Popular Posts

Wednesday, February 7, 2018

የአባካኙ ልጅ ታሪክ


እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን፦ አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው። ሉቃስ 15፡11-21
አባካኙ ልጅ ከአባቱ ጥላ መውጣትን አልፈራም
አባካኙ ልጅ አባቱ ያደርግለት የነበራቸውን ነገሮች እንደአስፈላጊ ነገር በፍፁም አላያቸውም፡፡ አባካኙ ልጅ የአባቱን ጥበቃ ዋጋ አልሰጠውም ነበር፡፡ አባካኙ ልጅ የአባቱን እቅርቦት ከምንም አልቆጠረውም ነበር፡፡ አባቱ በቀላሉ የሚያቀርበለት ነገር ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ቢሰሩለትና ቢለፉለትን እንኳን እንደማያገኙት ሲረዳ ብቻ ነው የአባቱን አቅርቦት አውቅና የሰጠው፡፡ አባቱ ምን ያህል ይንከባከበው እንደነበር ያወቀው የቤታቸው ባሮች በልተው የሚተርፋቸውን ምግብ አጥቶ ሲያየው ብቻ ነው፡፡  
አባካኙ ልጅ የቤተሰብን ዋጋ መረዳት አልቻለም
አባካኙ ልጅ የሚያውቁት የሚወዱት ሰዎች መካካል መኖሩን እንደጥቅም አላየውም፡፡ አባካኙ ልጅ ዋጋውን የሚያውቁ የሚያከብሩት የእኛ የሚሉት የሚጠነቀቁለት የቤተሰቦቹን እርዳታ ከምንም አልቆጠረውም፡፡ የቤተሰብን ጥቅም ያወቀው ምንም የማያውቁት ሰዎች መካከል ሲኖርና የማንም ልጅ እንደሆነ የማያውቁትና ዝቅ አድርገው የሚመለከቱት መካከል ሲገባ ነው፡፡  
አባካኙ ልጅ ከአባቱ ምሪት መውጣትን አልፈራም
አባካኙ ልጅ በአባቱ መሪነት ሲያድግና ሲኖር ነበር የቆየው፡፡ በአባቱን ምሪት ሲጠቀም ቆይቶዋል፡፡ የአባት ምሪት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ያወቀው የአባቱን ምክር ያጣው ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከአባቱ ሲርቅ ከአባቱ ምክር ራቀ፡፡ ገንዘቡን እንዴት እንደሚጠቀም የሚመራው አባቱ ነበር፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠውና ቅድሚያ የማይሰጠውንም ነገር ለይቶ የሚነግረው አባቱ ነበር፡፡ ከአባቱ ሲለይ ግን ገንዘቡን ማጥፋት በሌለበት ነገር ላይ አጠፋ፡፡ ገንዘቡ ሲያልቅ ነበር እንዳባከነው ያወቀው፡፡   
አባካኙ ልጅ የሚያውቅ መስሎት ነበር
አባካኙ ልጅ ለራሱ የተሳሳተ ግምት ነበረው፡፡ አባካኙ ልጅ የሚያውቅ ይመስለው ነበር፡፡ አባካኙ ልጅ እንደማያውቅ ያወቀው ከወደቀ በኋላ ነው፡፡ ማወቅ የሚገባውን ያህል እንዳላወቀ የተረዳው ህይወቱ ከባከነ በኋላ ነበር፡፡ አባካኙ ልጅ ከሆነው በላይ ትልቅ ሰው የሆነ መሰለው፡፡ ወደ ልቡ ሲመለስ ብቻ ነው ማወቅ የሚገባውን ያህል እነዳላወቀ ያወቀው በዚያም ምክኒያት ሁሉ ነገር እንደተዛባ ያወቀው፡፡
አባካኙ ልጅ ነፃነት ያለውን ሃላፊነት አልተረዳም
አባካኙ ልጅ ነፃ መሆን ፈለገ፡፡ አባካኙ ልጅ ለአባቱን ተጠሪ መሆንን አልፈለገውም፡፡ አባካኙ ልጅ የአባቱን አገዛዝ ከራሱ ላይ መጣል ፈለገ፡፡ ነገር ግን አባካኙ ልጅ ያልተረዳው ነገር ነፃነት የራሱ ሃላፊነት እንዳለበት ነው፡፡ ከሃላፊነት ውጭ የሆነ ነፃነት የለም፡፡ ለአባቱ መሪነት ተጠሪ ካልሆነ ለህሊናው ተጠሪ መሆን ነበረበት፡፡ ሃላፊነት የሌለበት ፍፁም ነፃነት የሚባለ ነገር የለም፡፡ ሁላችንም የአንድ ነገር አገልጋዮች ወይም ባሪያዎች ነን፡፡ ጥያቄው ባሪያ መሆንና አለመሆን ሳይሆን የምን ባሪያዎች መሆናችን ነው፡፡    
ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ። ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፥ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ሮሜ 6፡16-18
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ማክበር #መደሰት #አባት #ቤተሰብ #ጥላ #በረከት #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #እውቀት #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #ማስተዳደር #እረፍት

No comments:

Post a Comment