Popular Posts

Wednesday, February 28, 2018

ቃሉን ለመተግበር የሚጠቅሙ አምስት ምክሮች

የእግዚአብሄር ቃል የሚሰራ የሚለውጥ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን የሚሰራው ሲተገበር ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል ከሰሙ በኋላ እንዴት እንደሚተገብሩት ሳያውቁ ሲጨነቁ እናያለን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል በየደረጃው እንዴት እንደሚተገብሩት ሳያውቁ ግራ ሲገባቸው እንመለከታለን፡፡  
የእግዚአብሄርን ቃል በመተግበር ፍሬ የምናፈራበት ሰባት ምክሮች እነሆ፡፡
1.      በደንብ ያለተረዳኸውን የቃሉን ክፍል ለመተግበር አትሞክር
ሁሉንም የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል በአንድ ጊዜ ለመተግበር አትሞክር፡፡ ቤት ከመሰረት ተጀምሮ ቀስ በቀስ እንደሚገነባ ሁሉ የሰውም የእግዚአብሄር ቃል የመተግበር አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የመፅሃፍ ቅዱስ ቃል  ከትልቁ ጀምረህ በአንዴ ለመተግበር መሞከር ተስፋ ሊያስቆርጥህና የእግዚአብሄር ቃል ሊተገበር አይቻልም የሚል ደረጃ ላይ እንድትደርስ ሊያደርግህ ይችላል፡፡ እግዚአብሄርም ከሰው የሚጠብቀው የመታዘዝ መጠን ሰው ቃሉን የተረዳውን መጠን ብቻ ነው፡፡ የተረዳኸውን የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል እየተገበርክ ያልረተረዳኸውን ለመረዳት ቃሉን ፈልግ፡፡ ያልተረዳኸውን ስላልተገበርክ አትኮነን ይህ ኩነኔ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡
ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ሉቃስ 12፡48
2.     ቃሉን በትጋት ማሰላሰል ቃሉን ለመተግበር ጉልበት ይሆንሃል
ቃሉን ማሰላሰል በቃሉ ከባቢ ውስጥ እንድትሆን ያደርጋል፡፡ በቃሉ ከባቢ ውስጥ መሆን ደግሞ እንዳትታዘዝ ከሚገዳደርህ ከስጋህ ሃሳብ ይለይሃል፡፡ ቁጭ ብሎ ሌብነትን የሚያስብ ሰው ሌባ እንጂ ሌላ ምንም ለመሆን አቅም ያጣል፡፡ እንዲሁም ቃሉን ብቻ የሚያስብና የሚያሰላስል ሰው ቃሉን እንጂ ሌላ ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው ቃሉን የሚያስብና የሚያሰላስል ሰው እንደ እግዚአብሄር ያስባለ የሚባለው፡፡
የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። ኢያሱ ወልደ ነዌ 1፡8
3.     የቃሉን ትእዛዝ ብቻ ሳይሆን ለምን እንደታዘዘ እወቅ
አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል የሚያደርጉት እውነትነቱን ተረድተውት ሳይሆን ስለተባለ ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶች ሃጢያትን የማያደርጉት ሃይማኖታቸው ስለማይፈቅድ እንጂ የሃጢያትን ክፋት አውቀው አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትቅመስ አትንካ በሚል ትእዛዝ ብቻ የእግዚአብሄርን ቃል ለማድረግ ሲሞክሩ ጫና ይሆንባቸዋል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር ያዘዘውን ያዘዘው ለምን እንደሆነ ከቃሉ ፈልገው ሲያገኙትና ሲረዱ ቃሉን በደስታ ይተገብሩታል እንጂ እንደ ሃይማኖታዊ ወግ ብቻ አይፈፅሙትም፡፡ እግዚአብሄር ያዘዘውን ትእዛዝ ምክኒያቱን ማወቅ ሽክሙን እኛም እነደንወስደው ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሄር እንዳንሰክር የፈለገው ስንሰክር እግዚአብሄር የሚናገርበት ህሊና ስለሚደነዝዝና እግዚአብሄርን መስማት ስለማንችል በሰይጣን ሃሳብ ብቻ ውስጥ ስለምንወድቅ ነው፡፡
ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ቆላስይስ 2፡20-22
4.     ቃሉን ስታደርግ አታጠናክረው
የእግዚአብሄር ቃል በራሱ በቂ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የነጠረ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ቃል ሰባት ጊዜ የተፈተነ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለእግዚአብሄር በጣም ሲቀኑ ቃሉን ለማጠናከር እና ጉለበት ሊሰጡት ሲፈልጉ ይሽሩታል፡፡ ቃሉን በአስተያየትህ አታሻሽለው፡፡ ቃሉ መሻሻል አይፈልግም፡፡
ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። ሉቃስ 7፡13
5.     ቃሉን ከተገበርክ በኋላ መፅናት ያስፈልግሃል
ቃሉን ተገበርክ ማለት በአንድ ለሊት ውጤት ታያለህ ማለት አይደለም፡፡ ቃን ስትተገብር ውጤት ታያለህ፡፡ ነገር ግን መፅናት መጠበቅ መታገስ ይኖርብሃል፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። እብራዊያን 10፡36
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍሬያማነት #ፍሬ #ማፍራት #ስኬት #በእኔኑሩ #ቃል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መመዘኛ #መስፈርት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment