Popular Posts

Thursday, September 30, 2021

ግልፀ ደብዳቤ ለአገልጋይ ዮኒ

ግልፀ ደብዳቤ ለአገልጋይ ዮኒ

በቲክቶክ ላይ በብዙ ሰዎች የተካፈለ እና በከፍተኛ ሁኔታ የተዘዋወረ ቪድዮ አየሁ፡፡ በቪድዮ ላይ አገልጋይ ዮኒ ፖለቲከኞችን ሚንስቶሮችን እንዴት እንደሚያስተምርና እንሚመክር ይናገራል፡፡

አገልጋይ ዮኒ ስለሙስና እና በስልጣንን ካለ አግባብ ስለመጠቀም ሲናገር አትበሉም አልልም ትበላላችሁ በማለት ከአንድ የሃይማኖት መሪ የማይጠበቅ የብዙዎች መንፈሳዊ ንፅህና የሚያጎድል እና ቅዱሳንን ለሰይጣን ጥቃት የሚያጋልጥ ክፉ ምክር ይመክራል፡፡  

አትበሉም ብሎ መጀመር ሲኖርበት አትበሉም አልልም በማለት ማንም ፖለቲከኛ ላይበላ እንደሚችል አምኖ ተቀብሎዋል፡፡ ሰው ፖለቲከኛ ሆኖ ንፁህ ሊሆን እንደሚችል በቃሉ ተስፋ ቆርጦዋል፡፡ አጋልጋይ ዮኒ ከንግግሩ ሰው ፖለቲከኛም የማይሰርቅ ክርስትያንም ሊሆን እንደሚችል አያምንም፡፡ ሰው በተለይም ፖለቲከኛ እና ባለስልጣን በምድር ላይ ቅዱስ ሆኖ መኖር እንደማይችል ያለውን ተስፋ መቁረጥ በዚህ በተሸናፊነት ንግግሩ ያሳያል፡፡

ይባስ ብሎ ደግሞ "አትብሉ አልልም ብሉ" በማለት ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ጉባኤና ቪድዮ በሚለቀቅበት በመረጃ መረብ ፣ በማህበራዊ ትስስር ገፆች የእግዚአብሄርን ቃል ለማያውቁ የአስተማሪን ቃል በእግዚአብሄር ቃል መዝነው ለማይቀበሉ ተከታዮች የሌብነት ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ሲያስተምር የሚስሙት ሲደነግጡ ሳይሆን ሲስቁና ሲያጨበጭቡ ከጀርባ ይሰማል፡፡ በመረጃ መረብ ላይ በተለቀቀውም የቪድዮ ክሊፕ አስተያየት ላይ እውነቱን ተናገረ ተብሎ ሲደነቅ አንብቤያለሁ፡፡  

የመፅሃፍ ቅሱስ እውነት አትብሉ የሚለው ትእዛዝ ነው እንጂ ብሉም ፣ ትንሽ ትንሽ ብሉም እንደመፅሃፍ ቅዱስ እውነት ግልፅ የስህተት ትምህርት ነው፡፡

ትንሽ ትንሽ ብሉ ማለት ምን ማለት ነው? ትንሽ ትንሽ ብሉ ማለት ስንት ብሉ ማለት ነው? ትንሽ የሚለው ቃል ረቂቅና ሊመዘን የሚችል ስላይደለ አሻሚ ቃል ነው፡፡ ትንሽ የሚለው ቃል ሰው ለስጋው የምኞት ሃጢያት አርነት እንዲሰጥ ከማድረግ ውጭ ሰው ራሱን በመግዛት ለእግዚአብሄር አላማ እንዲኖር አያበረታታም፡፡ ትንሽ ማለት ስንት ነው በመቶዎች በሺዎች በሚሊዮኖች ?

አገልጋይ ዮኒ ከአንድ የሃይማኖት መሪ የማይጠበቅ የብዙዎች መንፈሳዊ ንፅህና የሚያጎድል ምክር ይመክራል፡፡

አገልጋይ ዮኒ በዚህ ንግግሩ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ከሚለው የእግዚአብሄር ቃል በተቃራኒ ያስተምራል፡፡ አገልጋይ ዮኒ በዚህ ትምህርቱ ራስን ከመግዛት ይልቅ ሰው በህይወቱ ለሰይጣን ስፍራን እንዲሰጥ የሚያደርግ ጤናማ ያልሆነ ትምህርትን ያስተምራል፡፡

የእግዚአብሄር አገልጋይ የሆነው መጥምቁ ዮሃንስ ስለባልስልጣኖች ሰልጣናቸውን ካለአግናባብ ሊጠቀሙ ስለሚችሉ ፖለቲከኞችና የአገር አስተዳዳሪዎች የመከረው ምክር አገልጋይ ዮኒ ከመከረው ምክር ተቃራኒ ነው፡፡

ወታደሮ ደግሞ፣እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣የማንንም ገንዘብ በግፍ አትንጠቁ፤ ሰውንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁ ይብቃችሁአላቸው። ሉቃስ 3:14

ይህ ማለት ግን አገልጋይ ዮኒ ያስተማራቸው ትምህርቶች ሁሉ ስህተት ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ይህ ትምህርት ግን ንስሃንና መመለስን የሚጠይቅ እርሱም በህይወቱ ሊተገብረው የማይገባው ሌሎችም ሊተገብሩት መምከር የሌለበት የስህተት ትምህርት መሆኑን  አውቆ በግልፅ ንስሃ መግባትና እንደመፅሃፍ ቅዱስ አስተምሮት አስተካክሎ ማስተማር አለበት፡፡


Tuesday, September 28, 2021

የሰይጣን መሳሪያ

 


የሰይጣን አላማው መስረቅ ማረድና ማጥፋት ነው፡፡ ሰይጣን ከመስረቅ ከማረድና ከማጥፋት ውጭ ሌላ ምንም አላማ የለውም፡፡

ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ የዮሐንስ ወንጌል 10፡10

ይህንን የመስረቅ የማረድና የማጥፋት አላማውን የሚያሳካው ደግሞ በውሸት ነው፡፡ ሰይጣን አለማማውን የሚያሳካው በመዋሸት እና በማታለል ነው፡፡

እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። የዮሐንስ ወንጌል 8፡44

ሰይጣን የራሱ ነገር የለውም፡፡  ሰይጣን የእግዚአብሄርን እውነትን አይቀበለም፡፡ ሰይጣን ከራሱ ሃሰትን ይናገራል፡፡ ሰይጣን ይዋሻል፡፡ ሰይጣን እውነትን ለውጦ ያቀርባል፡፡ ሰይጣን የሚያምኑትን ሰዎች ያታልላል፡፡

ሰይጣን ከመጀመሪያ ጀምሮ ውሸታም ነው፡፡ ከሰይጣን ውሸት እንጂ ምንም ሌላ ነገር አይጠበቅም፡፡ ሰይጣን ተንኮለኛ ነው፡፡ የሰይጣን ሃይል ማታለል ስለሆነ ሰይጣን ሃሰቱን እውነት አስመስሎ ለማቅረብ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ሰይጣን በተለይ በእግዚአብሄር ፊት ያለን ቦታ ላይ ይዋሻል፡፡ እግዚአብሄር እንዴት በክብር እንደሚያየን በእግዚአብሄር ፊት ያለንን የክብር ቦታ ላይ በልባችን ጥርጥር ማስገባት ከተሳካለት ሰይጣን ህይወታችንን በቀላሉ ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ እንደሚችል ያውቃል፡፡

ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡3

ሰይጣን ዲያብሎስ በእግዚአብሄር ልጅነታችን ላይ እንዲዋሽ ካልፈቀድንለት ግን ህይወታችንን የሚያጠቃበት ምንም ፈንታ እና ስፍራ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለሰይጣን በፍርሃት ስፍራን የምንሰጠው ወይም በእምነት ስፍራን የምናሳጣው እኛው ራሳችን ነን፡፡

ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡27

ሰይጣን ሔዋንን ያሳሳታት በእግዚአብሄር ፊት ባላት ስልጣን በማንነትዋ ላይ በመዋሸት ነው፡፡ እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮአት እያለ ልጅነትዋ ምንም እንዳይደለ ፣ ምንም ሊጠቅማት እንደማይችል ፣ ከንቱ እንደሆነ እና የጎደላት ብዙ ነገር እንዳለ በውሸት በማሳመን በአመፃ ከእግዚአብሄር ክብር እንድትወድቅ አታለላት፡፡

እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ኦሪት ዘፍጥረት 3፡5

ዲያቢሎስ ኢየሱስን በምድር ላይ ሲፈትነው የሰይጣን የውሸትና የንቀት ስልቱ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሰይጣን "የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ" በሚለው የማናናቂያ እና የማጣጣያ የንቀት ንግግሩ በኢየሱስ ማንነት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሮዋል፡፡ የሰይጣን "የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ" የሚለው ንግግር ኢየሱስ በእግዚአብሄር ፊት ያለውን ልጅነት የሚያንቋሽሽ ምን ታመጣለህ? ዝም ብለህ ነው ! ምንም አይደለህም! ከማንም አትበልጥም! የሚል መልእክት ነበረው፡፡

ዲያብሎስም፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ፦ እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። የሉቃስ ወንጌል 4፡3

ኢየሱስ ግን የልጅነት ቦታውንና ስልጣኑን አጥብቆ ያውቅ ስለነበር ለሰይጣን ማንቋሸሽ እና ማጣጣል አልተንበረከከም፡፡ ኢየሱስ የሰይጣንን የውሸት ንግግር በልቡ አላስተናገደውም፡፡ ኢየሱስ የሰይጣንን የማንቋሸሽ ንግግር ተቀብሎ እግዚአብሄር ከሰጠው አላማ ወጥቶ ለአንድም ሰአት ለሰይጣን ሃሳብ አልተገዛም፡፡ ኢየሱስ የሰይጣንን የንቀትና የፍርሃት ንግግር ንቆ እግዚአብሄር የሰጠውን አላማ በድፍረት ፈፀመ፡፡

የሰይጣን የፍርሃት አላማ ሰውን ከአላማው ማስቆም እንደመሆኑ መጠን የሰይጣን ፍርሃት እና ጥርጥር የሚጭር ንግግር ኢየሱስን ከአላማው እና ከእርምጃው አላቆመውም፡፡ የፍርሃት አላማ እኛን ለምንም የማንጠቅም ፣ ሽባ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስን በፍርሃት ሽባ ሊያደርገው እና ከአላማው ሊያስቆመው አልቻለም፡፡  

አሁንም ሰይጣን እኛን የሚፈትነን ልጅነታችንን እና በልጅነታችን ያገኘነውን ነገር ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት ነው፡፡ አሁንም የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ እስኪ ከዚህ ሁኔታ አምልጥ ፣ የእግዚአብሄ ልጅ ከሆንሽ ይህ ለምን ደረሰብሽ? የእግዚአብሄር ልጅ ከሆንክ እንዲህ እና እንዲያ ለምን ሆነ? በማለት በእግዚአብሄር ፊታ ያለንን ልጅነት ሊያጣጥል ይጥራል፡፡

እህህ ብለን ውሸቱ ከሰማነውና በማጣጣል ወጥመዱ ውስጥ ከገባንለት የእግዚአብሄር ልጅ አይደላችሁም ፣ ዝም ብላችሁ ነው ፣ ከእኔ ሃይል አታመልጡም ብሎ ሊያሳምነን ይፈልጋል፡፡

ሰይጣን የህይወት ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን ውሸታም ነው፡፡ ሰይጣን የሚጠቀመው በማታለል ነው፡፡ በህይወታችን አሸናፊ ለመሆን ከሰይጣን ንግግር በላይ እና ከሁኔታ በላይ የእግዚአብሄርን ቃል ልናምን ይገባናል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ዲያቢሎስ #ጠላት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ሐሰት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ውሸት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ማታለል #የተሸነፈ #በረከት #ትግስት #መሪ


Monday, September 13, 2021

የአርባ ቀን የፈውስ ትምህርት ጉዞ ቁጥር 20

 


የእግዚአብሄርን ፈውስ በህይወታችን ስንፈልግ በእምነት መቅረብ ይኖርብናል፡፡

በእምነት መቅረብ ማለት ደግሞ በአንድ ልብ መቅረብ ማለት ነው፡፡

ወደእግዚአብሄር ስንቀርብ በእምነት መቅረብ ይጠበቅብናል፡፡ ወደ እግዚአብሄር ስንቀርብ በጥርጥር መወላወል መቅረብ የለብንም፡፡

ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። ያዕቆብ 1፡6-8

እግዚአብሄርንና የእግዚአብሄርን ነገር በፍፁም ልባችን መፈለግ አለብን፡፡

በሙሉ ልብ ፈውስን የመፈለግ ምሳሌ የምትሆነን ሴት በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌዋን እናገኛለን፡፡

እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። እርስዋ ግን መጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ማቴዎስ 15፡22-28

ይህች ሴት የእግዚአብሄርን ፈውስ ባጣ ቆየኝ አላደረገችውም፡፡ ይህች ሴት አንተ ካልፈወስክልኝ ማንም ሊፈውስልኝ አይችልም ብላ በፍፀም ልብዋ በፅናት ፈውስን ፈለገች፡፡

ኢየሱስ እምነትዋን ታላቅ እንደሆነ መሰከረላት፡፡

እምነትዋም ፈውስን ከእግዚአብሄር እንድትቀበል አደረጋት፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Friday, September 3, 2021

የአርባ ቀን የፈውስ ትምህርት ጉዞ ቁጥር 19

 

የአርባ ቀን የፈውስ ትምህርት ጉዞ ቁጥር 19

ምንም እንኳን የሰው ልጅ የነፍስ ፈውስና የስጋ ፈውስ ተሰርቶ ያለቀ ቢሆንም ማንኛውንም መንፈሳዊን ነገርን ለመቀበል እምነት ይጠይቃል፡፡

ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራዊያን 11፡6

ፈውስን በህይወታችን ለመቀበል እምነት ይጠይቀናል፡፡

በመንፈሳዊ ልውውጥ ወይም ግብይት እምነት ወሳኝ ነው፡፡

በምድራዊ ግብይት የምንፈልገውን እቃ ለመግዛት ገንዘብን እንደሚጠይቅ ሁሉ በመንፈሳዊ አለም የእኛ የሆነውን በነፃ የተሰጠንን ለመቀበል እምነት ይጠይቃል፡፡

በምድራዊው አለም የአንድ ነገር ዋጋ የሚለካው በገንዘብ እንደሆነ ሁሉ በመንፈሳዊ አለም የአንድ ነገር ዋጋ የሚለካውና የሚወሰነው በእምነት ነው፡፡  

በምድራዊው አለም ገበያ ገንዘብ መግባቢያ ቋንቋ እንደሆነ ሁሉ በመንፈሳ አለም መግባቢያ ቋንቋው እምነት ነው፡፡

ሃዋሪያው ጳውሎስ በምድር ላይ ባገለገለበት ጊዜ የእግዚአብሄርን ቃል ያስተምር ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ሲናገር ይሰማ ስለነበረው ሰው የእግዚአብሄር ቃል ሲናገር "ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜምነት እንዳለው ባየ ጊዜ" ይላል፡፡

ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኵር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ድምፅ፦ ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም አለው። ብድግ ብሎም ተንሥቶ ይመላለስ ነበር። ሐዋሪያት 14፡9-10

ሃዋሪያው ጳውሎስ የእግዚአብሄርን ቃል ይሰብካል፡፡ ለፈውስ እምነት ስለሚጠይቅ ቃሉን ሰምተው ያመኑ ሰዎች ይፈወሱ ነበር፡፡

በኢየሱስ አገልግሎት ሰዎች ሊሰሙትና ሊፈወሱ ይመጡ ነበር፡፡

ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ሉቃስ 6፡17

ኢየሱስ ሰዎች በኢየሱስ አገልግሎት ከተፈወሱ በኋላ እምነትሽ አድኖሃል የሚለው ስለዚህ ነው፡፡

እርሱንም፦ ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ሉቃስ 17፡19

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


Thursday, September 2, 2021

የአርባ ቀን የፈውስ ትምህርት ጉዞ ቁጥር 18

 


የእግዚአብሄር የመጀመሪያ ፈቃዱ ሰው በጤንነት እንዲኖር ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ሰው በማንኛውም ምክኒያት ጤንነቱን ቢያጣ እግዚአብሄር ሊፈውሰው ይፈልጋል፡፡

ሰው በስጋ የሚፈወሰው እግዚአብሄር በክርስቶስ የተገረፈለትን ሲመለከት እና ሲረዳ ብቻ ነው፡፡

ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡24

ሰው ካልተፈወሰ ያልተፈወሰው እግዚአብሄር ስላልፈቀደ ሳይሆን ሰው ለጤናው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ፈልጎ ስላላገኘ ነው፡፡ ሰው ለመፈወስ ስለፈውሱ የእግዚአብሄርን ቃል ፈልጎ ማግኘት እና መረዳት አለበት፡፡ ሰው ስለስጋው ፈውስ የእግዚአብሄርን ሃሳብ መረዳት ሲጀምር ፈውሱ ይበቅላል፡፡

እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17

ሰው ከነፍስ የሃጢያት ህመም የማይፈወሰው እግዚአብሄር ፈውሱን ስላልፈቀደ አይደለም፡፡

ሰው ለነፍሱ መድሃኒት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገለትን ነገር ሲመለከት ከነፍስ የሃጢያት ህመም ይፈወሳል፡፡ እንዲሁም ሰው ከስጋ በሽታ የማይፈወሰው እግዚአብሄር ስላልፈቀደ አይደለም፡፡ ሰው እግዚአብሄር በክርስቶስ የሰራለትን ነገር ሲመለከት ይፈወሳል፡፡

ሰው በነፍሱ ከሃጢያት ለመዳን የእግዚአብሄር ፈቃድ ከሆነ ያድነኛል ብሎ ዝም ብሎ መቀመጥ የለበትም፡፡ ሰው በነፍስ ለመዳን እግዚአብሄርን መፈለግና የእግዚአብሄር ቃል ስለነፍሱ የሚለውን ነገር መቀበል ይገባዋል፡፡

እንዲሁም ሰው እግዚአብሄር ከወደደ ያድነኛል ብሎ ስለስጋ ፈውሱ ምንም ነገር ሳያደርግ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ የለበትም፡፡ እግዚአብሄር የሰውን መፈወስ ይፈልጋል፡፡

ብዙን ጊዜ እኛ ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንደምንመለከተው እግዚአብሄር አያየንም፡፡ እግዚአብሄር ቃሉን እንድንፈልግና እንድናምን ይጠብቅብናል፡፡ እግዚአብሄር ሰው በህይወቱ ስለሚፈልገው ነገር እርሱን እንዲፈልገውና በቃሉ የተናገረውን እንዲያምነው ይጠብቃል፡፡

ፈውሳችንን በእምነት እንድንወስድ እግዚአብሄር ይጠብቅብናል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Wednesday, September 1, 2021

የአርባ ቀን የፈውስ ትምህርት ጉዞ ቁጥር 17

 

ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ። 3 ዮሐንስ 12

ሰው ጤናውን ጨምሮ በነገር ሁሉ እንዲከናወንለት እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡

ሰው በምድር ላይ ለመኖር ለመስራትና ለመንቀሳቀስ ጤና ያስፈልገዋል፡፡ እግዚአብሄርን ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ያበጀው በምድር ላይ የሚኖርበትን ስጋውን ነው፡፡ ሰው ነፍሱ ተከናውኖ ነገር ግን በስጋው ደካማና የማይችል ከሆነ ክንውኑ ሙሉ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰው ነፍሱ ከጠላት ዲያቢሎስ ጥቃት አምልጣ ስጋው ግን የሰይጣን በሽታ መጫወቻ ከሆነ በምድር ላይ ያለውን ተልእኮ በሙላት መፈፀም አይችልም፡፡ 

እውነት ነው እግዚአብሄር ከነፍስ ፈውስ ይልቅ ለስጋ ፈውስ ቅድሚያ አይሰጥም፡፡ ሰው ደግሞ ነፍሱ እንድትድን ስጋው ተፈውሶ የመዳኛ እድልን ማግኘት አለበት፡፡ ስለዚህ ሰው ተፈውሶ ረጅም እድሜ እንዲኖርና የመዳኛን እድልን እንዲያገኝ እግዚአብሄር እርሱን የሚከተል ሰው ብቻ ሳይሆን ያልዳነንም ሰው ስጋ ይፈውሳል፡፡

ኢየሱስ ሰውን ይፈውስና ደግመህ ሃጢያትን አታድርግ ብሎ ማዘዙ የሚያሳየው በሃጢያት ውስጥ ያለ ሰው እንኳን እንዲፈወስና ለእግዚአብሄር ለመኖር እንዲወስን እግዚአብሄር ሌላ እድል መስጠትን እንደሚወድ ነው፡፡ 

ኢየሱስ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፦ እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ዮሃንስ 5 8-914-15

እግዚአብሄር በመለኮታዊ ፈውስ ብቻ ሳይሆን ለህክምና ባለሙያዎች በሰጠው ተፈጥሮአዊ ጥበብ አማካኝነት በህክምና የሰዎችን ጤና ይመልሳል፡፡ ሰው በምድር ኖሮ እርሱን ለመከተልና ለማገልገል እንዲችል እግዚአብሄር ሰውን በመለኮታዊውም መንገድ ይሁን በተፈጥሮአዊው መንገድ ተጠቅሞ ሰዎችን ከበሽታቸው ያድናል፡፡   

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ