Popular Posts

Friday, February 23, 2018

ለራስህና . . . ራስህንም

#ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ #ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና። 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡16
አገልግሎት የሚጀመረው ከራስ ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ስለቤተክርስትያን መሪነት መመዘኛ ሲናገር የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር ይላል፡፡
ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ #የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ሰው ግን #የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? 1 ጢሞቴዎስ 34-5
የራሱን ህይወት በመልካም የማያስተዳድር ሰው የራሱን ቤት በመልካም ሲያስተዳድር አይችልም፡፡ ሰው ቤተክርስትያንን የሚጠብቀውና ለቤተክርስትያን የሚጠነቀቀው ለራሱ ህይወት ሲጠነቀቅ ነው፡፡
ሰው ሌላውን ከማገልገሉ በፊት ማገልገል ያለበት ራሱን ነው፡፡ ሰው የመጀመሪያ ጥሪው ሌላውን ማገልግል ሳይሆን ራሱን ማገልግል ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል እየተራበ ሌላውን ሊመግብ አይችልም፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል ሳያደርግ ቃሉን ስለማድርግ ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰው ለራሱ ሳይጠነቀቅ ለሌላው ሊጠነቀቅ አይችልም፡፡
ሰው ለራሱ ሳይፀልይ ለሌላው ሰው ብቻ ሊፀልይ አይችልም፡፡ ሰው የራሱን የፀሎት ህይወት አፍርሶ የሌላውን ህይወት ሊገነባ አይችልም፡፡ ማገልግል ያለብን ከህይወት ትርፋችን እንጂ በዋናችን በህይወታችን ወጭ አይደለም፡፡ የምናገለግለው መንፈሳዊ ህይወታችንን ሰውተን አይደለም፡፡ የምናገለግልው ከመንፈሳዊ ህይወታችን ትርፍ ነው፡፡ ህይወታችን የሚነካ አገልግሎት ቢቀርብን ይሻላል፡፡ ቅድሚያ የምንሰጠው ለራሳችን መንፈሳዊ ህይወት ነው፡፡    
ሰው የራሱን ጥሪ ትቶ ሌላውን ጥሪ ሊረዳ አይችልም፡፡ ሰው የሌላን ጥሪ ሊረዳና ሊደግፍ የሚችለው የራሱን ጥሪ እያደረገ ነው፡፡ ሰው ለሌላ ሰው ያለው ጥሪ ከራሱ ሞልቶ ሲተርፍ ያለ ጥሪ ብቻ ነው፡፡ ያልሞላ ብርጭቆ ተዘቅዝቆ በግድ ካልሆነ በስተቀር ሊያካልፍ ለሌላ ሊያፈስ አይችልም፡፡ ሞልቶ የተረፈው ግን በቀላሉ ለሌላው ያፈሳል ያካፍላል፡፡  
ሰው ማንንም ማዳን ካላቻለ ማዳን ያለበት ራሱን ነው፡፡ ሰው ሌላውን ካላዳነ መመለስ ያለበት ራሱን ወደ ማዳን ነው፡፡ ሰው በአገልግሎት ሲደክም መመለስ ያለበት ወደ ራሱ ነው፡፡ ሰው መጀመሪያ ማበርታት ያለበት ራሱን ነው፡፡ ራሱን ያላበረታ ሰው ሌላውን ያዳክማል እንጂ ማንንም አያበረታም፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን #ራስህን ጠብቅ። ገላትያ 6፡1
ሰው የእግዚአብሄር ቃል ሲያነብ ማንበብ ያለበት ለራሱ ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል ሲሰማ መስማት ያለበት ለራሱ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሌላው ሰው ከመናገሩ በፊት ለተናጋሪው አስቀድሞ ይናገራል፡፡
ከራስ ያልጀመረ አገልግሎት አገልግሎት ሳይሆን ስራ ነው፡፡ ራስን ያልነካ መንካት ትክክለኛ መንካት አይደለም፡፡ ህይወትህ እየተጎዳ ማገልገል ማለት በቀዳዳ ባሊ ውስጥ ውሃ እስኪሞላ እንደመጠበቅ ከንቱ ነው፡፡ አገልግሎር የሚመነጨው ከእውቀት አይደለም፡፡ አገልግሎት የሚነሳው ከብልጠት አይደለም፡፡ አገልግሎት የሚነሳው ከህይወት ነው፡፡ የአገልግሎት መሰረቱ ህይወት ነው፡፡ ከእውነተኛ ህይወት እውነተኛ አገልግሎት ይመነጫል፡፡  
እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ #ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር #ራሳችሁን ጠብቁ። ይሁዳ 1፡20-21
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራስ #ራስህን #ጠብቅ #ለራስህ #ተጠንቀቅ #ቃል #ህይወት #አገልግሎት #አምልኮ #ፀሎት #ጥሪ #ተመልክተን #መቃጠል #መቀጣጠል #ክብር #አገልግሎት #መዋረድ #መርካት #ፀጋ #እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment