መንግስት ከመፈለግ ይልቅ ስለሚበላና ስለሚጠጣ ላይ ታች ማለቱ መልካም ተጋድሎ አይደለም፡፡  
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ማቴዎስ 6፡31
ይህን ተጋድሎ ልዩ የሚያደርገውና መልካም ያሰኘው እግዚአብሄር ከእኛ የሚጠብቀው ብቸኛ ተጋድሎ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ተጋድሎ እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው ብቸኛው ተጋድሎ ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ይህ ተጋድሎ እግዚአብሄር አብሮት የሚሰራ ተጋድሎ ነው፡፡ ይህ ተጋድሎ ብክነት የሌለበት ፍሬያማ ተጋድሎ ነው፡፡ ይህ ተጋድሎ ውጤቱ ሁልጊዜ ድል የሆነ ተጋድሎ ነው፡፡
ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 1ኛ ዮሐንስ 5፡4
የእምነት ገድል እግዚአብሄር ቃል ላይ በመቆምና በመፅናት የምንጋደለው ተጋድሎ ነው፡፡ የእምነት ገድል ኢየሱስ በመስቀል ላይ የፈፀመልንን ድል የእኛ ድል አድርገን መኖር ነው፡፡ የእምነት ገድል እግዚአብሄር በምድር ላይ የሰጠንን አላማ እስከመጨረሻው ማስፈፀም ነው፡፡ የእምነት ገድል እግዚአብሄር የሰጠንን አገልግሎት መምድር ላይ ፈጽመን እግዚአብሄን ማስከበር ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ተጋድሎ #አላማ #ቃል #ውጤት #ድል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Monday, January 23, 2017

የእውነተኛ ስኬት ምንጭ

ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። መዝሙር 1፡1-3
በእግዚአብሄር ህግ ደስ የሚለው ሰው ምስጉን ነው
የእግዚአብሄር ቃል ተስፋችን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስኬታችን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ህይወታችን ነው፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ደስ የሚለው ሰው እንደሚሳካለት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ለእግዚአብሄር ቃል እክብሮት ያለው ሰው ሊወድቅ አይችልም፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚወድ ሰው እንደሚወጣና እንደሚወርስ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ብርሃን እንደሆነና የትኛውም ጨለማ ሊያሸንፈው እንደማይችል እንዲሁ የእግዚአብሄርን ቃል የያዘ ሰው ሊቋቋመው የሚችል  ከሰማይ በታች ምንም ሃይል የለም፡፡
ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ዮሐንስ 1፡5
የእውነተኛ ስኬት ምንጩን ያገኘ ሰው የተመሰገነ ነው
የእውነተኛ ስኬት ምንጩ የእግዚአብሄር ቃል ስለሆነ ሰው ለስኬት የሚያስፈልገው የእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መልክ ስለተፈጠረ ካለ እግዚአብሄር ቃል ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ስለተፈጠረ ካለ እግዚአብሄር ቃል ማሰብና ማሰላሰል እውነተኛ ስኬት ውስጥ መግባት አይችልም፡፡  
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ማቴዎስ 4፡4
ዘላቂ ስኬት ያለው ሰው የተመሰገነ ነው
ብዙ ስኬት የሚመስሉ ወቅታዊ ነገሮች አሉ፡፡ ስኬቶች ይመጣሉ ይሄዳሉ፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስኬት ግን ምንም የማይለውጠው ስኬት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስኬት ዘመን የማይሽረው ስኬት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስኬት በሌሎች በምንም ነገሮች የማይቀያየር ስኬት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስኬት ሰይጣንም ሆነ ምንም ሁኔታ የማይወሰን አስተማማኝ ስኬት ነው፡፡
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ኢያሱ 1፡8
ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። መዝሙር 1፡1-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ስኬት #ክንውን #ቃል #ማሰላሰል #አእምሮ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Saturday, January 21, 2017

ጆሮ ያለው ይስማ!

በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦ በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ። እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ራእይ 3፡14-22
ፍላጎት ማጣት
ሎዶቅያ ቤተክርስትያን የተወቀሰችበት የመጀመሪያው ነገር እግዚአብሄርን መፈለግ ማቆሟ ነው፡፡ እግዚአብሄርን መፈለግ ያቀመችበትም ምክኒያት ሃብታም ነኝ ብላ ስላሰበች ነው፡፡
ሃብት የሚለካው እግዚአብሄርን በመፈለግ ነው፡፡ እግዚአብሄርን መፈለግ በተውን ጊዜ ድሆች ነን፡፡ እግዚአብሄርን በሁሉም የህይወት ክፍላችን መፈለግ እውነተኛ ባለጠጋ ያደርገናል፡፡
የሎዶፂያ ቤተክርስቲያን የተጠራችንው በልታና ጠጥታ ለመኖር ሳይሆን የጌታን በጎነት ለመመስከር ነው የጠፉትን ለመፈለግ ነው ለአለም ብርሃን ለመሆን ነው፡፡ የሎዶቅያን ቤተክርስትያን ግን ምድራዊ ነገሮችን ስላገኘች ደረስኩበት አሁን ምንም አያስፈልግኝም በማለት ከዋናው አላማዋ እግዚአብሄርን ከመፈለግ ተመለሰች፡፡
እግዚአብሄርን የምንፈልገው ስለሚበላና ስለሚጠጣ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን የምንፈልግው በህይወታችን ስላስቀመጠው አላማ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የምንፈልግው  የእርሱ ስራ በምድር ሰርተን ጌታን ለማስከበር ነው፡፡ ጌታን የምንፈልገው የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን በመፈለግ ነው፡፡ ጌታን የምንፈልገው የመንግስቱን ወንጌል ለመስበክ ነው፡፡ ጌታን የምንፈልገው ሰዎችን ደቀመዝሙር ለማድረግ ነው፡፡
ይህ ክብራችን ነው፡፡ ይህ ጥሪያችን ነው፡፡ ይህ ህይወታችን ነው፡፡
የእይታ ችግር
ሰው ራቁቱ ሆኖ በልብሱ ከተመካ የጎደለው እይታ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ነገሮችን በትክክል ማየት ነው፡፡ የሰው አይን ጤነኛ ካልሆነ ሁለንተናው ይታመማል፡፡ ሰው በትክክል ካላየ ከፍተኛ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ሰው እግዚአብሄር እንደሚያያቸው ነገሮችን ካላየን ህይወታችን ይባክናል፡፡ ሰው እግዚአብሄር የሚንቃቸውን ካልናቀ ጌታ የሚያከብራቸውን ካላከበረ ህይወቱ የብከነት ህይወት ነው የሚሆነው፡፡   
በዚህ ምክኒያት ኢየሱስን ከሁኔታው አውጥታዋለች፡፡ እኔ እበቃለሁ ኢየሱስ አያስፈልግም ብላለች፡፡ ኢየሱስ በደጅ ቆሞ እያኳኳ ነው፡፡
እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሎዶቅያ #በራድወይምትኩስ #ድልለነሳው #ጆሮያለውይስማ #አእምሮ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ምን ብዬ ልጩኽ?

ጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው። ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። ኢሳይያስ 40፡6-8
የሰው ህይወት በምድር ላይ አጭር ነው፡፡ ሰው ሃላፊ ነው፡፡ የሰው ህይወቱ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ነው፡፡
ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። ያዕቆብ 4፡14
ሰው ሰማይና ምድርን ከፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም መኖር የሚችለው የእግዚአብሄርን የመዳኛ መንገድ ሲቀበል ብቻ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ለዘላለም መኖር የሚችለው የማይጠፋውን የእግዚአብሄርን ቃል ሲቀበል ብቻ ነው፡፡ ሰው የዘላለም ህይወት የሚኖረው እግዚአብሄር ስለመዳኑ ያዘጋጀውን የኢየሱስን የመስቀል ስራ ለእኔ ነው የሞተውና የተነሳው ብሎ ብቻ ነው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16
ሰው ዘላለማዊ ህይወትን የሚያገኘው ከእግዚአብሄር ቃል ዳግመኛ ሲወለድ ብቻ ነው፡፡
ሰማይና ምድር ያልፋሉ ከማይጠፋው ለዘላለም ከሚኖረው ከእግዚአብሄር ቃል የተወለደ ሰው ግን አያልፍም፡፡
ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ። ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።  1ኛ ጴጥሮስ 1፡23-25
ኢየሱስ ስለሃጢያቱ እንደሞተለትና ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ የሚያምን ሰው ይድናል፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10
ሰማይና ምድር ያልፋሉ፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ግን አያልፍም፡፡
ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ማቴዎስ 24፡35
የሚታየው ሁሉ የጊዜው ነው፡፡ የማይታየው ሁሉ ዘላለማዊ ነው፡፡
የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡18
ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሃንስ 2፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የጌታቃል #ዘላለም #የዘላለምህይወት #የእግዚአብሄርፈቃድ #የጊዜው #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ