Popular Posts

Thursday, February 8, 2018

በልቡ ሳይጠራጠር

እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ማርቆስ 11፡23
ጥርጥር የክርስትና የእምነት ጉዞ ህይወት ጠር ነው፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል መጠራጠር ከጀመረና እስከ መጨረሻው በእምነት ውስጥ የተዘጋጀለትን በረከት ያጣዋል፡፡
ሰው ስለ እምነቱ ከእግዚአብሄር ዘንድ ሽልማት ይቀበላል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ሰው ወይ ያምናል ወይ ይጠራጠራል፡፡ 50% አምኗል ተብሎ 50% ሽልማት የሚሸለም ሰው የለም፡፡ ከተጠራጠረ ተጠራጠረ 0% ሽልማት ያገኛል ካመነ አመነ 100% ሽልማት ያገኛል፡፡ ስለዚህ ነው ልባችንን ከየትኛውም አይነት ጥርጥር አጥብቀን መጠበቅ ያለብን፡፡   
ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። ያዕቆብ 1፡6-8
ሰው ካመነ በኋላ ጥርጥርን ላለማስተናገድ መጋደል አለበት፡፡ ሰው ጥርጥርምን ለማስተናገድ ቸልተኛ ከሆነና መንገድ ከከፈተ ሳያውቅው በእምነት ምክኒያት ያገኘውን ወይም ማግኘት የሚገባውን በረከት ያጣዋል፡፡
እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል እንደመሆኑ መጠን ጥርጥር የሚመጣው ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ የሆነን ነገር በመስማት  ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ቃል ተቃራኒ የሚናገረውን ሁኔታን ከሰማን እንጠራጠራለን፡፡
ጴጥሮስ ና የሚለውን ቃል ሰምቶ በውሃ ላይ መራመድ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን የነፋሱን ሃይል አይቶ ተጠራጠረ እምነቱን አጣው፡፡  
ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው። ማቴዎስ 14፡30-31
ሰው የሰማውንም የእግዚአብሄርን ቃል ትቶ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጭ የሚናገሩትን የሰዎችን ቃል ከሰማ ጥርጥርን ያስተናግዳል፡፡
የምኵራብ አለቃው ስለልጁ ፈውስ ከአዚየሱስ ጋረ እየሄደ ሰዎች ከፈውስ ተቃራኒ ነገር ነገሩት፡፡ ኢየሱስን እምነቱ እንዳይጠፋ መስማት ያለበትን የእርሱን ቃልና መስማት የሌለበትን የጥርጥር ቃል እንደገና አስታወሰው፡፡
እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት፦ ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ፦ እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። ማርቆስ 5፡35-36
እምነታችን እንዲሰራ በሰማነው በእግዚአብሄር ቃል ላይ መቆም አለብን፡፡ ሁኔታዎች ባይመሰክሩ እንኳን በሰማነው በእግዚአብሄር ቃል ላይ መቆም አለብን፡፡ ሰዎች የተለየ ሃሳብ ቢኖራቸው እንኳን  መጀመሪያ በሰማነው በእግዚአብሄር ቃል ላይ መቆማችን እግዚአብሄር በእምነት ውስጥ ያስቀመጠውን ሽልማታችንን መውሰድ ያስችለናል፡፡  
እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ማርቆስ 11፡23
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #አለማመን #ጥርጥር #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment