Popular Posts

Friday, August 31, 2018

የአዲስ ዓመት ውሳኔ - ስለ ኢየሱስ አዳኝነት ለሰዎች መናገር


በምድር ላይ ያለንበት አንደኛውና ዋናው ምክኒያት በኑሮ እና በቃል ስለእግዚአብሄር ልጅ ኢየሱስ ክርሶስ አዳኝነት ለሌሎች እንድንመሰከር ነው፡፡
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡9
መንፈስ ቅዱስ የሰዎችን ህይወት ስለሃጢያት የሚወቅሰው የምንኖረውን ነፁህ ኑሮና የምንናገረው የምስክርነት ቃል ተጠቅሞ ነው፡፡
እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ የዮሐንስ ወንጌል 16፡8-10
የእግዚአብሄር መንፈስ ንግግራችንን ተጠቅሞ ሰዎችን ስለሚወቅስ ማን ሰማ? ማን ተቀበለ? ማን ዳነ? ብለን ሳንጠይቅ ባገኘነው አጋጣሚ ስለ ኢየሱስ አዳኝነት ለሰዎች መመስከር ይገባናል፡፡
ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም። የሐዋርያት ሥራ 26፡22-23
የሰይጣን አላማ በተቃዋሚዎች ተቃውሞ ተጠቅሞ እኛን ዝም ማሰኘት ነው፡፡ እኛ ግን ወንጌልን ስንናገር የሚቃወኑ እነዳሉ ሁሉ የሚሰሙና የሚድኑ እንዳሉ አውቀን ዝም ማለት የለብንም፡፡
የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን፦ ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት። አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ የሐዋርያት ሥራ 17፡32፣34
በተቃውሞ መፍራት የለብንም፡፡ ፈዝንና ስድብን አንፈራም አናከብርም፡፡ ወንጌልን ለመመስከር ነፍሳችን በእኛ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር መቁጠር ይጠብቅብናል፡፡  
ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ። የሐዋርያት ሥራ 20፡24
ሰዎች ዛሬ ይቀበሉ ነገ አናውቅም፡፡ የእኛ ሃላፊነት የመዳንን እውቀት ለሰዎች መስጠት ነው፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡9-10
በአዲሱ አመት በቀን አንድ ሁለት ሶስት ሰው እያልን ስለጌታ የሱስ ከሃጢያት አዳኝነት ለመመስከር ራሳችንን መስጠት አለብን፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ወንጌል #ስብከት #ቃል #ዝራ #የምድርጨው #የአለምብርሃን #የአመፃገንዘብ #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

እግዚአብሔር ተቀብሎታል

በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ። ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደ ተፈቀደለት የሚያምን አለ፥ ደካማው ግን አትክልት ይበላል። የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል። ወደ ሮሜ ሰዎች 14፡1-4
በእምነት የደከመውን እግዚአብሄር ተቀብሎታልና እናንተም ተቀበሉት፡፡
እግዚአብሄር የተቀበለውን የማንቀበልበት ምንም ምክኒያት የለንም፡፡ እግዚአብሄር የተቀበለውን በመቀበላችን አንሳሳትም፡፡ እግዚአብሄር የተቀበለውን ባለመቀበል ግን በግልፅ እንስታለን፡፡
በመጀመሪያ እኛ ራሳችን እንደማንኛውም ፍጥረት በእግዚአብሄር ተፈጠርን እንጂ ሌላውን አልፈጠርንም፡፡ እኛ ራሳችን እንደ ማንኛውም ሰው በጌታ ዳንን እንጂ ማንንም አላዳንም፡፡
ሁለተኛ ለእያንዳንዱ የሰጠውን የሚያውቅው እግዚአብሄር እንጂ እኛ አይደለንም፡፡ ለእኛም የሰጠውን የሚያውቅ እግዚአብሄር እንጂ ሌላው ሰው አይደለም፡፡ እኛ በአንደ በኩል ድነን ከሆነ እገዚአበሄር ይመስገን፡፡ ደህንነቱ የእኛ አይደለም፡፡ ደህንነቱ የእግዚአብሄር ስጦታ ነው፡፡ ሌላው አልዳነም ብለን ካሰብን እንኳን ልንደግፈው ልናዝንለት እንጂ ልንፈርድበት አይገባንም፡፡
ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡3-4
ስለዚህ እንዳልተቀበልነው መመካት አይገባንም፡፡ በእኛ ዘንድ ያለ ምንም አይነት በጎነት ቢኖር ከእግዚአብሄር የተቀበልነው ነው፡፡  
አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው? 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡7
ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። የሉቃስ ወንጌል 12፡48
እኛ እግዚአብሄር ስለሌላው ሎሌ ካልመራን በስተቀር ማንንም መኮነን አንችልም፡፡ እንደ እግዚአብሄር ቃል የምናምነውን መናገር እንችላለን፡፡ ነገር ግን እምነታችንን በሌላው ሎሌ ላይ መጫን ግን አንችልም፡፡ የእያንዳንዳችን የመንፈሳዊ እድገት ደረጃ ይለያያል፡፡ ክርስትና እንደ ቤተሰብ አባላት የተለያየ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ሁላችንም ወደ ፍፁምነት እንሄዳለን ስንሄድ እያንዳንዱ በደረሰበት የእውቀት ደረጃ ይመላለሳል እንጂ አንድ ወጥ የእውቀት ደረጃ የለም፡፡  
እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3፡15-16
ለእያንዳንዳችን ጌታ ያሰመረልን መሮጫ መስመር አለ፡፡ እያንዳንዳችን የምንወቀሰው ከዚያ ከጥሪያችን እንጻር እንጂ ከሌላ ሰው ጥሪ አንፃር መሆን የለበትም፡፡
ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡17
እግዚአብሄር የጠራው ለምን እንደሆነ ምን መንፈሳ ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያይ እውነተኛም ፈራጅ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ሌላው ላይ ሊፈርድ የሚችልው እግዚአብሄር ስለሌላው ሎሌ የገለጠለትና እንዲገስፀው የላከው ሰው ብቻ  ነው፡፡
ማድረግ የምንችለው አንድ ነገር እግዚአብሄር እንዲረዳው ለእግዚአብሄር ማሳወቅ እንዲሁም የደከመውን የምንረዳበትን መንገድ መፈለግ ብቻ ነው፡፡
ማንም ሰው ሰራተኛውን ሌላ ማንም እንዲፈርድበት እንደማይፈልግ ሁሉ እግዚአብሄርን ሰራተኛውን ማንም እንደ እርሱ ያለ ሰራተኛ እንዲፈርድበት አይፈልግህም፡፡
ሰው በሌላው ሰራተኛ ላይ መፍረድ ድንበርን መዝለል ነው፡፡ ሰው በሌላ ሰራተኛ ላይ መፍረድ ካለ ደረጃ አላግባብ ማንጠራራት ነው፡፡ ሰው በሌላው ሰራተኛ ላይ መፍረድ የእግዚአብሄርን የፍርድ ወንበር መያዝ ነው፡፡
ለእግዚአብሄር የማየጠቅም ሰው የለም፡፡ እግዚአብሄር የሳተውን እንዴት እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር ያመፀበትን ስጋ እንዴት እንደሚቀጣው ያውቃል፡፡
አገልጋዩ ቢወድቅ መጀመሪያ ከማንም በላይ የሚጎዳው ተገልጋዩ እግዚአብሄር ነው፡፡ አገልጋይ ቢወድቅ ከማንም በላይ መጀመሪያ የሚያውቀው ተገልጋዩ እግዚአብሄር ነው፡፡ አገልጋዩ ቢወድቅ መጀመሪያ ከማንም በፊት የሚያገባው ባለቤቱ እግዚአብሄር ነው፡፡
ስለ እግዚአብሄር አገልጋይ ከእግዚአብሄር በላይ አናውቅም፡፡ ስለ እግዚአብሄር አገልጋይ ከእግዚአብሄር በላይ አንቀናም፡፡ ስለ እግዚአብሄር አገልጋይ ከእግዚአበሄር በላይ መጨነቅ አይገባንም፡፡
ስለራሳችሁ ህይወት ሀላፊነት ትወስዳላችሁ፡፡ ስለሌላው ህይወት ሃላፊነት ላለመውሰድ ግን መፍራት አለባችሁ፡፡ ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ እስከማለት ድረስ በእግዚአብሄር ላይ መደገፍና ማረፍ አለባችሁ፡፡  
ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። የዮሐንስ ራእይ 22፡11-12
እረፉ ይላል አግዚአብሄር እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ፡፡ እግዚአብሄር በማንም ሰው አይረዳም፡፡ እግዚአብሄርን ልጆቹን ለማሳደግና ለመቅጣት አትረዱትም፡፡
ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። የያዕቆብ መልእክት 1፡19-20
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #የሚፈርድ #የሚያማ #ወንጌል #መውደድ #ፍቅር #የህይወትምስክርነት #መታዘዝ #ማገልገል #መውደድ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Thursday, August 30, 2018

ከጥበብ የተለየች ቆንጆ

የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት። መጽሐፈ ምሳሌ 11፡22
የኛውም ወርቅ እርያን አንደማያሳምረው ሁሉ የትኛውም የውጭ ውበት የውስጡን ሰውን አያሳምረውም፡፡ ሰው የሚያምረው በውስጡ ነው፡፡ የሰው ውበቱ የውስጥ ማንነቱ ነው፡፡ የሰው ማንነቱ ውስጡ ነው፡፡ የሰው ዋናው ክፍል ባህሪው ነው፡፡ የሰው ዋናው ስብእናው ነው፡፡ በእርያ አፍንጫ ላይ እንዳለ የወርቅ ቀለበት ጥበብ የሌለው ሰው ውበትንም እንዲሁ ግንጥል ጌጥ ነው፡፡  
 ሲጀመር ቁነጅና የተለያየ ነው፡፡ የሰው መልክ እንደ እጁ አሻራ የተለያየ ነው፡፡ የስው የመልክ አይነት እንዲሁ እጅግ ብዙ ነው፡፡ የሰው የቁንጅና መመዘኛም እንዲሁ የተለያ ነው፡፡
የሰው መመዘኛ እንደስሜቱ እጅግ ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ ቁንጅናችን በየሰአቱ የሚለዋወጥ ሁሉ ይመስለናል፡፡ እንዳንድ በጣም ቆንጆ የሆንን አንዳንዴ ደግሞ ያን ያህል ቆንጆ እንዳልሆንን እናስባለን፡፡ አንዳንዴ መስታዎች ከፊታችን እንዲነሳ አንፈልግም፡፡ ሌላ ጊዜ ግን በመስታዎት ራሳችንን ማየት ሊያስፈራን ይችላል፡፡ የሰው ስሜት በተለዋወጠ ቁጥር ለቁንጅና ያለው መመዘኛም ይለዋወጣል፡፡
ውበት ቋሚ የታመነ ምስክር ሊሆን አይችልም፡፡ ውበት አታላይ ነው፡፡ ውበት ዋናውን የውስጠኛውን ሰው ባለቤቱን ሰው ሊሸፍንብን ይችላል፡፡ ውበትን ተከትለን እግዚአብሄርን የምትፈራውን ሴት ልናጣ እንችላለን፡፡ ውበትን ተከትለን እግዚአብሄርን የማትፈራው ሴት ላይ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ ውበትም ከቆዳ ያለፈ ስለሰው ሁለንተና ሊነግረን አይችልም፡፡
ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። መጽሐፈ ምሳሌ 31፡30
ውበት ዘላቂ አይደለም፡፡ ውበት ከንቱ ነው፡፡ ውበት ጊዜያዊ ነው፡፡ ቁንጅና ያልፋል ይጠፋል፡፡ እግዚአብሄርን መፍራት ግን የማያልፍ የማይጠፋ ሁል ጊዜ ሃብትና ውበት ነው፡፡
የውጭው ውበት እየጠፋ ይሄዳል፡፡ የውስጡ ውበት ግን በጊዜ ብዛት እየታደሰ እየቆነጀ እያማረ ውብ እየሆነ ይሄዳል፡፡
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡16
እውነተኛ ውበት የልብ ውበት እንጂ የወንድ ቁመና አይደለም
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16፡7
ደግነቱ እውነተኛ ውበት ጥበብ ነው፡፡ እውነተኛው ውበት የልብ ባህሪ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ውበት የየዋህነትና የዝግተኝነት ባህሪ ነው፡፡
ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡3-4
እውነተኛው ውበት መልካምነት ነው
እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡9-10
የሰው ውበቱ በውጭ የሚታየው አይደለም፡፡ የሰው ውበቱ በልቡ ያለው ነው፡፡
እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 23፡28
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ውበት #ቁንጅና #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #የዋህ #ዝግተኛ #የመንፈስፍሬ #ውበት #የልብሰው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የሙስና አስከፊ ገፅታ

ሙስና ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም ወይም በማጭበርበር ለግል የተለየ ጥቅም ማግኘት ሲሆን ሰዎች ያልተገባቸውን ነገር ለማድረግ የተገባቸውን ነገር ለመከልከል ጉቦ በመቀበልም በመስጠትም ሊገለጥ ይችላል፡፡
አንድ አገር የሚያድገው ህብረተሰቡ በነፃነት ያለውን እውቅትና ገንዘብ አውጥቶ ለብዙዎች ጥቅም ሲጠቀም ሲሰራና እና ሲያድግ ነው፡፡ ሰዎች ቢሮክራሲው ሳይበዛና ሳያማርራቸው ጉልበታችውንና እውቀታቸውን አውጥተው ከሰሩ የግለሰቦች እድገት የአገርን እድገት ያመጣል፡፡
ለምሳሌ አንድ ሰው ያለውን የስራ ፈጠራ ክህሎት ተጠቅሞ ስራ ቢጀምር ስራው ቢያድግለትና ስራው ያለብዙ ቢሮክራሲ በመንግስት ቢያስመዘግብ ከመንግስት እርዳታ ቢያገኝና በነፃነት ቢሰራ ያስዳል በስሩ የሚቀጥራቸውም ሰዎች ያድጋሉ፡፡ ስራወ ባደገ ቁጥር ድግሞ ለምግስት የሚያስገባው ቀረጥ ያድጋል የሚቀጥራቸው ሰዎች ብብዛትመ በክፍያም አያደጉ ይሄዳሉ፡፡
ሰው በነፃነት ከመንግስት ባለስልጣኖች ሳይጉላላ እንዲሁም በየደረጃው ጉቦ እንዲከፍል ሳይገደድ በነፃነት በመልካም ውድድር ከሰራ ድርጅቱ ያድጋል በስሩ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች ያድጋሉ አገሪቱም ታድጋለች፡፡
ነገር ግን ሙስና ባለበት ሁኔታ የሚያድጉት ሙሰኞች የመንግስት ባለስልጣኖችን በገንዘብ ጥቅም በማታለል የማይገባቸውን የሚያገኙ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ብዙዎች ሳይሆን ጥቂቶች ብቻቸውን በሙስና እንደ ተፈንጣሪ ኮከብ በፍጥነት ወደላይ የሚወጡበት ብቻቸውን የሚያድጉበት እድገቱ ለብዙዎች ጥቅም የማይውልበት ሰው ሰራሽ እድገት ይሆናል፡፡
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። መፅሃፈ ምሳሌ 28፡20
እነዚህ ሙሰኞች ገንዘባቸውን በስራ ላይ በማዋል ብዙዎችን ቀጥረው በማሰራት ከሌሎች ጋር አብረው ከማደግ ይልቅ ብቻቸውን ፈጥነው ለማደግ ባላቸው ክፉ ምኞት ባለስለጣኖችን በጉቦ በማታለል ብዙ ሰዎችን ይጎዳሉ፡፡ በሙስና የሚጎዳው በድርጅቱ ተቀጥረው መስራትና ማደግ የነበረባቸው ተቀጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ጉቦ የማይሰጡ ጉቦ ባለመሰጠታቸው የፈቃድና የግብር ስርአቱ የሚጠብቅባቸውና የሚያማርራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር የእነዚህን ሰዎች እንባ ያያል፡፡ ሙሰኛ ሰው ግብር በመክፈል ለብዙሃን መንገድ ድልድይና እና ተቋማት መገንባት አስተዋፅኦ ማድረግ ሲገባው ከደሃ ነጥቆ ከመንግስት ደሞዝ ለሚከፈለው ባለስልጣን ጉቦ በመስጠት ለባለጠጋ ይሰጣል፡፡
ይህ ሙሰኛ ግብር በመክፈል ለህብረተሰቡ መመለስ ያለበትን ገንዘብ ከደሃ ነጥቆ በመንግስት ደሞዝ ለሚከፈለው በአንፃራዊነት ለባለጠጋ ለሆነ ሰው በመስጠት እግዚአብሄርን ያሳዝናል፡፡ ሙሰኛ ሰው በተዘዋዋሪ ደሃን ይጎዳል፡፡ ሙሰኛ በክፉ ምኞቱ ወደ ድህነት ይወድቃል፡፡
ለራሱ ጥቅም ለመጨመር ሲል ድሀን የሚጐዳ፥ ለባለጠጋም የሚሰጥ፥ እርሱ ወደ ድህነት ይወድቃል። መጽሐፈ ምሳሌ 22፡16
እግዚአብሄር ህዝቡን ስለሚወድ ሙሰኞችን በተያየ መልኩ ያስጠነቅቃል፡፡ በግብር አሰባሰብ የተሰማሩትን ሙሰኛ ባለስልጣኖች እንዲመለሱ እግዚአብሄር እድልን ይሰጣቸዋል፡፡
ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉት። ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ አላቸው። የሉቃስ ወንጌል 3፡12-13
እግዚአብሄር ወደ እርሱ የሚጮኸውን የደሃውን ጩኸት ስለሚሰማ በስልጣናቸው አላግባብ የሚጠቀሙትንና ከደሞዛቸቸው በላይ ጥቀም ለማግኘት የሚገባውን የሚከለክሉትን የማየገባውን የሚሰጡትን ማናቸውንም ባለስልጣናት ያስጠነቅቃል፡፡
ጭፍሮችም ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ አላቸው። የሉቃስ ወንጌል 3፡14
እግዚአብሄር ደጋግሞ ተናግሮ ካልተመለሱ ግን ስብራታቸው ድንገት ይሆናል፡፡ በሙስና ከደሃ ቀምተው ለባለጠጋ የሚሰጡ ሰዎችም ይሁን ከድሃ ተቀምቶ እንዲሰጣቸው ሰዎችን የሚያጎሳቁሉ ሰዎች ስብራታቸው ድንገት ይሆናል ፈውስም አይኖራቸውም፡፡  
ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፥ ፈውስም የለውም። ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል፤ ኀጥኣን በሠለጠኑ ጊዜ ግን ሕዝብ ያለቅሳል። መጽሐፈ ምሳሌ 29፡1-2
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ባለስልጣን #ሙስና #ጉቦ #ፀሎት #ወታደር #ቀራጭ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Wednesday, August 29, 2018

የመንጋ ፖለቲካ አደጋዎች

የመንጋ ፍትሕ በእንግሊዝኛው Mob justice የሚባለው ነው፡፡ የመንጋ ፍትሕ በማህበረሰብ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ህዝብ በመንግስት የፍትህ አካላት ላይ እምነት ሲያጣ ነው፡፡ ፍትህን ያመጣሉ በሚባሉት የመንግስት የፍትህ አካላት በሙስናና በተለያዩ ችግሮች ከመዘፈቃቸው የተነሳ ህዝቡ በእነርሱ ላይ እምነት ሲያጣ ፍትህን በራሱ እጅ ለማምጣት በስሜታዊነት የሚወስደው የተሳሳተ የጥቃት እርምጃ አማራጭ የመንጋ ፍትህ ነው፡፡   
የመንጋ ፍትህ እጅግ አደገኛ አካሄድና እና የታለመለትን የፍትህን ጥያቄ በፍፁም ሊመልስ የማይችል ዲሞክራሲንና የህግ የበላይነትን የሚያቀጭጭ ፍትህን የሚያዛባ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
ለዲሞክራሲያዊ ሃገር የህግ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ማለት ደግሞ ሰው ሁሉ በሀገሪቱ ህግ የሚተዳደርና ማንም ሰው በህግ ከተቀመጠለት ገደብ የማያልፍ ካለፈም በህጉ መሰረት የሚቀጣበት አካሄድ ነው፡፡
የህግ የበላይነት አንዱ መግለጫ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ነው፡፡ ከሰብአዊ መብቶች አንዱ ደግሞ አንድ ሰው በነፃ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ታይቶ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ጥፋተኛ እንዳልሆነና ነፃ እንደሆነ የሚቆጠርበት የህግ ሽፋን ነው፡፡  
አንድ ሰው በተከሰሰበት በማንኛውም ወንጀል በፍርድ ቤት እስኪፈረድበት ድረስ ወንጀለኛ አይደለም ነፃ ሰው ነው፡፡ አንድ ሰው በተከሰሰበት በማንኛውም ወንጀል በፍርድ ቤት እስካልተፈረደበት ድረስ ነፃ ሰው ሆኖ ይኖራል፡፡  
ይህ የመንጋ ፍትህ ይህንን የሰውን የሰብአዊ መብት የሚጋፋ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
አንድ ነፃ ፍርድ ቤት የተከሳሹን ክስ ሰምቶ የመከላከያ ሃሳቡን አዳምጦ የቀረቡትን ማስረጃዎች ሰምቶ ውሳኔን ይሰጣል፡፡ ይህ የሚደረገው ማንም ስለተጠረጠረ ብቻ እና ስለተከሰሰ ብቻ ባልሰራው ወንጀል እንዳይቀጣ ለመከላከል ነው፡፡
በመንግስት አሰራር እንኳን መንግስት ራሱ ጠርጥሮ ፣ ራሱ ፈርዶ ራሱ እንዳይቀጣ የመንግስት አካላት በሶስት ክፍሎች ተከፍለዋል፡፡
በዲሞክራሲያዊ ስርአት መንግስት ያለውን ስልጣን በአግባቡ እንዳይጠቀም በሶስት ክፍሎች የተከፈለና ሶስቱ የመንግስት ክፍሎች እርስ በእርሳቸው የሚጠባበቁና የሚተራረሙ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በየደረጃው ያሉ ህግ አውጪ ምክር ቤቶች አሉ፡፡ ህግን ተርጓሚ የመንግስት አካል ፍርድ ቤት አለ፡፡ እንዲሁም ህግን አስፈጸፃሚ ፖሊስና የአቃቢ ህግ አካላት አሉ፡፡
የመንግስት ስልጣን እንኳን በሶስት ክፍሎች የተከፈለበት ምክኒያት መንግስት በአንድ የመንግስት ቢሮ ራሱ ህግ አውጪ ፣ ራሱ ከሳሽ ፣ ራሱ ፈራጅና ራሱ ቀጪ እንዳይሆን ነው፡፡ መንግስት እንኳን በሶስቱ የመንግስት ክፍሎች የተከፈለበት ምክኒያት ከመንግስት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም ህዝቡን ለመከላከል ነው፡
ሶስቱ የመንግስት አካላት እርስ በእርሳቸው ይጠባበቃሉ ይተያያሉ ይተራረማሉ፡፡
በመንጋ ፍትህ የህግ አውጪው ፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው በሌሉበት ሁኔታ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው አንዱን ሰው የሚጠረጥሩት ፣ የሚከሱት ፣ የሚፈርዱበትና ፍርዱን የሚያስፈፅሙበት ከሆነ የህግ የበላይነት አይኖርም፡፡ መንግስት ስልጣኑን አላግባብ እንዳይጠቀም በሶስት ዋና ክፍሎች ከተከፈለ በመንጋ ፍትህ ግን የሰዎች ስብስብ በመንግስት የሚፈራው ስልጣንን አላግባበ መጠቀምን ከመፀመ በጣም አሳዛኝና ዘግናኝ ነው፡፡ ይህ አንድ ቡድን የሚያደርገው የመንጋ ፍትህ የህግ የበላይነት ይሸረሽራል ስርአት አልበኝነት እንዲሰፍንና እውነተኛ ሳይሆን ጉልበተኛ የሚኖርባት አገር ያደርጋል፡፡
ከዚህ በፊት በቪድዮ የተለቀቀው በመስቀል አደባባይ ለተቃውሞ በወጡት ሰዎች ላይ የተደረገው መግረፍ እና ማሰቃየት የፍትህ ስርአቱን ያልተከተለ የመንግስት የህግን ስርአት መጣስ ምሳሌ ነው፡፡ የህግ አስፈፃሚው ጥፋተኛ ነው ብሎ የጠረጠረውን ሰው ይዞ ለህግ ተርጓሚው አካል ለፍርድ ቤት ከመስጠት ይልቅ ራሱ ጠርጥሮ ፣ ራሱ ፈርዶ ፣ ራሱ ፍርዱን ያስፈፀመበት ሁኔታ የመንግስት አካላት የስልጣን ድንበራቸውን መጣሳቸውን የሚያሳይ ምሳሌ ነው፡፡
እውነት ነው አስፈፃሚውም አካል ይሁን ህዝብ ራሱንና ሌላውን ለመከላከል የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ፖሊስ ምንም ማድረግ የማይችለውን በእጁ የገባውን ሰውን እንደዚያ ቀጥቅጦ ማሰቃየትና በአካል ላይ ጉዳት ማድረስ ራስን ወይም ሌላውን ከመከላከል መርህ ውጭ ነው፡፡
እንዲሁም በሰኔ 16 በጠቅላይ ሚንስሩ ላይ የሞከረን የቦንብ ጥቃት አደጋ ለመከላከል በህዝቡ የተወሰደው እርምጃ መልካም እና ራስንና  ሌላውን ለመከላከል እርምጃ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ነግር ግን ከዚያ በኋላ መኪናን በማቃጠል የታየው የህዝብ ጥቃት የዚሁ የመንጋ ፍትህ ምሳሌ ነው፡፡
በዚያ በሰኔ 16 በህዝቡ የተደረገው የመንጋ ፍትህ በከፋ መልኩ በሻሸመኔ ታይቷል፡፡ ቦንብ ይዟል ተብሎ የተጠረጠረ ሰውን ይዞ ለፍትህ አካላት ከማቅረብንና ፍትህ የራሱን መንገድ እንዲከተል ከመትው ይልቅ ራስ ጠርጥሮ ራስ ፈርዶ ራስ ፍርድን ማስፈፀም ዲሞክራሲንና የህግ የበላይነትን የሚጎዳ የታሪክ ጠባሳ ነው፡፡
እነዚህ አይነት የመንጋ ፍትህ አካሄድ እንዳይደገም የዲሞክራሲ አስተሳሰብ ያለውን ትውልድ ለመፍጠር የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎችና የመንግስት አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት ህብረተሰቡን የማስተማር ትልቅ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ፍርድቤት #ህግአውጪ #ህግአስፈፃሚ #ምክርቤት #ፖሊስ #ዲሞክራሲ #ህግተርጉዋሚ #ተቃውሞ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል

ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ። የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ። ፈሪ ልብ ላላቸው፦ እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው። ትንቢተ ኢሳይያስ 35፡1-4
·         ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥
ምድረ በዳ የተጠማ ደረቅ ምድር ነው፡፡ የእግዚአብሄር ክንድ ሲመጣ ምድረበዳው በውሃ ይረሰርሳል፡፡ ውሃ በማጣት የደረቀውና ህይወት ያጣው መሬት ህይወት ያገኛል፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በራሱ ምክና እምሳለ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በክብሩ ነው፡፡ የሰው ጉስቁልና የእግዚአብሄር ፈቃድ አይደለም፡እግዚአብሄር በሰው መለምለም ፣ ማበብ ፣ መሳካትና መከናወን እንጂ እግዚአብሄር በሰው ጉስቁልና አይደሰትም፡፡
·         በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል
መሬት ለልምላሜ እና ለፍሬያማነት ሰለተሰራ ድርቀትና በረሃማነት መሬትን ያሰቃየዋል፡፡ ነገር ግን የእግአብሄር ክንድ ሲገለጥ በረሃው ወደ ተፈጥሯዊ ደስታው ይመለሳል፡፡ ፅጌረዳም የሚያምርበት ሲጠወልግ ሲጎሳቆል ሳይሆን ሲለምልም አበባ ሲያወጣ  ነው፡፡  
·         እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል
ፅጌረዳ እንዲያብብና እንዲያፈራ ስለተሰራ ፅጌረዳ ሲጠወልግና ሲከስም ደስ አይልም፡፡ ፅጌረዳ ሲያብብ ለራሱም ለሌሎችም ደስታ ይሆናል፡፡
·         የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል
የእግዚአብሄር ክብርን ግርማ እናያለን፡፡
·         የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።
ይህ ሁሉ የእግዚአብሄር ክብር በህይወታቸን መገለጥ የተስፋ ቃል በህይወታችን እንዲፈፀምና ሁላችንም አብረን እንድንወርስ ማድረግ ያለብንን ነገር ይናገራል፡፡
·         የደከሙትን እጆች አበርቱ፥
ይህ የተስፋ ቃል እንደሚፈፀም ማመን በሚገባ እንድንዘጋጅ ያደርገናል፡፡ ይህ ተስፋ ያለው ከእነዚህ ነገሮች ራሱን ያጠራል ይላል መፅሃፍ ቅዱስ፡፡
በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል። 1 የዮሐንስ መልእክት 3፡3
·         የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ።
በላላ ጉልበት ወደ እግዚአብሄር ክብር ውስጥ መግባት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የላሉትን ጉልበቶች አፅኑ፡፡
የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ ትንቢተ ኢሳይያስ 40፡3-4
·         ፈሪ ልብ ላላቸው፦ እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው
አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ። የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና። ትንቢተ ኢሳይያስ 40፡1፣5
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #ሃይል #ዘላለም #ጥበብ #የእግዚአብሄርመንግስት #ንጉስ #እርሾ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Tuesday, August 28, 2018

የቅዱሳን ህብረት ለማካፈል ለመባረክና ለመጥቀም

የቅዱሳን ህብረት በክርስትና ህይወት በጣም ወሳኝ የሆነ ስርአት ነው፡፡ የክርስትና ህይወታችን በሚገባ እንዲገነባና እንዲያድግ የቅዱሳን ህብረት የሚያበረክትው አስተዋኝኦ በቀላ የሚገመት አይደለም፡፡ እንዲያውም ለተሟላ ፍሬያማ የክርስትና ህይወት የቅዱሳን ህብረት ወሳኝ ነው፡፡
በአሁኑ ዘመን ከማህበራዊ መገናኛዎች መስፋፋት አንፃር ብዙ ሰዎች የተለያዩ መንፈሳዊ ጥቅሞችን በማህበራዊ መገናኛዎች እየተጠቀሙ ነው፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ወንጌልን ለመስበክና የእግዚአብሄር ቃል ለማስፋት በጣም ጠቃሚ መሳሪያ ነው፡፡
የማህበራዊ መገናኛን ግን በትክክል አለመጠቀም በክርስትና ህይወታችን ላይ ጉዳትን ያስከትላል፡፡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ከአቅማቸው በላይ ማጋነና የሌላቸውን ነገር እንዲሰጡን መጠበቅ መንፈሳዊ ህይወታችንን የማቀጨጭ አደጋ አለው፡፡ የማህበራዊ መገናኛ የቅዱሳን ህብረትን አይተካም፡፡ የማህበራዊ መገናኛ የቅዱሳን ህብረት ተጨማሪ ነገር እንጂ የቅዱሳንን ህብረት ሙሉ ለሙሉ የሚተካ ነገር አይደለም፡፡
ብዙ ሰዎች ቤተክርስትያን ላለመሄድ ምክኒያት የሚያገኙት ከቴሌቪዝን ከማህበራዊ መገናኛ እንደፌስቡክ ትዊተር እና ዩቱብ ባሉ መገናኛዎች ለመጠቀም እሞክራለሁ በማለት ነው፡፡
ስለ ማህበራዊ መገናኛዎች እግዚአብሄርን እናመሰግናለን፡፡ ብዙ ሰዎች ስለጌታ ኢየሱስ አዳኝነት በማህበራዊ መገናኛዎች እየሰሙ ነው፡፡ በማህበራዊ መገናኛዎች ዘዴዎችም አምልኮና የእግዚአብሄር ቃል ትምህርት ሰምተው የሚፅናኑና የሚታነፁ ሰዎች አሉ፡፡
ነገር ግን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አሉና ከቅዱሳን ጋር ህብረትን ማድረግ አያስፈልግም የሚል አመለካከት ስህተት ነው፡፡ በማህበራዉ መገናኛዎች የማናገኛቸው ትምህርትና አምልኮዎች አሉ፡፡ በቤተክርስትያን ከቅዱሳን ጋር ህብረት የምናደርገው ከእግዚአብሄርን ለመጠቀም እና ለመቀበል ብቻ አይደለም፡፡ ወደ ክርስትያን የምንሄደው ለመስጠትም ነው፡፡
ወደ ቤተክርስትያን ህብረት የምንሄደው ለቅዱሳን ህብረት ትብብርን ለመስጠት ነው፡፡ የቅዱሳን ህብረት ቤተሰባችን ነው፡፡ የቤተሰቡ ጥንካሬ የሚለካው በቤተሰቡ አባላት መሰጠት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ወደቤተክርስትያን የምንሄደው ለሌላው ወድማችን መፅናናት መታነፅና መበረታታ ምክኒያት ለመሆን ነው፡፡
ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ወደ ዕብራውያን 10፡24-25
ቤተክርስትያን የምንሄደው በህብረት አምልኮን ለመስጠት ነው
ቤተክርስትያን የምንሄደው በህብረት አምልኮን ለጌታ ለመስጠት ነው፡፡ የትኛውም የግል አምልኳችን የህብረቱ አምልኳችንን አይተካም፡፡ እግዚአብሄር እርሱን የምንፈራና የምናመልክ ሁላችን በህብረት ሆነን ስናመልከው ማየት ይፈልጋል፡፡
የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፥ ሰማም፥ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ። ትንቢተ ሚልክያስ 3፡16
ቤተክርስትያን የምንሄደው ጊዜያችንን ለመስጠት ነው
ቤተክርስቲያን ቤታችን ነው፡፡ ቤተክርስትያን ቤተሰባችን ነው፡፡ ቤተክርስትያን ካሸነፈች ቤታችን አሸነፈ፡፡ ጊዜያችን ጉልበታችን እውቀታችን ሁሉ ከእግዚአብሄር በአደራ የተሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ደጋግ መጋቢዎችና እንደ እግዚአብሄር ስጦታ አስተዳሪዎች በሁለንተናችን ቤተክርስቲያንን ለመደገፍ ራሳችንን እንሰጣለን፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፡1-3
ቤተክርስትያን የምንሄደው ቃላችንን ለመስጠት ነው
ቤተክርስትያን የምንሄደው ወንድማችንን እና እህታችንን በቃል ለማፅናናትና ለማፅናት ነው፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው እኛን ሲያዩን የሚፅናኑ ሰዎች ስላሉ ነው፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው በቃላችን ፀጋን የሚካፈሉ ሰዎች ስላሉ ነው፡፡ እግዚአብሄር በፀጋ ባሳደገን መጠን በቃል አማካኝነት ፀጋን የሚያስችል ሃይልን ለሌሎች እናካፍላለን፡፡
ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡29
ቤተክርስቲያን የምንሄደው ማበረታቻ ለመስጠት ነው
ቤተክርስቲያን ቤተሰብ ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ልጆች እንዳሉ ሁሉ በቤተክርስቲና እንዲሁ የተለያየ የእድገት ደረጃ ያላቸው ልጆች አሉ፡፡ በቤተሰብ ትልቁ ትንሹን እየረዳ ለእድገቱ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ሁሉ በቤተክርስቲያን አንዱ ለአንዱ ያስፈልገዋል፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው ታናናሾቻችንን ለመንከናከብ እና ከታላለቆቻችን እንክብካቤ ለማግኘትና ለመማር ነው፡፡ ወደ ቤተክርስትያን የምንሄደው የታላላቆቻችንን ምሳሌነት ለመከተልና ለታናናሾቻችን ለክርስትና ህይወት ምሳሌ ለመሆን ነው፡፡፡
አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤ 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡10
ቤተክርስትያን የምንሄደው በፀጋ ስጦታችን ቅዱሳንን ለማገልገል ነው
ስንሰበሰንብ እግዚአብሄር በእኛ ተጠቅሞ ሌሎችን ያንፃል በሌሎች ተጠቅሞ እኛን ያነፀናል፡፡
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው፥ ትምህርት አለው፥ መግለጥ አለው፥ በልሳን መናገር አለው፥ መተርጐም አለው፤ ሁሉ ለማነጽ ይሁን። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 14፡26
ቤተክርስትያን የምንሄደው በጋራ እና በአንድነት የስምምነት ፀሎት ለመፀለይ ነው
የግል ጸሎት አለ የህብረት ፀሎት አለ፡፡ የግል ፀሎት የሚሰራው ስራ አለ የህብረት ፀሎት ደግሞ የሚሰራው ስራ አለ፡፡ የህብረት ፀሎት ተጠቃሚ ለመሆን በህብረት መስብሰብ ወሳኝ ነው፡፡
ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። የማቴዎስ ወንጌል 18፡19-20
ቤተክርስትያን የምንሄደው ለሽማግሌዎች ህይወታችንን ለማሳየት ነው
የቤተክርስትያን ሽማግሌዎች እና መጋቢዎች ለነፍሳችን የሚተጉ የእግዚአብሄር ስጦታዎች ናቸው፡፡
ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። ወደ ዕብራውያን 13፡17
ወደ ቤተክርስቲያን ህብረት የምንሄደው ወንድሞቻችን በህይወታችን ችግር ካዩ እንዲወቅሱንና እንዲያስተካክሉን ህይወታችንን ለማሳየትና ግልፅ ለማድረግ ነው፡፡ ሰውን የምንበድለው አብረን ስንኖር ነው፡፡ ራስ ወዳድነታችን የሚገለጠው የክርስትናን ህይወት ደረጃ የሚያውቁ ቅዱሳን ጋር አብረን ስንኖር ህይወታችንን ሲያዩ ነው፡፡ ስጋዊ ባህሪያችን የሚታየውና የምንወቀሰው የእግዚአብሄርን ቃል በሚያውቁ ቅዱሳን መካከል ስንኖር አስተሳሰባችንነ ንግግራችንና ድርጊታችን ሲያዩ ነው፡፡ የተበደለ የሚወቅሰን እና የሚያስተካከልን አብርን ስንኖር ነው፡፡
ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። የማቴዎስ ወንጌል 18፡15-17
ቤተክርስቲያን የምንሄደው ለህብረቱ የሚያመጣውን የጊዜውን ቃል ለመካፈል ነው
ምንም አይነት መንፈሳዊ እወቀት ቢኖረን ለህብረቱ ለዚያ ሳምንት አግዚአብሄር የሚልከውን የጊዜውን ቃል የምናገኘው ከቅዱሳን ህብረት ነው፡፡
የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው። መጽሐፈ ምሳሌ 25፡11
ቤተክርስቲያን የምንሄደው ለቅዱሳንና ለሽማግሌዎች ህይወታችንን ለማሳየት ነው
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙረ ዳዊት 133፡1-3
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #ህብረት #በረከት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ