ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። መክብብ 3፡1
እግዚአብሄር የፈጠረን በአላማ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያቀደውን ነገር የሚፈፅመው በአላማ ነው፡፡ እግዚአብሄር አላማውን በትጋት አየፈፀመ ይገኛል፡፡
እግዚአብሄር ሁሉን ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር በነገሮች አይናወጥም፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስደንቁት ነገሮች የሉም፡፡ እግዚአብሄር ያላቀደውን እንዲያደርግ ሁኔታዎች አያስቸኩሉትም፡፡ እግዚአብሄር ነገሮችን የሚሰራው በቅደም ተከተል ነው፡፡
እግዚአብሄር ነገሮችን የሚሰራው በዘፈቀደ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር እቅዱን የሚፈጽፅመው በጊዜ ውስጥ ነው፡፡
እያንዳንዱ ነገር ራሱ መፈፀሚያ ጊዜ አለው፡፡ እያንዳንዱ ነገር ለመፈፀም የራሱ ጊዜ ይጠብቃል፡፡ እያንዳንዱ ነገር ውበት የሚኖረው በራሱ መፈፀሚያ ጊዜ ሲደረግ ነው ፡፡
ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ መክብብ 3፡11
አንድ ነገር በራሱ መፈፀሚያ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ አይሆንም፡፡ በራሱ መፈፀሚያ ጊዜ ግን ሲሆን ሙሉ ይሆናል፡፡ ሁሉም ነገሮች ወደዚያ ነገር ያመለክታሉ፡፡ ባረሱ ጊዜ ሁሉም ነገር ይሰካካል፡፡ ሁሉም ነገር ከዚያ ጋር ይስማማል፡፡ ሁሉም ነገር የራሱን ቦታ ይይዛል፡፡ ሁሉም ነገር ስለባለጊዜው ተፈጻሚነት ይሰራል፡፡
በጊዜው የሆነ ነገር የሚቋቋመው የለም፡፡ በጊዜው ሲሆን ነገሩ የማይሆንበት ምክኒያቶች ሁሉ ይጠፋሉ፡፡ በጊዜው ሲሆን ሲቋቋሙ የቆዩት ሁሉ እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡
በክርስትና የምንሰራውን ነገር ብቻ ሳይሆን መቼ እንደምንሰራው ጊዜውን ማወቅ ከብዙ አላስፈላጊ የጉልበት ብክነት ያድነናል፡፡ ከጊዜው በፊት ብዙ ለፍተን ትንሽ ያገኘንበት ነገር ጊዜው ሲመጣ የትጋታችንን ሙሉ ውጤት እናገኝበታለን፡፡ በዘመኑ ማድረግ ያለብንን ማወቃችን ነገሮችን ካለ ዘመኑ እንዳናደርግ ይጠብቀናል፡፡
ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ኤፌሶን 5፡16
ከእግዚአብሄር ጊዜ ጋር አብሮ መፍሰስና ለእግዚአብሄር ጊዜ ስፍራ መስጠት ጥበብ ነው፡፡ ጊዜን ማወቅ በጊዜ ውስጥ ብቻ በሚለቀቀው ጥበብ ፣ ፀጋ እና ክንውን ሙሉ ተጠቃሚ እንድንሆን ያስችለናል፡፡
ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። መክብብ 3፡1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #ውብ #ፀጋ #ጥበብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #ዛሬ #ነገ #ትላንት #መሪ
No comments:
Post a Comment