Popular Posts

Follow by Email

Monday, February 26, 2018

ሰማያዊ መዝገብ

የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ይኸውም ትርፉ ለእናንተ እየበዛ እንዲሄድ እንጂ ስጦታውን ጓጒቼ አይደለም። ፊልጵስዩስ 4፡15-17
የምድር መዝገብ አለ፡፡ የሰማይ መዝገብ አለ፡፡ የአንዳንድ ሰዎች የምድር የባንክ ሂሳብ ዳጎስ ያለ ነው፡፡ የሰማይ የባንክ ሂሳባቸው ግን የተመናመነ ነው፡፡ የአንዳንድ ሰዎች የምድር የባንክ ሂሳባቸው የተመናመነ የሰማይ የባንክ ሂሳባቸው ግን ዳጎስ ያለ ነው፡፡ ሃዋሪያው ታዲያ ለእግዚአብሄር ስራ ገንዘባችሁን ስትሰጡ የሰማይ ባንክ ስሌታችሁ እንዲበዛ ነው የምፈልገው ይላቸዋል፡፡
የምድር መዝገብ ውስን ነው፡፡ የምድር መዝገብ የሚሰራው በምድር ብቻ ነው፡፡ የምድር መዝገብ ዋጋው ርካሽ ነው፡፡ የምድር የሚያልቅ የሚጠፋ ነው፡፡ የምድር ገንዘብ ወደ ሰማይ ሊሄድ የማይችል የመሬት ስበት ይዞ የሚያስቀረው ውስን ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ የአመፃ ገንዘብ የሚለው፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16:9
በምድር አገሮች ከአገሮች ጋር የሚገበያዩት በአለም አቀፍ ምንዛሬዎች ነው፡፡ በኢትዮጲያ ውስጥ ያላችሁን ብር ከኢትዮጲያ ውጭ አይሰራም፡፡ የኢትዮጲያ ገንዘብ እንዲሰራላችሁ ከፈለጋችሁ ወደ አለማቀፍ ምንዛሪ መመንዘር አለባችሁ፡፡ ወደ አለም አቀፍ ምንዛሬ ያልተለወጠ የኢትዮጲያ ብር በውጭ አገር ምንም አይጠቅምም፡፡
እንደዚሁ የምድር ገንዘብ የሚጠቅመው ምድር ላይ ብቻ ነው፡፡ የምድርን መዝገብ ዋጋውን ከፍ ለማድረግ ወደ ሰማይ መዝገብ መመንዘር አለበት፡፡ የምድር መዝገብ ዋጋው ከፍ የሚለው ወደ ሰማይ መዝገብ ሲለወጥ ብቻ ነው፡፡ የምድር ገንዘብ በእግዚአብሄር ዘንድ ዋጋ አለው የሚባለው በመልካም ስራ ላይ ሲውል ብቻ ነው፡፡ የምድርን ገንዘብ ዋጋውን ከፍ ለማድረግ እና በሰማይ ምንዛሬ ለመመንዘር በመልካም ስራ ላይ መዋል አለበት፡፡
ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ሉቃስ 12፡21
በገንዘብ ባለጠጋ የሆነ ሰው ባለጠግነቱን በመልካም ስራ ካልቀየረው የምድር ገንዘቡ ጊዜ ያልፍበታል ይቃርዳል ተራ ወረቀት ይሆናል፡፡  
በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡17-19
መፅሃፍ ቅዱስ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የተባረከ ነው የሚለው የምድርን ገንዘብ ከሚቀበል ይልቅ በመልካም ስራ ወደ ሰማይ መዝገብ የሚለውጠው ሰው ይበልጥ የተባረከ እንደሆነ ለመግለፅ ነው፡፡  
ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ፡፡ ሐዋርያት 20፥35
በምድር ያለ ገንዘብ በተራ ሁኔታ ላይ ሊውል ይችላል በከበረ ነገር ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የምድር ገንዘብ ለሰዎች ስለጌታ በድርጊትም በቃልም በመመስከር ላይ ሊውል ይችላል ወይም ደግሞ በአልባሌ ነገር ላይ ሊውል ይችላል፡፡ በምድር ገንዘብ ተጠቅመን ለሰዎች የጌታም መልካምነትና ፍቅር ልናሳይበት እንችላለን፡፡ ወይም የምድርን ገንዘብ ለሌላ ለተራ ነገር ልናውለው እንችላለን፡፡
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴዎስ 5፡1
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ የምድር ገንዘባችንን የዘላለም ዋጋ ያለው መልካምነት ላይ ማዋል እንዳለብን የሚመክረን፡፡ የምድር ገንዘባችንን ተጠቅመን ለሰዎች መልካምነትን በማሳየት የሰዎችን ልብ ለእግዚአብሄር ለመማረክ መጠቀም ይገባናል፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16:9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የሰማይመዝገብ #መስጠት #መልካምስራ #በረከት #ስኬት #ስሌት #ስምረት #ገንዘብ #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መርካት #ደስታ #የልብስፋት #ማስተዳደር #እረፍት

No comments:

Post a Comment