Popular Posts

Thursday, April 25, 2019

የተከፈለለት ባለእዳ



እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ትንቢተ ኢሳይያስ 55፡1-2
የሃጢያት ደሞዝ ሞት ነው፡፡ በሃጢያታችን ባለ እዳ ነበርን፡፡ ሃጢያት ከእዳዎች ሁሉ የከፋ እዳ ነው፡፡ ሃጢያት ሸክም ነው፡፡ ሃጢያት እስራት ነው፡፡ በሃጢያታችን ለዘለዓለም ከእግዚአብሄር መለያየት ነበረብን፡፡
ስለሃጢያትን በራሳችን ዋጋ መክፈል አንችልም፡፡ የትኛውም መልካም ስራችን ስለሃጢያታችን ክፍያ በቂ አይደለም፡፡
እኛ በሃጢያታችን ምክኒያት ለዘላለም ከእግዚአብሄር እንዳንለያይ ሃጢያት የሌለበት ኢየሱስ ስለሃጢያታችን እኛን ተክቶ በመስቀል ላይ ሊሞት ወደምድር መጣ፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለሃጢያታችን ሙሉ ዋጋን ከፍሏል፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለሃጢያቱ ሙሉ ክፍያን እንደከፈለ ያላመነ ሰው ባለእዳ ሆኖ ይኖራል፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለለትን ለእኔ ነው ብሎ የማይቀበል ሰው የእግዚአብሄር ቁጣ በእርሱ ላይ ስለሚኖር በምድር ባለእዳ ሆኖ በጉስቁልና ይኖራል፡፡  
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። የዮሐንስ ወንጌል 3፡36
ኢየሱስ እኛን ሃጢያተኞችን ወክሎ በእኛ ፋንታ በመስቀል ላይ እንደሞተ የሃጢያታችንን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ እንደከፈለ የማያምን  ሰው ለዘላለም ከእግዚአብሄር በመለያየት የሃጢያቱን እዳ በራሱ ይከፍለዋል፡፡
በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 3፡13
ኢየሱስ በመስቀል ላየ ዋጋ መክፈሉ የሚጠቅምህና ከዘላም ጥፋተ የሚያድንንህ በእምነት ስትቀበልው ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ አንተን ተክቶ  በመስቀል ላይ የከፈለውን ዋጋ በእምነት ካለተቀበልክ እና ከሃጢያት እዳ ካልዳንክ እስከ ሃጢያትህ ትኖታለህ ትሞታለህ፡፡  
ይህንን ፀሎት ከልብህ በመፀለይ የእግዚአብሄር ልጅ አድርጎ እግዚአብሄር እንዲቀበልህ ማድረግ ትችላለህ፡፡
እግዚአብሄር ሆይ ሃጢያተኛ ነኝ፡፡ የሃጢያት ደሞዝ ደግሞ ለዘላለም ከአንተ መለየት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሃጢያት ለመዳኛ ያዘጋጀኸውን የሃጢያት መስዋእት ኢየሱስን እቀበላለሁ፡፡ እየሱስ ስለሃጢያቴ በእኔ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለና እንደሞተ ከሞትም እንደተነሳ አምናለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ላይ ጌታ አድርጌ እሾመዋለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ዘመን ሁሉ እከተለዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ልጅህ አድርገህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ የዘላለም ህይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡
Abiy Wakuma Dinsa አቢይ ዋቁማ ዲንሳ
#አዲስፍጥረት #አዲስ #መዋጀት  #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ንስሃ #አቁማዳ #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ኦርቶዶክስ #ተዋህዶ #ጌታ #ማሪያም #መላእክት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ሰላም ትግስት #ልጅ

Wednesday, April 24, 2019

ወደድክም ጠላህም አመለካከትህ ይታያል



ስለሰው ያለህ አመለካከት በተለያየ ምክንያት ሊለወጥና የተበላሸ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሰው ያለህ አመለካከት እንዳይበላሽና ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ስለ ሰው ያለህ አመለካከት በተለያየ ምክንያት ቢበላሽም በፍጥነት ማስተካከል ግዴታ የአመለካከት መበላሸት የሚያስከትለውን ጉዳት ይቀንሳል፡፡
ሰው በሌለበት ጊዜ ስለ አንድ ሰው ስለምታስበው ነገር እጅግ መጠንቀቅ አመለካከትህ እንዳይበላሸ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ስለ አመለካከትህ መጠንቀቅ ያለብህ ስለእርሱ ያለህ አመለካከትህ የተበላሸብህ ሰው አጠገብህ ስላለ ወይም ስለሌለ አይደለም፡፡ ስለ አመለካከትህ መጠንቀቅ ያለብህ ሰው አመለካከትህን ስለሚያየው ወይም ስለማያየውም አይደለም፡፡ ሰው ቢኖርም ባይኖርም አመለካከትህ መልካም ካልሆነና ከተበላሸ የሚያበላሻቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡  
ሰው በሌለበት ጊዜም ቢሆን ስለሌላው ሰው ስለምታስብው ነገር መጠንቀቅ ያለብህ ይፍጠንም ይዘግይም ስለሰው ያለህ አመለካከት ስለሚገለጥ ነው፡፡ ሰው በማይሰማህ ጊዜ ለራስህ ወይም ለሌላው ሰው የምትናገረው ነገር በአንድም በሌላ መልኩ ይሰማል፡፡ ሰው በማይኖርበት ጊዜ የምታሳየው አመለካከት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይንፀባረቃል፡፡
የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። የሉቃስ ወንጌል 8፡17
ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካከት ማስተካከል ያለብህ በግልህ ነው፡፡ ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካከት ማስተካከል ያለብህ ሰውየው በሌለ ጊዜ ነው፡፡ ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካከት ማስተካል ያለብህ ብቻህን ባለህበት ጊዜ ነው፡፡ ስለሌላው ያለህን አመለካት ማቅናት ያለብህ ሰውየው አጠገብህ በሌለበት ጊዜ ስለዚያ ሰው በምታስብበት ወቅት ነው፡፡ ስለሌላው ሰው ያለህን አመለካት ማቃናት ያለብህ ከራስህ ጋር ስታወራ ነው፡፡
ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል። መጽሐፈ ምሳሌ 20፡5
ሰው ለእርሱ ያለህን አመለካከት ያውቃል፡፡ በተለይ መንፈሳዊ ሰው ሁሉ ይመረምራል፡፡
የተበላሸ አመለካከትህ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ የምትችለው ብቸኛ ነገር አመለካከትህን ቀድሞ ማስተካከል እንጂ አመለካከትን መደበቅ አይደለም፡፡ ጠረኑን ያመጣውን ነገር በማጥፋት የአፍን መጥፎ ጠረን ማስተካከል እንጂ ጠረኑ እንዳይታወቅ መመኘት ብቻ መፍትሄ ጠረኑ እንዳይወጣ አያግደውም፡፡  
ሰዎችን እግዚአብሄር እንደሚያያቸው ማየት አመለካትህን ያስተካከልዋል፡፡ ሰዎችን እግዚአብሄር እንደሚያከብራቸው ማክብር አመለካከትህን ቀና ያደርገዋል፡፡ ከሰዎች በላይ ራስን ከፍ አድርጎ በትእቢት ላለመመልከት በአስተሳሰብ ህይወትህ መጠንቀቅ አመለካከትህን ጤናማ ያደርገዋል፡፡  
ሄዋን ለእግዚአብሄር ያላት አመለካከት የተበላሸው ብቻዋን በነፃነት መልካም እንዳልሆነ ስለእግዚአብሄር ማሰብ ስትጀምር ነው፡፡ ሄዋን የቅንነት አመለካከትዋ እንዳይበላሽና ከእግዚአብሄር ጋር ያላትን ግንኙነት እንዳያበበላሽ ማድረግ የምትችለው የቅንነት አስተሳሰብዋን መበላሸት በእንጭጩ ብትቀጭ ነበር፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡3
ለሰው ያለህ ቅንነት እንዳይበላሽ አመለካከትህን የሚያበላሽን ነገር ማስተናገድ ይኖርብሃል፡፡ ስለሰው ያለህን ቅንነትን የሚያበላሽን ፍቅር የሌለበትን ነገር በነፃነት እያስብክና ግንኙነቴን አያበላሽም ብለህ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ስለሰው ያለህን አመለካከት የሚያበላሽን አክብሮት የሌለበትን ነገር በነፃነት እያሰብክ አመለካከቴ አይታወቀም ብለህ መመኘት ከንቱ ነው፡፡ ስለሰው ያለህን ቅንነትን የሚያበላሽ እንደእግዚአብሄር ቃል ያልሆነ ሃሳብን በአስተሳሰብ ህይወትህ እያስተናገድክ ይህ አመለካከቴ ሌላውን አይጎዳም ብለህ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ስለሰው ያለህን አመለካከት ተበላሽቶ ሌላው ሰው በንግግር ወይም በድርጊትህ አይረዳውም ማለት ሞኝነት ነው፡፡
ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡12-13
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አመለካከት #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Tuesday, April 23, 2019

የውስንነት ወሰን


እግዚአብሄር ለክብሩ የፈጠረን የእግዚአብሄር ፍጥረት ነን፡፡ እግዚአብሄር አይወሰንም፡፡ እግዚአብሄር ታላቅ አምላክ እንደሆነ ሁሉ እኛም ልጆቹ የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ እግዚአብሄር እንደማይወሰን ታላቅ ሃይሉን የሚያሳየው እኛ በልጆቹ ነው፡፡
እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን። ትንቢተ ኢሳይያስ 818
የእግዚአብሄር ሙሉ ድጋፍ ያለን በምንም ነገር የማንወሰን የእግዚአብሄር ህዝቦች ነን፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄር ሃያል በእኛ ታላቅ ስለሆነ ጠላት ሁልጊዜ ይዋሻል፡፡
እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፦ ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ። መዝሙረ ዳዊት 663
እግዚአብሄር ለእኛ ያለው ሙላትና መትረፍረፍ ነው፡፡
እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። የዮሐንስ ወንጌል 10፡10
እግዚአብሄር በውስጣችን ያስቀመጠውን ታላቅ እምቅ ጉልበት እንዳናወጣ የጠላት ተግዳሮት አለብን፡፡ እግዚአብሄር ወደአየልን ታላቅ ደረጃ እንዳንደርስ የሚያስፈራራና የሚያናንቅ ጠላት አለብን፡፡ እግዚአብሄር ያየልንን ሁሉ እንዳንወርስ የሚያጣጥልና የሚያሳንስ ብዙ ነገር በህይወታችን ይገጥመናል፡፡
ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እግዚአብሄር እንዲሰራ የሰጠውን ስራ እንዳይሰራ ሰይጣን ሊያሳንሰውና የሰው ልጆችን ከማዳን ከአላማው ሊያስቆመው ይገዳደረው ነበር፡፡
ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 43
አሁንም እግዚአብሄር እንድንሆን ያሰበውን ሁሉ እንዳንሆን እግዚአብሄር አላችሁ የለንን ሁሉ እንዳይኖረን እንዲሁም እግዚአብሄር ታደርጋላችሁ የሚለንን ሁሉ እንዳናደርግ ሰይጣን ሊወስነን ይሰራል፡፡
እግዚአብሄር ወደ አየልን የክብር ቦታ እንዳንሄድ ሰይጣን ሊገድበን ከዚህ ማለፍ አትችልም ብሎ ሊያሳምነን ይጥራል፡፡ የሰይጣንን ውሸት አምነን ከቆምን ከዚያ ሁሉ ብርቱ የጦር መሳሪያችን ጋር እንማረካለን፡፡ የሰይጣንን አታልፉም ግርግር ከሰማነው እግዚአብሄር ወደአለለን ደረጃ ሳንደርስ ከዚያ ሁሉ እምቅ የእግዚአብሄር ሃይል ጋር እናልፋለን፡፡    
የእኛ ወሰን እግዚአብሄር ያየልን እንጂ ሰይጣን የሚለው ውሸት አይደለም፡፡ የእኛ ልክ ሰይጣን የሰፋልን የንቀት ልብስ ሳይሆን እግዚአብሄር ያየልን የክብር ልብስ ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/AbiyWakumaDinsa/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ዘመን #እድል #ዋጁ #ጥበብ #መተርጎም #ገደብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, April 22, 2019

የሚሰራው እግዚአብሄር



ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። መጽሐፈ መክብብ 3፡11
በህይወታችን ምንም አይነት ትርጕም ያለው ነገር ከሰራን የሰራው እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡ በህይወታችን ትርጉም ያለው ነገር ካቀድን ያቀደው እግዚአብሄር ነው፡፡ በህይወታችን ትርጉም ያለው ነገር ካሰብን መጀመሪያ ያሰበው እግዚአብሄር ራሱ ነው፡፡  
እግዚአብሄር ጀማሪ ነው፡፡ እግዚአብሄር ቀዳሚ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከመጀመሪያ ያስባል፡፡ እኛ ከመወለዳችን በፊት ስለእኛ ህይወት አስቦ ጨርሷል፡፡ አለም ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሄር የህይወት እቅዳችንን ሰርቶት ጨርሷል፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11
እኛ ወደ ምድር ከመምጣታችንና ስራችንን ከመጀመራችን በፊት እግዚአብሄር መጨረሻውን ከመጀመሪያው አይቶታል፡፡  
በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። ትንቢተ ኢሳይያስ 46፡10
እኛ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ያደረግነው ጥሩ አሳቢዎች ስለሆንን አይደለም፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በህይወታችን የፈፀምነው ጥሩ ተመራማሪዎች ስለሆንን አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ በህይወታችን የተፈፀመው ምርጥ እቅድ አውጪዎች ስለሆንን አይደለም፡፡
በልባችን መልካም ሃሳብ ካለ እግዚአብሄር አስቀድሞ ያሰበው የራሱ ሃሳብ ነው፡፡ በልባችን መልካም ነገርን ካቀድን እግዚአብሄር የዘላለም እቅዱን በልባችን አካፍሎን ነው፡
በምድር ላይ የሰራነው አንዳች ነገር ቢኖር እግዚአብሄር ሰርቶ የጨረሰውን ብቻ ነው፡፡
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። መጽሐፈ መክብብ 311
በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። ምሳሌ 1921
በምድር ላይ የምንፀልየው ለእግዚአብሄር ስለህይወት እቅዳችን ሃሳብ ልናቀብለው አይደለም፡፡ የምንፀልየው እግዚአብሄር የህይወት እቅዳችንን እንዲሰራ ሃሳብን ልናካፍለው አይደለም፡፡ የምንፀልየው ስለህይወት እቅዳችን እግዚአብሄርን ልናማክረው አይደለም፡፡ የምንፀልየው ለእግዚአብሄር ሃሳብ ካልሰጠነው የሚረሳ እና የሚዘለል ነገር ስላለና የህይወት እቅዳችን ጎዶሎ ስለሚሆን አይደለም፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡11
ወደ እግዚአብሄር የምንፀልየው እግዚአብሄር ለህይወታችን አስቀድሞ ሰርቶ የጨረሰወን እቅድ ለመረዳትና ከእርሱ ጋር ለመተባበር አብረነው ለመስራት ነው፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አላማ #ተስፋ #ፍፃሜ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተስፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Sunday, April 21, 2019

ይቻላል



ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። የማርቆስ ወንጌል 9፡23
እግዚአብሄር ሁለን ቻይ አምላክ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ሁለል የሚችለውን እግዚአብሄርን ተከትሎ ሁሉን እንዲችል ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄር በምድር ላይ እንዲፈፅም የፈለገውን አላማ ከመፈፀም ምንም ነገር እንዳያግደው ተደርጎ ነው፡፡
ሰው የተፈጠረው የእግዚአብሄር ቃል ታደርጋለህ የሚለውን ሁሉ ማድረግ እንዲችል ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእምነት የእግዚአብሄርን ሃይል በምድር ላይ እንዲጠቀም ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን በቃሉ እየተከተል ለሰው የማይቻለውን ነገር እንዲችል ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን በማመን ለሰው የማይቻለውን ነገር በእምነት እንዲችል ነው፡፡
እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከማወቅ ነው፡፡ እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ፈቃድ አውቆ በመከተል ነው፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን እንደሚችል ሁሉ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የተረዳ ሰው በእምነት ፈቃዱን ለመፈፀም የማይችለው ነገር አይኖርም፡፡
ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። የሉቃስ ወንጌል 1፡37
የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሊያስቆም የሚችል ምንም ሃይል እንደሌለ ሁሉ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚከተልን ሰው የሚያቆም ምንም ሃይል የለም፡፡ ለእግዚአብሄር የሚሳነው ነገር እንደሌለ ሁሉ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ከቃሉ አግኝቶ ለሚከተል ሰው የሚሳነው ነገር የለም፡፡
እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ እኔን የሚያቅተኝ ነገር አለን? ትንቢተ ኤርምያስ 32፡27
እግዚአብሄር ፈቃዱን ለመፈፀም የሚያቅተው ነገር እንደሌለ ሁሉ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለሚፈፅም ሰው የሚያቅተው ነገር የለም፡፡
ለሚያምን ሁሉ ይቻላል !
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/AbiyWakumaDinsa/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Saturday, April 20, 2019

የማሪያም አማላጅነት



ማሪያም ታማልዳለች ወይስ አታማልድም የሚለው ጥያቄ በኢትዮጲያ ውስጥ ብዙ ክርክርን ሲያስነሳ የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንዶች ማሪያም በምድር ላይ እያለች አማልዳለች ነገር ግን ከሞተች በኃላ ማማለድ አትችልም ብለው ያምናሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ማሪያም አሁንም ታማልዳለች ወደ እግዚአብሄር ታቀርበናለች በማለት ይደገፉባታል ወደእርሷም ይፀልያሉ፡፡
ሲጀመር ማሪያም ታማልዳለች አታማልድም የሚለው ክርክር ከመዳን አንፃር ከቁጥር የሚገባ ክርክር አይደለም፡፡ መዳናችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው የህይወት ዋጋ የተገዛ ነው፡፡ መዳናቸነ የሚመሰረተው ኢየሱስ ስለሃጢያቴ ሞቷል ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል ብለን በማመናችን ነው፡፡
በበኩሌ ሰው ማሪታም ታማልዳለችም አታማልድምም ብሎ ቢያምን ደህንነቱን ቅንጣት ይለውጣል ብዬ አላምንም፡፡ የአንድ ሰው ደህንነት የሚመሰረተው ሰው ኢየሱስ ስለሃጢያቱ በመስቀል ላይ እንደሞተና በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ በማመኑ ላይ ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡9-10
እውነት ነው ጤናማ የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርትን መማራችን የምንኖረው የክርስትና ህይወት ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ሰው ከመሰረታዊው የመፅሃፍ ቅዱስ የደህንነት አስተምሮ ውጭ የሚያምነው ማንኛውም ጥቃቅን ትምህርት ደህንነቱ ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ማርያም አታማልድም ብሎ ቢያምን አይድንም፡፡ ዳግመኛ የተወለደ ሰው ማርያም ታማልዳለች ብሎ ቢያምን ደህንነቱን አያጣም፡፡
ኢየሱስ በምድር በሚመላለስበት ጊዜ አንድ የህግ መምህር ወደ ኢየሱስ ቀርቦ እንዲህ አለው፡፡
መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። የዮሐንስ ወንጌል 3፡2
ኢየሱስ ግን ስለመፅሃፍ ቅዱስ እውቀቱ አድንቆ በጣም አስፈላጊ ስላልሆነው አስተምሮት አላዋራውም፡፡ ኢየሱስ በቀጥታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነው የሰው ልጅ መሰረታዊ የደህንነት ፍላጎት እንዲህ ሲል ተናገረው፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። የዮሐንስ ወንጌል 3፡3
ለሰው ለደህነነት የሚያስፈልገው ጥሩ የመፅሃፍ ቅዱስ እውቀት ሳይሆን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡ ለሰው ደህንነት የሚያስፈልገው በጥቃቅን አስትምሮት ላይ ተከራክሮ ማሸነፍ ሳይሆን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡ ኢየሱስ ስለደህንታችን የሚያስፈልገውን የሃጢያት ዋጋ ሁሉ በመስቀል ላይ ከከፈለ በኃላ የሚያስፈልገን ሌላ ነገር ሳይሆን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡  
አሁንም የሚያከራክሩን ብዙ ነገሮች የማይገቡ ክርክሮች ናቸው፡፡ አሁን ጊዜያችንንና ጉልበታችን የሚያባክኑ ክርክሮች መሰረታው ያልሆኑ ትምህርቶች ናቸው፡፡ አሁን የሚያከራክሩንና የሚያጣሉን ክርክሮች ለመዳን ምንም የማይጨምሩ ምንም የማይቀንሱ ነገሮች ናቸው፡፡ አሁን የሚያከራክሩን ነገሮች አይቶ ሰይጣን የደህንነት አላማችንን መሳታችንን ደስ እንዲለው የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡
ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር በሚያደርገው ንግግር ለደህንነት አስፈላጊ ባልሆኑ ለመዳን በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ጊዜውን አልፈጀም፡፡ ኒቆዲሞስ አንዳንድ የሃይማኖት እውቀት ቢኖረውም ለመዳን ግን ምንም አይጠቅመውም፡፡ ኒቆዲሞስንም ሆነ እኛን የሚጠቅመን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡    
በእናቱ ማህፀን ውስጥ ያለ ህፃን አለምን ማየት እንደማይችልና ስላልተወለደበት አለም ምንም አይነት እውቀት ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በስተቀር ስለ እግዚአብሄር መንግስት ሊያውቅ አይችልም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት እውነተኛ እውቀት የሚጀመረው በመወለድ ብቻ ነው፡፡ ሰው ዳግመኛ ሲወለድ አይኖቹ ይከፈታሉ ነገሮችን ማየትና ማወቅ ይጀምራል፡፡ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሄርን መንግስት ነገሮችን ለማየትና  እና ለማወቅ የሚያደርገው ሙከራ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡
ሰው ዳግመኛ ከተወለደና የእግዚአብሄር የቤተሰብ አባል ስለሚሆንና ከእግዚአብሄር ጋር የአባትና የልጅ ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሚኖረው ስለማማለድ የሚኖረው ጥያቄ ሁሉ ይፈታል፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤የዮሐንስ ወንጌል 1፡12
መፅሃፍ ቅዱስ ስለዳግም መወለድና በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ በእምነት ከሃጢያት ትምህርቶች የተሞላ ነው፡፡ እንዲያውም መጽሃፍ ቅዱስ እራሱ የተፃፈበት አላማ እኛ በኢየሱስ አምነን ህይወት እንዲሆንልን ነው፡፡
ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል። የዮሐንስ ወንጌል 20፡31
ይህንን ፀሎት ከልብህ በመፀለይ የእግዚአብሄር ልጅ አድርጎ እግዚአብሄር እንዲቀበልህ ማድረግ ትችላለህ፡፡
እግዚአብሄር ሆይ ሃጢያተኛ ነኝ፡፡ የሃጢያት ደሞዝ ደግሞ ለዘላለም ከአንተ መለየት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሃጢያት ለመዳኛ ያዘጋጀኸውን የሃጢያት መስዋእት ኢየሱስን እቀበላለሁ፡፡ እየሱስ ስለሃጢያቴ በእኔ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለና እንደሞተ ከሞትም እንደተነሳ አምናለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ላይ ጌታ አድርጌ እሾመዋለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ዘመን ሁሉ እከተለዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ልጅህ አድርገህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ የዘላለም ህይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#አዲስፍጥረት #አዲስ #መዋጀት  #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ንስሃ #አቁማዳ #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ኦርቶዶክስ #ተዋህዶ #ጌታ #ማሪያም #መላእክት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ሰላም ትግስት #ልጅ

Friday, April 19, 2019

ሁሉም ሊፀልየው የሚገባ የፀሎት ርእስ



እግዚአብሔር ሆይ እኔ ልቀየር የማልችላቸውን ነገሮች በዝምታ እንድቀበል ፀጋን ስጠኝ፡፡ እኔ መለወጥ የሚገባኝን ነገር ለመቀየር ድፍረት ስጠኝ፡፡ ልቀይር በምችላቸውና ልቀይር በማልችላቸው በሁለቱ ነገሮች መካከል መለየት እንድችል ጥበብን ስጠኝ፡፡ ሬይንሆልድ ኑይበር
God, give me the grace to accept with serenity the things that cannot be changed, Courage to change the things which should be changed, and the Wisdom to distinguish the one from the other. Reinhold Niebuhr
በህይወት ማድረግ የምንችለቸው ነገሮች አሉ ማድረግ የማንችላቸው ነገሮች ደግሞ አሉ፡፡ ውስን እንደሆንን ሁሉን ነገር ማድረግ እንደማንችል ካልተረዳን  እረፍት በህይወታችን አይመጣም፡፡ በህይወት የሚያርፉና ህይወታቸውን በሚገባ ተደስተውበት የሚያልፉ ሰዎች ማድረግ የሚችሏቸው ታላላቅ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ማድረግ የማይችሉት አንዳንድ ነገር እንዳለ በሚገባ የተረዱ ሰዎች ናቸው፡፡
ማድረግ የምንችለውን ነገር ማወቅ በጣም ወሳኝ እንደመሆኑ መጠን ማድረግ የማንችለውን ነገር ማወቅ ደግሞ እንደሁ ወሳኝ ነው፡፡
በህይወት የሚለወጡና ቢያንስ ለጊዜው የማይለወጡ ነገሮች አሉ፡፡ የሚለወጡ ነገሮችን ማወቅ እንድንለውጣቸው ድፍረት ይሰጠናል፡፡ የማይለወጡ ነገሮችን ማወቅ እንድንታገስ ያስተምረናል፡፡
መለወጥ የማይችለውን ነገር የማያውቅ ሰው መለወጥ በማይችለው ነገር ላይ በከንቱ ጊዜውንና ጉልበቱን ይፈጃል፡፡ መለወጥ የሚችለንውን ነገር የማያውቅ ሰው በከንቱ ተስፋ በመቁረጥ ነገሮችን ሊለውጥ የሚችልበትን በውስጡ ያለውን የተጠራቀመ ጉልበት ሳይጠቀምበት ያባክነዋል፡፡
በወትድርና የበሰለ ወታደር የሚባለው የሚተኩስ ሳይሆን መቼ እንደሚተኩስ የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ መቼ መተኮስ እንዳለበት የሚያውቅና መቼ ደግሞ መተኮስ እንደሌለበት የሚያውቅ ወታደር ውጤታማ ወታደር ነው፡፡ የበሰለ ወታደር አንዳንዴ መተኮስ እየቻለ እስከሞት ድረስ በሚያስፈራ ሁኔታ ላላመተኮስ ይታገሳል፡፡
እግዚአብሄር ነገሮችን የምንለውጥበት ጉልበትን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄር ግን ነገሮችን የምንለውጥበትን ጉልበት ብቻ ሳይሆን የሚሰጠን የማይለወጡትን ነገሮች የምንታገስበትን ፀጋም ይሰጠናል፡፡
አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡1፣4
አንዳንዴ በህይወታችን ያለውን ተራራ ከፊታችን እንድናነሳው ድፍረትን ይሰጠናል ሌላ ጊዜ ደግሞ ተራራውን የምንወጣበት ፀጋን ያበዛልናል፡፡
በእያንዳንዱ የህይወት እርምጃችን እግዚአብሄርን መፈለግ ያለብን በእነዚህ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ነው፡፡
እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ወደ ዕብራውያን 4፡16
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #ብቃት #የእግዚአብሄርችሎታ #ትግስት #የእግዚአብሄርሃይል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ፅድቅ #እግዚአብሄርንመምሰል #ራስንመግዛት #ልብ