አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፦ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤ ዘፍጥረት 17፡1
ብዙ ጊዜ ሰዎችን የሚያስጨንቃቸው የማያስጨንቅ ነገር ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገር የእግዚአብሄርና የሰው ስራ ውጤት ነው፡፡ ሰው የማይሰራው የእግዚአብሄር ስራ አለ፡፡ እግዚአብሄር የማይሰራው የሰው ደግሞ ስራ አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች የራሳቸው ድርሻ ላይ አያተኩሩም፡፡ ሰዎች የራሳቸውን ድርሻ ትተው የእግዚአብሄር ድርሻ ላይ ሲያተኩሩ ይጨነቃሉ በክርስትና ህይወታቸው መደሰት ያቅታቸዋል፡፡
ሰዎች በህይወት ያላቸውን ሃላፊነት ሳይረዱ ሲቀሩ በእግዚአብሄር ስራ ውስጥ ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ሰዎች የራሳቸውን ስራ ሰርተው ካላረፉ የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት ሲሞክሩ ህይወታችውን ያባክናሉ፡፡
እግዚአብሄር ለአብርሃም ልጅን እሰጥሃለሁ ብሎታል፡፡ እግዚአብሄር ካለ ሆነም ነው፡፡ አብርሃም ማድረግ ያለበት በእምነት ተቀብሎ መኖር ብቻ ነው፡፡ አብርሃም ማድረግ ያለበት እግዚአብሄር ከእርሱ የሚፈልገውን ነገር በትጋት ማድረግ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከአብርሃም የሚፈልገው ነገር አብርሃም እግዚአብሄርን እንዲከተል ብቻ ነው፡፡
አብርሃም እግዚአብሄር የሰጠውን የራሱን ሃላፊነት ትቶ ግን እግዚአብሄር ቃሉን እንዴት ሊፈጽመው ነው እያለ ቢጨቅ የሚያመጣው ነገር የለም፡፡ አብርሃም እግዚአብሄር እንዴት ቃሉን እንደሚያደርገው ቢያወጣና ቢያወርድ ለራሱ የተሰጠውን ሃላፊነት መወጣት ያቅተዋል፡፡
በአዲስ ኪዳንን ኢየሱስ ያለው ይህንኑ ነው፡፡ የሰው ድርሻ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ ሁል ጊዜ በእግዚአብሄር ፊት ትክክል ሆኖ መገኘት ነው፡፡ የሰው ድርሻ ኢየሱስን ፈፅሞ መከተል ነው፡፡ የሰው ድርሻ የእግዚአብሄር መንግስትን ጥቅም መፈለግ ነው፡፡ የሰው ድርሻ ለእግዚአብሄርን መንግስት በጎነትና ማሸነፍ በትጋት መስራት ነው፡፡
የእግዚአብሄር ድርሻ ሰው ለኑሮ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ለሰው ማሟላት ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
ብዙ ሰው ማድረግ የሚፈልገው ግን የራሱን ድርሻ የእግዚአብሄርን ፅድቅና መንግስቱን ከመፈለግ ይልቅ እግዚአብሄር ይጨመርላችኋል ያለውን ስለሚበላላና ስለሚጠጣ መጨነቅ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር እንዲተላለፍ የሚያደርገው እግዚአብሄር አድርግ ያለውን የራሱን ድርሻ ትቶ ይህ የእኔ ድርሻ ነው አትሞክረው ያለውን የእግዚአብሄን ድርሻ ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡
እግዚአብሄር አብርሃምን ያለውም የአንተ ድርሻ በፊቴ መመላለስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያለው ተከተለኝ ስማኝ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያለው ህይወትህን ጠብቅ ንፅህናህን ጠብቅ ቅድስናህን ጠብቅ ነው፡፡
ከዚያ ውጭ ምንም የሚያሳስብህ ነገር የለም፡፡ ነገርህ በእኔ እጅ ነው፡፡ ሌላው የእኔ ሃላፊነት ነው፡፡ ቃሌን መፈፀም የእኔ ስራ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሁሉ እችላለሁ፡፡ እኔ የማደርገው አያሳስብህ፡፡ ለማድረግ ብቃቱ አለኝ እያለው ነው፡፡
አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፦ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤ ዘፍጥረት 17፡1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፍፁም #ተመላለስ #ኤልሻዳይ #እምነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment