Popular Posts

Follow by Email

Saturday, February 17, 2018

ወንድም ለመከራ ቀን ይወለዳል

ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል። ምሳሌ 17፡17
እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥረው ራሱን አባት አድርጎ እጅግ ልዩ ስጦታ ከመስጠቱ ውጭ ወንድሞችና እህቶች እንዲኖሩን ፈለገ፡፡ እግዚአብሄር ልጆቼ አባት ብቻ አይደለም ወንድሞችም ያስፈልጋቸዋል ብሎ ወንድሞችና እህቶች ፈጠረልን፡፡ እንደ እግዚአብሄር አባትነት ክብር አባትነቱ ብቻ ይበቃን ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን አባት ብቻ ሳይሆን በስጋ ውስጥ የሚኖሩ ወንድምና እህት ያስፈልጋቸዋል ብሎ እህቶችና ወንድሞችን ሰጠን፡፡
ኢየሱስም እንድንከተለው ሲጠራን ስለእርሱ ብለን የምንተዋቸውን ወንድሞችና እህቶች መቶ እጥፍ እንደምንቀበል ቃል ገብቷል፡፡
ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። ማቴዎስ 19፡29
የወንድምና የእህት ጥቅሙ ደግሞ በምቹ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ እውነት ነው ሰው ከሰው ጋር እንዲኖር ማህበራዊ ፍጡር ተደርጎ ስለተፈጠረ በምቹ ጊዜም ሰው ሰውን ይፈልጋል፡፡ ወንድም ይበልጥ የሚያስፈልግበት ዋናው አላማ ግን ለመከራ ቀን ነው፡፡ በምቾት ቀን አብሮ የሚሆን በመከራ ቀን የማይገኝ ወንድም የተወለደበትን አላማ አልፈፀመም፡፡
ሰው በከፍታውና በደስታው ብቻ ሳይሆን በዝቅታው አብሮት መቆም የወዳጅነት አላማ ነው፡፡ እውነተኛም የወንድምነት ሃላፊነት የሚፈተነው በምቹና በከፍታ ቀን ሳይሆን በዝቅታ ፣ በመከራ በሃዘን ቀን ነው፡፡
በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ምሳሌ 24፡10
ከወዳጅ ጋር ሁሌ አብረን መቆም እንዳለብንና የደስታና የሃዘን ህይወቱን መካፈል እንዳለብን መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ የወዳጃችንን የሃዘን ስሜት መካፈል ክብራችን ነው፡፡
ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ።ዕብራውያን 13፡3
የወዳጃችንን ኑሮና ህይወት እንደ ራሳችን አድርገን መካፈል የተወለድነበት አላማ ነው፡፡ የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የወዳጆቻችንን ዝቅታ አብረን እንድንካፈል እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡  
ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። ሮሜ 12፡15
እንዲያውም መፅሃፍ ቅዱስ በመከራ ቀን ከወዳጃችን ጋር መቆም በደስታው ቀን ከመቆም እንደሚሻል ያስተምራል፡፡  
ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። መክብብ 7፡2
ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል። ምሳሌ 17፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ወዳጅ #ጓደኛ #መታመን #ጥበብ #ፍቅር #መከራ #እዘኑ #ደስይበላችሁ #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment