Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, February 28, 2018

ቃሉን ለመተግበር የሚጠቅሙ አምስት ምክሮች

የእግዚአብሄር ቃል የሚሰራ የሚለውጥ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን የሚሰራው ሲተገበር ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል ከሰሙ በኋላ እንዴት እንደሚተገብሩት ሳያውቁ ሲጨነቁ እናያለን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል በየደረጃው እንዴት እንደሚተገብሩት ሳያውቁ ግራ ሲገባቸው እንመለከታለን፡፡  
የእግዚአብሄርን ቃል በመተግበር ፍሬ የምናፈራበት ሰባት ምክሮች እነሆ፡፡
1.      በደንብ ያለተረዳኸውን የቃሉን ክፍል ለመተግበር አትሞክር
ሁሉንም የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል በአንድ ጊዜ ለመተግበር አትሞክር፡፡ ቤት ከመሰረት ተጀምሮ ቀስ በቀስ እንደሚገነባ ሁሉ የሰውም የእግዚአብሄር ቃል የመተግበር አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የመፅሃፍ ቅዱስ ቃል  ከትልቁ ጀምረህ በአንዴ ለመተግበር መሞከር ተስፋ ሊያስቆርጥህና የእግዚአብሄር ቃል ሊተገበር አይቻልም የሚል ደረጃ ላይ እንድትደርስ ሊያደርግህ ይችላል፡፡ እግዚአብሄርም ከሰው የሚጠብቀው የመታዘዝ መጠን ሰው ቃሉን የተረዳውን መጠን ብቻ ነው፡፡ የተረዳኸውን የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል እየተገበርክ ያልረተረዳኸውን ለመረዳት ቃሉን ፈልግ፡፡ ያልተረዳኸውን ስላልተገበርክ አትኮነን ይህ ኩነኔ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡
ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡48
2.     ቃሉን በትጋት ማሰላሰል ቃሉን ለመተግበር ጉልበት ይሆንሃል
ቃሉን ማሰላሰል በቃሉ ከባቢ ውስጥ እንድትሆን ያደርጋል፡፡ በቃሉ ከባቢ ውስጥ መሆን ደግሞ እንዳትታዘዝ ከሚገዳደርህ ከስጋህ ሃሳብ ይለይሃል፡፡ ቁጭ ብሎ ሌብነትን የሚያስብ ሰው ሌባ እንጂ ሌላ ምንም ለመሆን አቅም ያጣል፡፡ እንዲሁም ቃሉን ብቻ የሚያስብና የሚያሰላስል ሰው ቃሉን እንጂ ሌላ ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው ቃሉን የሚያስብና የሚያሰላስል ሰው እንደ እግዚአብሄር ያስባለ የሚባለው፡፡
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፡8
3.     የቃሉን ትእዛዝ ብቻ ሳይሆን ለምን እንደታዘዘ እወቅ
አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል የሚያደርጉት እውነትነቱን ተረድተውት ሳይሆን ስለተባለ ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶች ሃጢያትን የማያደርጉት ሃይማኖታቸው ስለማይፈቅድ እንጂ የሃጢያትን ክፋት አውቀው አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትቅመስ አትንካ በሚል ትእዛዝ ብቻ የእግዚአብሄርን ቃል ለማድረግ ሲሞክሩ ጫና ይሆንባቸዋል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ያዘዘውን ያዘዘው ለምን እንደሆነ ከቃሉ ፈልገው ሲያገኙትና ሲረዱ ቃሉን በደስታ ይተገብሩታል እንጂ እንደ ሃይማኖታዊ ወግ ብቻ አይፈፅሙትም፡፡ እግዚአብሄር ያዘዘውን ትእዛዝ ምክኒያቱን ማወቅ ሽክሙን እኛም እነደንወስደው ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሄር እንዳንሰክር የፈለገው ስንሰክር እግዚአብሄር የሚናገርበት ህሊና ስለሚደነዝዝና እግዚአብሄርን መስማት ስለማንችል በሰይጣን ሃሳብ ብቻ ውስጥ ስለምንወድቅ ነው፡፡
ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ቆላስይስ 2፡20-22
4.     ቃሉን ስታደርግ አታጠናክረው
የእግዚአብሄር ቃል በራሱ በቂ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የነጠረ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ቃል ሰባት ጊዜ የተፈተነ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለእግዚአብሄር በጣም ሲቀኑ ቃሉን ለማጠናከር እና ጉለበት ሊሰጡት ሲፈልጉ ይሽሩታል፡፡ ቃሉን በአስተያየትህ አታሻሽለው፡፡ ቃሉ መሻሻል አይፈልግም፡፡
ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። ሉቃስ 7፡13
5.     ቃሉን ከተገበርክ በኋላ መፅናት ያስፈልግሃል
ቃሉን ተገበርክ ማለት በአንድ ለሊት ውጤት ታያለህ ማለት አይደለም፡፡ ቃን ስትተገብር ውጤት ታያለህ፡፡ ነገር ግን መፅናት መጠበቅ መታገስ ይኖርብሃል፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። እብራዊያን 10፡36
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍሬያማነት #ፍሬ #ማፍራት #ስኬት #በእኔኑሩ #ቃል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መመዘኛ #መስፈርት #ፅናት #ትግስት #መሪ

በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም

ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። ዕብራውያን 4፡2
እግዚአብሄር የእኩል እድል አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም፡፡ እግዚአብሄር ለእያንዳንዱ ሰው እኩል እድል ይሰጣል፡፡ ያለተሳካለት ሰው እግዚአብሄርን ጥፋተኛ ማድረግ አይችልም፡፡ ያልተሳካለት ሰው ራሱን መመርመር አለበት፡፡
ወደእግዚአብሄር እረፍት ለመግባት ስላልተሳካላቸው እስራኤላዊያን መፅሃፍ ሲናገር የምስራቹ ቃል ለእነርሱም እንደተሰበከላቸው ይናገራል፡፡ ነገር ግን ልዩነት ያመጣው የሰሙት ቃል ከሰሚዎችቹ ጋር በእመነት መዋሃዱ እና አለመዋሃዱ ነው፡፡ ሁለት ክርስትያኖች የእግዚአብሄርን ቃል እኩል ሊሰሙ ይችላሉ ነገር ግን በሁለቱ ላየ የሚያመጣው ውጤት ይለያል፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ሁሉ በማንኛውም ሰው ላይ በማንኛውም ሁኔተያ ላይ የሚሰራ ነው፡፡
ልዩነቱ የእግዚአብሄር ቃል ሳይሆን ልዩነቱ የእግዚአብሄርን ቃል አሰማም ነው፡፡ እስራኤላዊያን የእምነቱ ቃል ከሰሚዎቹ ጋረ አልተወቃሃደም ስለዚህ አልጠቀማቸወም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የሚጠቅመን የእግዚአብሀዌር ቃል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ከሰሚዎቹ ጋረ ሲዋሃድ ብቻ ነው፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ከሰሚዎቹ ጋር እንዳይዋሃድ የሚያደርጉ አምስት እንቅፋቶች
1.      ከልብ አለመሆን
እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስንሰማ እንደእግዚአብሄር ቃል ካልተቀበልነው አይጠቅመንም፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስንሰማ እንደታሪክ ከሰማነው አይጠቅመንም፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስንሰማ እንደ ንጉስ ቃል ከልባችን ልንሰማው ይገባል፡፡ ሱነማዊትየዋ ሴት ኢየሱስ ልጅዋን እስኪፈውስላት አልለቀቀችውም፡፡ ሱነማይትዋ ሴት ወደ ኢየሱስ ስትመጣ ከልብዋ ነበር፡፡  
የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። ማቴዎስ 13፡19
እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። እርስዋ ግን መጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ማቴዎስ 15፡22-28
2.     የኑሮ ጭንቀት
የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን የእረፍት ፍሬ እንዳያፈራ የሚያደርገው የኑሮ ጭንቀት ነው፡፡ የኑሮ ጭንቀት ከሰማነው በቁማችን ሊውጠንና ከንቱ ሊያፈደርገን የሚችል ትልቅ ሃይል ያለው እንቅፋት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች እግዚአብሄርን ከማገልገል የተመለሱት በኑሮ ፍርሃት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጌታን ቢያገለግሉም ያን ያህል ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው የኑሮ ሃሳብና የባለጠግነት ምቾት ነው፡፡  
በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። ሉቃስ 8፡14
3.     እንደ ሌላ አማራጭ መስማት
ሌላ አማራጭ ይዞ የእግዚአብሄርን ቃል እንደባጣ ቆየኝ መፈለግ በእምነት እነዳይዋሃደንና እንዳይጠቅመን ወደእረፍትም እንዳንገባ ያደርጋል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል እንደመጨረሻ አማራጭ ካየነው አይጠቅመንም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል እንደመጀመሪያ አማራጭ ሊታይ ይገባዋል፡፡
ያው የሚሰራው የእግዚአብሄር ቃል በእምነት እንዳይዋሃደን የሚሆንበት ምክኒያት ቃሉን በሁለት ሀሳብ መስማት ነው፡፡ ቃሉን እንደ ሌላ አማራጭ መስማት ቃሉ በእምነት ከእኛ ጋር እንዳይዋሃድ ያደርጋል፡፡ ቃ በእምነት ካልተዋሃደን ወደእረፍት አንገባም፡፡  
ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። ያዕቆብ 1፡6-8
4.     የእግዚአብሄር ቃል ለአእምሮ እውቀት ብቻ መስማት መፈለግ
የእግዚአብሄርን ቃል እንደሚሰራ ቃል ካለሰማነው ለአእምሮ ማስፊያ  እንደሰው ቃል እና እንደ ታሪክ ከሰማነው ለአእምሮዋችን ይጠቅማል አእምሮዋችንን ያሰፋል ነገር ግን በቃሉ ውስጥ ወደ ተቀመጠው እረፍት መግባት በፍፁም እንችልም፡፡ በዩኒቨርስቲዎች መፅሃፍ ቅዱስን እንደ ፊዚክስና እንደ ሂሳብ የሚያጠኑ ነገር ግን ከሚሰጠው ቃሉ ከሚሰጠው የህይወት እረፍት የራቁ ብዙ ሰዎች ይገኛሉ፡፡
ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። 1ኛ ተሰሎንቄ 2፡13
5.     የእግዚአብሄርን ቃል ለመታዘዝ አለመስማት
የእግዚአብሄርን ቃል ስንሰማ ለመታዘዝ ተዘጋጅተን መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ለመታዘዝ በሆነ በተጠንቀቅ ካልሰማነ እስከምንታዘዘው አይዋሃደንም አይጠቅመንም፡፡ ወደ እረፍቱ ለመግባት የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን ውስጥ ገብቶ ተዋህዶ ሊጠቅመን ያስፈልጋል፡፡
ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው? ገላትያ 3፡2-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ጭንቀት #ከልብ #አማራጭ #መታዘዝ #የኑሮሃሳብ #ብልፅግና #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Tuesday, February 27, 2018

እግዚአብሄር ይበልጥ ይታመናል

እግዚአብሄርን ባወቅነውና በተጠጋነው ቁጥር እግዚአብሄር ይበልጥ እንደሚያስፈልገንና ይበልጥ እርሱን ማመን እንዳለብን እንረዳለን፡፡ እግዚአብሄርን እያወቅነው በሄድን ቁጥር እግዚአብሄርን የምንፈልግበት የህይወት ክፍል እየበዛ ይሄዳል፡፡ ከዚህ በፊት ለዚህ ደግሞ ምን እምነት ያስፈልገዋል ለምንለው ጥቃቅን ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማመን እንጀምራለን፡፡
እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ከእምነት ነፃ አንወጣም፡፡ ከእምነት ነፃ የሚያወጣ እውቀት የተሳሳተ እውቀት ነው፡፡ ልቡን እግዚአብሄርን ከማመን የሚመልስ በልቡ በሌላ ነገር ላይ የሚታመን ሰው የተባረከ ሰው አይሆንም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። ኤርምያስ 17፡5
ከእምነት ነፃ እንደሆንን ከተሰማን ሳናውቀው የተሳሳተ ምግብ በልተናል ማለት ነው፡፡ ይህን ያህል በእምነት ኖርክ አሁን ደግሞ በማየት ቀጥል የሚል ትምህርት ከእግዚአብሄ አይደለም፡፡ እስካሁን ታመንከው አሁን ግን በአእምሮ ተመላለስ የሚል ትምህርት የስህተት ትምህርት ነው፡፡ እስካሁን የሚታየውን አላየህን አሁን ግን በሚታየው ኑር የሚል ትምህርት መፅሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ እስካሁን የማይታየውን አይተሃል አሁን ግን የማይታየውን አትይ የሚል ትምህትርት የሰይጣን ማታለል ነው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
ንፁህ ምግብ የበላ ሰው እምነትን ባየውና ጥቅሙን ባጣጣመው መጠን ይበልጥ በእምነት ለመኖር ይወስናል፡፡ እግዚአብሄርን አምኖ የኖረ ሰው እግዚአብሄርን ለሚበልጥ ነገር ለማመን ፍላጎቱ ይነሳሳል፡፡ እግዚአብሄርን በእምነት ፈልጎ ያገኘው ሰው እግዚአብሄርን ከመፈለግ አይጠግብም፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ባደግን መጠን ራሳችንን ትሁት ስለምናደርግ በህይወታችን ክፍል ሁሉ እግዚአብሄርን በእምነት ለመፈለግ እንዘረጋለን፡፡ በተለወጥን ቁጥር ካለ እግዚአብሄር ምንም ማድረግ እንደማንችል ስለምንረዳ እግዚአብሄርን የማንፈልግበት የህይወት ክፍል አይኖርም፡፡
እግዚአብሔርን፦ አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። መዝሙር 16፡2
በእግዚአብሄር ነገር በተሳካልን ቁጥር በራሳችን ውስን መሆናችንን ይበልጥ ስለምንረዳና በእግዚአብሄር ደግሞ ሁሉን ማድርግ እንደምንችል ስለምናውቅ እግዚአብሄርን የምንፈልግበት የህይወታችን ክፍል እየሰፋ እየበዛ ይሄዳል፡፡
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ዮሃንስ 15፡5
እግዚአብሄርን ስናምን እምነታችንም እግዚአብሄር ሲሆን ብሩካን ነን፡፡ እግዚአብሄርን ስንታመን እምነታችንም ይበልጥ በእግዚአብሄር ሲሆን ይበልጥ በእምነት ጋሻ ደህንነታችን እየበዛ ይሄዳል፡፡ እግዚአብሄርን ስንታመን እምነታችንም ይበልጥ በእግዚአብሄር ሲሆን ይበልጥ ነፃ እንወጣለን፡፡ እግዚአብሄርን ስንታመን እምነታችንም በእግዚአብሄር ሲበዛ በረከታችን አብልጦ ይበዛል፡፡
በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል። ኤርምያስ 17፡7-8
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

በእግዚአብሔር እመኑ

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ። ማርቆስ 11፡22
በእግዚአብሔር እመኑ
ጌታን ለሚያውቅ ሰው በእግዚአብሄር እመን የሚለው ምክር ከንቱ ምክር ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ጌታን የሚያውቅ ሰው ስለመዳኑ ኢየሱሰን እንደአዳኙ ተቀበለ ማለት እምነት ሁሉ አለው ማለት አይደለም፡፡ ለመዳን ከእግዚአብሄር ጋር ለመታረቅ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ እርምጃችን እምነት ያስፈልገናል፡፡
በእግዚአብሔር እመኑ
ክርስትያን ነን ማለት ከመቀፅበት ለሁሉም ነገር እምነት ይኖረናል ማለት አይደለም፡፡ በህይወታችን ክፍሎች እምነት እየኖረን የምንሄደው የእግዚአብሄርን ቃል ስለዚያ የህይወታችን ክፍል የሚናገረውን ሰምተን ስናምንና በቃሉ እውነት ላይ ስንቆም እግዚአብሄር በቃሉ ያለን ነገር ሁሉ ይሆናል፡፡ ስለአገልግሎታችን ስለቤተሰባችን ስለስራችን ስለትዳራችን ስለጤናችን የእግዚአብሄር ቃል ምን እንደሚል ፈልገን ካገኘንና እምነት ከመጣልን በእምነት የማይቻለን ነገር አይኖርም፡፡  
በእግዚአብሔር እመኑ
በአንዱ የክርስትና ህይወቱ ክፍል እምነት ያለው ሰው ስለዚያ ነገር የእግዚአብሄርን ቃል በመስናት እምነት ካልመጣለት በስተቀር በሌላው የክርስትና የህይወት ክፍሉ እምነት ሊጎድለው ይችላል፡፡
በእግዚአብሔር እመኑ
ክርስትያኖች ሆነን በተለይ በሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ነገሮችን ቴክኒካዊ እናደርጋቸዋለን፡፡ ከማመን ይልቅ ነገሮችን በአእምሮዋችን ለመፍታት እንሞክራለን፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ትእዛዝ ግን በእግዚአብሄር እመኑ የሚል ነው፡፡
በእግዚአብሔር እመኑ
እግዚአብሄርን ማመንን የሚተካው ምንም ነገር የለም፡፡
ከምናስበው በላይ ብዙ ነገሮች መንፈሳዊ ናቸው፡፡ ከምናስበው በላየ ብዙ ነገሮች እምነት ይጠይቃሉ፡፡ ከምናስበው በላይ ብዙ ነገሮች ቁልፋቸው መንፈሳዊ ነው፡፡ የምድር የስኬት ቁልፍ ማንም ባለጠጋ ጋር ማንም ሃያል ጋር ማንም ጠቢብ ጋር የለም፡፡ የስኬት ቁልፉ ያለው እግዚአብሄር እጅ ነው፡፡ በህይወት መልስ የሌለው ጥያቄ የለም ነገር ግን በእግዚአብሄር ማመን ይጠይቃል፡፡
በእግዚአብሔር እመኑ
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርሚያስ 9፡23-24
ካለ እምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ከእግዚአብሄር እጅ ስኬትን ለመቀበል እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄርን ፈልጎ ዋጋን ለመቀበል እምነት ይጠይቃል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። ዮሐንስ 14፡1
በእግዚአብሔር እመኑ
 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Monday, February 26, 2018

ለሚጠፋ መብል አትስሩ

ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሐንስ 6፡27
በምድር ላይ ለሚጠፋ መብል የሚሰራ ሰው አለ፡፡ በምድር ላይ ለማይጠፋ መብል የሚሰራ ሰው አለ፡፡
ለሚጠፋ መብል የሚሰራ ሰው የሚያስበው የምድሩን ብቻ ነው፡፡ ለሚጠፋ መብል የሚሰራ ሰው ቅድሚያ የሚሰጠው የምድሩን ኑሮ ምቾት ብቻ ነው፡፡ ለሚጠፋ መብል የሚሰራ ሰው እይታው አጭር ነው፡፡ ለሚጠፋ መብል የሚሰራ ሰው ከምድር ኑሮ ያለፈ የሰማዩን ማየት አይችልም፡፡
ሰው ለሚጠፋ መብል የሚሰራው እምነት ሲያጣ ነው፡፡ ሰው ለሚጠፋው መብል የሚሰራው መንፈሳዊውን ማየት ሲሳነው ነው፡፡
ለማይጠፋ መብል ለመስራት እምነት ይጠይቃል፡፡ ለማይጠፋ መብል ለመስራት ራስን መካድ ይጠይቃል፡፡ ለማይጠፋ መብል ለመስራት ነፍስን መካድ ይታወቃል፡፡ ለማይጠፋው መብል ለመስራት የሚታየውን አለማየት ይጠይቃል፡፡ ለማይጠፋው መብል ለመስራት የማይታየውንም ማየት ይጠይቃል፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
የሚጠፋ መብል አለ፡፡ የማይጠፋ መብል አለ፡፡ የሚጠፋው መብል ይጠፋል፡፡ ምክኒያቱም መብል ለሆድ ነው፡፡ ሆድም ለመብል ነው፡፡ ሁለቱም ጊዜያዊ ናቸው ይጠፋሉ፡፡
መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። 1ኛ ቆሮንቶስ 6፥13
አንዳንድ ሰዎች ሰርተው ለፍተው ዋጋቸውን በምድር ይቀበላሉ፡፡ የልፋታቸውና የስራቸው ዋጋ በምድር ላይ ብቻ ይቀራል፡፡ ለምድር ክብርና ለምድር ጥቅም የሚሰሩ ሰዎች ሁሉ ዋጋቸውን በምድር ተቀብለው አወራርደው ጨርሰው ነው ከምድር የሚለቁት፡፡ ለሚጠፋ መብል የሚሰሩ ሰዎች ከምድር የሚሄዱት የሰጡትን እያንዳንዷን ተቆጣጥረው መልሰው ተቀብለው ነው፡፡   
እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። ማቴዎስ 6፡2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #የሚጠፋመብል #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የማይጠፋ #መብል #የምድርክብር #ሆድ #እምነት #የባለግነትምቾት #ራስንመካድ #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ሰማያዊ መዝገብ

የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ይኸውም ትርፉ ለእናንተ እየበዛ እንዲሄድ እንጂ ስጦታውን ጓጒቼ አይደለም። ፊልጵስዩስ 4፡15-17
የምድር መዝገብ አለ፡፡ የሰማይ መዝገብ አለ፡፡ የአንዳንድ ሰዎች የምድር የባንክ ሂሳብ ዳጎስ ያለ ነው፡፡ የሰማይ የባንክ ሂሳባቸው ግን የተመናመነ ነው፡፡ የአንዳንድ ሰዎች የምድር የባንክ ሂሳባቸው የተመናመነ የሰማይ የባንክ ሂሳባቸው ግን ዳጎስ ያለ ነው፡፡ ሃዋሪያው ታዲያ ለእግዚአብሄር ስራ ገንዘባችሁን ስትሰጡ የሰማይ ባንክ ስሌታችሁ እንዲበዛ ነው የምፈልገው ይላቸዋል፡፡
የምድር መዝገብ ውስን ነው፡፡ የምድር መዝገብ የሚሰራው በምድር ብቻ ነው፡፡ የምድር መዝገብ ዋጋው ርካሽ ነው፡፡ የምድር የሚያልቅ የሚጠፋ ነው፡፡ የምድር ገንዘብ ወደ ሰማይ ሊሄድ የማይችል የመሬት ስበት ይዞ የሚያስቀረው ውስን ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ የአመፃ ገንዘብ የሚለው፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16:9
በምድር አገሮች ከአገሮች ጋር የሚገበያዩት በአለም አቀፍ ምንዛሬዎች ነው፡፡ በኢትዮጲያ ውስጥ ያላችሁን ብር ከኢትዮጲያ ውጭ አይሰራም፡፡ የኢትዮጲያ ገንዘብ እንዲሰራላችሁ ከፈለጋችሁ ወደ አለማቀፍ ምንዛሪ መመንዘር አለባችሁ፡፡ ወደ አለም አቀፍ ምንዛሬ ያልተለወጠ የኢትዮጲያ ብር በውጭ አገር ምንም አይጠቅምም፡፡
እንደዚሁ የምድር ገንዘብ የሚጠቅመው ምድር ላይ ብቻ ነው፡፡ የምድርን መዝገብ ዋጋውን ከፍ ለማድረግ ወደ ሰማይ መዝገብ መመንዘር አለበት፡፡ የምድር መዝገብ ዋጋው ከፍ የሚለው ወደ ሰማይ መዝገብ ሲለወጥ ብቻ ነው፡፡ የምድር ገንዘብ በእግዚአብሄር ዘንድ ዋጋ አለው የሚባለው በመልካም ስራ ላይ ሲውል ብቻ ነው፡፡ የምድርን ገንዘብ ዋጋውን ከፍ ለማድረግ እና በሰማይ ምንዛሬ ለመመንዘር በመልካም ስራ ላይ መዋል አለበት፡፡
ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ሉቃስ 12፡21
በገንዘብ ባለጠጋ የሆነ ሰው ባለጠግነቱን በመልካም ስራ ካልቀየረው የምድር ገንዘቡ ጊዜ ያልፍበታል ይቃርዳል ተራ ወረቀት ይሆናል፡፡  
በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡17-19
መፅሃፍ ቅዱስ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የተባረከ ነው የሚለው የምድርን ገንዘብ ከሚቀበል ይልቅ በመልካም ስራ ወደ ሰማይ መዝገብ የሚለውጠው ሰው ይበልጥ የተባረከ እንደሆነ ለመግለፅ ነው፡፡  
ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ፡፡ ሐዋርያት 20፥35
በምድር ያለ ገንዘብ በተራ ሁኔታ ላይ ሊውል ይችላል በከበረ ነገር ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የምድር ገንዘብ ለሰዎች ስለጌታ በድርጊትም በቃልም በመመስከር ላይ ሊውል ይችላል ወይም ደግሞ በአልባሌ ነገር ላይ ሊውል ይችላል፡፡ በምድር ገንዘብ ተጠቅመን ለሰዎች የጌታም መልካምነትና ፍቅር ልናሳይበት እንችላለን፡፡ ወይም የምድርን ገንዘብ ለሌላ ለተራ ነገር ልናውለው እንችላለን፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡1
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ የምድር ገንዘባችንን የዘላለም ዋጋ ያለው መልካምነት ላይ ማዋል እንዳለብን የሚመክረን፡፡ የምድር ገንዘባችንን ተጠቅመን ለሰዎች መልካምነትን በማሳየት የሰዎችን ልብ ለእግዚአብሄር ለመማረክ መጠቀም ይገባናል፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16:9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የሰማይመዝገብ #መስጠት #መልካምስራ #በረከት #ስኬት #ስሌት #ስምረት #ገንዘብ #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #የልብስፋት #ማስተዳደር #እረፍት

Sunday, February 25, 2018

የትእቢት ምንጭ

ትእቢት በእግዚአብሄር ፊት እጅግ አፀያፊ ነገር ነው፡፡ ትእቢተኛ ሰው ትእቢተኛ ለሁን ብሎ ላይሆን ይችላል ትእቢተኛ የሚሆነው፡፡ ትእቢት ቀስ በቀስ ሰው ላይ የሚያደባና ሰውን የሚጥል የሃጢያት ማታለል ነው፡፡ ነገር ግን ትእቢት የሚመጣበትን ምንጩን ማወቅ ከትእቢት የምንጠበቅበትን መንገድ ይመራናል፡፡  
እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል። መዝሙር 138፡6
ትእቢት ካለማወቅ ይመጣል
እግዚአብሄርን የሚያውቁ ሰዎች ትሁታን እንጂ ትእቢተኛ አይሆኑም፡፡ ትእቢት እግዚአብሄርን በሚገባ ካለማወቅ ይመጣል፡፡ እግዚአብሄርን ባወቅንና በተረዳን መጠን መንፈሳችን እየተሰበረ ትሁት እየሆንን ራሳችንን እያዋረድን እንጂ ትእቢተኛ እየሆንን አንመጣም፡፡ ጥቂት እውቀት ታስታብያለች፡፡ ትእቢት የሚያመለክተው የእግዚአብሄርን ሃይል በሚገባ አለማወቅን ነው፡፡ ሰው በትእቢት የሚስተው ቅዱሳን መፅሃፍትንና የእግዚአብሄርን ሃይል በሚገባ ካለመረዳት ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ። ማቴዎስ 22፡29
ትእቢት ከስጋት ይመጣል
በህይወቱ በጌታ ያልታመነ ሰው በእግዚአብሄር አቅርቦት ያልተማመነ ሰው ስጋቱ የሚገለፀው በትእቢት ነው፡፡ ትእቢት የእምነት ተቃራኒ ነው፡፡ ትእቢት የስጋት ምልክት ነው፡፡ በህይወቱ የተማመነ ሰው በህይወቱ የረካ ሰው ራሱ ከፍ ማድረግ ትእቢተኛ መሆን አያስፈልገውም፡፡ በራሱ ማንነት የተማመነ ሰው ትልቅነቱ ለማሳየት ምንም ማድረግ አያስፈልገውም፡፡ በራሱ የተማመነ ሰው ተፅእኖውን  ለክፉ ላለመጠቀም ይጠነቀቃል፡፡ ሃይል እንዳለው የሚያውቅ ሰው ጉልበቱን በመልካም ነገር ላይ ብቻ ለማዋል ያስባል፡፡ ሃይል እንዳለው በእርግጥ የማይተማመን ሰው ግን በክፉ ነገር ሁሉ ሃይሉን ይሞክራል፡፡ ትእቢት በልብ ያለን አለመረጋገትና ትእቢት ያሳያል፡፡
እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። ዕንባቆም 2፡4
ትእቢት ከራስ ወዳድነት ይመጣል
ትእቢት ከራስ ወዳድነት ይመጣል፡፡ በቂ ነገር እንዳለው የረካ ሰው በትህትና ሌሎችን ሊያገለግል ይተጋል፡፡ የረካ ሰው ሌላውን ሊያረካ ይተጋል፡፡ የተቀበለ ሰው ሊሰጥ ይተጋል፡፡ በልቶ ያልጠገነበ ሰው ግን ራስ ወዳድ ይሆናል፡፡ ራስ ወዳድ ደግሞ ሃሳቡን ሊያስፈፅም የሚችለው በከፍተኝነት ስሜት ነው፡፡ ትእቢተኛ ሰው ከፍ ብሎ ካልታየ በስተቀር ወደኋላ የሚቀር ፍላጎቱ የማይሞላ ይመስለዋል፡፡
ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡1
ትእቢት ከዝቅተኝነት ስሜት ይመነጫል
የበላይ ሰወ የበላይ ለመምሰል አይጥርም የበላይ ነውና፡፡ የበታች የሆነ ሰው ግን የበላይ ለመምሰል ይጥራል የበታች ነውና፡፡ እንዲሁ የዝቅተኝነት ስሜት ያለበት ሰው የዝቅተኝነት ስሜቱን ለማካካስ የከፍተኝነትን ስሜት በማሳየት ትእቢተኛ ይሆናል፡፡ የዝቅተኝነት ስሜት የሌለበት ሰው ግን የሚያካክሰው ምንም የዝቅተኝነት ስሜት ችግር ስለሌለበትና በራሱ የረካ ስለሆነ ትእቢተኛ ሲሆን እንመለከትም፡፡ ራሱን የሚያውቅና የዝቅተኝነት ስሜት የሌለበት ሰው ትሁት ለመሆን አይቸገርም፡፡
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 13፡3-5
ትእቢት ከእረፍት ማጣት ይመጣል
ሰው በጌታ እንዲያርፍና እንዲተማመን ተፈጥሮአል፡፡ ሰው የሚያርፍበትና የሚተማመንበት አንድ ነገር ይፈልጋል፡፡ ሰው በጌታ ካላረፈ የሚያርፈበት ሌላ ነገር ይፈልጋል፡፡ በጌታ ደስ ያለው ሰው ትሁት እንጂ ትእቢተኛ አይሆንም፡፡ በጌታ ያረፈ ሰው የሚያርፍበት ነገር ስላገኘ ከእረፍት ተነስቶ ሌሎችን ያገለግላል፡፡ በጌታ ያላረፈ ሰው ግን በራሱ ጉልበትና እውቀት ለማረፍ ሲሞክር ትእቢተኛ ይሆናል፡፡ በጌታ ያረፈ ሰው በራሱ ማረፍ አይጠበቅበትም፡፡ በጌታ የተማመነ ሰው በራሱ መተማመን አይጠበቅብትም፡፡ በጌታ ያልተማመነ ሰው ግን ተጣልቶም ተዋግቶም በክንዱ ነገሮችን ማድረግ እንጂ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡  
ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ያዕቆብ 3፡14
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ያዕቆብ 4፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ