የእስራኤል ህዝብ በውሃ እጦት በተሰቃየበት ጊዜ እግዚአብሄር ውሃን እንደሚያመጣ በነቢዩ ተናገራቸው፡፡ ነገር ግን ውሃ ከመምጣቱ በፊት ውሃውን የሚይዘውን ጉድጓድ እንዲቆፍሩም ተናገራቸው፡፡
እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፈሩ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። 2ኛ ነገሥት 3፡16-17
ይህ ታሪክ በህይወታችን ለሚመጣው ታእምር የሚመጥን ነገር መዘጋጀት እንዳለበት ያስተምረናል፡፡ አሁን ያለን ነገር ካልተለወጠ ወደፊታችን ሊለወጥ አይችልም፡፡ ህይወታችን የሚመጣውን በረከት ለመያዝ እንዲችል አድርጎ ካልተለወጠ በረከተን መጠበቅ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ አሁን ያለን የህይወት ደረጃ ወደፊት የሚመጣውን ሃላፊነትና ስልጣን ሊሸከም አይችልም፡፡ አሁን ያለን የመያዝ አቅም ነገ ሊመጣ ያለውን በረከት ሊይዝ አይችልም፡፡ አሁን ለነገ ህይወታችን ካልተለወጠ ነገ የሚመጣወን ከፍታ መያዝ ያቅተዋል፡፡
በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል የወይኑም ጠጅ ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ። ማርቆስ 2፡21-22
አሁን ያለንበት የህይወት ደረጃ እግዚአብሄር ይመስገን አሁን ላለንበት ሃላፊነት በቂ ነው፡፡ አሁን የደረስንበት የህይወት ደረጃ አሁን ላለን ስልጣን በቂ ነው፡፡ አሁን ያለንበት የህይወት ደረጃ አሁን ላለን ተፅእኖ መጠን በቂ ነው፡፡
ነገር ግን እኛ ማደግ እንፈልጋለን፡፡ እኛ ማደግ ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር እንድናድግ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር እኛን መለወጥ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር አዲስን ነገር ማድረግ ይፈልጋል፡፡
እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ። ኢሳይያስ 43፡19
አሁን ባለን የህይወት ደረጃ መኖር የምንችለው አሁን ላለው ህይወት ብቻ ነው፡፡ አሁን ባለን የህይወት አቅም መያዝ የምንችለው አሁን ያለንን ስልጣን ብቻ ነው፡፡ አሁን ባለን የህይወት ብስለት ማስተናገድ የምንችለው የአሁኑን የህይወት ደረጃ ብቻ ነው፡፡ ለማደግና መለወጥ ወሳኝ ነው፡፡ ስለነገ ዛሬ መስራት ወሳኝ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ለመድረስ ለምንፈልገው የህይወት ልክ ሌላ የህይወት ደረጃ ልክ ይጠይቃል፡፡ ለመድረስ ለምንፈልገው የስልጣን ልክ ሌላ የብስለት ደረጃ ይጠይቃል፡፡ ለመድረስ ለምንፈልገው የህይወት ከፍታ ሌላ የባህሪ ደረጃ ይጠይቃል፡፡
መድረስ ወደምንፈልግበት የህይወት ደረጃ ከፍ ለማለት መለወጥ ግድ ይላል፡፡ ወደምናየው የህይወት ከፍታ ለመውጣት መለወጥ ወሳኝ ነው፡፡ ወዳየንበት የህይወት የስልጣን ደረጃ ለመድረስ ይህ ያለንበት ህይወት ሊለወጥ ይገባዋል፡፡
ባለንበት ህይወት ከፍ ያለ ደረጃ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ባለንበት ብስለት ከፍ ያለ ስልጣን መለማመድ የማይቻል ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ #ለውጥ #ማደግ #ብስለት #ስልጣን #ፍቅር #ልብ #ህይወት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment