Popular Posts

Follow by Email

Saturday, February 10, 2018

አይናማው ፍቅር

ብዙ ጊዜ ፍቅር እውር ነው ሲባል ሰምተናል፡፡ ይህ ፍቅር እውር ነው የሚለው ንግግር የሚያደናግር ንግግር ነው፡፡ እውነት ነው እውር የሚያደርግ ፍቅር የሚባል ነገር አለ፡፡ ነገር ግን ያ እውነተኛው ፍቅር አይደለም፡፡ ያ ማስመሰያው ፍቅር እንጂ እውነተኛው ፍቅር አይደለም፡፡ እውነተኛው ፍቅር ጥበበኛና አስተዋይ እንጂ እውር አያደርግምን እውርም አይደለም፡፡  
እንደ ፍቅር የተነገረለት ነገር በምድር ላይ የለም፡፡ እንደ ፍቅር ደግሞ ግራ የተጋባ ትርጉንም የተሰጠው ምንም ነገር የለም፡፡
ሰዎች ፍቅር ብለው የሚጠሩት ሁሉ ፍቅር አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ፍቅር ብለው የሚጠሩር ስሜትን ነው፡፡ ሰዎች ስሜታቸውን ሰምተው ፍቅር ያዘኝ በፍቅር ወድቅኩ ሲሉ ይሰማል፡፡ ይህ አይነቱ ስሜት ድንገት የሚይዛቸው ድንገት ደግሞ በፈለገ ጊዜ የሚለቃቸው ነገር ነው፡፡ በፍቅር ወደቅኩ እንዳሉት ከፍቅር ወደቅኩ ይላሉ፡፡ ወድድኳት እንዳሉ ጠላኋት ይላሉ፡፡ ፍቅር ይዞኛል እንዳሉ ፍቅር ለቆኛል ይላሉ፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ አምኖን የተባለው የንጉስ ዳዊት ልጅ ትዕማር የምትባል ሴት ወድጃለሁ ይላል፡፡ ስለዚህ ታምሜያለሁ ብሎ እንድታስታምመው ይጠይቃል፡፡ ልታስታምመው ስትሄድ ምግብ ስሪልኝና በእጅህሽ አብይኝ ይላታል፡፡ መብሉም በቀረበ ጊዜ ደግሞ ነይ ከእኔ ጋር እንተኛ ይላታል፡፡ እርስዋ ግን ተው ይቅርብህ አታስነውረኝ ብላ ለመነችው፡፡ እርሱ ግን አስገድዷት ከእርሷ ጋር ተኛ፡፡ ከዚያም በኋላ ከቤቱ ተነሺ ውጪ አላት፡፡ 
ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም፦ ተነሥተሽ ሂጂ አላት። 2ኛ ሳሙኤል 13፡15
ይህ የአምኖን ስሜት ፍቅር ሳይሆን ስስት ነው፡፡ ይህ ፍቅር ሳይሆን ራስ ወዳድነት ነው፡፡ ይህ ፍቅር ሳይሆን በስሜት መነዳት ነው፡፡ ይህ ፍቅር ሳይሆን በስጋዊ ምኞት መመራት ነው፡፡ ለሌላው ሰው ምንም ግድ የሌለው የራሱን ጥቅም ብቻ የሚፈልግ ፍቅር ሳይሆን ስግብግብነት ነው፡፡  
ይህ አይነቱ ስሜት የሰውን ሃላፊነት የማይጠይቅ ሰውን እንደፈለገ የሚያሽከረክር ክፋትን የሚያሰራ ስሜት ነው፡፡ ይህን ፍቅር ብሎ መጥራት ፍቅርን ማንቋሸሽ ነው፡፡ ፍቅርን የሚያክል ታላቅ ነገር ከዚህ ከተራ ስሜት ጋር በአንድ ስም መጠራቱ ትክክል አይደለም፡፡ ፍቅር የከበረ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ነው ፍቅር የሚለው ቃል እጅግ የሚያደናግር የሆነው፡፡
ፍቅር ሌላውን መረዳት ነው፡፡ ፍቅር ከሌላው ጋር ራስን በመረዳት ማስተባበር ነው፡፡ ፍቅር ያለንን ነገር ለሌላው ማካፈል ነው፡፡ ፍቅር መስጠት ነው፡፡
ፍቅር ግብታዊ ስሜት አይደለም፡፡ ፍቅር በመረዳት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ነው፡፡ ፍቅር ወስኖ ሌላውን መቀበል ነው፡፡ ፍቅር በውሳኔ ራስን ከሌላው ጋር ማስተባበር ነው፡፡ ፍቅር በውሳኔ ከሌላው ጋር ለመተባበርና ከሌላው ጋር ለመጠራት መፍቀድ ነው፡፡
ስለዚህ ነው እውነተኛው ፍቅር አይናማ ነው እንጂ እውር አይደለም የሚባለው፡፡ ስለዚህ ነው እውነተኛው ፍቅር በደንብ አጥርቶ የሚያይ ነው የሚባለው፡፡ ማስመሳያው ግን እውር ነው፡፡ ማስመሰያው ሰዎች በትክክል እንዳያስቡ እውር ያደርጋል፡፡ ማስመሰያው ስሜት እንጂ ፍቅር አይደለም፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #መውደድ #ስሜት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ትዕግስት #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ  

No comments:

Post a Comment