እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-4
እኛ ኢየሱስን እንደ አዳኛችን የተቀበልን ሁላችን ካህናት ነን፡፡ ሰዎችን ይዘን በእግዚአብሄር ፊት እንቀርባለን እንፀልይላቸዋለን፡፡ እኛ ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን ስለ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሄር ፊት መፀለይ የዘወትር ስራችንና ሃላፊነታችን ነው፡፡
እንደ እግዚአብሄር ካህናት በስልጣን ላይ ያሉትን ይዘን በእግዚአብሄር ፊት ስለ ባለስልጣኖች እንፀልያለን፡፡
እኛ ጌታን የምንከተል ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት እንደምንነጋገርና እንዴት እንደምንፀልይ እናውቃልን፡፡ ከእግዚአብሄር ፀልየን እንዴት እንደምንቀበል እናውቃለን፡፡ ሰዎችን በእግዚአብሄር ፊት እንዴት ከፍ እንደምናደርግና እንደምንፀልይላቸው እናውቃለን፡፡
ተስፋችን ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሄር ነው፡፡ ውስን በሆኑ በሰዎች ከመጠን በላይ እንታመንም፡፡ እግዚአብሄር ካላገዛቸው ምንም ማድረግ በማይችሉት በስጋ ለባሽ ነገስታት አንደገፍም፡፡ የምንፀልየው የነገስታትን ልብ እንደውሃ ፈሳሾች ወደወደደው ወደሚያዘነብል ጌታ ነው፡፡
የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሾች በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ ወደ ወደደውም ያዘነብለዋል። ምሳሌ 21፡1
እኛ ለባለስለጣኖች ካልፀለይን ግን ለማን እንተዋቸዋለን? እኛ በፀሎት ከእግዚአብሄር ጋር እንዴት እንደምንነጋገር የምናውቅ ባለስልጣኖች በፀሎት ካልደገፍናቸው ሰይጣን ክፍተቱን ይጠቀማል፡፡
ሰይጣን የሚመጣው ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋ ነው፡፡ ለባለስልጣኖች ካልፀለይን ሰይጣን ክፍተቱን ይጠቀማል የሰዎችን ህይወት ያጠፋል፡፡ ሰይጣን ባለስልጣኖችን በጥላቻና በራስ መወዳድነት ካጠቃ በእነርሱ ተጠቅሞ ህዝቡን ይሰርቃል ያርዳል ያጠፋል፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሃንስ 10፡10
ሰይጣን ባለስልጣኖችን በራስ ወዳድነትና በሙስና ከመታ ህዝቡን ድሃ ያደርጋል ያጎሳቁላል፡፡ ሰይጣን ባለስልጣኖችን በራስ ወዳድነትና በረብሻ ከመታ የህዝቡን ሰላምና ስኬት ይመታል፡፡
እግዚአብሄር ህዝቡን ይወዳል፡፡ እግዚአብሄር ሁሌ ስለነገስታትና ስለመኳንንት ስለሰዎች ሁሉ የሚፀልይን ሰው ይፈልጋል፡፡
በፀሎታችን ውስጥ የታመቀ ታላቅ ሃይል አለ፡፡ ስልፀልይ የሚለወጥ ነገር አለ፡፡ ስንፀልይ የሚሆን ነገር አለ፡፡ ስንፀልይ የሚስተካካለ ነገር አለ፡፡ ስንፀልይ የሚነቀል ነገር አለ፡፡ ስንፀልይ የሚተከል ነገር አለ፡፡
የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ያዕቆብ 5፡16
ለህዝቡ በመፀለያችን ተጠቃሚ የምንሆነው እኛው ነን፡፡ ለህዝቡ በመፀለያችን እግዚአብሄር ህዝቡን ይባርካል፡፡ ለህዝቡ በመፀለያችን እግዚአብሄር ባለስልጣኖችን ከሰይጣን ጥቃት ይታደጋል፡፡ ለህዝቡ በመፀለያችን እግዚአብሄር ህዝቡ ፀጥና ዝግ ብሎ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ስንፀልይ ብቻ ነው ፀጥና ዝግ ብለን የእግዚአብሄርን መንግስት ስራ ሰርተን የምናልፈው፡፡ ስንፀልይ ብቻ ነው በእግዚአብሄር መንግስት የወንጌል ስራ ላይ ማተኮር የምንችለው፡፡ ፀጥና ዝግ ብለን ስንኖር ብቻ ነው ያዳንንን ወንጌል ለሌሎች ለማዳረስ የምንተጋው፡፡
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው ከሁሉ በፊት ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲፀለይ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ የሚለው፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-4
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ነገሥታትና #መኳንንት #ጸጥ #ዝግ #እግዚአብሄርንመምሰል #ወንጌል #ተስፋች #ሁሉንቻይ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment