Popular Posts

Follow by Email

Monday, October 22, 2018

ታማኝነት ሲፈተን


እግዚአብሄር ሊያሳድገን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር በተሻለ ነገር ላይ ሊሾመን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር አሁን ካለንበት የተሻለ ነገር አለው፡፡ እግዚአብሄር ለተሻለ ነገር አጭቶናል፡፡
ታማኝነት አግዚአብሄር ከሰጠን ሃላፊነት በምንም ምክኒያት ወደኋላ አለማለት ነው፡፡ ታማኝነት እግዚአብሄር የሰጠንን ስጦታ እንደ ባለአደራ እርሱ እንደፈለገው መጠቀም ነው፡፡ ታማኝነት ቢመችም ባይመችም እግዚአብሄርን በትህትና ማገልገል ነው፡፡ ታማኝነት ለፈተና እጅ ሳይሰጡ እና ከመንገድ ሳያቋርጡ ጉዞን መፈፀም ነው፡፡ ታማኝነት እግዚአብሄር እስከሚናገረን ድረስ በሁኔታዎች ቦታችንን አለመልቀቅ ነው፡፡
ነገር ግን እግዚአብሄር እኛን ለተሻለ ነገር ሲያጨን ለዚያ ሃላፊነት ከመሾሙ በፊት ለከፍታው እንደምንመጥን ማወቅ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ከመሾሙ በፊር ለቦታው እንደምንስማማ አቅማችንን ማየት ይፈልጋል፡፡  
የሚሆንልን ነገር ልንሸከመው ከምችልው በላይ ሆኖ እንዲያስጨንቀን እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡ የምናገኘው ነገር ከአቅማችን በላይ ሆኖ እኛንም ይዞን እንዲጠፋ እግዚአብሄር ይጠነቀቃል፡፡
ስለዚህ እግዚአብሄር ከማሳደጉ በፊት መፈተን ይፈልጋል፡፡ በተለያየ ነገር ሳይፈትን የሚያሳድገው ሰው የለም፡፡
እነዚህም ደግሞ አስቀድሞ ይፈተኑ፥ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡10
እግዚአብሄር ስለምንደርስበት ቦታ የሚፈትነን አሁን ባለንበት ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር ስለምናገኘው ነገር አያያዝ የሚፈትነን አሁን ያለንን ነገር በምንይዘበት አያያዝ ነው፡፡ እግዚአብሄር ስለምንነሆነው ነገር የሚፈትነን በሆንነው ነገር ነው፡፡
ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። የሉቃስ ወንጌል 16፡10
በትንንሽ ሃላፊነቶች ተፈትነን ካለፍን በታላላቅ ሃላፊነቶች ይባርከናል፡፡
ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። የማቴዎስ ወንጌል 25፡21
በትንንሽ ሃላፊነት ካለታመንን ግን ለትልቅ ሃላፊነት አንታመንም፡፡ በትንንሽ ሃላፊነቶች ካልታመንን ያለን ሃላፊነት እንኳን ይወሰዳል፡፡
ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ የማቴዎስ ወንጌል 25፡27-28
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #ታማኝ #የታመነ #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መደገፍ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Sunday, October 21, 2018

በሮች ሲዘጉ መረዳት ያለብን 3 ወሳኝ ነገሮች


በህይወታችን ይከፈታሉ ብለን የጠበቅናቸው በሮች ወይም እድሎች ላይከፈቱ ይችላሉ፡፡ በሮች ላለመከፈት የተለያየ ምክኒያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሮች ያለተከፈቱበትን ምክኒያት ካወቅን ስለበሮች አለመከፈት ማድርግ የሚገባንን ትክክለኛውን ነገር እናውቃለን፡፡
በሮች ካልተከፈቱ በጠበቅነው ሁኔታ አይደለም ማለት ነው
አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሄር የተናገረንን ብንሰማም ምን እንደተናገርንም ብናውቅም ነገር ግን እንዴት በህይወታችን እንደሚፈፀም በትክክል ላንረዳው እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ምን ሊያደርግ እንደፈለገ ብናውቅም እንዴት እንደሚፈፅምው መንገዱን ሙሉ ለሙሉ ላንረዳው እንችላለን፡፡ 
እግዚአብሄር ለበልአም ሂድ ብሎ ከተናገረው በኋላ ፊቱ የቆመው በዚህ መክኒያት ይመስለኛል፡፡
እግዚአብሔርም ወደ በለዓም በሌሊት መጥቶ፦ ሰዎቹ ይጠሩህ ዘንድ መጥተው እንደ ሆነ፥ ተነሣ ከእነርሱም ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ታደርጋለህ አለው። ኦሪት ዘኍልቍ 22፡20
የእግዚአብሔርም መልአክ በለዓምን፦ ከሰዎቹ ጋር ሂድ፥ ነገር ግን የምናገርህን ቃል ብቻ ትናገራለህ አለው። በለዓምም ከባላቅ አለቆች ጋር ሄደ። ኦሪት ዘኍልቍ 22፡35
እግዚአብሄር ስለ አንድ ነገር ተናገረን ማለት እግዚአብሄርን ከዚያ በኋላ ስለዚያ ነገር አንፈልገውም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ስለአንድ ነገር ተናገረን ማለት ከዚያ ጊዜው ጀምሮ ስለዝርዝር ጉዳዪ እግዚአብሄርን እንፈልዋለን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር አንድ ስለሚሆን ነገር ተናገረን ማለት ስለአፈፃፀሙ ጥበብን እንዲሰጠን እግዚአብሄርን አብዝተን መፈለግ አለብን ማለት ነው፡፡   
በሮች ካልተከፈቱ ጊዜው አይደለም ማለት ነው
በሮች ከተዘጉ ወደፊት ይከፈታሉ አሁን ግን የመከፈቻ ጊዜያቸው አይደለም ብለን ማሰብ እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ከተናገረን በሮች ይከፈታሉ፡፡ እግዚአብሄር ስለአንድ ነገር ሲናገረን ሁለት ምኞቶች በልባችን ይነሳሉ፡፡ አንደኛው ምኞት የእግዚአብሄርን ፈቃድ በመፈፀማችን ያለ ትክክለኛ ምኞት ሲሆን ሁለተኛው ምኞት ደግሞ ስጋዊ ራስ ወዳድነት የተሳሳተ ምኞት ነው፡፡ ንፁህ ምኞት ሰዎችን ስለመወደድ እና ስለማገልገል ያለ ምኞት ሲሆን ሁለተኛው ምኞት በሰዎች ስለመጠቀም ራስ ወዳድነት ምኞት ነው፡፡ ይህ ንፁህ ያልሆነው የልብ ሃሳብ እሰኪጣራ ድረስ እግዚአብሄር የተናገረን ነገር በህይወታችን ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሄር የተናገረን ነገር በህይወታችን እንዲሆን ይህ መልካም ያልሆው የልብ ሃሳብ በጊዜ ውስጥ መጥራት እና መሞት ይኖርበታል፡፡   
በሮች ካልተከፈቱ አይከፈቱም ማለት ነው
ከተባበርነው እግዚአብሄር በህይወታችን የሚፈልገውን ነገር ማድረግ ይችላል፡፡ እግዚአብሄር መክፈት የማይችለው በር የለም፡፡ በሮች ካልተከፈቱ የእግዚአብሄር ፈቃድ የለበትም ብለን ማሰብ እንችላለን፡፡ በሮች ካልተከፈቱ በዚያ በር መከፈት ለህይወታችን አደጋ አለው ማለት ነው፡፡ በሮች ካልተከፈቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ማለት ነው፡፡ በሮች ካልተከፈቱ የእግዚአብሄር ፈቃድ የለበትም ብለን ማሰብ እንችላለን፡፡
ባለጠጎች ደኸዩ፥ ተራቡም፥ እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም። መዝሙረ ዳዊት 34፡10
በሮች ካልተከፈቱ የእግዚአብሄር ፈቃድ የለበትም ብለን ማሰብ እንችላለን፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ ሰዎች ዘጉብኝ ማለት እግዚአብሄርን ማሳነስ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ ሰይጣን ዘጋው ማለት እግዚአብሄር ሁሉን አይችልም እንደማለት ነው፡፡
እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡28
በማይከፈት በር ላይ ጊዜን ማጥፋት ህይወትን ማባከን ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ የተሻለ ነገር እንዳለው አውቆ ለእግዚአብሄር ድምፅ ራስን መክፈት መልካም ነው፡፡ እግዚአብሄር ያልከፈተበት ምክኒያት እንዳለው ተረድቶ ለእግዚአብሄር ቀጣይ መሪነት ራስን መክፈት ያስፈልጋል፡፡  
እግዚአብሄር እረኛችን ሆኖ ከሚያስፈልገን ነገር የምናጣው ነገር የለም ብለን ማመን አለብን፡፡ እግዚአብሄር እረኛችን ሆኖ ያጣነው ነገር ሁሉ የማያስፈልገን ነገር ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ሃያል #ሁሉንቻይ #የሚዘጋ #የሚከፍት #በር ##ፍፁም #ተመላለስ #ኤልሻዳይ #እምነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Saturday, October 20, 2018

በእግዚአብሄር ላይ የምንደገፍባቸው አምስት የህይወታችን ክፍሎች


ሰው በእግዚአብሄር የተፈጠረው በእግዚአብሄር በራሱ ላይ ተደግፎ እንዲኖር ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ላይ እንዲደገፍ ዲዛይን ስለተደረገ ከእግዚአብሄር ነፃ መውጣት በፈለገ መጠን ሁሉ ለዚያ ስላልተሰራ አይሳካለትም፡፡ ሰው ግን ራሱን ትሁት አድጎ በእግዚአብሄር ላይ በተደገፈ መጠን ይከናወንለታል ይሳካለታል ህይወትንም ያያል፡፡ ሰው የህይወትን ጣእም የሚቀምሰው በእግዚአብሄር ላይ ብቻ ሲደገፍ ነው፡፡  
በእግዚአብሄር ላይ ከምንደገፍባቸው ዋና ዋና የህይወት ክፍላችን በጥቂቱ እንመልከት
ለእኛ የተለየ አላማ እንዳለው በእግዚአብሄር እንታመናለን
የተፈጠረንው በድንገት አይደለም፡፡ የተፈጠርነው በአላማ ነው፡፡ ህይወታችንን ከጥፋት የሚጠብቀውና ስኬት ውስጥ የሚያስገባን አንድ ነገር ስለ ህይወት አላማችን በእግዚአብሄር ላይ መደገፍ ነው፡፡ እኛ ራሳችንን አልፈጠርንም፡፡ እግዚአብሄር የህይወታችን ፈጣሪና ባለቤት ነው፡፡ እኛ የራሳችን አይደለንም፡፡ እኛ ብንረሳው እንኳን በህይወታችን ያለውን አላማ እግዚአብሄር አይረሳውም፡፡ እኛ ባይገባን እንኳን የህይወታችን ያለውን አላማ እግዚአብሄር እስኪፈፅመው ድርስ አያርፍም፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያለውን አላማ ለመፈጸፀም እስከፈለግን ድረስ የእግዚአብሄርን አላማ አንስተውም፡፡ እግዚአብሄር በህይወቱ ያለውን አላማ መፈፀም የሚፈልግ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር አይተላለፍም፡፡ የእግዚአብሄር አላማ በህይወቱ እንዲፈፀም ራሱን የሰጠ ሰው አላማውን አይስተውም፡፡
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። የዮሐንስ ወንጌል 7፡17
እግዚአብሄር የሚያስፈልገን እንደሚያሟላ በእግዚአብሄር እንታመናለን  
እግዚአብሄርን የምናምነው በእኛ ላይ ታላቅ የህይወት አላ እንዳለው ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ለህይወታችን የሚያስፈክገው ነገር ሁሉ እንደሚሰጠን እንታመነዋለን፡፡ በራሳችን እግዚአብሄርን ማገልገል የምንችል ቢሆን ኖሮ አግዚአብሄር አያስፈልገንም ነበር፡፡ እግዚአብሄርን የምንከተለውና የምናገለግለው በእርሱ ወጪ ነው፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2 የጴጥሮስ መልእክት 1፡2-3
እግዚአብሄር እንደሚጠብቀን በእግዚአብሄር እንታመናለን
እግዚአብሄር ሁሉን እንደሚያውቅና በምናልፍበት ነገር ውስጥ ሁሉ እንደሚጠብቀን በእግዚአብሄር እንታመናለናለን፡፡   
እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም። እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል። ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት። እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል። መዝሙረ ዳዊት 121፡4-8
ብንስት እንደሚመልሰን በእግዚአብሄር እንታመናለን 
እኛ ሁሉን አናውቅም፡፡ እግዙአብሄር ግን ስለ እኛ ሁሉን ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር እንዳንሰት የጠብቀናል፡፡ እግዚአብሄር ብንስት እንኳን ይገስፀናል ይመልሰናል፡፡ ብንስት እግዚአብሄር ይቅር ይለናል፡፡ እግዚአብሄር ሁለተኛ እድልን ይሰጠናል፡፡
በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፡9
ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። መዝሙረ ዳዊት 23፡3
ፀጋውን እንደሚያበዛልን በእግዚአብሄር እንታመናለን
እግዚአብሄርን እንድንኖርለት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጠን በእግዚአብሄር ላይ እንደገፋለን፡፡ በእርሱ በሚያስችል ሃይል እና ፀጋ እግዚአብሄርን ለማስደሰት እንደምንችል እናምናለን፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ፀጋ በቂ እንደሆነና እግዚአብሄርን በአካሄዳችን እንደምናረካውና እንደምናስደስተው በእግዚአብሄር አሰራር እንታመናለን፡፡
እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። የዮሐንስ ወንጌል 1፡16-17
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መደገፍ #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መታመን #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Friday, October 19, 2018

ተስፋ መቁረጥ


በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡8-9
ተስፋ መቁረጥ የህይወት ፈተና ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ እንደ ሙሴ አይነቶቹን አገልጋዮች ፈትኗል፡፡
እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ልሸከም አልችልም። እንዲህስ ከምታደርግብኝ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ በእኔ ላይ የሚሆነውን መከራ እንዳላይ፥ እባክህ፥ ፈጽሞ ግደለኝ። ኦሪት ዘኍልቍ 11፡14-15
ተስፋ መቁረጥ አነደኤልያስ ያሉትን ታላቅ ነቢያት ተፈታትኗል፡፡
ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፥ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፥ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ። እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና፦ ይበቃኛል አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ ብሎ እንዲሞት ለመነ። መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 19፡3-4
ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ለመተውና እጅ ለመስጠት የማይፈተን ሰው ካለ በህይወት የለማይኖር የሞተ ሰው ብቻ ነው፡፡ አቁም የሚል ተስፋ የሚያስቆርጥ ብዙ ድምፅ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተስፋ የማንቆርጥባቸው ከአልጋችን ላይ መነሳት በማይሰማን ጊዜ ለጌታ እንደገና በሃይል ለጌታ ለመኖርና በአዲስ ጉልበት ጌታን ለማገልገል አስፈንጥርው ከአልጋችን የሚያስነሱን አምስት ዋና ዋና ምክኒያቶች፡  
1.      መቼም እጅ የማንሰጠው በህይወታችን ከእኛ በላይ የሆነ የእግዚአብሄር አላማ ስላለ ነው፡፡
ራሳችንን ብቻ ብናይ ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ በአካባቢያችን ባለው ነገር ላይ ብቻ ብናተኩር ተስፋ ለመቁረጥ ይቀለናል፡፡ ነገር ግን ከራሳችን በላይ የምናያው ለአላማው የፈጠረን እግዚአብሄር አለ፡፡ ከሁኔታችን ባሻገር የምንመለከተው በምድር ላይ ልንፈፅመው የተወለድነለት የእግዚአብሄር አላማ አለ፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን ሃላፊነት እኛ ካልሰራነው ማንም ሊሰራው አይችልም የሚል ሸክም አለን፡፡
ጲላጦስም፦ እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። የዮሐንስ ወንጌል 18፡37
2.     ለምንም እጅ የማንሰጠው በህይወታችን የምንሰራው ነገር በዘላለማዊ እይታ ትርጕም ስላለው ነው፡፡
በህይወታችን የምንኖረው ለምድራዊው ነገር ብቻ ቢሆን ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነበር፡፡ ነገር ግን ከምድር ህይወት በኋላ ህይወት እንዳለ በክርስቶስ ፍርድ ፊት እንደምንቀርብ ስለምናውቅ ተስፋ መቁረጥ አይታሰብም፡፡ የምድር ኑሮ አጭር እንደሆነ እና እኛ በህይወት ከቆየን ክርስቶስ ተመልሶ እንደሚመጣና እንደሚወስድን ስለምናውቅ ተስፋ እንቆርጥም፡፡  
ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፡2-3
3.     በህይወታችን የምንሰራው ለትውልድ የሚሆን መሰረት ስለሆነ ነው
ህይወታችን በእኛ የሚያልቅ ቢሆን ተስፋ መቁረጥ ይቀል ነበር፡፡ ነገራቸን ከመቃብር ባሻገር የማይዘልቅ ቢሆን ተስፋ ለመቁረጥ ፊት በሰጠነው ነበር፡፡ ነገር ግን እኛን የሚመለከቱ እኛ ምሳሌ የምንሆናቸው ጌታ እንዲከተሉና እንዲያገለግሉ ብርታት የምንሆናቸው የሚመጣ ትውልድ ምሳሌ መሆን ስላለብን ስለራሳችን ብቻ ሳይሆን ስለመጪው ትውልድ እናስባለን እንጠነቀቃለን፡፡ የእኛ ተስፋ መቁረጥ እኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በሚመጣው ትውልድ ላይ ሁሉ ያለውን ተፅእኖ ስለምንረዳ እጅ አንሰጥም፡፡
እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ ከእርሱ የተቈረጣችሁበትን ድንጋይ ከእርሱም የተቈፈራችሁበትን ጕድጓድ ተመልከቱ። ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም። ትንቢተ ኢሳይያስ 51፡1-2
በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ፤ ይህም እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ በእናትህም በኤውንቄ ነበረባቸው፥ በአንተም ደግሞ እንዳለ ተረድቼአለሁ። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡5
አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡10
4.     በህይወታችን የምንሰራው ነገር ሽልማት ስላለው ነው
እግዚአብሄርን ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ኑሮ ብቻ ቢሆን ተስፋ መቁረጥ ቀላል ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ተስፋ አለመቁረጣችን ዋጋ አለው፡፡ ተስፋ አለመቁረጣችን ታላቅ ብድራት ያስገኛል፡፡
የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። ወደ ዕብራውያን 10፡34-35
5.     ተስፋ የማንቆርጠው በህይወት የምንፈልገው ነገር ባይሆንም እግዚአብሄር የሚፈልገው ነገር እየሆነ ስለሆነ ነው፡፡
በሆነው ባልሆነው እጅ የማንሰጠው እኛ ባይመቸንም እግዚአብሄር አላማውን እየፈፀመ ስለሆነ ነው፡፡ እኛን ደስ ባይለንም የእግዚአብሄር አሰራር ስራውን እየፈፀመ ስለሆነ ነው፡፡ የተለያዩ ነገር ቢያስጨንቀንም እንኳን ለመልካም ስለሚሆን ነው፡፡
እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡28
የውጭው ሰውነት ቢጠፋ ዋናው የውስጡ ሰውነት እለት እለት እየታደሰ ስለሆነ ነው፡፡
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡16-18
ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡27
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ  Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #መከራ #ፈተና #ሞት #በሁሉ #እንገፋለን #አንጨነቅም #እናመነታለን #ተስፋአንቆርጥም #እንሰደዳለን #አንጣልም #እንወድቃለን #አንጠፋም #ህይወት #ስጋ #መፅናት #መታገስ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Tuesday, October 16, 2018

ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ


የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16
ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
የሰው እውቀት የሚለካው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያሉትን ሰዎች እንዴት እንደሚይዝ በማወቁ ነው፡፡ የሰው ሃያልነት የሚለካው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሚይዝበት የጥንቃቄ አያያዝ መጠን ነው፡፡ የሰው ባለጠግነት የሚለካው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ባለው የአክብሮት ግንኙነት ነው፡፡
እውነተኛ እውቀት ያለው ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር አብሮ ለመሆን አይፈራም፡፡ እውነተኛ ሃያል ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች ጋር አብሮ በመሆኑ ይቀንስብኛል ብሎ የሚፈራው ምንም ነገር የለም፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ ለመሆን ይደፍራል፡፡
የእውነት እውቀት የሌለው ሰው ግን ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር መታየት አይፈልግም፡፡ ሃያል እንደሆነ በራሱ የማይተማመን ሰው ግን ዝቅተኛ ኑሮ ካላቸው ጋር አብሮ መሆኑ ሃያልነቱ የሚቀንስበት ይመስለዋል፡፡ ባለጠጋ እንደሆነ እርግጠኛ ያልሆነ ሰው ዝቅተኛ ኑሮ ካላቸው ጋር አብሮ መሆኑን የሰዎቹ ዝቅተኛ ኑሮ ይጋባብኛል ብሎ ስለሚፈራ አይደፍርም፡
እውነተኛ እውቀት የሌለው ሰው ሁሉ ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ መሆኑ ከፍተዕነት ስሜት እንዲሰማው ደርገዋል፡፡ ደካማ የሆነ ሰው የሃላልነት ስሜቱን የሚገኘው ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች አካባቢ በመሆን ነው፡፡ የአእምሮ ደሃ ሰው በራሱ ባለጠግነት ስለማይተማመን ባለጠጋ እንዶሆነ ራሰን የሚያታልለው ከፍተኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች ዙሪያ በመሆን ነው፡፡
እውነተኛ ባለጠጋ ድህነትን አይፈራም፡፡ ድህነትን እንዳይመጣበት የሚፈራና የሚሰግድለት ሰው ድሃ እንዳይሆን ምንም ክፉ ነገርን ከመስራት አይመለስም፡፡
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡10
እውነተኛ እውቀት ያለው ሰው የሰውን ስኬት በሰውነቱ እንጂ በኑሮ ከፍታና ዝቅታ አይለካም፡፡ እውነተኛ ሃያል የሰው ሃያልነት በሰውነት እንጂ ባለው ቁሳቁስ እንደሆነ አያምንም፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ሰው ባለጠግነት ሰውነት እንጂ የኑሮ ከፍተኝነት እና ዝቅተኝነት እንዳልሆነ ይረዳል፡፡
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን? የያዕቆብ መልእክት 2፡5
እውነተኛ እውቀት ያለው ሰው ከፍ ባለ ቁጥር ራሱን ያዋርዳል፡፡ እውነተኛ ሃያል ሰው እርሱ ብቻ እድለኛና ተወንጫፊ ኮከብ ስለሆነ ሳይሆን ማንም ሃያል ሊሆን እንደሚችል በሰው ያምናል፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ሰው ሁሉም ሰው በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ባለጠጋ እንደሆነ ስለሚያውቅ ራሱን ያዋርዳል፡፡ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ሰዎች የሚጠላና ዝቀተኛ ኑሮዋቸው ይተላለፍብኛል ብሎ ከእነርሱ ጋር መታየትም ሆነ አብሮ መሆን የማይፈል ሰው የአእምሮ ደሃ ነው፡፡  
የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡9-10
እውነተኛ አዋቂ የእግዚአብሄር እርዳታ እንጂ እውቀቱ ምንም እንደማያመጣ የተረዳ ሰው ነው፡፡ እውነተኛ ሃያል ሰው እግዚአብሄር እንጂ ሃይሉ የትም እንደማያደርስ አውቆ የናቀው ሰው ነው፡፡ እውነተኛ ባለጠጋ ድህነትም ባለጠግነትም ምንም እንደማያመጡ በመረዳት እና ድህነትንም ባለጠግነትንም የማይፈራ ሰው ነው፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡12-13
ገንዘብን የማይወድ ከምንም ባለጠግነትም ይሁን ድህነት አልፎ ሰውን የተሚወድ ሰው የተባረከ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ  Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #ትህትና #ባህሪ #ምሪት #ዘላለም #መተው #ልብ #ፉክክር #ቁሳቁስ #መታመን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #መሪ

Monday, October 15, 2018

አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ ከዚህ አታውጣን።


እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው። ኦሪት ዘጸአት 33፡15-16
ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር ለመግባትና ለመውጣት ነው፡፡
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር መውጣትና መግባት ባቆመ ጊዜ ነገሩ ሁሉ ሞተ፡፡ ሰው እግዚአብሄርን መከተል ባቆመ ጊዜ መንገድ ጠፋበት፡፡ ሰው የህይወት ምንጭ እግዚአብሄርን መከተል ባቆመ ጊዜ ህይወት ራቀው፡፡ ሰው የብርሃን አምላክን መከተል ባቆመ ጊዜ በጨለማ ተዋጠ፡፡
የእግዚአብሄርን መልካምነት ጣእሙን የቀመሱ ሰዎች በፅናት አንተ ከልወጣህ አታውጣን  ይላሉ፡፡ የእግዚአብሄርን አብሮነት ጣእሙን የቀመሱ ሰዎች የዘወትር የልብ ጩኸት አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ ከዚህ አታውጣን ነው። እገዚአብሄርን የሚያውቁ ሰዎች ካለእግዚአብሄር ለአንድ ሰከንድ ካለእግዚአብሄር መውጣት አይፈልጉም፡፡ የእግዚአብሄርን ክብር የተለማመዱ ሰዎች ካለ እግዚአብሄር አንድ እርምጃ መራመድ አይደፍሩም፡፡
እግዚአብሄርን የተገናኙ ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር ካልወጡ የህይወትን ትርጉም አያገኙም፡፡ የእግዚአብሄርን ህልውና የተለማመዱ ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር ካልሆነ የመውጣት አስፈላጊነት ይጠፋባቸዋል፡፡ እግዚአብሄርን ያዩት ሰዎች ካለ እግዚአብሄር ከመውጣት አለመውጣትን ይመርጣሉ፡፡
ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው? መጽሐፈ መክብብ 2፡25
የእግዚአብሄርን ክብር ያዩ ሰዎች ካለእግዚአብሄር የሚገኝ ምንም ነገር አያጓጓቸውም፡፡ የእግዚአብሄርን አብሮነት የተለማመዱ ሰዎች እግዚአብሄር የሌለበትን ቦታ አጥብቀው ይጠየፋሉ፡፡ እግዚአብሄርን የተረዱ ሰዎች እግዚአብሄር የሌለበት ቦታ ያለውን አደጋ በእጅጉ ይፈራሉ፡፡ መዝሙረኛው እንዲህ የሚለው ስለዚህ ነው፡፡
ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ። መዝሙረ ዳዊት 84፡10
እርሱም፦ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን።
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ፀሎት #ልመና #እንዲሰማን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ምስጋና