Popular Posts

Tuesday, February 20, 2018

ስለ ገንዘብም መመካት

ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
ሰው በእግዚአብሄእንዲኖር በእግዚአብሄር ብቻ እንዲደገፍና እንዲመካ ተፈጥሮአል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር የማይመካ ከሆነ የሚመካበት ሌላ ነገር ይፈልጋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በእግዚአብሄር የማይመካ ሰው በገንዘብ ይመካል፡፡ በእግዚአብሄር ያልረካ ሰው በገንዘብ ለመርካት ይሞክራል፡፡ በእግዚአብሄር ተስፋ የማያደርግ ሰው በገንዘብን ተስፋ ያደርጋል፡፡ በእግዚአብሄር የማይደሰት ሰው በገንዘብ ይደሰታል፡፡ እግዚአብሄር ጌታው ያልሆነለት ሰው ገንዘብን ጌታ ያደርገዋል፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
ሰው በገንዘብ ለመመካት ብዙ ገንዘብ እንዲኖረው አያስፈልገውም፡፡ ሰው ባለው በትንሽዋ ገንዘብ ከተመካ በገንዘብ መመካት ወጥመድ ተይዟል፡፡ ሰው ለገንዘብ ያለውን ጉጉትና ጥማት አይተን ስለገንዘብ እንደሚመካና እንደማይመካ ማወቅ እንችላለን፡፡ ሰው ገንዘብ ባይኖረውም ገንዘብ ምን ሊያደርግለት እንደሚችል ያለውን አስተሳሰብ አይተን በገንዘብ እንደሚመካና እንደማይመካ ማወቅ እንችላለን፡፡ ሰው አሁን ብዙ ገንዘብ ባይኖረውም ለገንዘብ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤን አይተን በገንዘብ እንደሚመካና እንደማይመካ መረዳት አያስቸግርም፡፡ ሰው አሁን ብዙ ገንዘብ ባይኖረውም ለገንዘብ ያለው የተሳተ ግምት በገንዘብ ይመካ አይመካ ያመለክታል፡፡ ሰው ገንዘብ ቢያገኝ ህይወቱ እንደሚለወጥ ካሰበ በገንዘብ መመካት ወጥመድ ውስጥ ወድቋል፡፡
ገንዘብ ያለውም ሰው በገንዘቡ ምንም ነገር ሊያደርግ የሚችል ከመሰለው በገንዝብ መመካት ሃጢያት ውስጥ ወድቋል፡፡ ገንዘብ ያለው ሰው የገንዘብን ውስንነት ካልተረዳና ገንዘብ ሊያያደርግ የሚችለው እጅግ ጥቂት ነገር ብቻ እንደሆነ ያልተረዳ ሰው በገንዘብ መመካት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ገንዘብ ያለው ሰው የገንዘብን ውስንነት ካልተረዳ በገንዘብ መመካት አደጋ ላይ ነው፡፡ ፅድቅና ፍርድን ምህረት የሚያደርግ እግዚአብሄር እንጂ ባለጠግነት ምንም የሚያመጣው ነገር እንደሌለ ያልተረዳ ገንዘብ ያለው ሰው ስለ ገንዘብ ሊመካ ይችላል፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርሚያስ 9፡23-24
ገንዘብ ያለው ሰው ሁሉንም እግዚአብሄር እንደሚያከናውን የሰው ሃይልና ጥበብ ምንም እንደማያደርግ ያለተረዳ ሰው በገንዘን መመካት ይሰቃያል፡፡
ገንዘብ መኖሩ ወይም አለመኖሩ ሳይሆን ለገንዘብ ያለ የተበላሸ እይታ ፣ ለገንዘብ ያለ የተሳሳተ ግምት እና ከገንዘብ ጋር ያለ የተበላሸ ግንኙነት የክፋት ሁሉ ስር ነው፡፡
ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡10
ብዙ ገንዘብ ላለው ሰውና ብዙ ገንዘብ ለሌለው ሰው ያለን አቀባበል ስለ ገንዘብ መመካታችንን ወይም አለመመካታችንን ያሳያል፡፡ ብዙ ገንዘብ ያለው ሰው የህይወት ቁልፍ እንዳለው ብዙ ገንዘብ የሌለው ሰው የህይወት ቁልፍ እንደሌለው የምናስብን ከሆነ ስለገንዘብ የመመካት አደጋ ውስጥ ነን፡፡ ብዙ ገንዘብ ያለውን ሰው የምናከብር ብዙ ገንዘብ የሌለውን ሰው የምንንቅ ከሆንን በገንዘብ መመካት ሃጢያት ውስጥ ወድቀናል፡፡  
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
ስለምንበላው ምግብ ፣ ስለምንጠጣው መጠጥ ፣ ስለምንለብሰው ልብስ ፣ ስለምንነዳው መኪና ፣ ስለምንኖርበት ቤት የምንመካ ከሆንን ስለገንዘብ መመካት ንስሃ ገብተን ልንመለስ ይገባል፡፡ በተቃራኒው ስለምንበላው ምግብ ፣ ስለምንጠጣው መጠጥ ፣ ስለምንለብሰው ልብስ ፣ ስለምንነዳው መኪና ፣ ስለምንኖርበት ቤት የምናዝንና የምንዋረድ ከሆንን እንዲሁ ንስሃ ገብተን መመለስ አለብን፡፡ ስለሌለን መዋረዳችን የሚያመለክተው ሲኖረን እንደምንመካበት ነው፡፡  
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት . . . 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ንስሃ #ገንዘብ #ሃብት #ንብረት #ተስፋ #መደሰት #መመካት #ባለጠግነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አለም #ሃጢያት #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የህይወትፍሬ #መናገር #ቅባት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment