Popular Posts

Saturday, February 10, 2018

የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁ

ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። ያዕቆብ 3፣1
አስተማሪዎች ቢበዙ ብዙ ሰዎች ይታነፃሉ ብዙ ሰዎች ይለወጣሉ፡፡ አስተማሪነት ግን ታላቅ ተፅእኖ እንደሚያመጣ ሁሉ ታላቅም ሃላፊነት አለበት፡፡
አስተማሪ የሰዎችን አእምሮ በመለወጥ ህይወታቸውንም የመለወጥ ታላቅ ስልጣን ያለው አገልግሎት ነው፡፡
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
ሰዎች የስህተት አስተምህሮ ሰምተው ሃይማኖትን እስከመካድ ይደርሳሉ፡፡ ሰዎች እውነተኛ አስተማሪን ሰምተው ከስህተት ይመለሳሉ፡፡
መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥ 1 ጢሞቴዎስ 4፡1-2
በተፈጥሮ ሰው ለትክክለኛ እድገትና ብስለት ምግብ ብቻ ሳይሆን የተመጣጠነ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ ሰው አንድ አይነት ምግብ ብቻ ከበላና ጉልበት የሚሰጠው ፣ ከበሽታ የሚከላከልለትና የሚገነባው የተሟላ ምግብ ካልበላ ጤነኛ አይሆንም፡፡
እንዲሁም ሰዎች ሚዛኑን ያልጠበቀ በአንድ ወገን ብቻ የተለጠጠ ትምህርትን አስተምረው የሚሰሟቸውን ለመንፈሳዊ በሽተኝነት ያጋለጣሉ፡፡
ስለዚህ አስተማሪነት እውቀት ብቻ ሳይሆን እውቀትን እንዴት ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ ጥበብን ይጠይቃል፡፡ አስተማሪነት እውቀት ማግኘት ብቻ ሳይሆን እውቀትን ሚዛናዊነቱን ጠብቆ ማስተላለፍን ይጠይቃል፡፡
ዛሬ የምናስተምረው ትምህርት ነገ ለምናስተምረው ትምህርት እንቅፋት የሚሆን ከሆነ ሚዛኑን አልጠበቀም፡፡ በባህሪው ስጋዊ ባህሪያችን ማጋነን ይወዳል፡፡ ስናስተምር ትምህርቱን ለማጋነን እንፈተናለን፡፡ ትምህርትን ማጋነን ግን እንዳውም ሃይሉን ያሳጣዋል እንጂ አያጠናክረውም፡፡
ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። ማርቆስ 7፡13
ስናስተምር በጣም ትምህርቱን ከሚገባው በላይ ከመለጠጣችን የተነሳ ከፅንፉ ለመመለስ ድፍረቱ ከሌለን ሰውን እያሳሳትን ነው፡፡ ዛሬ የምናስተምረው ትምህርት ነገ ለምናስተምረው ትምህርት እንቅፋት ከሆነ ሚዛኑን ያልጠበቀ ትምህርት እያስተማርን ሰውን ግራ እያጋባን እንዲሁም ከማበርታት ይልቅ እያደከምነው ነው፡፡ ዛሬ የምናስተምረው ትምህርት ነገ ማስተማር ካለብን ትምህርት ጋር የሚጋጭ ከሆነ ተጋኗል፡፡
አስተማሪዎች ስንሆን አንዳንዱን ብቻ ሳይሆን መሉውን የእግዚአብሄር ምክር ማስተማር አለብን፡፡
የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ ነግሬአችኋለሁና፥ ምንም አላስቀረሁባችሁም። ሐዋርያት 20፡27
ሙሉው የእግዚአብሄር ምክር ነው የሚማሩትን ሰዎች ወደ ሙላት የሚያመጣው፡፡
ከተሳሳትን ደግሞ ይቅርታ ባለፈው ያስተማርኩት ትምህርት ስህተት ነበር ብለን ፈጥነን ማስተካከል ይጠብቅብናል፡፡
እውቀት ስላለን ብቻ አናስተምርም፡፡ በእግዚአብሄር ፊት እንፀልያለን፡፡ እግዚአብሄር በልባችን የሚያፈሰውን መልክት ይዘን እናጠናለን እንዘጋጃለን፡፡ መልክቱን ጊዜ ወስደን እናወጣለን እናወርዳለን፡፡ እንዴት እንደምናስተላልፈው ከእግዚአብሄር ጥበብን እንጠይቃለን፡፡ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል አውቀን በትህትና በፍርሃት ሁሉ እናስተምራለን፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። ያዕቆብ 3፣1
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ማስተማር #ቃል #ማሰላሰል #የእግዚአብሄርቃል #ሚዛን #ምክር #አስተማሪ #መምህር #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አእምሮ #ፍርድ #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment