Popular Posts

Wednesday, April 27, 2016

እኛም ተነስተናል

ትንሳኤ ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ ብዙ ሰዎች የትንሳኤን ትርጉምና ከእኛ ህይወት ጋር ያለውን ተዛምዶ በፍፁም አይረዱትም፡፡ በዚያም ምክኒያት የትንሳኤን ሙሉ ጥቅም በህይወታቸው ተጠቃሚ መሆን አይችሉም፡፡

ለአንዳንዶች የአመት አንድ ቀን ብቻ ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ እየሱስ ስለሃጢያታችን ይቅርታ ከሙታን የተነሳበት ቀን ነው፡፡

የትንሳኤው አላማ ይህንን የሚያጠቃልልም ቢሆንም ከዚህ ሁሉ ግን ያለፈ ትርጉም አለው፡፡ እየሱስ በመስቀል የሞተውና በሶስተኛ ቀን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው የሃጢያታችንን ዋጋ ለመክፈል ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ ከሃጢያት በላይ ሆነን እንድንኖር ይህን የሃጢያት ስጋችንን በመስቀል ላይ ለመስቀልና ለመግደል ነው፡፡

እየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞትና ሲነሳ እኛም ለሃጢያት ሞተን ለእግዚአበሄር ፅድቅ ህያዋን እንድንሆን ራሳችነነ በእምነት እንድናስተባብር ነው፡፡

እየሱስ በመስቀል ላይ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ያደረገው ለራሱ አልነበረም፡፡ እየሱስ በመስቀል ላይ የሞተውና የተነሳው ለእኛ ነው፡፡ እየሱስ ይህንን ሁሉ ያደረገው እኛን ተክቶ ነው፡፡ እየሱስ ሲሞትና ሲነሳ የእኛን ታሪክ እየሰራው መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡
እየሱስ ሲሞት የሞትኩት እኔ ነኝ ብለን መውሰድ እየሱስ ሲነሳ እኔም ከእርሱ ጋር ተነስቻለሁ ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡
እየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የእኛ የሃጢያት ስጋ ከእየሱስ ስጋ ጋር አብሮ ተሰቅሎዋል ፡፡ እየሱስ ሲሞት የሃጢያት ስጋችን አብሮ ሞቷል፡፡
የስቅለቱ ታሪክ የእየሱስ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የእኛም ታሪክ ነው፡፡ በዚህ በእግዚአብሄር አሰራር እየሱስ ሲሞትና ከሞት ሲነሳ በእኛም ህይወት ውስጥ የተከናወነ ነገር አለ፡፡ ይህም፡-
  • 1.ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለናል፡፡


ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ገላትያ 2፡20

  • 2.     ለሃጢያት ሞተናል

ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን? ሮሜ 6፡2

  • 3.     ከሃጢያት እስራት ነፃ ወጥተናል

ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። . . . አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። ሮሜ 6፡18 እና 22

  • 4.     ሃጢያት በእኛ ላይ ስልጣን የለውም

ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። ሮሜ 6፡14

  • 5.     በአዲስ ህይወት ለመመላለስ ከሞት ተነስተናል፡፡

እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሮሜ 6፡4

  • 6.     የፅድቅ ባሪያዎች የእግዚአብሄር አገልጋዮች ተደርገናል

አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። ሮሜ 6፡22

  • 7.     ለሃጢያት ሙት ለእግዚአብሄር ህያዋን ነን

እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደ ሞታችሁ፥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ ራሳችሁን ቁጠሩ። ሮሜ 6፡11

Tuesday, April 26, 2016

የትንሳኤው ሃይል ለእኛ ነው

ሰዎች ለምዕተ አመታት ሞት የበለጠ ኃይልን ሲፈልጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም አልተሳካላቸውም፡፡  ሞት እጅግ ታላቅ ሃይል ስላለው የቱም ሰብዓዊ ፍጡር ለሞት መድሃኒት ሊያገኝለት አልቻለም፡፡

የምስራች!

ኢየሱስ ከሙታን ሲነሳ ሃያሉ ሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ተነሳ፡፡ በምድር ላይ በወቅቱ በጣም ኃያል የነበረውን ሞትን ስላሸነፈ የትንሣኤ ኃይል ከታላላቅ ሃይላት ሁሉ በላይ ልዕለ ሃያል ሊሆን በቅቶዋል፡፡  

እየሱስ ከሙታን በመነሳቱና ሞት በህይወት ስለተረታ አሁን በትንሳኤው ሃይል በማመን  ከእግዚአብሄር ጋር በህያውነት ለዘላለም  መኖር እንችላለን፡፡

ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ሮሜ 10፡9-10

እየሱስ የሞተው ስለራሱ ሃጢያት አይደለም፡፡ እየሱስም ከሞት የተነሳው እኛን ከሞት ሃይል በላይ ለማድረግ ነው፡፡ እየሱስ ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሳ ስናምን ይህ የትንሳኤ ሃይል በህይወታችን መስራት ይጀምራል፡፡ ኢየሱስ ከሞት ተነሳው እኛ ይህንን የትንሳኤ ሃይል እንድንለማመድ ነው፡፡

እየሱስን ባመንን በሁላችን ውስጥ ከሙታን በሃይል የተነሳው እየሱስ ይኖራል፡፡ እየሱስን ከሙታን ያስነሳው ያው ተመሳሳይ ሃይል በእኛ ውስጥ ይሰራል፡፡ እየሱስ በመንፈስ በልባችን የሞኖረው ከዚህ የትንሳኤ ሃይል ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ነው፡፡ እየሱስ በልባችን ስለሚኖር ከአሸናፊዎች በላይ ነን፡፡

በኢየሱስ ትንሳኤ "ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ" የሆነ ሃይል ታይቶዋል፡፡ ኤፌሶን 1፡20-2

ኢየሱስ በትንሳኤ የጠላትን ሃይል ሁሉ አሸንፎታል፡፡

መፅሃፍ ቅዱስ ስለ እየሱስ የጠላትን ሃይል ሁሉ ፈፅሞ ስለማሸነፍ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡

አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ 2:15

እኛም በትንሳኤ ከእየሱስ ጋር ተነስተናል፡፡ በሰማያዊ ስፍራ ከክርስቶስ ጋር በአብ ቀኝ ተቀምጠናል፡፡

ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ኤፌሶን 2፡6

እየሱስን ከሙታን ባስነሳው በእግዚአብሄር አሰራር ያመንን ሁላችን ከእየሱስ ጋር ተነስተናል፡፡ እየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ እኛንም በሰማያዊ ስፍራ ከክርስቶስ ጋር በአብ ቀኝ አስቀምጦናል፡፡ በዚህም በሞት ላይ ስልጣን ባለው በዲያቢሎስ ሃይል ሁሉ ላይ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡

እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ሉቃስ 10:19

ቤተ-ክርስቲያን እኛ የእግዚአብሄር ህዝቦች በምድር ላይ አካሉና የእየሱስ ክርስቶስ ሙላት ስለሆንን በእየሱስ የሚሰራው የትንሳኤ ታላቅ ሃይል ሁሉ ለእኛ ነው፡፡

ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው። ኤፌሶን 1፡18-22

Sunday, April 24, 2016

የሰላም እንቅፋት

ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ዮሃንስ 14፡27
ነገር ግን እኛ ነን ሰላማችንን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለብን ፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ እኛ ይህንን የተሰጠንን ሰላም እንዴት መጠበቅ እንዳለብን የሚያስተምረን፡፡

ሰላማችንን ሊሰርቁ የሚመጡ የሰላማችን ጠላቶች አሉ እነርሱም፡-

·        እግዚአብሄር እየመራን እንደሆነ አለማወቅ፡፡

እግዚአብሄርን በሁለንተናችን መከተል የልባችን መሻት ስለሆነ የእግዚአብሄርን ምሪት የሳትን ሲመስለን ሰላማችን ይሰረቃል፡፡ እግዚአብሄር ግን አሁንም እየመራን ነው፡፡ የእግዚአብሄር መሪነት አስተማማኝነቱ ከተመሪዎቹ ከእኛ ችሎታ ሳይሆን ከመሪው ከእግዚአብሄር የመምራት ችሎታ ነው፡፡ ከእኛ መስማት ብቻ ሳይሆን ከእርሱ የመናገር ችሎታ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪያችን ነው፡፡ የመረዳታችንንና የቋንቋ ችሎታችንን እንዴት እንደሚናገረን ያውቀዋል፡፡ በርሱ ደረጃ ሳይሆን በእኛ ደረጃ ወርዶ ነው የሚናገረን፡፡ ስለዚህ ፈቃዱን ለማድርግ እየወደድን እግዚአብሄን አንስተውም፡፡

ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል።ዮሃንስ 7፡17

የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፡፡       ዮሃንስ 10፡4 እኛ በጎች እንጂ ፍየሎች አይደለንም፡፡

·        ጆሮን ለሰይጣን መስጠት

ጆሮዋችንን ለሰይጣን ውሸትና ማስፈራሪያ ስንሰጥና ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ የሆነን ወሬ ስንሰማ ሰላማችን ይሰረቃል፡፡
በአለም ላይ መሰማት የሚመኙ ካልሰማሀን እያሉ የሚያስፈራሩ ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ ለነዛ ድምፆች ጆሮዋችንን ከሰጠን ሰላማችን ይወሰዳል፡፡ ሁሌ ጆሮዋችንንና ልባችንን መስጠት ያለብን ለእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡  
አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ኤርሚያስ 11፡4

በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ፊልጵስዩስ 4፡8-9

·        እግዚአብሄር ለእኛ ግድ እደሚለው አለማወቅ፡፡

ሰው ሁሉንም ነገር በራሱ እንዲሚያደርግ ሲሰማው ለማድረግ አቅሙ ስለሌለው ሰላሙ ይወሰዳል፡፡ እግዚአብሄር ስለእኛ ህይወት ግድ ይለዋል፡፡ እንዲያውም እግዚአብሄር ከምናስበው በላይ ስለ ዝርዝር የህይወት ጉዳያችን ይጠነቀቃል ግድም ይለዋል፡፡

እንዲያውም የእኛ ሃላፊነት ስለመንግስቱ ግድ መሰኘት ብቻ እንደሆነ እየሱስ ያስተምራል፡፡ ስለእኛ ግድ መሰኘትን  እግዚአብሄር የራሱ ስራ አድርጎ ወስዶታል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ እኛን መንከባከብ ያውቅበታል፡፡ እኛን በሚገባ ለመንከባከብ ምንም አስተማሪና አማካሪ አይፈልግም፡፡


ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።ማቴዎስ 6፡32-33

·        የአለም ከንቱ ውድድር

በአለም ውድድር ውስጥ ገብተን ከሚያስፈልገን መሰረታዊ ፍላጎት ውጭ መኖር ስንሞክር ሰላማችን ይወሰዳል፡፡

እግዚአብሄር ለህይወትና እግዚአብሄርን ለመምሰል የሚያስፈልገንን ሁሉ ሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን ከጎሮቤታችን እንድንበልጥ የሚያስችለንን ነገር አልሰጠንም፡፡ ወይም በአለም የቁሳቁስ (MATERIALISM) ውድድር ውስጥ ገብተን በምቾቶቻችን ለመክፈል የምንፈልገውን ስለማይሰጠንና እግዚአብሄር አብሮን ስለማይቆም በራሳችን ብቻ ስለምንፍጨረጨር ሰላማችንን እናጣለን፡፡

ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም።ያዕቆብ 4፡3
መፅሃፍ ቅዱስ ህይወታችንነ ቀለል አድርገን ጌታን እንድናገለግልና ለሌሎች በረከት አንድንሆን ያስተምረናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ህይወታችንን ከመራን በሰላም እንኖራለን፡፡ የእግዚአብሄርን ሃሳብ በምድር ላይ አድርገን እግዚአብሄርን እናከብራለን፡፡  


ባለጠጋ ለመሆን አትድከም፤ የገዛ ራስህን ማስተዋል ተው። በእርሱ ላይ ዓይንህን ብታዘወትርበት ይጠፋል፤ ባለጠግነት ወደ ሰማይ እንደሚበርር እንደ ንስር ለራሱ ክንፍ ያበጃልና።ምሳሌ 23፡4-5

አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቲዮስ 6፡8

·        እግዚአብሄር ለእኛ እንደሆነ አለማወቅ

እግዚአብሄር ሁሌ ለእኛ መልካምነት ይሰራል፡፡ ብንወድቅ እንኳን እንዴት እንደምንሳ ነው የሚያስበው  ተግቶም የሚሰራው፡፡
እግዚአብሄር ተቀብሎናል፡፡ እግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ እንደተቀበለንና በእኛ ደስተኛ እንደሆነ ካላወቅን ሰላማችን ይወሰዳል፡፡ እየሱስ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ እኛን ለመቀበል አርክቶታል፡፡

በእርግጥ በህይወታችን የማይወደው ነገር ካለ ያሳየናል፡፡ ከዚያ ውጭ እግዚአብሄር በእኛ በልጆቹ ደስተኛ ነው፡፡
እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።2ኛ ቆሮንጦስ 5፡19

·        ትግስት ማጣት

ሌላው እየሱስ ሰላምን ሰጥቶን እያለ ሰላማችንን እንድናጣው የሚያደርገው ነገር የእግዚአብሄርን እርምጃ አለመታገስ ነው፡፡

እግዚአብሄር የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ይሰጠናል፡፡ የሚሰጠን ግን በእኛ ጊዜ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገሮች በፍጥነት እንዲሆኑልን ስንምፈልግና የእግዚአብሄርን ፍጥነት ለመታገስ ራሳችንን ትሁት ካላረግንና በጌታ ላይ ካልተደገፍን ሰላማችን ይወሰዳል፡፡

እግዚአብሄር አመጣጡ የዘገየ ቢመስልም ከእርሱ በላይ ፈጣን ስለሌለ የእግዚአብሄርን ላይ ብንደገፍ በሰላም እንኖራለን፡፡ የእግዚአብሄርን እርምጃ መታገስ ሰላማችንን እንዳናጣ ያስችለናል፡፡

2ኛ የጴጥሮስ 3፡9 ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥

·        ይቅር አለማለት

ሰላማችንን የሚሰርቅ ሌላው ነገር የበደሉንን ይቅር አለማለት ወይም በምህረት አለመመላለስ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ኢነርጂ በተፈጠርንበት በፍቅርና በመልካም ስራ ላይ ከማፍሰስ ይልቅ ከሰይጣን ጋር ተባብረን በሰዎች ጥፋትና ክፋት ላይ እንድናፈሰው ስለሚያደርግ ሰላማችንን ይሰርቃል፡፡ ይቅር ማለት ቀላል አይደለም ነገር ግን ሁሌ ይቅር ማለት ይቻላል፡፡ ይቅር ማለት የስሜት ጉዳይ ሳይሆን የውሳኔ ጉዳይ ነው፡፡ ይቅር ለማለት ከወሰንን በምህረት ለመመላለስ ራሳችንን ማስለመድ እንችላለን፡፡  

ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል። 1ኛ ቆሮንጦስ 10፡13 

እግዚአብሄር ባደረገልን ምህረትና ምን ይቅር ያለንን ስለሚያውቅ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ልንል የምንችልበት ብዙ የምህረት ካፒታል በቂ ጠቀማጭ እናዳለን ይተማመናል፡፡ ይቅር ማለት ከፈለግን እንደምንችል ያውቃል፡፡

ይቅር አለማለት ግን ከእግዚአበሄር ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻል፡፡ ይቅርታ ሰላማችንን እንድንጠብቅ ያደርገናል፡፡



Thursday, April 21, 2016

ከእምነት ጡረታ


በነገር ሁሉ በእግዚአብሄር ላይ እንዳንደገፍ የማያቋርጥ ፈተና አለብን፡፡ እምነት ለስጋ አይመቸውም፡፡ ስጋ የሚፈልገው በስጋ አይን የሚታይ መተማመኛን እንጂ በእግዚአብሄር መታመንን አይደለም፡፡ ስጋ በፍፁም በእግዚአብሄር መታመን  ስለማይፈልግ ሌሎችን አማራጮች ሁሉ ይጠቀማል፡፡  

እየሱስ ስለዘሪው ምሳሌ ሲያስረዳ የእግዚአብሄር ቃል በሙላት ሊሰራባቸው ስላልቻለውና  ሙሉ ፍሬ ማፍራት ስለማይችሉ ሰዎች ችግር ሲናገር እንዲህ ይላል፡-

በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። ሉቃስ 8፡14

በዚህ ቃል Çበሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾትÈ የሚለውን በማርቆስ ላይ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡፡

Çየዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞትÈ ማርቆስ 4፡19

ስጋ ነው ቶሎ ቶሎ ሃብትን አከማችቶ በእግዚአብሄር ላይ ከመታመን ነፃ መውጣት የሚፈልገው፡፡

ሰው በአለም ላይ ያለው ገንዘብ ሁሉ ቢኖረው ህይወት ይኖረዋል ማለት አይደለም፡፡ በህይወት ገንዘብ  የማይሰራቸው እጅግ በጣም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እንዲያውም በህይወት በጣም ወሳኝ ነገሮች ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችላቸው ነገሮች አይደሉም፡፡

ሰው ሙሉ በሙሉ በሁሉም የህይወቱ አቅጣጫ በእግዚአብሄር ላይ እንዲደገፍ ዲዛይን ስለተደረገና ስለተሰራ በሁሉም የህይወቱ አቅጣጫ ሁል ጊዜ እግዚአብሄር ያስፈልገዋል፡፡    

የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል፦ አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። እርሱም፦ ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፦ አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። እግዚአብሔር ግን፦ አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ሉቃስ 12፡15-21


ይህ ባለጠጋ እግዚአብሄርን ከመታመን ለመገላገል ንብረትና ሃብት አከማችቶዋል፡፡ የሰው ህይወቱ በገንዘቡ ብዛት ስለመሰለው በእግዚአብሄር ላይ ከመታመን ጡረታ ለመውጣት ቸኩሎዋል፡፡  

የሰው ህይወቱ ግን በገንዘቡ ብዛት አይደለም፡፡ ትንሽ ገንዘብ ያለው ትንሽ ህይወት የለውም፡፡ ብዙ ገንዘብ ያለው ብዙ ህይወት የለውም፡፡ ብዙ ገንዘብ ያለው ትንሽ ህይወት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሰው ደግሞ ትንሽ ገንዘብም ኖሮት ብዙ ህይወት ሊኖረው ይችላል፡፡ የሰው ህይወቱ በገንዘቡ ብዛትና ማነስ አይወሰንም፡፡

ይልቁንም የሰው ህይወቱ በገንዘቡ ብዛት ሳይሆን በእምነቱ ብዛት ነው፡፡  

ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ዕንባቆም 2:4

ሰው ግን የተፈጠረውና ዲዛይን የተደረገው በሁሉ ነገሩ በእግዚአብሄር ላይ ብቻ እንዲታመን ነው፡፡

ስለዚህ ነው የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ ማቴዎስ 6:11 በማለት እንድንፀልይና በየእለቱ በእግዚአብሄር ላይ እንድንደገፍ የሚያስተምረን፡፡

መቼም ቢሆን በእግዚአብሄር ላይ ያለንን እምነት በሚታይ ነገር መለወጥ የለብንም፡፡ እንዲያውም ከጊዜ ወደጊዜ በእግዚአብሄር ላይ ያለንን መታመናችንን ማብዛት ነው የሚገባን፡፡

ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። ሮሜ 1፡17

Wednesday, April 13, 2016

ፍቅር ምርጫ ነው

ፍቅር ስሜት አይደለም፡፡ ፍቅር ከሆነ ቦታ መጥቶ የሚይዘን ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር በራሱ ጊዜ የሚመጣ በራሱ ጊዜ የሚሄድ ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር የምንወድቅበት ከዚያ ደግሞ የሚለቀን ነገር አይደለም፡፡

ፍቅር ውሳኔ ነው፡፡ ፍቅር ምርጫ ነው፡፡ ፍቅር በመረዳት የምንከተለው ነገር ነው፡፡

እራሱ ፍቅር ነው የተባለውም እግዚአብሄር ፍቅርን ያሳየን እንደዚህ ነው፡፡ ጠላቶች ሳለን ወደደን፡፡ የቁጣ ልጅ በነበርን ጊዜ ይቅር አለን፡፡ እግዚአብሄርን በምንጠላው ጊዜ ልጁን ለእኛ እንዲሞት ላከልን፡፡

ሮሜ 5፡8 ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።

ፍቅር ለሌላው መስራት ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን ማገልገል ነው፡፡ ፍቅር በሌላው ላይ ዋጋን /value/ መጨመር ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን ማንሳት ነው፡፡ ፍቅር ሌላውን መጥቀም ነው ፡፡ ፍቅር ሌላውን ማሳደግ ነው፡፡ ፍቅር ለሌላው መትጋት ነው፡፡

በአጭሩ ፍቅር በመረዳት ከሌላው ጋር ራስን ማስተባበር የስሜዝት ጉዳይ አይደለም፡፡ Love is identifying yourself with the other in understanding.

በእውነት ለመውደድ ከወሰንን እንችላለን፡፡

ያ ፍቅር የተባለው እግዚአብሄር ፍቅርን በልባችን በመንፈስ ቅዱስ ስላፈሰሰ ሰውን ሁሉ መውደድ እንችላለን፡፡

ሮሜ 5፡5 በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።


ላለምወደድ ደግሞ ምንም ሰበብ የለንም፡፡ ፍቅር ይቻላል፡፡

Saturday, April 9, 2016

እመን ብቻ እንጂ አትፍራ!


በክርስትና ጉዞ እግዚአብሄር ወዳየልን የህይወት ስፍራ ለመግባትና የእግዚአብሄርን አላማ ፈፅመን እርሱን ለማክበር እንዳንችል የሚያስፈራሩ ከጉዞዋችን ሊያስቀሩን የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

እነዚህን ብዙ ነገሮች መስማትና መከተል እንደሌለብን ይልቁንም ማድረግ ያለብንን እየሱስ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡፡ 

እመን ብቻ እንጂ አትፍራ

በህይወታችን ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ልንሰጠው የማይገባው ነገር ፍርሃት ነው፡፡ በልባችን ስፍራ ልንሰጠው የማይገባው ነገር ጭንቀትና ፍርሃት ነው፡፡ 

በህይወታችን ደግሞ ጊዜያችንን ልናሳልፍበትና በትጋት ልንገነባው የሚገባው ነገር እምነትን ነው፡፡በህይወታችን ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ነገር እምነት የሚመጣበትን የእግዚአብሄርን ቃል መስማት ነው፡፡  በህይወታችን ልንመካበት ደስ ልንሰኝበት ልንጓደድበት የሚገባው ነገር እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ፈቃዱን ነው፡፡ በህይወታችን ልባችንን ልንጥልበት በሙሉ ልባችን ተስፋ ልናደርገው የሚገባው ነገር የእግዚአብሄርን ቃል ነው፡፡

ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ሌሎቹንእኛን ስማን ተከተለንካለበለዚያ “ወዮልህ ጠፋህ ተበላህ” የሚሉትን ብዙ ድምፆች ትተን እግዚአብሄር  ስለህይወታችን ያለውን አላማ በቃሉ በማግኘት ቃሉን መቀበልና በእምነት መኖር ብቻ ነው ፡፡

እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፡፡ ማርቆስ 536

እግዚአብሄር ለልጆቹ ለእኛ ያዘጋጀውን ከቃሉ ተረድተን እንደቃሉ በእምነት ከቀረብነው እግዚአብሄር ባለጠጋ ነው፡፡ ለሁላችን የሚበቃ ሃብት አለው፡፡ የሃብትና የአቅርቦት ችግር የለበትም፡፡ እግዚአብሄር ግን እንደልጅ በእምነትና በድፍረት እንድንቀርበው ይፈልጋል፡፡

በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ ሮሜ 10፡12

እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፡፡


Sunday, April 3, 2016

በኃይልና በብርታት አይደለም!

መልሶም፦ ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፡፡ዘካርያስ 4:6

    v  አንድን ነገር እንድታደርግለት እግዚአብሄር እንዳዘዘህ ተሰምቶህ ይሆን ?
    v  በአንድ አቅጣጫ እንድትሄድ እግዚአብሄ ተናግሮህ ይሆን ?
    v  አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብህ አውቀህ ማረጋገጫውንም ከጌታ አግኝተህ ይሆን?

መልካም ደረጃ ላይ ደርሰሃል ፡፡ እግዚአብሄር እንድትሰራለት የፈለገውን ነገር ማወቅ በጣም አስፈላጊው እርምጃ ነው፡፡ ፈቃዱን እንድታውቅ እግዚአብሄር ረድቶሃል፡፡ እግዚአብሄርን ስለዚህ አመስግን፡፡

አሁንም ይህንን ያየኸውን ነገር እንድትፈፅም እግዚአበሄር ራሱ ዝርዝር ምሪቶችን ሊሰጥህ ይፈልጋል፡፡ ባሳየህ መንገድም መሄድ እንድትችል የሚያበረታህም እርሱ ራሱ ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካወቁ በኋላ እግዚአብሄር እንደማያስፈልጋቸው ይመስቸዋል፡፡ ያንንም ያሳያቸውን በራሳቸው ለመፈፀም ሲጥሩ ራሳቸውን አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ይጨምራሉ፡፡ በእያንዳንዱ የመታዘዝ ህይወትህ እርምጃ እግዚአብሄር ያስፈልግሃል!

ለህይወትህ ያለውን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስታውቅ ሁሉንም ነገር ከእግዚአብሄር አትረከበውም፡፡

የእግዚአብሄር እርዳታ ፈቃዱን በማሳየት ይጀምራል እንጂ  በዚያ ላይ አያበቃም፡፡

እግዚአብሄር በእርምጃህ ሁሉ ሊረዳህ ካንተ ጋር ስላለ ተረጋጋ፡፡ ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያሳይህ በፀሎት ምሪቱን ጠብቅ፡፡ ከ ፈቃድ ለህይወትህ ያሳየህ እግዚአብሄር ፈቃዱ በተግባር እንዴት እንደሚተረጎም ደግሞ ያሳይሃል፡፡ በዚያ ባሳየህ መንገድ እንድትሄድ ሃይልን ያስታጥቅሃል ያበረታሃል፡፡

ፈቃዱን የሚያሳይህ እርሱ ነው፡፡ በውስጥህም የሚፈፅመው እርሱ ነው፡፡

ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ሮሜ 11፡36

ተጀምሮ እስከሚጨረስ ድረስ በመንፈሱ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥