Popular Posts

Friday, June 30, 2023

ከፈለግን እና ከተዘጋጀን እንሰማዋለን


እግዚአብሔር አምላካችን ነው፡፡ እኛ ለክብሩ የፈጠረን የእርሱ ህዝቦች ነን፡፡ እግዚአብሔር እንድንፈለገው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን ስንፈልገው ደስ ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር እርሱን ለመስማት ጆሮዋችንን እንድናዘነበል ይፈልጋል፡፡

እግዚአብሔርን በእውነት ከፈለግነው ይገኝልናል፡፡ እግዚአብሔር ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም፡፡

እኛ እግዚአብሔርን መስማት ከምንፈልገው በላይ እርሱ በእኛ እንዲሰማ ይፈልጋል፡፡ እኛ ለህይወታችን ካለን አላማ በላይ ለእኛ የተሻለ አላማ አለው፡፡

ፈቃዱን ለማድረግ የምንወድ ከሆንን የእርሱን ፈቃድ እንረዳለን፡፡ ምክኒያቱም እግዚአብሔር ከተናገረ እኛ እንሰማለን፡፡ ፈቃዱን ለማድረግ እየወደድን እርሱን አለመስማት የማይታሰብ ነገር ነው፡፡

ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ . . . ያውቃል። የዮሃንስ ወንጌል 7፡17

እግዚአብሔር መንገዳችን እንዲቀና ይፈልጋል፡፡ እርሱን ለመስማት ራሳችንን ከሰጠን መንገዳችን ሁሉ ቀና ይሆናል፡፡

በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። መጽሐፈ ምሳሌ 3፡5-6

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

 

Thursday, June 29, 2023

በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ

 


በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ የዮሐንስ ወንጌል 10፡27

ከጥንት ከእግዚአብሔር እረኝነት ስር ተፈጥረን ነበር፡፡

እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙረ ዳዊት 95፡7

በሃጢያት ምክኒያት እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን እያንዳንዱ ወደገዛ መንገዱ አዘነበለ፡፡

እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡25

ክርስቶስን እንደአዳኝ የተቀበለን ሁላችን ወደነፍሳችን እረኛ እና ጠባቂ ተመልሰናል፡፡

ኢየሱስ እረኛችን ሆኖዋል፡፡ እኛም እንደበጎች ድምፁን እንሰማለን፡፡ በጎች ከሆንን ድምፁን እንሰማለን፡፡ ክርስቶስን እንደጌታ በተቀበልንበት በዚያች ቅጽበት በጎቹ ሆነናል ድምጹንም መስማት ጀምረናል፡፡ ከቆየ በኃላ ሳይሆን ድምፁን መስማት የጀመርነው በዚያች ጀዳንንበት ቅጽበት ጀምሮ ነው፡፡

ድምፁን የምንሰማው ጌታን በመከተል ከቆየን በክርስትና ከበሰለን በኃላ አይደለም፡፡ እንደበጎች የእረኛን ድምፅ መስማት ለጥቂት ሰዎች የተሰጠ ስጦታ አይደለም፡፡ ድምፁን መስማት ለዳንን ለሁላችንም ነው፡፡

እውነት ነው በግ ካልሆንን ድምፁን አንሰማም፡፡ በግ ከሆንን ግን ድምፁን እንሰማለን፡፡  ድምፁን የምንሰማው ከእኛ ችሎታ ሳይሆን ከእረኛው ድምፁን የማሰማት ችሎታ የተነሳ ነው፡፡ እርሱ ተፈጥሮዋችንን ያውቃል እርሱ ፈቃዱን ሊያሳውቀን ሲፈልግ ይችልበታል፡፡ እርሱ ከተናገረ ደግሞ እንሰማዋለን፡፡

አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ መዝሙረ ዳዊት 103፡13-14

በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ የዮሐንስ ወንጌል 10፡27

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Wednesday, June 28, 2023

ህግ በህግ ብቻ ይሻራል

 


በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡2

ከሃጢያት ነፃ የምንወጣው በውስጣችን ያለውን በክርስቶስ ያለውን የህይወት መንፈስ ህግ ስንሰማ ብቻ ነው፡፡ በውስጣችን ያለው በክርስቶስ ያለው የህይወት መንፈስ ድምፅ አለው፡፡ በውስጣችን ያለውን የህይወት መንፈስ ከሰማን እና ከተከተለን ሃጢያትን መስራት አንችልም፡፡

ጽድቅን በማድረግ ብቻ ከመቀፅበት ከሃጢያት እንጠበቃለን፡፡

ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 6፡13

ከሃጢያት የመጠበቂያው ፍቱን መድሃኒት ሃጢያትን አለመከተል ሳይሆን የህይወት መንፈስ ህግን መከተል ነው፡፡  የህይወት መንፈስ ህግን በመከተል ብቻ ይህ ሃጢያት ነው አይደለም ብለን በአእምሮዋችን መመራመር ሳይጠበቅብን እግዚአብሄር የሚወደውን የቅድስናን ህይወት መኖር እንችላለን፡፡

ሃጢያትን ብቻ እያሰብን ከሃጢያት ለመዳን ከመፍጨርጨር የመንፈስን ድምፅ በመስማት ብቻ ሳናውቀው ከሃጢያት መጠበቅ እንችላለን፡፡

ስለመንፈስ በማሰብ ብቻ ስለስጋ ከማሰብ እንጠበቃለን፡፡

እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡5-6

እንደብሉይ ኪዳን ጊዜ አይደለም፡፡ ክርስቶስን የምንከተል ሁላችን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ይኖራል፡፡ መንፈሱን ተከትለን በምንም ሃጢያት ልንኮነን እስከማንችል ድረስ ከሃጢያት አርነት መውጣት እንችላለን፡፡ መንፈሱን በመከተል አትያዝ አትቅመስ አትንካ ሳንባል ሙሉውን የእግዚአብሄርን ህግ መፈፀም እንችላለን፡፡

እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፡22

እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡1-2

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Tuesday, June 27, 2023

ድምፅ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ የምናውቀው

 


ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ። የዮሐንስ ወንጌል 16፡13-15

መንፈስ ቅዱስ ሊመራን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ አዳኝ በተቀበልን በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት የምንለየው ክርስቶስን በማክበሩ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንኳን ሌላውን ሰው ሊያከብር ይቅርና እራሱን እንኳን አያከብርም፡፡ መንፈስ ቅዱስ እኛን በመምራት ክርስቶስን ሊያከብር በእኛ ውስጥ አለ፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንዳልሆነ የምናውቅው ታዲያ የምንሰማው ድምፅ ክርስቶስን በማክበሩ እና ባለማክበሩ ነው፡፡ ክርስቶስን ካላከበረ በፋንታው ሰውን የሚያከብር ከሆነ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት አይደለም፡፡

መንፈስ ቅዱስ ሲናገር ለሰው ጥቅም ለክርስቶስ ክብር ነው፡፡ ክርስቶስን የሚሸፍን ሰውን የሚያሳይ ነገር ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Monday, June 26, 2023

እግዚአብሄርን ከመስማት የሚያግዱን ነገሮች


እግዚአብሄር ሁልጊዜ መናገር ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ሊናገረን ብሎም ወዳሰበልን መዳረሻ ሊመራን ይፈልጋል፡፡ የእግዚአብሄር መፈለግ ግን በቂ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ነገር የእግዚአብሄርም የሰው የቅንጅት ስራ እንደመሆኑ መጠን እግዚአብሄር ቢናገርም እኛ ካልሰማን የትም አንደረስም፡፡

እግዚአብሄርን ከመስማት ከሚያግዱን ነገሮች አንዱ ፈቃዱን ለማድረግ አለመራብ እና አለመጠማት ነው፡፡

ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። የማቴዎስ ወንጌል 5፡6

ፈቃዱን ለማድረግ ብርቱ ፍላጎት ካለን እግዚአብሄርን ለመስማት የሚያስችለንን ምቹ ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡

ሌላው እግዚአብሄርን በመስማት ሙሉ ፍሬ እንዳናፈራ የሚያደርገን ለኑሮ ጭንቀት ፊት መስጠ ነው፡፡ ለኑሮ ሃሳብ እና ለባለጠግነት ምኞት ፊት ከሰጠነው በቁማችን ሊውጠን የሚችል አደገኛ ነገር ነው፡፡

በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። የሉቃስ ወንጌል 8፡14

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


 

Sunday, June 25, 2023

በውስጣችን የሚኖር መለኮታዊ ህይወት

 


ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሃጢያታችን እንደሞተ እና ከሙታን እንድተነሳ በምናምን እና በምንመሰክር ሁሉ ውስጥ መለኮታዊ ህይወት በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡

በውስጣችን የሚኖረው መለኮታዊ ህይወት የራሱ አላማ አለው፡፡ በውስጣችን የሚኖረውን የመለኮታዊ ህይወት መነሳሳት ከተከተልን እግዚአብሔርን ሙሉ ለሙሉ መከተል እንችላለን፡፡

የእኛ ድርሻ በውስጣችን ያለውን መለኮታዊ ህይወት መስማት እና መከተል ብቻ ነው፡፡ የእኛ ድርሻ ለራሳችን አላማ እና ፈቃድ መሰቀል መሞት ነው፡፡

በውስጣችን ያለው  መለኮታዊ ህይወት አንድን ነገር ለማሰብ ከተነሳሳ አብረን እናስባለን፡፡

በውስጣችን ያለው  መለኮታዊ ህይወት መሄድ ከፈለገ እግር እንሆንለታለን፡፡

በውስጣችን ያለው  መለኮታዊ ህይወት መናገር ከፈለገ እግር እንሆንለታለን፡፡

በውስጣችን ያለው  መለኮታዊ ህይወት መቀመጥ ከፈለገ እንቀመጣለን፡፡

በውስጣችን ያለው  መለኮታዊ ህይወት መፀለይ ከፈለገ እንፀልያለን፡፡

በውስጣችን ያለው  መለኮታዊ ህይወት መሄድ ከፈለገ እግር እንሆንለታለን፡፡

በውስጣችን ያለው  መለኮታዊ ህይወት አንድን ነገር ለማድረግ ከተነሳሳ አብረን እንሰራለን፡፡

ሃዋርያው ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1፡21 ላይ ለእኔ ህይወት ክርስቶስ ነው የሚለው ስለዚህ ነው፡፡

ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።

በውስጣችን ያለውን መለኮታዊ ህይወት ማመን አለብን፡፡

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ወደ ገላትያ ሰዎች 2፡20

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Saturday, June 24, 2023

አእምሮን በማደስ የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት

 

የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡1

እግዚአብሔር ከመናገር አቋርጦ አያውቅም፡፡ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመለየት ከሚጠቅሙን ነገሮች አንዱ በቃሉ አእምሮዋችንን ማደስ ነው፡፡

የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስብ እንደ እግዚአብሔር ያስባል ይባላል፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አብሮ ይሄዳል፡፡ የእግዚአብሔር ድምፅ በቃሉ ከታደሰው አእምሮ ጋር ይስማማል፡፡

አእምሮዋችን በቃሉ ሲታደስ የምንሰማውን የእግዚአብሔርን ድምፅ በቀላሉ መለየት እንችላን፡፡ በእግዚአብሔርን ቃል አእምሮን ማደስ ከቃሉ ጋር አብሮ የሚሄደውን ድምፅ ለመለየት ያስችለናል፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Thursday, June 22, 2023

የእግዚአብሔርን ድምፅ የምንለይበት መንገድ

 


በምድር ላይ የእግዚአብሔር ድምፅ እንዳለ ሁሉ የእግዚአብሔርን ድምፅ እንዳንሰማ እና እንዳንታዘዝ የሚገዳደር የጠላት የዲያቢሎስ ድምፅ አለ፡፡

የእግዚአብሔርን ድምፅ የምንለየው ድምፁ በጨዋነት ለማቅናት የሆነ ድምፅ መሆኑ ነው፡፡ የጠላት ድምፅ አንተ አትረባም አትጠቅምም ዋጋ የለህም በሚል በማጣጣል ሲመጣ የእግዚአብሄር ድምፅ ግን በማበረታታት ትችላለህ በሚል የአክብሮት አመለካከት ይመጣል፡፡

ፈታኝም ቀርቦ፦ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 4፡3

ሌላው የእግዚአብሔርን ድምፅ የምናውቀበት መንገድ ድምፁ በደስታ የሚያነሳሳ መሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲናገር ሰው እግዚአብሔርን ለማስደሰት በራሱ አነሳሽነት የሰማውን ለማድረግ ይቸኩላል እንጂ እግዚአብሔር ሰውን ካለፈቃዱ አያስቸኩልም፡፡

እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን፦ ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።የማቴዎስ ወንጌል 16፡23

የሰይጣን ድምፅ ሲመጣ ግን ይገፈትራል፡፡ የሰይጣን ድምፅ የእኛን መረዳት አይጠብቅም፡፡ የሰይጣን ድምፅ የእኛን እርምጃ አይጠብቅም፡፡ የሰይጣን ድምፅ አሁን ካላደረከው ያመልጥሃል ብሎ ካለፈቃዳችን እንድናደርገው ያጣድፋል ያስፈራራል ያስቸኩላል፡፡ 

መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል። ትንቢተ ኢሳይያስ 40፡11

የእግዚአብሔር ምሪት አጥብቃችሁ እስክትረዱት ይታገሳችሁዋል፡፡ ባልተረዳችሁት ነገር እርምጃ እንድትወስዱ አይጠብቅባችሁም፡፡ ሰይጣን ግን እንዳያመልጥህ ለማንኛውም አድርገው በል ፍጠንን በማለት ካለፍላጎታቸን ይገፈታትረናል፡፡ 

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Wednesday, June 21, 2023

በእግዚአብሔር ቃል ከባቢ ድምፁን መስማት

 


እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ቢናገርም ሰው ድምፁን ለመስማት ራሱ ካላዘጋጀ በእግዚአብሔር ምሪት ተጠቃሚ አይሆንም፡፡

ታዲያ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመለየት ከሚጠቅሙ ከባቢዎች መካከል የእግዚአብሔርን ቃል መሰላሰል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰል የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመለየት ያስችለናል፡፡

ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ እያሰብን እና እያሰላሰልን የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመለየት መቻል ዘበት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰላችን የእግዚአብሔርን ድምፅ የመስማት እና የመለየት እድላችንን በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል፡፡ 

የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰላችን የእግዚአብሔርን ድምፅ የመለየት አቅማችንን ከፍ ከማድረጉ በተጨማሪ የሰማነውን ድምፅ እንድንተገብረው አቅምን ይሰጠናል፡፡

የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፡8

እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ይናገረናል፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ከመናገሩ በተጨማሪ የእግዚአብሔርን ቃል ስናሰላስል የእግዚአብሄርን ድምፅ እንድንለይ ከባቢያችንን የተመቻቸ ያደርገዋል፡፡  

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Tuesday, June 20, 2023

ድምፁን ለመስማት የሚጠቅም የፀጥታ ከባቢ

 

እግዚአብሔር ይናገራል፡፡ መናገር የእግዚአብሔር ሃላፊነት ነው፡፡ መስማት ደግሞ የሰው ሀላፊነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ለመስማት ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡

ራሳችንን በሚገባ በማዘጋጀት በአለም ላይ መስማት ከሚፈልጉ ከብዙ ድምፆች መካካል የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማት ራሳችንን መለየት ይገባናል፡፡

ልጄ ሆይ፥ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሌም ጆሮህን አዘንብል። መጽሐፈ ምሳሌ 4፡20

የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመለየት ለእግዚአብሔር ጊዜ መስጠት እና ድምፁን ለመስማት መለማመድ ይጠይቃል፡፡ ኢየሱስ ስትፀልይ በርህን ዝጋ ያለው ስለዚህ ነው፡፡ ስንፀልይ እግዚአብሄርን ለመስማት ወዲህ እና ወዲያ የሚወስደንን አሳባችንን ዝም ማሰኘት ይጠይቃል፡፡ 

አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡6

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Sunday, June 18, 2023

እግዚአብሔር እረኛ

 


እግዚአብሔር እረኛችን ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመራናል፡፡ የእግዚአብሔርን ምሪት ከተከተለን በህይወታችን የምናጣው ምንም መልካም ነገር የለም፡፡ 

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም። በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፤ በዕረፍት ውኃ ዘንድ ይመራኛል። ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ። መዝሙረ ዳዊት 23፡1-3

እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙረ ዳዊት 95፡7

እግዚአብሄርን የመሰለ ማስተዋሉ የማይመረመር እረኛ እያለን እረኛ እንደሌላቸው በጎች አንቅበዝበዝ፡፡ ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሄር እረኛችን ሆኖ በትህትና እንከተለው እንጂ ወደገዛ መንገዳችን አናዘንብል፡፡ ይልቁንም ወደነፍሳችን እረኛ እና ጠባቂ እንመለስ፡፡ 

እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡25

እግዚአብሔርን እንደ እረኛ ሁልጊዜ እውቅና እንስጠው፡፡ 

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

Friday, June 16, 2023

ሰላም በልባችሁ ይግዛ

 


በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡15

ክርስቶስ ኢየሱስን እንደአዳኝ አምነን ከተቀበልንበት ቅፅበት ጀምሮ ክርስቶስ በልባችን ይኖራል፡፡ በውስጣችን ያለው የክርስቶስ ሰላም ምን ማድረግ እንዳለብን ይመራናል፡፡

አእምሮዋችን ቢጨነቅም እንኳን በልባችን ሰላም ከተሰማን ልናደርገው ያሰብነው ነገር የእግዚአብሄር ፈቃድ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን አንድን ነገር ለማድረግ ስናስብ ልባችን የሚረበሽ እና የውስጥ ሰላማችንን የምናጣ ከሆንን ያ ነገር ለእኛ የእግዚአብሄር ፈቃድ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡

የአእምሮዋችንን አስተሳሰብ ሰምተን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ልንስተው ልንሳሳት እንችላለን፡፡ ነገር ግን በልባችን ያለውን ሰላም ሰምተን እና ተከትለን ልንሳሳት አንችልም፡፡ ለአእምሮዋችንም ባይገባውም በልባችን ያለውን ሰላም በመከተል ብቻ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መከተል አንችላለን፡፡ በልባችን ሰላም ከተሰማን እና ልባችን የማይፈርድብን ከሆነ ሰላም ከሆነ የእግዚአብሄር ፈቃድ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

መፅሃፍ ቅዱስ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ የሚለው ሰላምን እንደመሪ እንድንሰማው እና እንድንከተለው                      ነው፡፡

በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡15

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


ክርስቶስ በእኔ ይኖራል

 


ክርስቶስ ኢየሱስን እንደአዳኛችን የተቀበልን ሁላችን በመንፈሱ አማካኝነት ክርስቶስ በውስጣችን ይኖራል፡፡ ይህ መለኮታዊ ህይወት በውስጣችን መኖር ያስፈለገው ምክኒያቱ እንዲመራን እና እግዚአብሄር በምድር ላይ እንድንፈፅመው የሰጠንን ስራ እንድናከናውን እንዲያስተምረን ነው፡፡

በውስጣችን ያለው መለኮታዊ ህይወት አንድን ነገር ማሰብ ሲፈልግ አብረነው እናስባለን ፣ መናገር ሲፈልግ አብረነው እንናገራለን ፣ ዝም ማለት ሲፈልግ አብረነው ዝም እንላለን መሄድ ሲፈልግ አብረነው አንሄዳለን ፣ መቀመጥ ሲፈልግ አብረነው እንቀመጣለን፡፡ በአጠቃላይ በውስጣችን ለሚኖረው ኢየሱስ አይን እግር እጅ አፍ እንሆንለታለን፡፡

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። ወደ ገላትያ ሰዎች 2፡20

ይህን በውስጣችን የሚኖረውን የእግዚአብሄርን ህይወት ከሰማን በሰላም ወደ መዳረሻችን እንደርሳለን፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


Thursday, June 15, 2023

የህይወት መንፈስ ህግ ወይስ ክፉና ደጉን የምታስታውቀው ፍሬ

 



እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጠር በየዋህነት እርሱን እንሰዲከተለው ፈጠረው፡፡ ሰው ይህ ክፉ ነው ይህ መልካም ነው ብሎ መለየት አልነበረበትም፡፡ የሰው ብቸኛ ድርሻ እግዚአብሔርን  በየዋህነት ማመን እና መከተል ብቻ ነበር፡፡

አሁንም እግዚአብሄር በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንጂ ክፉውንና ደጕን በምታስታውቀው ፍሬ እንድንኖር አይፈለግም፡፡ ሰው በውስን አእምሮው አስቦ ክፉ የሚለው ሁሉ ክፉ አይደለም ሰው መልካም የሚለው ሁሉ መልካም አይደለም፡፡

እግዚአብሄር መልካም ነው ካለው ብቻ መልካም ነው እግዚአብሄር ክፉ ነው ካለው ብቻ ክፉ ነው፡፡

እግዚአብሄር በመንገዳችን ሁሉ ለእርሱ ምሪት እውቅና እንድንሰጥ እንጂ በራሳችን ማስተዋል እንድንደገፍ አይፈልግም፡፡

በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። መጽሐፈ ምሳሌ 3፡5-6

ሰው መልካም የሚለውም እንኳን የእግዚአብሄር ፈቃድ ላይሆን ይችላል፡፡

ይልቁንም የአእምሮዋችንን ጫጫታ ዝም አሰኝተን በልባችን ባለው በህይወት መንፈስ ህግ ስንመራ ብቻ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈፀም እንችላልን፡፡

በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡2

ከክፉና ደግ ምርጫ ነፃ የምንወጣው በውስጣችን የሚኖረውን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን የህይወት መንፈስን ህግ ስንከተል ብቻ ነው፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa