Popular Posts

Follow by Email

Monday, September 30, 2019

እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንምዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም። ኦሪት ዘዳግም 28፡13-14
ሰው በእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረው ለእግዚአብሄር እየተገዛ እንዲገዛ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው የበላይ ለሆነው ለእግዚአብሄር እውቅና እየሰጠ የበላይ ለመሆን ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን ብቻ እያመለከ ራስ እንዲሆን ነው፡፡
የመጀመሪያው ሰው አዳም ለእግዚአብሄር በተገዛበት ጊዜ ሁሉ ራስ ነበረ፡፡ አዳም ከእግዚአብሄር ቃል ወደግራም ወደቀኝንም ባላለ ጊዜ የበላይ እንጂ የበታች አልነበረም፡፡
ሰው ለእግዚአብሄር አምላክነት በታዘዘ ጊዜና ለእግዚአብሄርና ለእግዚአብሄር ብቻ በሚገዛበት ጊዜ ነገሮች ሁሉ በሙሉ ልባቸው ለእርሱ ይሰሩለት ነበር፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ቃል በታዘዘበት ዘመን ሁሉ ተፈጥሮ እንደ ሃይሉ መጠን ይሰጠው ነበር፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ቃል ወደ ቀኝ ወደ ግራም ፈቀቅ ባላለበት ጊዜ ሁሉም ነገሮች ሁሉ ይሰሩለት ይታዘዙት ይሰሙት ነበር፡፡
ሰው አሁንም ለእግዚአብሄር ቃል እውቅና በሰጠ መጠን ነገሮች ለእርሱ እውቅና ይሰጣሉ፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ቃል ልቡን በሰጠ መጠን ነገሮች ለእርሱ ልባቸውን ይሰጡታል፡፡
ሰው ከእግዚአብሄር ቃል ወደቀኝና ወደግራ ሲል ነገሮችም ከትእዛዙ ያፈነግጣሉ፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ቃል ችላ ባለ መጠን ነገሮች ችላ ይሉታል፡፡ ሰው ራሱን ለእግዚአብሄር አምላክነት ባስገዛ መጠን ሁኔታዎች ለእርሱ ይገዙለታል፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል። መዝሙረ ዳዊት 1፡2-3
ሰው የእግዚአብሄርን ቃል ብቸኛ የህይወቱ መመሪያ ሲያደርግ በሚሰራው ነገር ሁሉ ይከናወንለታል፡፡
ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፡7-8
ሰው እንደእግዚአብሄር ቃል ለእግዚአብሄር ከተገዛ እግዚአብሄርን አልፎ የሚገዛው ሌላ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ሰው ግን ለእግዚአብሄር ስልጣን ካልተገዛ ለሌላ ነገር እንደማይገዛ ምንም ማስተማመኛ አይኖረውም፡፡  
ዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም። ኦሪት ዘዳግም 2813-14
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ስኬት #ክንውን #መታዘዝ #ስልጣን #ሃይል #መገዛት #መታዘዝ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና

Saturday, September 28, 2019

ይቅርታ አንጠይቅም
ስለአፈጣጠራችን ማንምም ሰው ይቅርታ አንጠይቅም፡፡
እግዚአብሄር አንድ ቀን ተገልጦ እኛን እንደዚህ አድርጌ ስለፈጠርኳቸው ይቅርታ እጠይቃለሁ ሲል አታገኙትም፡፡ እግዚአብሄር እንደዚህ አድርጎ ስለፈጠረን አይፀፀትም፡፡ እግዚአብሄር ስለአፈጣጠራችን ማንንም ይቅርታ አይጠይቅም፡፡ እግዚአብሄር ስለፈጠረን ስለባህሪያችን ፣ ስለመልካችን ፣ ስለዘራችን ስለአገራችን ማንንም ይቅርታ አይጠይቅም፡፡ እግዚአብሄር ግሩምና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮናል፡፡
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። መዝሙረ ዳዊት 139፡14
ሰው ሲያየን እንዲህ ተደርገው ቢፈጠሩ ኖሮ መልካም ነበር ብለው አፈጣጠራችንን ለማስተካከል ሊፈተኑ ይችላሉ፡፡ ሰው አንዳንድ ጊዜ ነሸጥ ሲያደርገው እግዚአብሄርን ሊያርም ይዳዳዋል፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፍጥረት ለማስተካል መፈተኑ የእርሱ ችግር እንጂ የእግዚአብሄር ወይም የተፈጠረው ሰው ችግር አይደለም፡፡
ስለደረስንበት መንፈሳዊ ደረጃ ማንንም ይቅርታ አንጠይቅም
አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን ከሚያመጣብን ኩነኔ ተነስተን ያለንበትን መንፈሳዊ ደረጃ መቀበል ያቅተናል፡፡ ስለዚህ ስለመንፈሳዊ የህይወት ደረጃችን እንሳቀቃለን፡፡ ስለደረስንበት መንፈሳዊ ደረጃችን እናዝናለን እንኮነናለን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ ስለደረስንበት መንፈሳዊ ደረጃ ማነስ ስለምንሳቀቅ ከደረስንበትን መንፈሳዊ ደረጃ በላይ እንደደረስን ለሌሎች ለማሳየት እንፈተናለን፡፡ የደረስንበትን መንፈሳዊ ደረጃ አጋንነን መናገር መፈለጋችን ስላለንበት መንፈሳዊ ደረጃ ደስተኞች አለመሆናችንን ያመለክታል፡፡ ስለደረስንበት መንፈሳዊ ደረጃ ምቾት ስለማይሰማን መድረስ ይገባን ነበር ብለን ስለምናስበው መንፈሳዊ ደረጃ ሰዎችን ሃገርን ራሳችንን እንኮንናለን፡፡   
እውነት ነው ልደርስበት ካለው መንፈሳዊ ደረጃ እንፃር ያለንበት መንፈሳዊ ደረጃ ያነሰ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ያለንበት መንፈሳዊ ደረጃ ከነበርንበት መንፈሳዊ ደረጃ እንፃር ደግሞ ህልምን በእውን እንደመኖር በብዙ እጅ የተሻለ ነው፡፡ ያለሁንበት መንፈሳዊ ደረጃ ወደፊት መድረስ ካለብን መንፈሳዊ  ደረጃ ቢያንስም ከነበርንበት መንፈሳዊ ደረጃ ቢበልጥም ላለንበት ጊዜ ፍፁም ነው፡፡
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 43
ስለደረስንበት የገንዘብ ሁኔታ ማንንም ይቅርታ አንጠይቅም
አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን ካለአግባብ ከሌሎች ጋር በማስተያየት እና በማወዳር በስራ አለም ይሄን ያህል ቆይቼ በማለት ምን አለኝ ብለን ራሳችንን እንኮንናለን፡፡ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ካስተያየን ያለንበትን የገንዘብ ሁኔታ ለመቀበል ይቸግረናል፡፡ ስለዚህ ከአቅማችን በላይ ውድ ነገሮችን በመግዛት ካለን ገንዘብ በላይ እንዳለን ለሌሎች ለማሳየት እንፈተናለን፡፡ እግዚአብሄር ያለንበትን የገንዘን ሁኔታ አበጥሮ ያውቃል፡፡ የገንዘብ ሁኔታችንን በተመለከተ እግዚአብሄር ከየት እንደመጣን ፣ አሁን የት እንደደረስንና ወደየት እየሄድን እንዳለን ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር ስለእኛ የገንዘብ ሁኔታ አይሳቀቅም፡፡ እግዚአብሄር እኛ ስላለንበት የገንዘብ ሁኔታ ማንንም ይቅርታ አይጠይቅም፡፡
እኛም ስላለንበት የገንዘብ ሁኔታ ምንንም ይቅርታ መጠየቅ የለብንም፡፡ እግዚአብሄር ስላደረሰን የገንዘብ ሁኔታ እርማት እና ማስተካያ ሊሰጥ የሚፈተን ሰው ካለ ያ የእርሱ ችግር እንጂ የእኛ ችግር አይደለም፡፡  
ስለሌለን ስጦታ ማንንም ይቅርታ አንጠይቅም፡፡
ወደምድር ስንፈጠረ ሁላችንም ለምድር ከሚጠቅም ስጦታ ጋር ተፈጥረናል፡፡ ማን ከምን ስጦታ ጋር እንደሚፈጠር የሚወስነው እኛ ሳንሆን እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡ ሌሎች በጣም ስልተካኑት እኛ ግን ስለሌለን ስጦታ ማንም እንዲኮንነን አንፈቅድለትም፡፡
በክርስትናም መንፈስ ቅዱስ እንደወደደ ስጦታዎችን ያካፍላል፡፡ ስጦታን የሚሰጠው እግዚአብሄር እንጂ እኛ ስላይደለን ስለሌለን መንፈሳዊ ስጦታ ማንንም ይቅርታ መጠየቅ የለብን፡፡
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡1
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ግሩም #ድንቅ #ክርስቶስ #ህይወት #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #መፀለይ #ሞገስ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #እረፍት

Thursday, September 26, 2019

በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ የመግባት አስሩ ጥቅሞች
1.      አፈጣጠራችን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ በመኖር እንዲሳካልንና እንዲከናወንልን ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ፈቃድ ሲወጣ ያልተሰራበትን ስሪት ለመስራት እንደመሞከር ነው፡፡ ቤት መጥረጊያ የተፈጠረበት አላማ አለው፡፡ ብረት መቁረጫ መጋዝ ደግሞ የተፈጠረበት ሌላ አለማ አለው፡፡ ከእግዚአብሄር ፈቃድ መውጣት ቤትን ለመጥረግ የተሰራ መጥረጊያን ብረትን ለመቁረጥ እንደተሰራ እንደመጋዝ እንደመጠቀም ነው፡፡ 
2.     ክብራችን ያለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመታዝ ውስጥ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከመታተዝ ሲወጣ ክብሩን ያጣል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን በመታተዝ በንግስና እንዲኖር ተፈጥሮአል፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ፈቃድ ሲስተው ከንግስናው ይሻራል፡፡
ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ኦሪት ዘፍጥረት 2፡17
3.     ስልጣናችን ያለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በማድረግ ውስጥ ነው፡፡ የሰው ስልጣን የሚመነጨው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ነገሮችን ሊገዛ የሚችለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ በማድረግ ለእግዚአብሄር ሲገዛ ብቻ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሲያጣው ስልጣኑን ያጣል፡፡ ሰው የእግዚአብሄር ፈቃድ መከተል ቸል ሲል ነገሮች ቸል ይሉታል፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከመከተል ሲመለስ ነገሮች እርሱን ከመስማትና ከመታዘዝ ይመለሱበታል፡፡ 
ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ። ኦሪት ዘፍጥረት 4፡12
4.     ጥበቃችን ያለው የእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ከማንኛውም የመድህን ድርጅት በላይ አስተማማኝ መድን ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ከሰይጣን በላይ ሃያል ነገር ነው፡፡ ሰይጣን ብዙ ነገሮችን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰይጣን የእግዚአብሄርን ፈቃድ የያዘ ሰው ሊቋቋም አይችልም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚከተል ሰው ሰይጣንና በሰይጣን የሚመራ ሰው ሊያስቆመው አይችልም፡፡
በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፡5
5.     ሰው በህይወቱ እውነተኛን ፍሬን የሚያየው በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ በመቆይት ብቻ ነው፡፡ ሰው በተለያየ ነገር ውስጥ ሊወጣና ሊወርድ ይችላል፡፡ ሰው ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካላገኘና ካላደረገው በስተቀር እውነተኛ ፍሬያማነት የህልም እንጀራ ነው፡፡
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል። የዮሐንስ ወንጌል 15፡5፣8
6.     የደስታና የእርካታ ስሜታችን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ከመኖር ብቻ ይመጣል፡፡ እውነት ነው ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሲያደርግ በከፍታና በዝቅታ ያልፋል፡፡ ነገር ግን ህይወቱን መልስ ብሎ ሲያየው ለእግዚአብሄር በሚገባ የተኖረ ህይወት ብሎ መደሰትና መፈንደቅ የሚችለው የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው ብቻ ነው፡፡ እውነተኛን ደስታን የሚያጣጥመው ፈቃዱን የሚያደርግ ሰው ብቻ ነው፡፡ ምንም ዋጋ ቢያስከፍል እውነተኛን እርካታን የሚረካው ፈቃዱን የሚያደርግ ሰው ብቻ ነው፡፡  
ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” መጽሐፈ መክብብ 2:25
ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። ትንቢተ ኢሳይያስ 54፡13
7.     ፈቃዱን የሚከተል ሰው የእግዚአብሄር ጥበብ ይሰጠዋል፡፡
የእግዚአብሄር ጥበብ የሚሰራው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለሚከተል ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ የሚደግፈው እግዚአብሄርን ፈቃድ የሚኖርን ሰው ነው፡፡ እግዚአብሄር ስንፈተን መውጫውን የሚያዘጋጀው በፈቃዱ ወሰጥ ስንኖር ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስንከተል የእግዚአብሄር ጥበብ ሙሉ ለሙሉ ከእኛ ጋር ለእኛ ጥቅምና ማሸነፍ ይሰራል፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። የያዕቆብ መልእክት 1፡2-3፣5
8.     ፈቃዱን የሚከተል ሰው ብቻ ነው ዘላለለማዊ ቅርስን የሚተወው፡፡ ጊዜያዊና ምድራዊ ነገርን አድርገን ህይታችንን በከንቱ ማሳለፍ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ዘላለም የሚያስተጋባ ዘላቂን ነገርን የምናደርገው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስናደርግ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካላደረገና ለሚጠፋ መብል ለከንቱነት እንሰራለን፡፡
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። የዮሐንስ ወንጌል 6፡27
9.     የእግዚአብሄርን ህልውና የምናረጋገጥው በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ በመኖር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር አብሮን ካለ ደግሞ ምንም ሌላ ነገር አያስፈልገንም፡፡
ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የዮሐንስ ወንጌል 14፡23
10.    አክሊልን የምንሸለመው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስንከተል ብቻ ነው፡፡
በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡12
ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡12-15
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ህልውና #አብሮነት #ደስታ #እርካታ #ሰላም #ጥበቃ #ቅርስ #ሽልማት #አክሊል #ፀሎት #ልመና #እንዲሰማን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ምስጋና

Tuesday, September 24, 2019

የምታስበው ክፉ ሀሳብ ይታያልብዙ ሰው የሚያስበው አሳብ በሌላ ሰው እንደሚታይ አያስብም:: እግዚአብሄር ወደአእምሮህ የመጣውን አሳብ በአጭሩ የቀጨኸውን ሃሳብ ያስተናገድከውንና በውስጥህ የበቀለውን እና ፍሬ ያፈራውን አሳብ ሁሉ ያያል ያውቃል፡፡
መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት። ኦሪት ዘፍጥረት 4፡7
ብዙ ሰው የሚያስበው አሳብ በሌላ ሰው እንደሚታይ አድርጎ አይጠነቀቅም:: ብዙ ሰው ሃሳቡ እንደማይታይ አድርጎ ስለሚኖር ብዙ ጊዜ ችግር ውስጥ ይገባል::
ሰው የሚኖረው ያሰበውን አሳብ ነው፡፡ ሰው የሚተገብረው ያሰበውን አሳብ ነው፡፡
በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ መጽሐፈ ምሳሌ 23፡7
ያሰብነውን ስለምንኖረው በእኛ ውስጥ ያስተናገድነው አሳብ ሁሉ ይታያል::
እውነት ነው ወደአእምሮዋችን የሚመጣ ሃሳብ ሁሉ አይታይም:: ነገር ግን የምናስተናግደው ሃሳብ ይፍጠንም ይዘግይም ይታያል:: ወደ አእምሮዋችን ሲመጣ እንደቆሻሻ ቆጥረን እሽቀንጥረን ከአእምሮዋችን የማናስወጣው ክፉ ሃሳብ በሰው ዘንድ ይታያል ያዋርደናል::
ወደአእምሮዋችን የሚመጣውን የንቀት ሃሳብ በፍጥነት በእንጭጩ ካልቀጭነው ወደድንም ጠላንም በዝንባሌያችንንና በአመለካከታችን ይንፀባረቃል:: ስለሌላው ሰው የንቀት ሃሳብ ሲመጣልን ደስ ከተሰኘንበት ካስተናገድነውና ካሰላሰልነው በአመለካከታችን ይንፀባረቃልሸ  
አንዳንድ ሰዎች ስለክፉ ንግግራቸው ስለዝንባሌና አመለካከታቸው መነሻ ችግር ከስር መሰረቱ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ከንፈራቸው ላይ ሊያስተካክሉ ይፈልጋሉ::
ችግሩ ክፉ ሃሳብ በንግግርም ባይታይ በአመለካከት ይታያል:: ክፉ ሃሳብ በአመለካከት ባይታይም በንግግር ይታያል፡፡
የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም ይባላል:: እውነት ነው የንግግር ስህተት አይስተካከልም:: የአፍ ወለምታ የአስተሳሰብ ወለምታ ማሳያው ነው:: ንግግር የአስተሳሰብ መስታወት ነው:: ዛፍ የሚቃናው በችግኝነት ደረጃ እንደሆነ ሁሉ ንግግር የሚስተካከለው በሃሳብ ደረጃ  ብቻ ነው::
ሃሳባችንን እንደፈለግን ለቀነው በእግዚአብሄር እውቀት ላየ የሚነሳውን የሰውን ሃሳብ ካላዋረድነው ሃሳብ ይታያል፡፡
የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡5
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አመለካከት #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Sunday, September 22, 2019

ሁልጊዜ የፀሎት መልሳችንን የምንቀበልባቸው አምስቱ ጥበቦችከልባችን የፀለይናቸው ፀሎቶች ሁሉ ተመልሰዋል፡፡
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የማቴዎስ ወንጌል 7፡7
የሚለምነውም ሁሉ ይቀበላል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር መንገድ እንጂ በእኛ መንገድ አንቀበልም፡፡ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሄር ጊዜ እንጂ በእኛ ጊዜ አናገኝም፡፡ ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል፡፡ ነገር ግን የሚከፈትልን በእኛ ሁኔታ ሳይሆን በእግዚአብሄር ሁኔታ ነው፡፡
የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። የማቴዎስ ወንጌል 7፡8
1.      እግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን በእርግጥ ይመልሳል፡፡ እግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን በችኮላ አይመልስም፡፡ እግዚአብሄር ፀሎታችንን በጊዜው እንጂ በችኮላ አይመስለስም፡፡ እግዚአብሄር ማንም አይቀድመውም፡፡ እግዚአብሄር ጊዜ አያልፍበትም፡፡ እግዚአብሄር ከአላማው ጋር እንጂ ከጊዜ ጋር አይሮጥም፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ነገር ስለሚያይ እኛ እንደምንቸኩል አይቸኩልም፡፡ እግዚአብሄር እኛ በቸኮልንበት ጊዜ የፀሎት መልሳችንን በችኮላ ስላልመለሰ ያልተመለሰ ሊመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚለምነው ሁሉ በጊዜውና በሰአቱ በእግዚአብሄር መንገድ ይቀበላል፡፡
ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥ እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? የሉቃስ ወንጌል 18፡1፣7፣8
2.     የፀሎት ምለሳችን ሁሉ ይመጣል፡፡ ነገር ግን የፀሎት መልሳችን በጣም በጓጓን ጊዜ ላይመለስ ይችላል፡፡ ለፀሎት መልሳችን በጣም መጓጓት አይናችንን ከእግዚአብሄር ላይ አንስተን የፀሎት መልሳችን ላይ እንድናደርግ ያደርገናል፡፡ ለፀሎት መልሳችን በጣም መጓጓት የፀሎት መልሳችንን ጣኦት እንድናደርገው ያደርገናል፡፡ ለእግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን ለመመለስ ትክክለኛው ጊዜ ከመጠን ያለፈ መጓጓታችን ሲበርድልን ነው፡፡ እግዚአብሄር አንዳንዴ ፀሎታችንን የሚመልሰው ከመጠን ያለፈ ጉጉታችንን ከጨረስን በኃላ ነው፡፡ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላል ነገር ግን የለመንነውን ሁሉ ከመጠን በላይ በጓጓን ጊዜ አንቀበልም፡፡ ከመጠን በላይ መጓጓት የፀሎት መልሳችንን እንደሚገባ እንዳንይዘው ያደርገናል፡፡ ለፀሎት መልሳችን ከመጠን ያለፈ መጓጓት የፀሎት መልሳችንን እንድናመልከው ይፈትነናል፡፡
3.     የፀሎት መልሳችን በቅንጦት አይመለስም፡፡ እግዚአብሄር የሚያቀርበው እንደፍላጎታችን መጠን ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ፍላጎት ባለብን የህይታችን ክፍል በብዙ እንቀበላለን፡፡ ብዙ ፍላጎት በሌለን በህይወታችን ክፍል በብዙ አንቀበልምን፡፡ ብዙ ፍላጎት ላለበት ሰው እግዚአብሄር በብዙ ያቀርብለታል፡፡ ጥቂት ፍላጎት ላለለው ሰው በብዙ አያቀርብም፡፡ እግዚአብሄር በብዙ ካቀረበለን አሁንም ባይሆን ወደፊት ብዙ ፍላጎት እየመጣ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከላቀረበ ፍላጎት የለብንም ማለት ነው ብለን ማመን እና እግዚአብሄርን ማመስገን አለብን፡፡ ቀድሞ እንኳን ብዙ ካቀረበ ብዙ ፍላጎት እየመጣ ነው ብለን ለወደፊት ማስቀመጥ እንጂ ሁሉንም አቅርቦት በምቾቶቻችን መክፈል ወይም በቅንጦት ላይ ማዋል የለብንም፡፡
ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡3
4.     የፀሎት መልሳችን ሞቲቫችን ሲጣራ ይመልሳል፡፡ ብዙ ጊዜ ስንፀልይ በሁለት መነሻ ሃሳቦች እንፀልያለን፡፡ አንዱ በፀሎት መልሳችን እግዚአብሄርን የማክበር ንፁህ የልብ መነሻ ሃሳብ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከሌላው ሰው መብለጥ ታዋቂ መሆን ባለጠጋ መሆን ወይም ደግሞ ከሰው ሁሉ በልጦ ሃያል መሆን ነው፡፡ እግዚአብሄር የፀሎት መልሳችንን በእኛ ጊዜ ሳይሆን በራሱ ጊዜ ሲመልስ ንፁህ ያልሆነው የልባችን መነሻ ሃሳብ ከቀነሰ በኃላ ነው፡፡ ስጋችን የፀሎት መልሳችን እንዲመልስ የሚፈልገው ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅም ሳይሆን ለራሱ ምቾት ነው፡፡ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል ነገር ግን ብዙ ጊዜ የፈለግነውን ሁሉ እንዳለገኘን የሚሰማን የስጋ መነሻ ሃሳባችን ከጠፋ በኃላ የጸሎት መልሳችን ስለሚመለስ ነው፡፡
ሃና ልጅ የምትፈልገው የልብዋ መነሻ ሃሳብ ለእግዚአብሄር መልሳ ለመስጠት ሲሆን እግዚአብሄር መለሰላት፡፡
እርስዋም፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 1፡11
5.     የፀሎት መልሳችን ካደግን በኃላ ይመለሳል፡፡ ክርስቶስን የምንከተል ሁላችንም በየቀኑ እያደግን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የፀሎት መልሳችን እንዳልተመለሰ የሚሰማን ከፀሎት ጥያቄው አልፈን ወደሌላ የፀሎት ጥያቄ ውስጥ ከገባን በኃላ ስለሚመለስ ነው፡፡ እኛ ህይወታችን አድጎና የፀሎት ጥያቄያችን አድጎ ወደሌላ ከፍ ወዳለ የፀሎት ጥያቄ ውስጥ ከገባን በኃላ የበፊቱ የፀሎት መልሳችን ስለሚመጣ ያልተመለሰ ይመስለናል፡፡ የሚፈልገውም ያገኛል፡፡ የቀድሞውን የፀሎት ርእሳችንን አልፈን ሌላ ነገር በመፈለግ ላይ ስለተጠመድን የመጀመሪያውን የፀሎት መልስ ያገኘን  አይመስለንም፡፡
አብዝተን እንድንቀበል አብዝተን እንለምን፡፡ መቼ እንደምናገኝ ሳናስብ አብዝተን እንፈልግ፡፡ እንዴት እንደሚከፈት ሳንጨነቅው አብዝተን አናንኳኳ፡፡  
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። የማቴዎስ ወንጌል 78
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ለምኑ #ፈልጉ #አንኳኩ #ይቀበላል #ያገኛል #ይከፈትለታል #ቃል #ብልፅግና #ሃብት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርቃል  #የእግዚአብሔርፈቃድ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, September 18, 2019

ህይወታችን እንዳልተለወጠ ሲሰማን ማድረግ ያለብን 5 ነገሮችሁላችንን በየጊዜው ህይወታችን እንደቆመ እንደሚገባው እንዳልተራመድን እያደግን እየተለወጥን እንዳይደለ ይሰማናል፡፡ የእስራኤል ህዝብ በእግዚአብሄር ላይ እልከኛ በመሆንና ባለመታዘዝ አርባ አመት ሙሉ አንድን ተራራ ሲዞሩ ኖረዋል፡፡ እኛም በተለያየ ጊዜ እንደ እስራኤላዊያን የሴይርን ተራራ እንደምንዞር ፣ ህይወታችን ለውጥ አልባ እንደሆነና ህይወታችን እርምጃ እንደሌለው ሲሰማን ማድረግ ያለብን 5 ነገሮች
1.      በጌታ ፊት ጊዜ መውሰድ
እርምጃችን በእውነት መቆሙን ለማረጋገጥ በጌታ ፊት ጊዜ መውሰድ ይጠይቃል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ መሰማቱ ብቻ እርምጃችን በእውነትም መቆምሙን ሊያረጋጋጥ አይችልም፡፡ እርምጃችን እንደቆመ መሰማቱ መቆማችንን ሊያሳይ ወይም ደግሞ ላያሳይ ይችላል፡፡ ስለዚህ በህይወታችን እርምጃ ማጣት ሲሰማን እውነት እድገቴ ቆሟል ወይስ አልቆመመ ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ያለመራመድ ፣ ያለማደግና ያለመለወጥ ስሜት በሚሰማን ጊዜ የእግዚአብሄርን ፊት መፈለግፍ ወርቃማ አጋጣሚ ነው፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እግዚአብሄር ትኩረታችን ፈልጎና ከእኛ ጋር ህብረትን ለማድረግ ናፍቆን ሊሆን ይችላል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እርሱን በግል እንድንፈልገው ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እግዚአብሄር ወደሚቀጥለው የህይወታችን ምእራፍ ሊያሻግረን መለወጥ ያለብንን ነገር እንድንለውጥ ፈልጎ ሊሆን ይችላል፡፡ እርምጃችን እንደቆመ ሲሰማን እግዚአብሄር የነበርንበት የህይወት ምእራፍ በመዝጋት ስለሚቀጥለው የህይወት ምእራፍ እርሱን እንድንፈልገውና ምሪትን እንድንቀበል ምልክት እየሰጠን ሊሆን ይችላል፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛለችሁ፥ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፥ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11-13
2.     በእግዚአብሄር ቃል ራሳችንን ማየት
መራመድ እንዳቆምን የተሰማን እውነትም እድገታችን ቆሞ ሊሆን ይችላል፡፡ እድገትን ሊያቆም የሚችለውና ከእግዚአብሄር ጋር ያለንንን ግንኙነት እና ህብረት የሚያበላሸው ሃጢያት እና አለመታዘዘ ነው፡፡ እግዚአብሄር የመራንን መሪት ሳንከተል ሌላ ምሪትይ እንዲሰጠን መፈለግ አንችልም፡፡ እግዚአብሄር ያዘዝንን ትእዛዘ በእምነት ሳንፈፅጽም ህይወታችን እንዲለወጥ መጠበቅ የለብንም፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክለውን እምነታችንን ሳንጠቀም እምነት እንዲጨምርልን መፀለይና እምነት እንዳልጨመርን ሊሰማን አይገባም፡፡
ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። የሉቃስ ወንጌል 17፡5-6
እግዚአብሄር ያስረዳንን የእግዚአብሄርን ቃል ወተት መረዳት ሳንታዘዝ ጠንካራ ምግብ ለመመገብ መሞከር አይቻልም፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ልባችንን በመፈተሽና እርምጃችንን በእግዚአብሄር ቃል በመመርመር እየተራመድን ከሆነ ቆመን ከሆነ እግዚአብሄርን በማመስገን በዚያው መቀጠል ይገባናል፡፡ በእግዚአብሄር ቃል ራሳችንን ስንፈትሽ የሳትነው ነገር ካለ በእግዚአብሄር ፊት ሃሳባችንን ለውጠን የእግዚአብሄርን ቃል ለመታዘዝ መወሰን አለብን፡፡
ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። የያዕቆብ መልእክት 1፡22
3.     የእግዚአብሄርን እርምጃ መታገስ
እርምጃችን እንደቆመ እና ህይወታችን እንዳልተለወጠ ሲሰማን ስለእግዚአብሄር አሰራር ያለንን አመለካከት መፈተሽ አለብን፡፡ እግዚአብሄር አይቸኩልም፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። መጽሐፈ ምሳሌ 2820
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። መጽሐፈ ምሳሌ 1311
እግዚአብሄር ነገሮችን የሚያደርገው በራሱ ጊዜ እንጂ በእኛ ጊዜ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር መልካም አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ነገሮችን ውብ የሚያደርገው በጊዜው ነው፡፡
ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ መጽሐፈ መክብብ 3፡1፣11
ከእኛ የሚጠበቀው በጊዜው መልካም ማድረግ ፣ መልካምን በማድረግ አለመታከትና እንዲሁም መታገስና መጠበቅ ነው፡፡
ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡9
የእግዚአብሄር ፈቃድን ካደረግን በኃላ እንኳን የተሰጠንን የተስፋ ቃል እስክናገኝ መፅናት አለብን፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድን ስላደረግን ብቻ እግዚአብሄር ነገሮች ከመቀፅበት ይሆኑልናል ብለን ካሰብን እንሳሳታለን፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ወደ ዕብራውያን 10፡36
4.     ስለደረስንበት ደረጃ እግዚአብሄርን ማመስገን
ብዙ ጊዜ ህይወታችን እድገት እንደሌለው የሚሰማን ልንሄድበት የምንፈልገውንና ያለንበትን ደረጃ ስናነፃፅር ብቻ ነው፡፡ እውነት ነው የምንሄድበትንና ያለንበትን ማነፃፀር መልካም እና አስፈላጊም ነው፡፡  ነገር ግን የመጣንበትንና ያለንበትን ስናስተያይ ደግሞ ምን ያህል ህይወታችን እንደተለወጠ እናስተውላለን፡፡ ቀድሞ የነበርንበትንና አሁን ያለንበትን ስናስተያይ አሁን እየኖርነው ያለነው ህልማችንን እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ የነበርንበትንና ያለንበትን ደረጃ ስናነፃፅር አሁን ያለንበትን ደረጃ ከጊዜ በፊት ሊደረስበት የማይችል የመሰለን እንደተራራ የገዘፈብን የህይወት ደረጃ እንደነበረ እናስተውላለን፡፡
ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡17-18
5.     እየታዘዝነው ያለውን የእግዚአብሄርን ቃል በመታዘዝ መቀጠል  
ህይወታችን ካለ እድገት እንደቆመ ሲሰማን እየታዘዝነው ያለውን የእግዚአብሄርን ቃል በመታዘዝ መቀጠል ይኖርብናል፡፡ እድገት የሚመጣው ጥቃቅን የሚመስሉ የእለት ተእለት ተደጋጋሚ ነገሮችን በፅናት በማድረግ ነው፡፡ እውነተኛ እድገት የሚመጣው ከውስጥ ወደ ውጭ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ከሰማን ከታዘዝንና ከፀናንበት እድገትና ለውጥ የማይቀር ነገር ነው፡፡
በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። የሉቃስ ወንጌል 8፡15
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ጌታ #ኢየሱስ #ፅናት #መጠበቅ #ምስጋና ##ሃሳብ #ቃል #እግዚአብሄር #መንፈስቅዱስ #ንስሃ #መለወጥ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አእምሮ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ