Popular Posts

Follow by Email

Saturday, April 20, 2019

የማሪያም አማላጅነትማሪያም ታማልዳለች ወይስ አታማልድም የሚለው ጥያቄ በኢትዮጲያ ውስጥ ብዙ ክርክርን ሲያስነሳ የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንዶች ማሪያም በምድር ላይ እያለች አማልዳለች ነገር ግን ከሞተች በኃላ ማማለድ አትችልም ብለው ያምናሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ማሪያም አሁንም ታማልዳለች ወደ እግዚአብሄር ታቀርበናለች በማለት ይደገፉባታል ወደእርሷም ይፀልያሉ፡፡
ሲጀመር ማሪያም ታማልዳለች አታማልድም የሚለው ክርክር ከመዳን አንፃር ከቁጥር የሚገባ ክርክር አይደለም፡፡ መዳናችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው የህይወት ዋጋ የተገዛ ነው፡፡ መዳናቸነ የሚመሰረተው ኢየሱስ ስለሃጢያቴ ሞቷል ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል ብለን በማመናችን ነው፡፡
በበኩሌ ሰው ማሪታም ታማልዳለችም አታማልድምም ብሎ ቢያምን ደህንነቱን ቅንጣት ይለውጣል ብዬ አላምንም፡፡ የአንድ ሰው ደህንነት የሚመሰረተው ሰው ኢየሱስ ስለሃጢያቱ በመስቀል ላይ እንደሞተና በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ በማመኑ ላይ ብቻ ነው፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡9-10
እውነት ነው ጤናማ የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርትን መማራችን የምንኖረው የክርስትና ህይወት ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ሰው ከመሰረታዊው የመፅሃፍ ቅዱስ የደህንነት አስተምሮ ውጭ የሚያምነው ማንኛውም ጥቃቅን ትምህርት ደህንነቱ ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ማርያም አታማልድም ብሎ ቢያምን አይድንም፡፡ ዳግመኛ የተወለደ ሰው ማርያም ታማልዳለች ብሎ ቢያምን ደህንነቱን አያጣም፡፡
ኢየሱስ በምድር በሚመላለስበት ጊዜ አንድ የህግ መምህር ወደ ኢየሱስ ቀርቦ እንዲህ አለው፡፡
መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። የዮሐንስ ወንጌል 3፡2
ኢየሱስ ግን ስለመፅሃፍ ቅዱስ እውቀቱ አድንቆ በጣም አስፈላጊ ስላልሆነው አስተምሮት አላዋራውም፡፡ ኢየሱስ በቀጥታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነው የሰው ልጅ መሰረታዊ የደህንነት ፍላጎት እንዲህ ሲል ተናገረው፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። የዮሐንስ ወንጌል 3፡3
ለሰው ለደህነነት የሚያስፈልገው ጥሩ የመፅሃፍ ቅዱስ እውቀት ሳይሆን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡ ለሰው ደህንነት የሚያስፈልገው በጥቃቅን አስትምሮት ላይ ተከራክሮ ማሸነፍ ሳይሆን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡ ኢየሱስ ስለደህንታችን የሚያስፈልገውን የሃጢያት ዋጋ ሁሉ በመስቀል ላይ ከከፈለ በኃላ የሚያስፈልገን ሌላ ነገር ሳይሆን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡  
አሁንም የሚያከራክሩን ብዙ ነገሮች የማይገቡ ክርክሮች ናቸው፡፡ አሁን ጊዜያችንንና ጉልበታችን የሚያባክኑ ክርክሮች መሰረታው ያልሆኑ ትምህርቶች ናቸው፡፡ አሁን የሚያከራክሩንና የሚያጣሉን ክርክሮች ለመዳን ምንም የማይጨምሩ ምንም የማይቀንሱ ነገሮች ናቸው፡፡ አሁን የሚያከራክሩን ነገሮች አይቶ ሰይጣን የደህንነት አላማችንን መሳታችንን ደስ እንዲለው የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡
ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር በሚያደርገው ንግግር ለደህንነት አስፈላጊ ባልሆኑ ለመዳን በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ጊዜውን አልፈጀም፡፡ ኒቆዲሞስ አንዳንድ የሃይማኖት እውቀት ቢኖረውም ለመዳን ግን ምንም አይጠቅመውም፡፡ ኒቆዲሞስንም ሆነ እኛን የሚጠቅመን ዳግመኛ መወለድ ነው፡፡    
በእናቱ ማህፀን ውስጥ ያለ ህፃን አለምን ማየት እንደማይችልና ስላልተወለደበት አለም ምንም አይነት እውቀት ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በስተቀር ስለ እግዚአብሄር መንግስት ሊያውቅ አይችልም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት እውነተኛ እውቀት የሚጀመረው በመወለድ ብቻ ነው፡፡ ሰው ዳግመኛ ሲወለድ አይኖቹ ይከፈታሉ ነገሮችን ማየትና ማወቅ ይጀምራል፡፡ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሄርን መንግስት ነገሮችን ለማየትና  እና ለማወቅ የሚያደርገው ሙከራ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡
ሰው ዳግመኛ ከተወለደና የእግዚአብሄር የቤተሰብ አባል ስለሚሆንና ከእግዚአብሄር ጋር የአባትና የልጅ ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሚኖረው ስለማማለድ የሚኖረው ጥያቄ ሁሉ ይፈታል፡፡

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤የዮሐንስ ወንጌል 1፡12
መፅሃፍ ቅዱስ ስለዳግም መወለድና በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ በእምነት ከሃጢያት ትምህርቶች የተሞላ ነው፡፡ እንዲያውም መጽሃፍ ቅዱስ እራሱ የተፃፈበት አላማ እኛ በኢየሱስ አምነን ህይወት እንዲሆንልን ነው፡፡
ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል። የዮሐንስ ወንጌል 20፡31
ይህንን ፀሎት ከልብህ በመፀለይ የእግዚአብሄር ልጅ አድርጎ እግዚአብሄር እንዲቀበልህ ማድረግ ትችላለህ፡፡
እግዚአብሄር ሆይ ሃጢያተኛ ነኝ፡፡ የሃጢያት ደሞዝ ደግሞ ለዘላለም ከአንተ መለየት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሃጢያት ለመዳኛ ያዘጋጀኸውን የሃጢያት መስዋእት ኢየሱስን እቀበላለሁ፡፡ እየሱስ ስለሃጢያቴ በእኔ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለና እንደሞተ ከሞትም እንደተነሳ አምናለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ላይ ጌታ አድርጌ እሾመዋለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ዘመን ሁሉ እከተለዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ልጅህ አድርገህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ የዘላለም ህይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#አዲስፍጥረት #አዲስ #መዋጀት  #መዳን #ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ንስሃ #አቁማዳ #መታዘዝ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ኦርቶዶክስ #ተዋህዶ #ጌታ #ማሪያም #መላእክት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ሰላም ትግስት #ልጅ

No comments:

Post a Comment