Popular Posts

Follow by Email

Saturday, February 3, 2018

ለአንድ ጥሪ አልተጠራንም

ሁላችንም ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር በእያንዳንዳችን ህይወት ሊሰራ ያለው ልዩ አላማ አለ፡፡ ለዚያ አላማ ተጠርተናል፡፡ እግዚአብሄር ለምን አላማ እና አገልግሎት እንደጠራን ማወቅን የመሰለ በህይወት የሚያሳርፍና የሚያረጋጋ ነገር የለም፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ በጥሪያችን ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ የተከፈቱ እጅግ ብዙ በሮች ውስጥ አንገባም፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ከሙከራ እንድናለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ህይወትን መኖር እንጀምራለን፡፡
ጥሪያችን የሆነውን ነገር ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ መጠን ጥሪያችን ያልሆነውን ነገር ማወቅም በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነውን እንለያለን፡፡ ማን እንደሆንን ስንረዳ መን እንዳልሆንን ይገባናል፡፡ እሺ የምንለውን ስናውቅ እምቢ የምንለውን እናውቃለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ውስን የሆነውን ጊዜያችንን ጉልበታችንን እውቀታችንን ገንዘባችንን ባልተጠራንበት ነገር ላይ ከማፍሰስ እንድናለን፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ምንም ብንጥር ፍሬ ከማናፈራበት ቦታ እንርቃለን፡፡
እውነተኛ ፍሬ የሚፈራው በእድል አይደለም፡፡ ፍሬ የሚፈራው በቅልጥፍና አይደለም፡፡ ፍሬ የሚፈራው ጥሪን አውቆ በመከተል ነው፡፡  
ጥሪያችንን ስናውቅ ማድረግ የማንችለውን እንድናውቅ ለዚያ ለተጠሩት እንድንተወው ያስችለናል፡፡ ጥሪያችን ስናውቅ ራሳችንን ትሁት አድርገን ለተጠሩት ሰዎች እንድንተው ይረዳናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ከእኛ የተሻለ ለሚሰሩት በመተው በራሳችን ጥሪ ላይ እንድናተኩር ያስችለናል፡፡
ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነው ውስጥ ገብተን ጥሪያቸው ከሆኑ ሰዎች ጋር እንዳንጣላ ይጠብቀናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ጥሪያችን ያልሆነው ውስጥ ገብተን ጥሪያቸው የሆኑትን ሰዎች እንዳናስተጓጉል ይጠብቀናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ በራሳችን ጥሪ ላይ አተኩረን ጥሪያችንን በትጋት እንድንፈፅም ያደርገናል፡፡ ጥሪያችንን ስናውቅ ለጥሪያችን ብቻ ተለክቶ የተሰጠንን የእግዚአብሄር ፀጋ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ያደርገናል፡፡
ጥሪያችንን በሚገባ ካልተረዳንና ያየነውና የሰማነው ጥሪ ሁሉ የሚያመረን ከሆነ መኪናን እንደመንዳት ሳይሆን እንደመግፋት ይሆንብናል፡፡ በህይወታቸን የሚለቀቀው የእግዚአብሄር ፀጋ የጥሪያችን አይነትና ልክ ስለሆነ የእግዚአብሄርን ስራ በጭንቀት ሳይሆን በደስታ እናደርገዋለን፡፡ በህይወታችን ያለው የእግዚአብሄር ፀጋ ስለማያንስና ስለማይበዛ ለጥሪያችን ብቻ የሚበቃ ስለሆነ የሚረዳንና የሚያከናውንልን በጥሪያችን ላይ ብቻ ስንቆም ነው፡፡ ባለተጠራንበት ቦታ ቆመን የእግዚአብሄር ፀጋ ይደግፈናል ማለት የማይታሰብ ነገር ነው፡፡   
ሰው እግዚአብሄር እንደሚያስችለው እና እንደሚያበረታው እንደሚያውቀው ሁሉ ለሁሉም ነገር ደግሞ እንዳልተጠራ ማወቁ ወሳኝ ነው፡፡ የእርሱ ጥሪ በጣም ልዩ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል የሚመስለው ሰው ተታሏል፡፡ በእግዚአብሄር ነገር እየበሰለን ስንሄድ የምንረዳው በጣም አስፈላጊ ነገር ማድረግ የምንችለው በጣም ውስን ነገር ብቻ እንደሆነ መረዳት ነው፡፡ በዚያ በተጠራንበት ውስን ነገር ላይ ከተወሰንን ፍሬያማ እንሆናለን፡፡
በጥሪያችን ስትቆም እርሱ መሰረታዊ ፍላጎታችን ነው ፣ ሞገሳችን ነው ፣ ውበታችን ነው ፣ ዝናችን ነው ፣ እውቅናችን ነው ፣ እርካታችን  ነው እንዲሁም ደስታችን ነው፡፡ የተሳካልህ ለመሆን የራስህ ጥሪ ማድርግ በቂ ነው፡፡ እንዲከናወንልህ የሌላን ሰው ጥሪ ማድረግ እና እንደምትችለው ማሳየት የለብህም፡፡  
ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 7፡17
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ጥሪ #ምስክር #ፀጋ #ምናን ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment