Popular Posts

Showing posts with label church. Show all posts
Showing posts with label church. Show all posts

Sunday, May 17, 2026

የምንሞትለት እንጂ የምንገድልለት አምላክም ሆነ ሀይማኖት የለንም!

 የምንሞትለት እንጂ የምንገድልለት አምላክም ሆነ ሀይማኖት የለንም! 


አምላክ ሀያል ነው የእኛ እርዳታ አይፈልግም። እንዲገድሉለት የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት እውነተኛ ሀይማኖት አይደለም። የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት ሀሰተኛ ሀይማኖት ነው። የሰውን እርዳታ የሚፈልግ ሀይማኖት ከሰይጣን ነው። 

ብዙ ሀይማኖቶች በምድር ላይ ቢኖሩም በአጠቃላይ ምድር ላይ ያሉት ሁለት አይነት ሀይማኖቶች ብቻ ናቸው። በምድር ላይ እውነተኛ እና ሀሰተኛ ሀይማኖት አለ። እግዚአብሔር አንድ ነው። ከአንድ በላይ እውነተኛ ሀይማኖት ሊኖር አይችልም። በአለም ላይ ከአንድ በላይ  ሀሰተኛ ሀይማኖት ሊኖር ግን ይችላል። 

ታዲያ ሀይማኖት መያዙ ሳይሆን እውነተኛውን አምላክ መያዛችንን እርግጠኛ እንሁን። እኔን በተመለከተ ፍለጋ አቁሜያለው እውነተኛውን አምላክ አግኝቻለሁ።

እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። ዮሐንስ 17:3 ሁሉም ሀይማኖት ወደ አንድ ፈጣሪ ያደርሳል የሚሉ በሰይጣን የተታለሉ ናቸው። 

ኢየሱስም አለው፡— እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። ዮሐንስ 14:6 

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 

Sunday, April 12, 2026

ከእርሱ ጋር አስነሣን !



ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፣6 7

ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ስለእኛ ነው። ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው እኛ በሃጢያታችን ምክኒያት ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላላም እንዳንለያይ ነው።

ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፣21 22

ክርስቶስ ኢየሱስ የሞተው እኛ በሃጢያታችን መሞት የነበረበንን ሞት ነው። ክርስቶስ የሞተው በእኛ ምትክ ነው። ክርስቶስ የሞተው ለእኛ ነው።

በመጀመሪያ ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላላም እንዲኖር ነበር። በእግዚአብሔር የተፈጠረው ሃጢያትን የማያውቅ  ፍጹም ሰው ነበር።

ሰው ከእግዚአብሔር የተለየው ሃጢያት በሰራ ጊዜ ነበር።

እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፣16  17

ክርስቶስ የመጣው እኛ ወደፊት እንዳንሞት ከእግዚአብሔርም ጋር ለዘላላም እንዳንለያይ ነው።

ክርስቶስ ሃጢያት ያልተገኘበት ፍጹም ነው። ክርስቶስ መሞት አይገባውም  ነበር። ክርስቶስ የሞተው እኛ ሞት ሰለሚገባን ነበር። ክርስቶስ የሞተው እኛን ከሞት ሊያስነሳን በእኛ ምትክ ነው።  

ክርስቶስ የሞተው ለእኛ ትንሳኤን ሊሰጠን ነው።

እኛ ከክርስቶስ ጋር አብረነው ካልተነሳን ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።

የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ "ከእለታት አንድ ቀን ክርስቶስ ከሞት ተነሳ" ብለን ብቻ የምናስታውሰው የክርስቶስ ታሪክ አይደለም። የክርስቶስ ትንሳኤ የእኛም ከሙታን የመነሳት ልምምድ ነው። በክርስቶስ ሞትና ተንሳኤ የምናምን ሁላችን ከሞት ተነስተናል።

ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፣5-7

የትንሳኤ በአል የክርስቶስ ብቻ ሳይሆን የእኛም የትንሳኤ በአል ነው።

መልካም የትንሳኤ በአል

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

Tuesday, June 23, 2020

በምድራዊ እውቀት የማይደረስበት መንፈሳዊ ክልል



ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

በህይወታችን ላይ የሚነጣጠሩ ብዙ ጥቃቶች ከምናስበው በላይ መንፈሳዊ ናቸው፡፡

ለምሳሌ የጤና መታወክ ሲደርስብን ቶሎ የሚመጣልን የሳይንሱ እውቀትና የሳይንሱ መፍትሄ ነው፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን ቁሳዊ እናደርገዋለን፡፡ ብዙ ነገር ሲደርስብን በህክምና እውቀት ብቻ ልንተረጉመው እንፈተናለን፡፡

የበላሁት ምግብ ነው ወይም ቫይረስ ነው ብለን እንደሰው ልማድ ብቻ ጥቃቱን ልንዋጋው እንፈልጋለን፡፡ እንደሰው ልማድ ተዋግተን ከተሳካልን እሰየው፡፡ የሰይጣን ስራ ለማፍረስ ያለንን ነገር ሁሉ እምነታችን እና እውቀታችንን ሁሉ እንጠቀማለን፡፡

እንደሰው ልማድ ብቻ ከመዋጋት ያለፈ ነገር የሚጠይቅ ብዙ የዲያቢሎስ ጥቃት አለ፡፡  

የሰው ልጆች ጥቃት በቀጥታ ባይሆንም ቢያንስ በተዘዋዋሪ ከሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን ሌላ ራእይ የለውም፡፡ ራእዩ መስረቅ ማረድና ማጥፋት ብቻ ነው፡፡

ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። የዮሐንስ ወንጌል 10፡10

አንዳንዴ ሰይጣን በመንፈሱ በቀጥታ ባያጠቃንም ማድረግ ያለብንን ነገር በቸልተኝነት እንዳናደርግ በአእምሮዋችንም ቢሆን ያጠቃናል፡፡ ወይም የእግዚአብሄርን አላማ በምድር ላይ እንዳንፈፅም በፍርሃት ሽባ ያደርገናል፡፡ ሌላም ጊዜ በፀጋ ከተቀበልነው በሽታን በእኛ ላይ ሊያደርግ ይሞክራል፡፡

ተዘዋዋሪ የሰይጣን አላማ ቢሆኑም ንፅህናን ባለመጠበቅ የሚመጡ በሽታዎች ከሰይጣን አላማ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ጥንቃቄያችንንም ተጠቅሞ ከጠላት ጥቃት ያስመልጠናል፡፡

ተጠንቅቀንም እግዚአብሄር አስመለጠን ነው የምንለው እንጂ ጥንቃቄያችንም ፍፁም በማይሆነው በጥንቃቄያችንም አንታመንም፡፡

እግዚአብሄር ለእኛ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለደህንታችን ያለውንም ነገር ሁሉ ይጠቀማል፡፡ እግዚአብሄር የዶክተሮችን ጥበብ ተጠቅሞ በሽታን ይዋጋልናል፡፡ የዲያቢሎስን ስራ ለማፍረስ ያለንን ምድራዊ እውቀት እና መንፈሳዊ እውቀርት ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ ሰይጣን በህይወታቸን በጤናችን ምንም ስፍራ እንዳያገኝ እስከመጨረሻው ፀንተን እንቃወመዋለን፡፡

በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡9

ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፡8

ከዶክተሮች እውቀት በላይ ያለ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ዶክተሮች በምድራዊ ጥበባቸው የማይደርሱበት መንፈሳዊ ክልል አለ፡፡

ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።  1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡14

እግዚአብሄር እምነታችንን ተጠቅሞ ከበሽታው ጀርባ ያለውን መንፈሱን በኢየሱስ ስም እንድንቃወመው አይናችንን ይከፍታል ይመራናል፡፡

ይህችን ሴት በወቅቱ ዶክተሮች ጋር ብትታይ ዶክተሮች በምድራዊ እውቀታቸው የማይረዱት መንፈሳዊ ክልል ስላለ ስለበሽታዋ አንድ ምክኒያት ይሰጧታል፡፡  

ኢየሱስ ግን ከዚህ በሽታ ጀርባ ያለውን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣውን ሰይጣንን አየው፡፡ ኢየሱስ በሽታውን ሳይሆን ከበሽታው በስተጀርባ ያለውን የበሽታውን ምንጭ አደረቀው፡፡

ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። የሉቃስ ወንጌል 13፡16

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #ፈውስ #ስጋ #ጤንነት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ተስፋ #አሁን #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


Sunday, June 21, 2020

ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። መጽሐፈ መክብብ 3፡12-13 ፣ 8፡5

ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። መጽሐፈ መክብብ 3፡12-13 ፣ 8፡5

Monday, June 15, 2020

እግዚአብሔር የሚቀጣው እንዲበድል ያደረገውን ስጋዊ ፍላጎት ነው


ብዙ ሰዎች በደልን እንዴት እንደሚይዙ ስላማያውቁ በህይወታቸው ዘመን ይሰቃያሉ፡፡ ገንዘባችንን እንዴት እንድምንይዝ ፣ ጤናችንን እንዴት እንድምንጠበቅ ፣ ስራችንን እንዴት እንደምንሰራ የመሳሰሉትን ከምናውቀው እውቀት በላይ ከሰው ጋር እንዴት እንድምንኖር ማወቅ ከብዙ ኪሳራ ከብዙ የስሜት በሽታ ብሎም ከብዙ ችግሮች ይጠብቀናል፡፡

ሰውን እንድናምን ከሰው ጋር እንድንኖር ተፈጥረናል፡፡ ሰው ጠቃሚ እንደመሆኑም መጠን ግን በተለያየ ጊዜም ይበድለናል፡፡

ሰው አውቆም ይሁን ሳያውቅ ሰውን ስለሚበድል ሰው ሰውን የመበደሉ እውነት የማይቀር ነገር ነው፡፡ ዋናው ነገር ሰው ሰው ሰውን ይበድላለ ወይ የሚለው ጥያቄ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር የተበደለው ሰው በደሉን እንዴት ይይዘዋል የሚለው ጥያቁ ነው፡፡ ሰው ለበደል እንዴት እንደሚመልስ ካወቀ ያርፋል፡፡

ሰው በደሉን በትክክል ከያዘው ይማርበታል ያድግበታል የተሻለ ሰው ሆኖ ይለወጥበታል፡፡ ሰው በደሉን በትክክል ካልያዘው ይሰቃይበታል ህይወቱን ያባክንበታል፡፡

ሰው ሲበድለን በመጀመሪያ ደረጃ ነፃ የሚያወጣን ነገር ስለበደሉ የተቻለንን ያህል ሃላፊነት መውሰዳችን ነው፡፡ እርሱ 100 % ጥፋተኛ ነው እኔ 0% ጥፋተኛ ነኝ የሚለው ነገር አያዋጣም፡፡ ቢያንስ ሲያጠፋ እኛ ጥፋቱን የመለስንበት መንገገድ ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡

ሁለተኛ እግዚአብሄር የሚቀጣው የበደለውን ሰውዬ ሳይሆን እንዲበድል ያደረገውን ስጋዊ ፍላጎት ነው፡፡

ሶስተኛ ማወቅ ያለብን እርሱን እንዲበድል ያደረገው ያው ስጋዊ ፍላጎት እኛም ውስጥ እንደሚኖር አውቀን ትምህርትና ግሳፄ መውሰድ ነው፡፡ እኔ እንደዚህ መበደል አልችልም ማለት ሞኝነት ነው፡፡ በበዳዩ ውስጥ ያየነውን የስጋ አስከፊነት ካየን እኛ ውስጥ ያለው ስጋ በሌሎች ላይ ተመሳሳይ በደል እንዳያደርግ እንጨክንበታለን፡፡

አራተኛ የበደለን ሰው እስኪወድቅ አለመጠበቅ ነው፡፡ ሰው ስራውን ትቶ የበደለኝ ሰው ከመቼ መቼ ይቀጣል እያለ ስለበደለው ሰው የሚከታተል ከሆነ የራሱን የህይወት አላማ ትቶ ስቶዋል ማለት ነው፡፡ ከበደለው ሰው ጋር በመፎካከር የህይወት አላማውን አሽቀንጥሮ የሚጥል ሰው የህይወት አላማው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የማያውቅ ሰው ነው፡፡

የበደለ ሰው ስጋ በአስቸጋሪ ነገር ውስጥ በማለፍ የስጋ ፍላጎቱ ሊገደል ይችላል፡፡ በደል ያስደረገው ያ ስጋዊ ፍላጎት ዛሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በምን መጠን በምን ሁኔታ ይቀጣ አታውቅምና ትተኸው ህይወትህን ኑር፡፡

ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡19

አንተን ስለበደለህ እንዲጠፋ ከመፈለግ ይልቅ ሰው እንዲለወጥ እንዲሻሻል እንዲመለስ ፀልይለት፡፡ አንተን ስለበደለ እንዲቀጣ ብቻ ሳይሆን በዚህ አጋጣሚ እንዲመለስ እንዲስተካከል ፈልግ፡፡

ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡1

አንተ የበደለህ ሰው እርዳታህን በሚፈልግበት ጊዜ መርዳትህ እንዳልበደለህ አይናገርምና እርዳው፡፡ የበደለ ሰው ይታዘንለታል እንጂ አይቀናበትም፡፡

ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡20

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #ምህረት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 


Sunday, April 26, 2020

በምድር ያለነው


በተለያየ ጊዜ በህይወታችን የተለያዩ ተግዳሮቶች ይመጣሉ፡፡ ታዲያ ይህን አልፈው ይሆን ብለን የምናስብበት ውጥረት በህይወታችን ይመጣል፡፡ እንደዚህ አይነት ውጥረት በህይወታችን ሲገጥመን "በምድር ላይ ያለሁት ለምንድነው?" ብለን ይህን ጥያቄ ከልባችን እንጠይቃለን፡፡
በምድር ላይ ያለሁት ለምንድነው? የሚለው ጥያቄ ሁል ጊዜ መጠየቅና በትክክል መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡
እውነት ግን በምድር ላይ ያለነው ለምንድነው?
የማንሞተው ለምንድነው ? ወይም መሞት የማንፈልገው ለምንድነው ?
በምድር ላይ ያለነው ስላልሞትን ነው ? ወይስ በምድር ላይ ስለመኖራችን ሌላ አለማ አለ?
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው አስቦና አቅዶና በአላማ ነው፡፡
እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ኦሪት ዘፍጥረት 1፡26-27
ወደምድር ከመምጣታችን በፊት ወደምድር የመጣንበት ልዩ አላማ ነበር፡፡
ማንም ሰው በድንገት ውይም በአጋጣሚ በምድር ላይ የተወለደ ሰው የለም፡፡ ሰው በምድር ላይ የመወለዱ ምልክት ከመወለዱ በፊት የተወለደበት ልዩ አላማ የመኖሩ ምልክት ነው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርሚያስ 29፡11
እኛ በምድር ላይ ለመኖር ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር በምድር ላይ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በምድር ላይ ለመኖር ካለን ፍላጎት በላይ በምድር ላይ እንድንኖር የተፈለገበት የእግዚአብሄር አላማ ይበልጣል፡፡
በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል። ምሳሌ 19፡21
በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ። ኢሳያስ 46፡10
ይህን በህይወታችን ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን አላማ ስንረዳ እናርፋለን፡፡
እግዚአብሄር እንዴት እንደሚወደን ስንረዳ እና በህይወት ለመኖራችን ልዩ አላማ እንዳለው ስንረዳ ከፍርሃት ነፃ እንወጣለን፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡18-19
ፍርሃት የእግዚአብሄርን ፍቅር የመረዳታችንን ደረጃ ያመለክታል፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ያለውን የፍቅር አላማ በተረዳን መጠን ፍርሃት ከህይወታችን ቦታ እያጣ ይሄዳል፡፡  
የእግዚአብሄርን ፍቅር በተረዳን መጠን ከፍርሃት ነፃ እንወጣለን፡፡ እግዚአብሄር እንዴት በፍቅር እንደሚያየን በህይወታች ላይ ያለውን የእግዚአብሄርን የፍቅር አላማ እየተረዳን ስንመጣ በፍርሃት ሳይሆን በፍቅር እንንቀሳቀሳለን፡፡
የእግዚአብሄርን የፍቅር አለማ ስንረዳ የሚያንቃቅሰን ፍርሃት ሳይሆን ፍቅር ብቻ ይሆናል፡፡
በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 2፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አላማ #ተስፋ #ፍፃሜ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ተስፋ #ፍፃሜ #የእግዚአብሄርሃሳብ #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Wednesday, February 12, 2020

ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም



ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም። መጽሐፈ መክብብ 11፡4
ህይወት የእምነት ጉዞ ነው፡፡ ህይወትን በሚገባ ማጣጣም ከፈለግክ በእምነት መኖር መጀመር አለብህ፡፡ በእምነት መራመድ ካልጀመርክ የህይወትን እውነተኛውን ጣእም በፍፁም አታገኘውም፡፡ ሰው መኖር የሚጀምረው በእምነት መራመድ ሲጀምር ብቻ ነው፡፡ የሰው እውነተኛ መኖሪያ የእግዚአብሄር ቃል እምነት ነው፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 4፡4
ሰው ዲዛይን የተደረገው ለእምነት ኑሮ ነው፡፡ ሰው የሚኖረው በእምነት ነው፡፡
እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ትንቢተ ዕንባቆም 2፡4
እምነት የሚመጣው ከእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡17
በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ለተፈጠረው ክቡር ለሆነው ሰው ለሰው ልጅ ከእግዚአብሄ ቃል ያነሰ ኑሮ አይገባውም፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 4፡4
የሰው እውነተኛ እርካታ በእምነት ሲኖር ነው፡፡
ነገሮች ሆነው ከማየትህ በፊት የእግዚአብሄርን ቃል አምነህ እርምጃ ካለወሰድክ ከእግዚአብሄር ጋር መኖር አትችልም፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር የምትገናኘው በስጋ አይን የማይታየውን መንፈስ የሆነውን እግዚአብሄርን የምትሰማው ፣ እግዚአብሄርን የምትነካው ፣ እግዚአብሄርን የምታየው ሁሉ በእምነት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ነገር ሁሉ በእምነት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። መዝሙረ ዳዊት 334
ነገሮች ተለውጠው ደስ ለመሰኘት የምትጠብቅ ከሆነ ደስ መሰኘቱን እርሳው፡፡ ነገሩን የሚለውጠው በእምነት እርምጃ በመውሰድ ደስ በመሰኘትህ ብቻ ነው፡፡
የምትፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ኪስህ ከገቡ በኋላ እፎይ ለማለት እየጠበቅክ ከሆነ የማይፈፀም ተስፋ እየጠበክ ነው፡፡
ለማመን ፀሎትህ እስኪመለስ እየጠበቅክ ከሆነ ፀሎትህ ለመፈፀም የአንተን እምነት እየጠበቀ ነው፡፡
እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል። የማርቆስ ወንጌል 11፡23-24
ሁሉ ደህና ነው ለማለት ነገሮች ሁሉ ተስተካክለው እስክታይ አየጠበቅክ ከሆነ በከንቱ ትጠብቃለህ፡፡   
ከመዝራትህ በፊት ሁኔታዎችን እየጠበቅክ ከሆነ መቼም አታጭድም፡፡
ምልክት ከማየትህ በፊት ማመን አለብህ፡፡ እምነትንም የሚያመጣው የእግዚአብሄር ቃል እንጂ ምልክት እምነትን አያመጣም፡፡ ምልክቱን የሚያመጣው እምነትህ ነው፡፡  
ከውጤት እና ከምልክት በፊት የእምነት እርምጃ ይቀድማል፡፡
እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፥ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኛዋለህና። መጽሐፈ መክብብ 11፡1
አስቀድመው ምልክትን የሚፈልጉ ካላየሁ አላምንም የሚሉ ሰዎች እግዚአብሄርን የማይፈልጉ አሿፊ ሰዎች ናቸው፡፡
ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ። የማቴዎስ ወንጌል 16፡1፣4
ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፥ ደመናንም የሚመለከት አያጭድም። መጽሐፈ መክብብ 11፡4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ወንጌል #ስብከት #ቃል #ዝራ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ 

Thursday, July 12, 2018

የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው

በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡8
የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ገላትያ 5፡19-21
ስጋ እንደ መንፈስ ፍሬ የለውም፡፡ ስጋ ያለው ካለ ፍሬ የሆነ ስራ ነው፡፡ የስጋ ስራ ደግሞ ረቂቅ ማንም ሊያውቀው የማይችል አይደለም፡፡ የስጋ ስራ የተገለጠ ነው፡፡ የስጋን ስራ በህይወታችንም ይሁን በሰዎች ህይወት አይተን እናውቀዋለን፡፡ 
ዝሙት
ሚስት ወይም ባል ካልሆነ ሰው ጋር ያለ ልቅ የሆነ ግንኙነት
ርኵሰት፥
በአለም ስርአት አስተሳሰብ አመለካከት መርከስ
መዳራት፥
ፈር የለቀቀ ግንኙነት፡፡ ለስጋ ደስታ ልክ አለማበጀት፡፡ ልቅነት፡፡
ጣዖትን ማምለክ፥
ከእግዚአብሄር ውጭ መፍትሄን መፈለግ፡፡
ምዋርት፥
ሌላው ሰው ላይ ክፉ እንዲደርስበት መፈለግ መስራት ክፋት ለማድረግ እንግዳን ሃይል መፈለግ መጠቀም፡፡
ጥል፥
መብትን በራስ ጉልበት ለማስከበር ሲባል ሰው ላይ የስሜት ወይም የአካል ጉዳት ጉዳት ማድረስ
ክርክር፥
በንግግር ብዛት በሰው ላይ ተፅኖ ማድረግ ፣ ሌላውን ሰው አላግባብ ለመቆጣጠር መሞከር ፣ በእግዚአብሄር አለመታመን በቃል ብዛትና በንግግር ችሎታ ሌላውን ለመቆጣር መሞከር፡፡   
ቅንዓት፥
በሌላው ከፍታ ማግኘትና መከናወን ደስ አለመደሰት፡፡ በሌላው ስኬት መበሳጨት፡፡ የሌላው ከፍታ በሌላው ውድቀት ምክኒያት እንደመጣ መቁጠር፡፡
ቁጣ፥
በከፍታ ድምፅ ፣ በከፍተኛ ስሜት የራስን ፍላጎት ብቻ ለማስፈፀም መሞከር፡፡ ንግግርን ሃሳብ ከማስተላለፍ ያለፈ ፈር ለለቀቀ ሌላውን ለመቆጣጠር ክፉ አላማ መጠቀም፡፡
አድመኛነት፥
ሌሎችን ለራስ የግል አላማ በክፋት ማነሳሳት ማንቀሳቀስ፡፡ ለግል አላማ ሌላውን ማሰባሰብ በሌላው ላይ በክፋት ማስነሳት አብሮ መጣላት፡፡  የሌላውን ተሰሚነት እና ችሎታ ተጠቅሞ የግልን ድብቅ አላማ ማስፈፀም፡፡ የግል ድብቅ አላማን ለማስከበር ቡድን ፈጥሮ ሌላውን ማጥቃት፡፡ 
ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። የያዕቆብ መልእክት 3፡16
መለያየት፥
በሰዎች መካከል ክፍፍልን መፍጠር፡፡ ጥላቻን መቀስቀስ አንዱን ሰው ከሌላው ሰው ማለያየት አንድነት እንዳይኖረው ማድረግ፡፡
መናፍቅነት፥
ለእምነት ራስን ሙሉ ለሙሉ አለመስጠት መሰሰት ራስን መለየት አንድነት አለማድረግ ራስን ከሌላው ጋር አለማስተባበር
ምቀኝነት፥
በሌላ ሰው ማግኘት መከናወን ደስተኛ አለመሆን መበሳጨት ሌላው እንዳያድግ እንዳይለወጥ እንቅፋት ማድረግ፡፡
መግደል፥
ጥላቻ እንደእርሱ ያለ እግዚአብሄር የፈጠረውን ሰው እንዳይኖር መፍረድ ትእቢት ማን አለብኝነት፡፡
ስካር፥
እግዚአብሄር ለስው የሚናገርበትን የእግዚአብሄርን ድምፅ የሚሰሙበትን ህሊናን ማደንዘዝ፡፡ እግዚአብሄርን ለመስማት አለመፈለግ፡፡ ከመጠን በላይ መዝናናት
ዘፋኝነት፥   
ስጋን ያለልክ መልቀቅ፡፡ መዝናናትን ተድላን ከእግዚአብሄር ባለይ መውደድ ምንም ምንም ብሎ ነፍስን ማስደሰት፡፡
ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡7
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ክብር #ራእይ #ስጋ #ሃሳብ #የዘራውን #ያጭዳል #ዝሙት #ርኵሰት #መዳራት #ጣዖትንማምለክ #ምዋርት #ጥል #ክርክር #ቅንዓት #ቁጣ #አድመኛነት #መለያየት #መናፍቅነት #ምቀኝነት #መግደል #ስካር #ዘፋኝነት #አትሳቱ #አይዘበትበትም #መበስበስ #ሰላም #ህይወት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም

አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡7-8
ሰው ሰው ላይ ቀልዶ ምን አልባት ሊያመልጥ ይችል ይሆናል፡፡ ሰው እግዚአብሄር ላይ ቀልዶ ሊያመለጥ ግን አይችልም፡፡
ሰው መጠንቀቅ ያለበት በሰላም ጊዜ ነው፡፡ ሰው መጠንቀቅ ያለበት በእለት ተእለት ኑሮው ነው፡፡ የሰውን ህይወት የሚሰራውም የሚያፈርሰውም የእለት ተእለት ውሳኔና እርምጃ ነው፡፡
ሰው መጠንቀቅ ያለበት በዘር ጊዜ ነው፡፡ ሰው ዘሩን የሚመርጠውና የሚያስተካክለው በዘር ጊዜ እንጂ በአጨዳ ጊዜ አይደለም፡፡ ሰው ይፍጠንም ይዘግይም የሚያጭደው የዘራውን ያንኑ ነው፡፡ አጨዳው ስለዘገየ ዘሩን አይለውጠውም፡፡ ሰው የሚያጭደው የዘራውን ያንኑ ነው፡፡  
ሰው መጠንቀቅ መዘገየት ያለበት ከመዝራቱ በፊት ነው፡፡ ሰው ከዘራ በኋላ ስለዘሩ ምንም ማደርግ ስለማይችል ሰው ከመዝራቱ በፊት ቢጠነቅቅ መልካም ነው፡፡ ሰው ከመዝራቱ በፊት ካለተጠነቀቀ ከዘራ በኋላ የዘሩን ውጤት መጠበቅ እንጂ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ ሰው ከዘራ በኋላ ዘሩን ሊለውጥ አይችልም፡፡
መጽሃፍ ቅዱስ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው ይላል፡፡
እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና። የማቴዎስ ወንጌል 7፡12
በሌላ አነጋገር ሰዎች ሊያደርጉባችሁ የማትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አታድርጉባቸው ማለቱ ነው፡፡ ሰዎች እንዲያደርጉብን የማንፈልግውን ነገር ሰው ላይ ማድረግ የለብንም፡፡ ሰዎች ሊያደርጉባችሁ የማትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ማድረግ በንግግር ሳይሆን በድርጊት እኔ እንዲህ እንዲደረግብኝ እፈልጋለሁ ማለት ነው፡፡
አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡7
በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡8
ከሃሳብ ጀምሮ ስለስጋ ማሰብ ሞት ነው፡፡
ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡8
ሰው በስጋው ዘርቶ በመንፈስ አያጭድም፡፡ ሰው በስጋው የዘራውን መበስበስን ያጭዳል፡፡ ሰው በስጋው የዘራውን በሞት በመለየት በጥፋት ያጭዳል፡፡
ሰው በስጋው የስጋን ስራ ዘርቶ በመንፈስ ህይወትንና ሰላምን ሊያጭድ አይችልም፡፡ የስጋ ስራም አነዚህ ናቸው፡፡
የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡19-21
አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡7-8

#ክብር #ራእይ #ስጋ #ሃሳብ #የዘራወን #ያጭዳል #አትሳቱ #አይዘበትበትም #መበስበስ #ሰላም #ህይወት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #መንገድ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Wednesday, July 11, 2018

ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ

ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15፡22-23
እግዚአብሄር በቃሉ ፍላጎቱን ግልፅ አድርጓል፡፡
ብዙ ሰዎች እግዚአብሄር ሁልጊዜ በመስዋእት ደስ የሚሰኝ ይመስላቸዋል፡፡ ሁሉም መስዋእት አይደለም እግዚአብሄርን ደስ የሚያሰኘው፡፡ አንዳንዱ መስዋእት እግዚአብሄርን ደስ አያሰኘውም፡፡ ሃይማኖታዊ ስርአት ብቻ ስለሆነ እግዚአብሄር ደስ የሚሰኝበት የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዱ ሃይማኖታዊ ስርአት እግዚአብሄርን ደስ አያሰኘውም፡፡
ሕዝቤ፥ ስማኝ፥ ልንገርህ፤ እስራኤልም፥ ስማኝ፥ ልመስክርብህ፤ አምላክስ እኔ አምላክህ ነኝ። ስለ ቍርባንህ የምዘልፍህ አይደለሁም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህ ሁልጊዜ በፊቴ ነው። ከቤትህ ፍሪዳን ከመንጋህም አውራ ፍየልን አልወስድም፤ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው። ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? ሰው በራሱ አነሳሽነት ለእግዚአብሄር ከሚሰጠው መስዋእት ይልቅ እግዚአብሄር የጠየቀውን ነገር የሚታዘዝ ሰው ይበልጣል፡፡ መዝሙረ ዳዊት 50፡7-13
እግዚአብሄ ሰውን የፈጠረው እንዲታዘዘው ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው ውስብስብና ብዙ ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ከሰው የሚጠይቀው ከባድና አስቸጋሪ ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሄ የሚፈልገው የሚያስብለትን እቅድ የሚያወጣለትን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው ነገሮችን በአዲስ መልክ የሚሰራለትን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አዲስ ነገር የሚፈጥርን ሰው አይደለም፡፡ የሚፈልገው እግዚአብሄር የሚፈልገው መስማትን ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው ሰምቶት የሚታዘዝን ሰው ነው፡፡
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ትንቢተ ሚክያስ 6፡8
እግዚአብሄር የሚታዘዝለትን ሰው ይፈልጋል፡፡ ለእግዚአብሄር መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጥበታል፡፡ ለእግዚአብሄር ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጥበታል፡፡  
እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15፡22
በተለይ አለመታዘዝ እግዚአብሄርን ያስቆጣዋል፡፡ እግዚአብሄር አለመታዘዝን በቀላሉ አያየውም፡፡ እግዚአብሄር አለመታዘዝን አመጻ ይለዋል፡፡
እግዚአብሀረ ንጉስ ነው፡፡ አለመታዘዝ በእግዚአብሄር ዘንድ ስህተት ብቻ ሳይሆን አፀያፊም ነገር ነው፡፡
ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15፡23
በእግዚአብሄር ፊት አለመታዘዝና ምዋርተኝነት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ እልከኝነትና ጣኦትን ማምለክ አንድ ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ዓመፀኝነት ምዋርት የሚያያቸውና የሚፀየፋቸው በእኩል ደረጃ ነው፡፡ እግዚአብሄር እልከኝነትና ጣኦትን ማምለክ የሚቀጣው እኩል ነው ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#የእግዚአብሄርምክር #የእግዚአብሔርፈቃድ #እግዚአብሔር #እንደተፃፈ #ማታዘዝ #ዓመፀኝነት #ምዋርተኛ #ኃጢአት #እልከኝነትም #ጣዖትንና #ተራፊም #ማምለክ  #መባ #መሥዋዕት #አመፃ #እምነት #የሰውአሳብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

እግዚአብሔር በመሥዋዕት ደስ ይለዋልን?

ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15:22
እግዚአብሄር ድሃ አይደለም የሚያስፈልገውን ነገር አናቀርብለትም፡፡ እግዚአብሄር የጎደለው አይደለም የሚጎድለውን አናሟላለትም፡፡
የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው። ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? መዝሙረ ዳዊት 50:10-13
እግዚአብሄር እቅድ የሚያወጣለት ሰው አልፈለገም፡፡ እግዚአብሄር አማካሪ አላስፈለገውም፡፡ እግዚአብሄር ምክር የሚሰጠው ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር አቅድ የሚያወጣለት ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር ለእርሱ የሚያስብለት ሰው አይፈደልግም፡፡
ምድር ከመፈጠርዋ በፊት እግዚአብሄር ምድርን ለአላማው ፈጠረ፡፡ እኛ ከመፈጠራችን በፊት ለአላማ ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር ስለምድር እቅድ አለው፡፡ እግዚአብሄር ስለምድር የወደፊት ሁኔተ የሚያማክረው ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአበሄር ስለእኛ ህይወት ምክርን የሚለግሰው ሰውን አልፈለገም፡፡
የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?፡13-14
የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ወደ ሮሜ ሰዎች 11፡34-35
ሰው በራሱ አነሳሽነት እግዚአብሄርን ሊያገለግልበት የሚፈልገውን መንገድ እግዚአብሄር አይወደውም፡፡ ሰው በራሱ አነሳሽነት እግዚአብሄርን ሊያስደስት የሚሄድበትን መንገድ እግዚአብሄር አይፈልገውም፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ለማገልገል መሞከር ባዶ ሃይማኖት ነው፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ለማስደሰት መሞከር ሞኝነት ነው፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ደስ ለማሰኘት መሞከር የእግዚአብሄርን አዋቂነት አለመረዳት ነው፡፡
እግዚአብሄር የራሱ መንገድ አለው፡፡ እግዚአብሄር ሊመለክ የሚፈልገው በራሱ መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንድታስደስቱት የሚፈልገው በራሱ መንገድ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው መሪ ፈልጎ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ታዛዠ ፈልጎ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው አዲስ ነገር አንዲፈጥርለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ያዘዘውን እንዲያደርግ ነው፡፡
በራሳችሁ አነሳሽነት ለእግዚአብሄር ከምታደርጉለት ነገር በላይ ያዘዛችሁን ነገር ብታደርጉ ይበልጥበታል፡፡ ለእግዚአብሄር ትልቅ ነገር ከምታደርጉለት ያዘዛችሁን ትንሽዋን ነገር ብታደርጉለት ይመርጣል፡፡ ለእግዚአብሄር ልዩ ነገር ከምታደርጉለት እርሱ እንድታደርጉለት የፈለገውን ያንኑ ነገር ብታደርጉለት ይሻለዋል፡፡ ለእግዚአብሄር መልካም የሚመስለውን ነገር ከምታደርጉ እርሱ ያዘዘውን ነገር ብታደርጉ ይመረጣል፡፡
ሳኦል እግዚአብሄር ሲልከው ከብቶቹን ሁሉ ግደል ምንም ነገር እንዳታስቀረ ሁሉን አጥፋ ብሎ ነው፡፡ ሳኦል ግን ጠቢብ የሆነ መሰለው፡፡ ሳኦል ግን ከእግዚአብሄር በላይ አስተዋይ የሆነ መሰለው፡፡ ሳኦል ግን ከእግዚአብሄር የተሻለ ሃሳብ ያገኘ መሰለው፡፡ ሳኦል ግን አንድ አዲስ ሃሳብ መጣለት፡፡ ሳኦል ግን እግዚአብሄርን ማስደነቅ ፈለገ፡፡ ስለዚህ ሳኦል ለእግዚአብሄር የሚሰዋውን መርጦ በማስቀረት አታድርግ የተባለውን ነገር አደረገ፡፡ ሳኦል እግዚአብሄር ባልጠየቀው ነገር ሊያስደስተው ፈለገ፡፡
በዚህ አግዚአብሄር ጎሽ አላለውም፡፡ በዚህ እግዚአብሄር ተቆጣ፡፡ እግዚአብሄርን አለመታዘዝ እንደሟርተኛ ሃጢያት እንደሆነ እግዚአብሄር በነቢዩ ተናገረ፡፡
ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15:፡23 
አሁንም ብዙ ሰዎች እግዚአብሄር እንዲያደርጉ የጠየቃቸው ነገር ቀላል ሆኖባቸዋል፡፡ ምንም ቀላል ቢመስል እግዚአብሄር የተናገረህን ከማድረግ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አሁንም እግዚአብሄር የፈለገባቸውን ትተው የተሻለ ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፡፡ አሁንም ብዙዎች እግዚአብሄርን ከመታዘዝ ይልቅ መስዋእት በማቅረብ እግዚአብሄርን ሊያስደንቁት የሚጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ አሁንም እግዚአብሄርን ከመታዘዝ ይልቅ በራሳቸው መንገድ እግዚአብሄርን ለማገልገል በመሞከር ህይወታቸውን በከንቱ የሚያባክቡ ሰዎች አሉ፡፡
አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 11፡4
እግዚአብሄር ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰርፕሪዝ አይደረግም፡፡ እግዚአብሄር ሰርፕራዝ የሚያደርገው ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው ያለውን የሚሰማና የሚያደርግን ሰው ነው፡፡
ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15:22
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#የእግዚአብሄርምክር #የእግዚአብሔርፈቃድ #እግዚአብሔር #እንደተፃፈ #ማታዘዝ #ዓመፀኝነት #ምዋርተኛ #ኃጢአት #እልከኝነትም #ጣዖትንና #ተራፊም #ማምለክ  #መባ #መሥዋዕት ##እምነት #የሰውአሳብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ