Popular Posts

Tuesday, February 27, 2018

እግዚአብሄር ይበልጥ ይታመናል

እግዚአብሄርን ባወቅነውና በተጠጋነው ቁጥር እግዚአብሄር ይበልጥ እንደሚያስፈልገንና ይበልጥ እርሱን ማመን እንዳለብን እንረዳለን፡፡ እግዚአብሄርን እያወቅነው በሄድን ቁጥር እግዚአብሄርን የምንፈልግበት የህይወት ክፍል እየበዛ ይሄዳል፡፡ ከዚህ በፊት ለዚህ ደግሞ ምን እምነት ያስፈልገዋል ለምንለው ጥቃቅን ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ማመን እንጀምራለን፡፡
እግዚአብሄርን ባወቅነው መጠን ከእምነት ነፃ አንወጣም፡፡ ከእምነት ነፃ የሚያወጣ እውቀት የተሳሳተ እውቀት ነው፡፡ ልቡን እግዚአብሄርን ከማመን የሚመልስ በልቡ በሌላ ነገር ላይ የሚታመን ሰው የተባረከ ሰው አይሆንም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው። ኤርምያስ 17፡5
ከእምነት ነፃ እንደሆንን ከተሰማን ሳናውቀው የተሳሳተ ምግብ በልተናል ማለት ነው፡፡ ይህን ያህል በእምነት ኖርክ አሁን ደግሞ በማየት ቀጥል የሚል ትምህርት ከእግዚአብሄ አይደለም፡፡ እስካሁን ታመንከው አሁን ግን በአእምሮ ተመላለስ የሚል ትምህርት የስህተት ትምህርት ነው፡፡ እስካሁን የሚታየውን አላየህን አሁን ግን በሚታየው ኑር የሚል ትምህርት መፅሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ እስካሁን የማይታየውን አይተሃል አሁን ግን የማይታየውን አትይ የሚል ትምህትርት የሰይጣን ማታለል ነው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
ንፁህ ምግብ የበላ ሰው እምነትን ባየውና ጥቅሙን ባጣጣመው መጠን ይበልጥ በእምነት ለመኖር ይወስናል፡፡ እግዚአብሄርን አምኖ የኖረ ሰው እግዚአብሄርን ለሚበልጥ ነገር ለማመን ፍላጎቱ ይነሳሳል፡፡ እግዚአብሄርን በእምነት ፈልጎ ያገኘው ሰው እግዚአብሄርን ከመፈለግ አይጠግብም፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ባደግን መጠን ራሳችንን ትሁት ስለምናደርግ በህይወታችን ክፍል ሁሉ እግዚአብሄርን በእምነት ለመፈለግ እንዘረጋለን፡፡ በተለወጥን ቁጥር ካለ እግዚአብሄር ምንም ማድረግ እንደማንችል ስለምንረዳ እግዚአብሄርን የማንፈልግበት የህይወት ክፍል አይኖርም፡፡
እግዚአብሔርን፦ አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም። መዝሙር 16፡2
በእግዚአብሄር ነገር በተሳካልን ቁጥር በራሳችን ውስን መሆናችንን ይበልጥ ስለምንረዳና በእግዚአብሄር ደግሞ ሁሉን ማድርግ እንደምንችል ስለምናውቅ እግዚአብሄርን የምንፈልግበት የህይወታችን ክፍል እየሰፋ እየበዛ ይሄዳል፡፡
እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። ዮሃንስ 15፡5
እግዚአብሄርን ስናምን እምነታችንም እግዚአብሄር ሲሆን ብሩካን ነን፡፡ እግዚአብሄርን ስንታመን እምነታችንም ይበልጥ በእግዚአብሄር ሲሆን ይበልጥ በእምነት ጋሻ ደህንነታችን እየበዛ ይሄዳል፡፡ እግዚአብሄርን ስንታመን እምነታችንም ይበልጥ በእግዚአብሄር ሲሆን ይበልጥ ነፃ እንወጣለን፡፡ እግዚአብሄርን ስንታመን እምነታችንም በእግዚአብሄር ሲበዛ በረከታችን አብልጦ ይበዛል፡፡
በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል። ኤርምያስ 17፡7-8
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment