Popular Posts

Saturday, February 17, 2018

መከራ ተቀበል

እንግዲህ፥ ልጄ ሆይ፥ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል። 2 ጢሞቴዎስ 2፡1፣3
ኢየሱስ ጌታ ነው ብለን ከመሰከርን ጀምሮ ከመቀፅበት የሰይጣን ጠላቶች ሆነናል፡፡ ሰይጣን ደግሞ ጌታ ኢየሱስን መከተላችንን በዝምታ አይመለከተውም፡፡ ጌታን መከተላችን እርሱን ማገልገላችን ስህተት እንደሆነ ሊያሳምነን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ሰይጣን የህይወት ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን የሚመጣው ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋ እንጂ ስለሌላ አይመጣም፡፡
የእግዚአብሄርን መንግስት ስንከተል የሰይጣንን መንግስት ክደን ነው፡፡ ክርስቶስን ስንከተል የሰይጣን መንግስት ጠላቶች ሆነን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን መንግስት ስራ ስንሰራ ሰይጣን ሊያስቆምን የማያደርገው ጥረት የለም፡፡ ሊያስቆምን ባይችል እንኳን ጌታን በደስታ እንዳንከተለው ለማድረግ ይጥራል፡፡
የእግዚአብሄርን መንግስት ተቃዋሚ አላት ፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ትገፋለች፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል (በብርቱ የሚጋደሉ ያገኟታል) ።” ማቴዎስ 11፡12
እንደ እግዚአብሄር መንግስት መልክተኞች የሚገዳደረንን ተቋቁመን ማለፍ ግዴታ ነው፡፡ ለወንጌል ስንኖርና ወንጌልን ስንሰራ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንም፡፡ በምደር ላይ ጌታን የምናገለግለው ሰይጣን ፈቅዶልን ሳይሆን በግድ ነው፡፡ ህይወትና አገልግሎት አስቸጋሪ ሲሆን እኛ ግን እንቀጥላለን፡፡ ወንጌልን ስንሰራ መከራ ይገጥመናል፡፡
እውነተኝነታችን ደግሞ የሚለካው በመከራ ወቅት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሃይል ከእኛ ጋር እንዳለ የሚታየው በአስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ አለም ያልሆነ የእግዚአብሄር ድጋፍ እንዳለን የሚታየው በመከራ ስንፀና ነው፡፡ የእግዚአብሄር ህልውና አብሮን እንዳለ የሚታየው በሰው የማይታለፈውን መከራ በእግዚአብሄር ድጋፍ ስናልፈው ብቻ ነው፡፡  
በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን። ምሳሌ 24፡10
መከራ ሲገጥመን በክርስትና ታይቶ የማይታወቅ እንግዳ ነገር እንደገጠመን መቁጠር የለብንም፡፡ በክርስትና መከራ እንግዳ አይደለም፡፡ መከራን እንደ እንግዳ ነገር ካየነው በመከራ እንታገስም፡፡ መከራን እንደ እንግዳ ነገር ካየነው በመከራ ጊዜ ይከፋናል፡፡ መከራን እንደሚያጋጥም ካላወቅን ከጌታ መንገድ የሳትን ይመስለናል፡፡ መከራ ያለ እንደሆነ ካልተረዳን በጌታ መንገድ ላይ እንዳለን እንጠራጠራለን፡፡ መከራን የክርስትና ህይወት አንዱ ክፍል አድርገን ካላየነው በመከራ ሰላማችንን እናጣለን፡፡
ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት  ያዕቆብ 1፡2-3
የሃዋሪያው ጳውሎስ መልክት መከራን ተቀበል የሚል ነው፡፡
እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡8
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #መከራ #ፈተና #መፅናት #መታገስ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment