Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, February 7, 2018

የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል

የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል
ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 2 ጢሞቴዎስ 3፡1-5
የአምልኮ መልክ ኖሮዋቸው የእግዚአብሄርን ሃይል የካዱ ሰዎች በጣም የሚያሳዝኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ሃይሉን የካዱ ሰዎች በእግዚአብሄር ሃይል ስለማይታመኑ የራሳቸውን መንገድ ይሄዳሉ፡፡ በሃይሉ ስለማይታሙና የእግዚአብሄር ሃይሉ ይህን ያደርግልኛል ብለው ተስፋ ስለማያደጉ ማስመሰዩውን መንገድ ይሄዳሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ሃትል ስለካዱ የስጋን ሃይል ይጠቀማሉ፡፡ በፍቀር ስለማያምኑ ፍቅር የሌላቸው ሆነው ይመላለሳሉ፡፡ በእግዚአብሄር ሃየለ ስለማያምኑ በራሳቸው ቅልጥፍና ይታመናሉ፡፡ ራሰብን በመካድ ስለማያምኑ በ ስግብግብነት ይመላለሳሉ፡፡ በእግዚአብሄር ስለማያምኑ በረሳቸው ብልጠይት ይደገፋሉ፡፡ 
ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ
ሰዎች እግዚአብሄር እንደሚወዳቸው እርግጠኛ ስላይደሉ ደስተኞች አይደሉም፡፡ እግዚአብሄር እንደሚወደው የሚያውቅ ሰው ያርፋል ራስ ወዳድ አይሆንም፡፡ ሰዎች ራሳቸው ላይ ያተኩራሉ፡፡ ሌላውን መድረስ ፣ ሌላውን መጥቀም ፣ ማካፈል ፣ ለሌላው መኖር ፣ ሌላውን ማንሳት የሚባሉ ነገሮች ከራስ ወዳድንት ከፍ ያለ የከበረ ደረጃ እንደሆነ አያውቁም፡፡  
ገንዘብን የሚወዱ፥
ሰዎች ገንዘብን በመውደዳቸው ጌታን ይንቃሉ፡፡ ሰዎች ገንዘብን በመውደዳቸው ሰውን አይወዱም፡፡ ሰዎች ገንዘብን በመውደዳቸው ይሰርቃሉ ፣ ይዋሻሉ ፣ ያጭበረብራሉ ፣ ይክዳሉ ፣ ሰዎችን ይጠላሉ፡፡ ገንዘብን መውደድ የክፋይ ሁሉ ስር እንደመሆኑ ገንዘብን የሚወድ ሰው እግዚአብሄርንም ሰውንም ስለማይወድ ምንም ክፋት ሊያደርግ ይችላል፡፡ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡10
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ 6፡24
ትምክህተኞች፥
በገንዘብና በተለያዩ ጉሳቁሶች ይመካሉ፡፡ በራሳቸው ችሎታ ይመካሉ፡፡ ባላቸው ዝምድና በሚያውቁት ሰው በአራድነታቸው ይመካሉ፡፡
ትዕቢተኞች፥
ሰውን ሁሉ ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ባልጀራዬ ከእኔ ይሻላል አይሉም፡፡ ሰውን የሚፈልጉት ለጥቅማቸው ብቻ ነው፡፡ ካልጠቀማቸው ለሌላ ለምንም ነገር አይፈልጉትም፡፡ ከሁሉም የሚሻሉበትን መንገድ ባገኙት አጋጣሚ ያሳያሉ፡፡ ሁሉም እነርሱን ለመጥቀም የተሰራ እንጂ ልናገለግለው የሚገባ እንደሆነ አያውቁም፡፡    
ተሳዳቢዎች፥
በታላቅ ቃል ይሳደባሉ፡፡ ሲሳደቡ ለነገ አይሉም፡፡ ለመሳደብ አይፈሩም፡፡ ሲናገሩ ደፋሮች ናቸው፡፡ በድፍረት ንግግር ሁሉንም ለመብለጥ የሚፈልጉ ይመስላሉ፡፡ በፊታቸው የተከበረ የማይሰደብ ሰው የለም፡፡ በግል ጥቅማቸው ፊት የቆመን ማንም ሰው ለማዋረድ ወደኋላ አይሉም፡፡ በግል ጥቅማቸው ፊት የቆመን ሰው ለማዋረድ ያለችውን ተሰሚነት ሁሉ ለክፋት ይጠቀሙበታል፡፡
ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥
ስልጣንን አያከብሩም፡፡ የሚሰሙት ምንም ስልጣን የለም፡፡ ለእነርሱ ሁሉም ሰው አልገባውም፡፡ እነርሱ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ከመስቀላቸው አንፃር ማንም ሊሰሙት የተገባ አይደለም፡፡ ለማንም አይታዘዙም፡፡ ማንንም አይሰሙም፡፡ ለሁለም ሰው የሚያወጡት አቃቂር አለ፡፡ ሁሉም ሰው እነርሱም የሚሰማ እንጂ እነርሱ የሚሰሙት አንድም ሰው የለም፡፡

ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ። እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እርሱም፦ ጋኔን አለበት አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እርሱም፦ እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች። ማቴዎስ 11፡16-19
የማያመሰግኑ፥
ራሳቸውን ከመስቀላቸ አንፃር ይህ የሚኖሩበት ኑሮ የሚገባቸው እንደሆነ አያስቡም፡፡ ለአነርሱ የቱም ደረጃ አይመጥናቸውም፡፡ በየትኛውም ህይወት አይረኩም፡፡ በየትኛውም የህይወት ደረጃ ራሳቸውን ለማማጠን አይፈልጉም፡፡ ምንም ከፍ ያለ ደረጃ ለእነርሱ አይበቃል፡፡ እጅግ የተከበሩ ስለሆኑ ለክብራቸው የሚበቃ የህይወት ደረጃ የለም፡፡ ስለዚህ አያመሰግኑም፡፡ የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያደርጉት ከምስጋና ልብና በደስታ አይደለም፡፡
ቅድስና የሌላቸው፥
ህይወታቸው በመርህ አይመራም፡፡ ደስ ካላቸው የፈለጉትን ያደርጋሉ፡፡ ለእግዚአብሄር ነገሮችን መተው ፣ ከአለም እርኩሰት መለየት ፣ ራስን መካድ የሚሉት ቃላቶች በህይወታቸው የሉም፡፡ በቃሉ ሳይሆን በሁኔታው ነው የሚመሩት፡፡ የተሻለ ጥቅም ካስገኘላቸው ይዋሻሉ፡፡   
ፍቅር የሌላቸው፥
እግዚአብሄርን አያውቁም፡፡ እግዚአብሄርን አይወዱም ሰውን አይወዱም፡፡ ፍቅር የላቸውም፡፡ ሌላውም መጥቀም ፣ ለሌላው ማካፈል ፣ አብሮ ማደግ የሚባሉት ሃሳቦች ለእነርሱ እንግዳና የሞኝነት ሃሳቦች ናቸው፡፡
ዕርቅን የማይሰሙ፥
የራሳቸውን ሃሳብ እንጂ የማንንም ሃሳብ ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡እነርሱ ሃሳብ ብቻ ትክክል የሌላው ሃሳብ ሁሉ ስህተት ነው፡፡ ለሌላው ብለው ምንም ነገር ለመተው ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ እውቅና የሚሰጡት ለራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ብቻ ነው፡፡ የሚያርፉት የራሳቸውን ሃሳብ ሲያስፈፅሙ ብቻ ነው፡፡ ለጥቅማቸው እንጂ ለሰላም ምንም ፍላጎት የላቸውም፡፡  
ሐሜተኞች፥
የሰውን ገመና ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት የለም፡፡ ማንንም ሰው እንደ ቤተሰብ አያዩም፡፡ ማንም ሰው በፊታቸው የከበረ አይደለም፡፡ ሰውን በሌላ ሰው ፊት ዝቅ ዝቅ ለማድረግ አይፈሩም፡፡ የአንዱን ገመና በሌላው ሰው ፊት ለመግለጥ አይፈሩም፡፡ የሌላውን ስም ለማጥፋት ጨካኞች ናቸው፡፡ ሌላውን ለማዋረድና ስሙን ለማጥፋት ፈጥረውም በውሸት ያወራሉ፡፡ ሌላውን ሰውን ማጣጣል እነርሱን ከፍ የሚያደርጋቸው ይመስላቸዋል፡፡ 
ራሳቸውን የማይገዙ፥
የፈሉትን ነገር በፈለጉት ጊዜ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ፡፡ ትእግስት ፣ መጠበቅ ፣ መተው የሚሉትን መርሆች አያውቋቸውም፡፡ ከስጋቸው የሚሰሙት ድምፅ ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ራስን መግዛት ፣ ስጋ መጎሸም ፣ ስጋን መከልከል የሚሉት ሃሳቦት በፍፁም አይገባቸውም፡፡
ጨካኞች፥
ምህረትና ርህራሄ የላቸውም፡፡ ለጥቅም ሲባል ምንም ነገር ለማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ በጥቅም ላይ እነጂ በማንም ላይ ይጨክናሉ፡፡ ለእነርሱ ትክክል ጥቅም ማግኘት ነው፡፡ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ማንኛውም ነገር በምንም ይምጣ በምንም ትክክል ነው፡፡
መልካም የሆነውን የማይወዱ፥
ትክክለኛው ህይወት  ከእነርሱ ስለሚለይ ይጠሉታል፡፡ ቀስ ብላ የምትከማቸውን ሃብት ያላዋቂ ያደርጉታል፡፡ ራሱን የሚገዛ ሰው ሲያዩ ያልገባው እውቀት ያነሰው ይመስላቸዋል፡፡ እንደ እነርሱ የማይሄድ ማንም ሰውን ይጠላሉ፡፡ መልካመ የሆነው ህይወት የእነርሱን ህይወት ስለሚያጋልጥ አይወዱትም፡፡ 
ከዳተኞች፥
በቃላቸው አይታመኑም፡፡ ለመካድ ቅርብ ናቸው፡፡ ታማኝነት ስለሌላቸው ከተመቻቸው ቅጥፍ አድርገው ይክዳሉ፡፡ የተሻለ ነገር ሲያገኙ ወዲያው ተገልብጠው ይገኛሉ፡፡ ቀድመው የገቡትን ቃል በቀላሉ ያፈርሳሉ፡፡ ስለቃሌ ልታገስ የሚል ነገር የላቸውም፡፡
ችኩሎች፥
ሁሉ ነገር በፍጥነት እንዲሆንላቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ ነገር በፍጥነት ካልሆነላቸው ይሆናል ብለው አያምኑም፡፡ መጠበቅን ይፈሩታል፡፡ መታገስ አለማወቅ አለመረዳት ደካምነት ነው የሚመስላቸው፡፡
በትዕቢት የተነፉ፥
ማንም ሊያስተምራቸውና ሊመክራቸው አይችልም፡፡ ሁሉንም ያውቃሉ፡፡ አውቀውት ጨርሰዋል፡፡ ሌላው ሁሉ ሰው እንጂ እነርሱ መማር መለወጥ አያስፈልጋቸውም፡፡ ለመማር ለመለወጥ ዝግ ናቸው፡፡ በማንም ስልጣን ስር መግባት አይፈልሀጉም፡፡ ማንም እንዲያዛቸው አይፈልጉም፡፡ ማንንም መስማት አይፈልጉም፡፡
ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ
ደስታ መዝናናት የህይወታቸው ከፍተኛው አላማ ነው፡፡ የሚያስደስታቸውን ምንም ነገር ይቀበሉታል፡፡ የማያስደስታቸውን ምንም ነገር አይቀበሉትም፡፡ ህይወታቸውን በመሰረታዊ ፍላጎት ላይ ሳይሆን በቅንጦት ላይ ያባክኑታል፡፡ በህይወታቸው የሚመራቸው ደስታ ተድላ እንጂ ጌታ አይደለም፡፡
የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል
የክርስትና ቋንቋው ሁሉ አላቸው፡፡ ንግግሩ ቃላቶቹ ሁሉ አላቸው፡፡ መልኩ ሁሉ አላቸው፡፡ ለውጭው መልካቸው በጣም ይጠነቀቃሉ፡፡ ሁሉንም ነገር ከላይ ከላይ ትክክል ለማድረግ እጅግ ይጠነቀቃሉ፡፡ የውጭውን ነገር ሁሉ በደንብ ይይዙታል ለልባቸው ግን ግድ የላቸውም፡፡ ዋናው የውጭው ይመስላቸዋል፡፡ ከሰው የሚመጣውን ክብር እንጂ ከእግዚአብሄር የሚመጣውን ክብር አይፈልጉም፡፡ ልባቸው ግን ክፋትና ቅሚያ ሞልቶባቸዋል፡፡
ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። ዮሃንስ 12፡43
ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡1-5
 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ገንዘብን የሚወዱ #ትምክህተኞች #ትዕቢተኞች #ተሳዳቢዎች #ለወላጆቻቸውየማይታዘዙ #የማያመሰግኑ፥ #ቅድስና የሌላቸው #ፍቅርየሌላቸው #ዕርቅንየማይሰሙ #ሐሜተኞች #ራሳቸውን የማይገዙ #ጨካኞች #የማይወዱ #ከዳተኞች #ችኩሎች #በትዕቢትየተነፉ #ተድላን #እውቀት #ጥበብ #ማስተዋል #ቃል #መልካም #መታመን #መደገፍ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት  #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment